አንድ ግሪካዊ ፈላስፋ በጠራራ ፀሐይ መብራት ይዞ በአቴና ከተማ ይንጎራደድ ነበር። ሰዉ ሁሉ አበድክ እንዴ? በጠራራ ፀሐይ መብራት ይዘህ የምትሄደው ምን ሆነህ ነው? አሉት። ፈላስፋውም ፍግግ እያለ እኔማ ሰው ስለጠፋ ነው መብራቴን የያዝኩት አላቸው። ሕዝቡ እየተደመመ በዚህ ሁሉ ሕዝብ መካከል እንዴት ሰው ጠፋ ትላለህ? አሉት። ልክ ነው ውር ውር የሚል ሕዝብ አያለሁ ግና ለሀገሬ የሚጠቅም ሰው ጠፍቶ ነው መብራቴን ይዤ ሰው የምፈልገው አላቸው!
እትዬ ጣይቱ በአንድ ወቅት ያጫወቱኝ ታሪክ ነበር። እትዬ ጣይቱ ትምህርቱን በአጭሩ ቢቀጩትም ብስለታቸው ይገርመኛል። አቶ እድሜ የተባሉ መምህር ደህና አድርገው አስተምሯቸዋል። ፈላስፋው እንዳለው ለሀገር የሚሆን ሰው ጠፋ እንዴ? ለቤተክርስቲያን የሚሆን አባት ጠፋ እንዴ? “አስሰሽ አስሰሽ ምጣዱ ሲደራ አንቺ ወደ መሬት በላተኛው ሌላ” አሉ እትዬ ጣይቱ ምጣዳቸውን እያሰሱ።
እንዲያው ለሀገር ለቤተክርስቲያን ሰው ጠፋ? ብለው እትዬ ጣይቱ በጥያቄ አስተያየት አዩኝ። ሰውማ አለ። “ያን ሰው እኛ አናውቀው ይሆናል እንጂ እግዚአብሔር የሚያውቀው ሰውማ አለ” አሉ እትዬ ጣይቱ ወደ ሰማይ እያዩ። እንደ ገደል ማሚቱ እየደጋገሙ “ሰውማ አለ!” አሉ። ወዲያው እዚህ ቤት “ሰው አለ?” የሚል ድምጽ ተሰማ። የእትዬ ጣይቱ ጓደኛ ነበሩ። ይግቡ “ሰው አለ” አልኩኝ እንዲሰሙኝ ጮክ ብዬ። የእትዬ ጣይቱ ጓደኛ በሩን ከፍተው እኛ መኖራችንን ካረጋገጡ በኋላ “ሰው ካለ ጥሩ ነው ገበያ ደርሼ እመለሳለሁ” ብለው ሳይገቡ ሄዱ። እትዬ ጣይቱም የጓደኛቸውን አባባል ደግመው “ሰው ካለ ጥሩ ነው” አሉና ጨዋታቸውን ቀጠሉ። እኛ ሰው ስንፈልግ እንደ ፈላስፋው መብራት ይዘን ወደ አደባባይ ነው የምንሮጠው። ይህኮ ነው የኛ ችግሩ። ያ ሰው ያለው ግን በአደባባይ ሳይሆን በየገዳሙ ነው። መልካም እረኛ ስጠኝ ብለን ሳንጠይቅ እንዴት ያን ሰው እናገኘዋለን? ደገኛ ሰዎች እንደ መፋቂያ እንጨት ከመንገድ ላይ አይቀጠፉም እኮ። በአንድ ወቅት እስራኤላዊያን ሳኦልን አንግሥልን ብለው ሳሙኤልን ጠየቁ። ሳሙኤልም ወዲያው ሳኦልን ቀብቶ አነገሠላቸው። ሳኦል 40 ዓመት ሙሉ ክፉኛ ገዛቸው። መልካም እረኛ ስጠን ቢሉኮ በዛው ዘመን ዳዊት ነበረላቸው። እስራኤላዊያን ግን ሳይለምኑ ዐይናቸውን ጨፍነው ሳኦል ይንገሥ አሉ። ሳኦልም ዐይኑን ጨፍኖ ገዛቸው። የኛም ዕጣ ይህ ነው። “እያወቀ የገባን አብረህ ቅበረው አይደል ተረቱ” አሉ እትዬ ጣይቱ ገና በጠዋቱ።
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በ 57 ዓመታቸው ዐረፉ (1955-2012)
ኢትዮጵያ መሪዎቿ በሕይወት እያሉ ሥልጣን ሲቀያየሩ ሳያይ፣ የመሪዎች ለውጥ የሚመጣው አንድም በሞት አንድም በስደት ብቻ እንደሆነ ልንቀጥል ነው ማለት ነው፡፡ እናንተን ማስረዳት ቀባሪን ማርዳት እንዳይሆንብኝ እፈራለሁ። በአንድ ሰሞን ፓትርያርኩንና ጠቅላይ ሚኒስትሩን ያጣንበት ምክንያት ምን ይሆን? የእግዚአብሔርስ መልእክቱ ምንድን ነው? ብጹዕ አቡነ ቄርሎስ በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የኀዘን ቦታ ላይ ‹‹ሞት ታላቅ መጽሐፍ ነው፤ ነገርግን የሚያነበው የለም›› እንዳሉት ከሰሞኑ ሁኔታ የሃይማኖት አባቶች፣ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት፣ ሌሎቻችንስ ምን እንማራለን? አሁን ሀገሬ አዲስ መሪ፣ እናት ቤተክርስቲያኔ አዲስ ፓትርያርክ እየጠበቀች ነው። “ትሻልን ትተሽ ትብስን አመጣሽ” እንዳይሆንብን መለመን አለብን። ያረፉትንም እግዚአብሔር ነፍሳቸውን ይማር ማለት ባህላችን አንድም ሃይማኖታችንም ነው።
ቅዱስ ፓትርያርኩ እነሆ አረፉ። ቤተ ክርስቲያኒቱ በመስቀለኛ መንገድ ላይ እንደቆመች ናት። ይህንን የፕትርክና ምርጫ በሰላማዊና ክርስቲያናዊ መንገድ ማካሔድ ከቻለች ብሩህ ዘመን፣ አልያም ደግሞ በግርግር እና በጥቅመኞች ፍላጎት በሚመራ አሠራር ከተከናወነም ሌላ የመከራ ዘመን ሊጠብቃት ይችላል። አዲሱ ፓትርያርክ ከመመረጣቸው በፊት ፣ በሚመረጡበት ጊዜና ከተመረጡ በኋላ በጸሎት መትጋት የኛ ድርሻ ነው። የምንመርጠው ፓትርያርክ እንጂ የቀበሌ ሊቀ መንበር አይደለምና ቆም ብለን ማሰብ አለብን አሉ እትዬ ጣይቱ።
እትዬ ጣይቱ በመሪነት ጸጋ ላሉ አገልጋዮች የመከሩትን ምክር ሁሌም አልረሳውም። እንዲህ የሚል ነበር፡- “ልጆቼ ሆይ በጉዞ ላይ ካለ አንድ መኪና ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ተሳፋሪ ቢቅም ቢጠጣ ምንም ማለት ላይሆን ይችላል፡፡ ሾፌሩ ቢቅምና ቢያጨስ ግን ጉዞ አይኖርም፡፡ ምክንያቱም መሪው ያለው በእርሱ እጅ ነው፡፡ “መሪው ከተመታ መንጋው ይበተናል” የሚለውም ወታደራዊ ስልት ከዚሁ ሐቅ የመነጨ ነው” አሉኝ። እትዬ ጣይቱ የተናገሩት ለአጭር ጊዜና በአጭሩ ቢሆንም መልዕክታቸው የያዘው አሳብ ግን ብርቱና የዕድሜ ልክ ነው፡፡
“ለቤተክርስቲያን መልካም እረኛ ለእናት ለሀገሬ መልካም መሪ ስጥ” ብንለን ስንለምን ያ ፈላስፋው በጠራራ ፀሐይ መብራት ይዞ የፈለገው ሰው ይገኛል!
Visit this Blog! http://yonas-zekarias.blogspot.com/