Wednesday, 13 November 2013

''ይድረስ ለጠ/ሚ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ''



በዐረብ ሀገር የስንቱ እንባ ፈሰሰ? 
እንባስ እንባ ነው ውሃ ጅረት ነው
የስንቱ ደም እንደ ዐባይ ፈሰሰ?

ዓባይ ሊገደብ ነው አሉ

የህዝብ እንባ የህዝቡን ደም የሚገድብ ማን ይሆን???

አፍንጫ ሲመታ ዓይን ያለቅሳል ለካ
ወገኔ ሲሰቃይ አልችል አለ አንጀቴ
አንጀቴ ለዓይኔ ምስጢሩን ቢነግረው
ስቅስቅ ብዬ አለቀስኩ ገንፍሎ ስሜቴ
የወገኔ ደም ለሊት እየጮኸ
እንቅልፍ ይነሳኛል ድረሱልን እያለ።
የወገኔ ደም በቀን እየጮኸ
ሰላም ይነሳኛል አለቅን ድረሱ ፍጠኑ እያለ።

የቴዎድሮስ ደም ከሰሰ ሀገሩ እንዲህ ስትዋረድ እያየ
አጥንት ድረስ ዘልቆ ቅስሜ ተሰበረ
የዜግነት ክበሬ ስለተዋረደ

ለጣልያን ያልተንበረከከ ጉለበት ለአረመኔ አረብ ሰገደ
ምንይልክ ምን ይበል ይህን ሁሉ እያየ?

የዛሬ 10 ዓመት ለንደን የገባሁ እለት
አስተማሪው ሀገራችሁን አስተዋውቁ አለ

ደረቴን ነፍቼ አፌን ሞልቼ

በአፍሪካ ቅኝ ያልተገዛች ብቸኛዋ ሀገሬ ኢትዮጲያ ናት አልኩት!

ለካ ግን ባርያ ነን ፉከራው ሁሉ ከንቱ ነው።
አባቶቻችን የሞቱልን ለዜግነት ክብር መስሎኝ እኮ ነበር!

ዛሬ ግን ኢትዮጲያዊነት ያስግድላል! በአረቡ ኢትዮጲያዊያን ናችሁ ? ይባላሉ አዎ ካሉ ይታረዳሉ! አረብ በኢትዮጲዊያን ፖሊሶች ደህንነቱ ተጠብቆ በሀገሬ ሲዝናና ህዝቤ በአረብ ፖሊስ ይታረዳል!



ባንድ በኩል ህሊናዬ ይጠይቃል
አረብ ማለት ትርጉሙ እንስሳ ጨካኝ አረመኔ ማለት ነውን?

አጥንት ድረስ ዘልቆ ቁጣን ቀሰቀሰ
እልህ ተያያዘኝ የእናትና አባቴ
ዘራፍ የቴዎድሮስ ልጅ ዘራፍ የምንይልክ
የነ አቡነ ጴጥሮስ የጣይቱ ብጡል
እያልኩ በጀገንነት ልፎክር ተነሳሁ
ለካስ አጥንት ድረስ ዘልቆ ቅስሜ ተሰብሮ ኖሯል
ለካስ ባርያ ሆኜ ክብሬ ውርደት ሆኗል!


በአሜሪካ አንዱ በሽጉጥ ህዝቡን ሲፈጅ ባራክ ኦባማ እንባ እየተናነቃቸው ህዝቡን አጽናኑ። ክቡር ጠ/ሚ ሃይለማርያም ሆይ እርሶ ምን አደረጉ? ቢያንስ ህዝቡን ማጽናናት የአባት ነበር! ለዜግነት ክበር ዘብ መቆም ደግሞ የእናትነት ነው!


አንድ ወታደር ለማዳን 200 ወታደር የገበረች ሀገር ዐውቃለሁ
የሀገር የዜግነት ክብር ይህን ያህል ነውና።


ከመከራው ሀገር አንድ እህት እንዲህ ብላለች፦ ወላጆቻችን የት አሉ? ህዝብም መንግስትም ሬሳችንን ነው የምትጠብቁት?

እራሴን አመመኝ አዞረኝ ሊጥለኝ
መላ ሰውነቴን እራሴን እኔኑ አመመኝ
የማየው ፎቶ የማየው ቪዲዮ ዐይኔን አሳወረኝ።


ባለስልጣናት ሆይ ይህ የፖለቲካ ጫወታ አይደለም! በፍም አይደለም ! ይህ የዜግነት አንድም የህሊና ጉዳይ ነው!
ከፖለቲካ ጫወታ ውጪ ነኝና የመንግስት ደጋፊም ተቃዋሚም ዐይደለሁም!ስለ ሀገሬ ኢትዮጲያ ግን ከቶ ዝም ልል አልችልም።


በዐረብ ሀገር የስንቱ እንባ ፈሰሰ?
እንባስ እንባ ነው ውሃ ጅረት ነው
የስንቱ ደም እንደ ዐባይ ፈሰሰ?

ዓባይ ሊገደብ ነው አሉ

የህዝብ እንባ የህዝቡን ደም የሚገድብ ማን ይሆን??? 


147