Friday, 3 February 2012

ነነዌ እና ዮናስ፦

ትንቢተ ዮናስ ምዕራፍ ፩
  
ለነብዩ ዮናስ የእግዚአብ ቃል መጣ
ነነዌን ለመስበክ ተነሳና ውጣ
በህዝቡ ኃጢአት ቁጣዬ እንዳይመጣ

ነብዩ ይህን ግዜ በልቡ አሰበ
የጌታ ባህሪው ይቅርታ እንደሆነ
ዮናስ ወደ ተርሴስ መኮብለል ወደደ
ወደ ከተማይቱ ምታልፍ መርከብ አየ
ዋጋም ከፈለና በመርከብ ተጓዘ።

ማን ይኮበልላል ከእግዚአብሄር መዳፍ
ወደ ጥልቁ ቢሄድ እንደንስር ቢመጥቅ
ጌታ ሁሉን ገዝቷል በኀይልና ክብሩ
ታላቅ ንፋስ መጣ ማዕበልን ይዞ
መርከቡን ቢያናውጥ ሁሉም እጅግ ፈሩ
እንዲቀልላቸው እቃቸውን ወደ ባህር ጣሉ
ወደ አምላካቸው አበርትተው ጮሁ
በጉዞው ከባድ እንቅልፍ ይዞት
ኮብላዮ ነብይ ይህን ሁሉ አላየም
የመርከቡ አለቃ ወደ ዮናስ ቀርቦ
ምነው ተኝተሃል ስንጠፋ ዝም አትበል
ሁሉ እንደለመነ ፈጣሪህን ለምን
ደግሞም ይህ ነገር በማን እንዳገኘን
በመካከላችን እጣ እንጣጣል
እጣውም ተጣለ በዮናስ ደረሰ
ማበሉ ፀጥ እንዲል ወደ ባህር ተጣለ።
በፈተና ግዜ መውጫው ይሰጠናል
ዮናስ በባህር ውስጥ አሳ ታዞለታል
በአሳ ሆድ ውስጥ ሆኖ ወደ አምላኩ ጮኸ
በአምላኩም ተሰማ ባህር ተሻገረ
ወደ አምላካቹ ተመለሱ እያለ
ታላቋን ከተማ ነነዌን ሰበከ
ንጉስ ለአምላኩ ክብሩን አዋረደ
ትንሹም ትልቁም ወደ አምላኩ ጮኸ
ቀን በነነዌ ታላቅ ፆም ታወጀ
ጌታም ለዛች ሀገር ምህረትን ሰጠ።

ነብዮ ከፀሐይ ሊጠለል ወደደ
በ፩ ቀን ተክል እጅግ ተደሰተ
በንጋታው ቢያጣታ እጅግም አዘነ
ጌታም መለሰለት እንዴት እንደሆነ
አንተ ላልዘራኸው ምታዝን ከሆነ
እኔም ለህዝቤ አዘንኩ አይተህ ተማር አለ።

የዓሣ ሆድ ውስጥ ፀሎት”
ዮናስ በዓሣው ሆድ ውስጥ ሆኖ
ወደ አምላኩ እግዚአብሔር ፀለየ፤ እንዲህም አለ፤
ተጨንቄ ሳለሁ ወደ እግዚአብሔር ተጣራሁ፤
እርሱም መለሰልኝ፤

ከመቃብሩም ጥልቅ እርዳታን ፈልጌ ጠራውህ፤
አንተም ጩኸቴን ሰማህ፤
ጥልቅ ወደ ሆነው ወደ ባህሩ መካከል ጣልኸኝ
ፈሳሾችም ዙሪያዬን ከበቡኝ፤
እኔም ወደ ቅዱስ መቅደስህ እመለከታለሁ አልኩ
አቤቱ ጸሎቴ ወደ መቅደስህ ትግባ

እግዚአብሔር ዓሣ አንበሪውን አዘዘው
እርሱም ዮናስን በየብሱ ላይ ተፋው!!!
    ትንቢተ ዮናስ ምዕ. [፪ -ፍ]

ለአጽዋማትና ለበአላት መሰረታቸው ነነዌ ነው፤
ጾመ ነነዌ ፣ ዐብይ ጾም ፣ ጾመ ሐዋርያት ሁል ግዜ በሰኞ ቀን ይጀምራሉ።
ደብረ ዘይት ፣ ሆሣዕና ፣ በዓለ ትንሣኤ ፣ በዓለ ሃምሳ ደግሞ ሁል ግዜ በእሁድ ይውላሉ።
ርክበ ካህናትና ጾመ ድህነት ሁል ግዜ ረቡዕ ቀን ይውላል። ስቅለት ሁል ግዜ በአርብ ቀን ፣ ዕርገት ደግሞ ሁል ግዜ በሐሙስ ቀን ይውላል። ጾመ ነነዌ የበረከት ጾም ይሁንልን ፤ አሜን።
     ወሥበሐት ለእግዚአብሔር [ተክለ መድህን]