በአንድ ወቅት ነቢዩ ሚክያስ ሕዝቡን ሲያስተምር ውሎ ወደ ማታ በቤተልሔም በኩል ሲያልፍ ከተማዋ
እጅግ ጎስቁላ አየና እያዘነ እንዲህ አለ። “አንቺ ቤተልሔም ኤፍራታ ሆይ ከይሁዳ ነገሥታት ትንሿ ብትሆኚም ንጉሥ በአንቺ
ይወለዳልና ታላቅ ነሽ!” ሚክያስ [5: 2]
እነሆ ነቢዩ ሚክያስ ትንቢቱ ከመፈጸሙ ከ700 ዓመታት በፊት ጌታችን በቤተልሔም እንደሚወለድ
ተንብዮ ነበር። ነቢዩ እንዳለውም ቤተልሔም ታላቅ ከተማ ሆናለች።
/ጌታ ተወለደባት፣ ታላቁ ዘሩባቤል ነገሠባት/
* ቤተልሔም
ኤፍራታ ቤተሕብስት ስትባል የእንጀራ ቤት ማለት ነው። በእንጀራ ቤት /በቤተልሔም/ የተወለደው ጌታችን “እኔ የሕይወት እንጀራ ነኝ”
እያለ ሕይወትን ሰጥቶናልና። አንድም ቤተልሔም የእመቤታችን ምሳሌ ነው፤ እንዴት? ቢሉ ቤተልሔም የእንጀራ ቤት ስለሆነ
እመቤታችንም ለአማናዊው እንጀራ ለጌታችን ማደሪያው ስለሆነች ነው።
እንኳን ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አደረሰን!
የጌታችንን ልደት ከብሥራት አንሥቶ በሰፊው የተረከልን ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ነው፡- “በዚያም
ወራት ዓለሙ ሁሉ እንዲጻፍ ከአውግስጦስ ቄሣር ትእዛዝ ወጣች” በማለት የልደቱን ዘገባ ይጀምራል፡፡ በወቅቱ ዓለምን ሁሉ
የምትገዛው ሮም ነበረች፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም ቄሣር በሚል መዐርግ ይጠራ ነበር፡፡ መንበሩም ያለው በሮም ሲሆን ዓለሙንም
የሚያስተዳድረው በአጥቢያ ነገሥታት በኩል ነው፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ ዓለሙን የሚገዛው ከመንበሩ ሳይንቀሳቀስ ነው፡፡ በመልእክተኞቹ
አማካይነት ዓለሙን ይገዛል፡፡ ጌታችን የተወለደው ከዘመን መርጦ በሮም አገዛዝ ዘመን ነው፡፡ የሮም አገዛዝ ለእግዚአብሔር
መንግሥት ገላጭነት አለው፡፡ ይኸውም፡- እግዚአብሔር አብ ከሥፍራው ሳይናወጥ ይኖራል፤ ቃሉን ወይም ልጁን እንዲሁም መንፈስ
ቅዱስን እየላከ ዓለምን ይገዛል፡፡ ወደዚህ ዓለም በሥጋ የመጣው እግዚአብሔር ወልድ ነው፡፡ እርሱ ካረገ በኋላም መንፈስ ቅዱስ
መጥቷል። ክርስቶስ በትምህርቱ፣ በቤዛነቱ ዓለሙን ገዛ፡፡ መንፈስ ቅዱስም በጸጋው በተአምራቱ እንዲሁም በክርስቶስ ቃሎች ዓለምን
ይገዛል፡፡ እንዲህ ሲሆን ግን የሥላሴ መንግሥት አንዲትና እኩል ናት፡፡
ድንግል በድንግልና
ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች [ኢሳ. 7: 14]
በጥሊሞስ ፈላደልፈስ 72
ሊቃውንትን በአሌክሳንድርያ አካባቢ በምትገኘው በፋሮስ ደሴት ላይ በ72 ቀናት ውስጥ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን ከዕብራዊያን ወደ
ጽርእ /ግሪክ/ እንዲተረጎም አደረገ። ከ72ቱ ሊቃውን ሁለቱ መንገድ ላይ ሲሞቱ ሌሎቹ ሊቃውንት ብሉይ ኪዳንን ለመተርጉም
እየገሰገሱ ንጉሥ በጥሊሞስ ጋር ደረሱ!
ከነዚህ 70 ሊቃውንት
አንዱ አረጋዊ ስምኦን ነው። እነሆ ሰባው ሊቃውንት በሙሉ የየራሳቸውን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በእጆቻቸው ይዘዋል፤ አሁን
ሊተረጉሙ ብዕራቸውን ሁሉም ያዙ!
ለአረጋዊ ስምኦን የደረሰው
የብሉይ ኪዳን ወንጌል እየተባለ የሚታወቀው “ትንቢተ ኢሳይያስ” ነበር።
ሊቁ አረጋዊ ስምኦንም እነሆ ትንቢተ ኢሳያስን ሊተረጉም ፩ዱ ብሎ ጀመረ። እስከ ፯ኛው ምዕራፍ በደህና ደረሰ፤
ምዕራፍ ፯ ላይ ሲደርስ ግን ሊቁ ግራ ተጋባ! እንዴት ሊሆን
ይችላል እያለ ተገረመ! ምን ይሆን ያነበበው?
“ናሁ ድንግል ትፀንስ
ወትወልድ ወልደ ወይሰመይ ስሙ አማኑኤል” ይህችን ቃል አነበበና አሁንም ሊቁ ተደመመ!!! እንዲህ ማለት
ነበርና፦
ድንግል በድንግልና
ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች [ኢሳ. 7: 14]
ድንግል በድንግልና ትፀንሳለች! ከዚህ በፊት ሆኖ አያውቅም፤ በግዜውም አልተደረገም ወደፊትም
አይደገምም አለና ሊቁ አሁንም ተደመመ! አሁን ድንግል በድንግልና ትፀንሳለች ብዬ ብተረጉመው አይደለም በጥሊሞስ የአሕዛብ ንጉሥ
ቀርቶ የእስራኤል ንጉሥ ቢሆንስ ያምነኛልን? ብሎ ሊቁ አሰበ። እናም ድንግል ትፀንሳለች የሚለውን ሰርዞ ሴት ልጅ ትፀንሳለች
ብሎ ፃፈው። ሊቁ ስምኦን እስከ ፯ኛው ምዕራፍ ስለፃፈ ደከመው መሰል ሸለብ አደረገው።
ትንሽ እንዳረፈም ነቃ፤ ካቆመበት ሊቀጥል ቢል እነሆ የሰረዘው ተመልሶ “ድንግል በድንግልና
ትፀንሳለች” የሚለውን አነበበ። በጣም ደክሞኛል ማለት ነው? የሰረዝኩት መስሎኝ ነበር አለና አሁንም ደግሞ ሰረዘውና አሸለበ።
እንዲህ እያለ “ድንግል በድንግልና ትፀንሳለች” የሚለውን ፫ ግዜ ቢሰርዘው ፫ ግዜ “ድንግል በድንግልና ትፀንሳለች”የሚል ተጽፎ
አነበበ።
በመጨረሻም ሊቁ አረጋዊ ስምኦን የተጠራጠረውን ይህን “ድንግል በድንግልና ትፀንሳለች” የሚለውን
ቃል በዓይኑ ሳያይ እንደማይሞት መንፈስ ቅዱስ ገለፀለት። ስለዚህም ሉቃስ በወንጌሉ እንዲህ አለ፦ የጌታን መወለድ በዓይኑ
ሳያይ እንደማይሞት መንፈስ ቅዱስ ያደረበትና የገለጠለት ሰው ነበር [ሉቃስ 2: 26]
አረጋዊው ስምኦን እጅግ
የተደነቀበትን ቃል ለ500 ዓመታት ያህል በተስፋ ጠበቀ፤ እነሆ በዓይኑ የሚያይበት ግዜም ደረሰ፤ ይህም ጌታችን ከአንዲት የ15
አመት ታናሽ ገሊላዊት ብላቴና በህቱም ድንግልና በቤተልሔም በኤፍራታ መወለዱ ነው!!!
ነቢዩ ኢሳያስ ስለ ፅዮን /ስለእመቤታችን/ ዝም አልልም እያለ በቤተልሔም ኤፍራታ ተገኘና የመላዕክቱን የእረኞቹን
ዝማሬ ሰማና “ናሁ ድንግል
ትፀንስ” እነሆ ድንግል
በድንግልና ትፀንሳለች አለና የጌታን ልደት በዓይኑ ሊያይ ናፈቀና ትንቢቱ ከመፈፀሙ ከ700 ዓመታት በፊት አስቀድሞ ተነበየ፤
የዘመኑ ሰዎች አልታደሉምና እንዴት ድንግል በድንግልና ትፀንሳለች አሉና መጋዝ አመጡና ኢሳያስን ያዙና እነሆ ሥጋውን ለሁለት
በመጋዝ ቆራረጡት!
ነቢዩ ኢሳያስ የተነበየውን ትንቢት በዓይኑ አላየም። የኢሳያስን ትንቢት የተረጉመው አረጋዊ ስምኦን
ግን በዓይኑ አየ፤ አንዳንድ ጊዜ እኛ ከምንናገረው ይልቅ ሰምተው የሚተረጉሙት የእግዚአብሔርን ቸርነት በዓይናቸው ያያሉ!
አረጋዊ ስምኦን “ድንግል በድንግልና
ትፀንሳለች” የሚለውን ትንቢት ተረጎመ በዓይኑም አየ አመነም! እንዲህም አለ ፦
“ዓይኖቼ ማዳኑን አይተዋልና ይገባዋል ክብርና ምስጋና” ሉቃስ [2: 30]
የክርስቶስን ልደት ስናነሣ ፈረንጆቹ ስለ ገና አባትና ስለ ገና ዛፍ ስለ በረዶ ያስባሉ።
በአገራችንም ስለ ገና ጨዋታ ይታሰባል፡፡ በአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናትም ገና የሕፃናት ነው ተብሎ ለሕፃናት ከረሜላ በማደል
ይጠናቀቃል፡፡ የክርስቶስ ልደት ግን የመላው የሰው ዘር እንደገና የተወለደበት እንጂ ተራ የሕፃን በዓል አይደለም፡፡ የልደትን
በዓል ማክበር ብቻውን ክርስቲያን አያሰኝም፡፡ የእስልምና እምነት ተከታዮች የሆኑት የፍልስጤም አስተዳዳሪዎች የቀድሞ ያሲን
አራፋት አሁን ደግሞ ማሕሙድ አባስ በቤተ ልሔም ተገኝተው ያከብሩታል፡፡ የእኛ አከባበር ከዚህ የላቀ ካልሆነ ድካም ብቻ ነው፡፡
የተወለደውን ሕጻን በቁሳቁስ ሳይሆን በሕይወታችን ልናከብረው፤ ደስታችንም በመብልና በመጠጥ ሳይሆን በፍቅሩ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ብዙዎች
እንኳን ለብርሃነ ልደቱ አደረሰን እያሉ ይዘፍናሉ፣ ይጨፍራሉ፣ ይሰክራሉ፡፡ ክርስቶስ ግን የተወለደው ዘፈን፣ ኃጢአትና ዝሙት
ከተባሉት የጨለማ ሥራዎች ሊያድነን መሆኑን ገና አላወቁም፡፡ ይልቁንም ቃሉ፡- “የእግዚአብሔርን የአምላክህን ስም በከንቱ
አትጥራ÷ እግዚአብሔር ስሙን በከንቱ የሚጠራውን ከበደል አያነጻውምና” ይላል (ዘፀ. 20÷7)፡፡ የእግዚአብሔርን ስም
በከንቱ መጥራት ማለት በስሙ በተሰየሙ ቀናት ኃጢአትን መሥራት ነው፡፡ ይህ እግዚአብሔርን የኃጢአታችን ተባባሪ ማድረግ ነው፡፡
ፍርዱም ከፍ ያለ ነው።ይሁን እንጂ የእግዚአብሔር
ምህረቱ ሊነገር አይታሰብም ከቶም አይጀመርም። የዘመናት ጌታ ዘመኑ በተፈጸመ ጊዜ ከድንግል ተወልዶ “ዓመተ ምህረት”
ሰጥቶናልና። እንደ ዓባይ እንደ ጣና ባለ ባሕር ጽውዕ ምሉ ማር ጽውዕ ምሉ ቅቤ ቢጨምሩ ከመልኩ ከጣዕሙ እንደማይለውጠው ኹሉ
የእኛም ኃጢአት የእግዚአብሔርን ቸርነት አይለውጠውም። አንድም ወኃበ በዝንቱ ኃጢአት ህየ ፈድፈደት ጸጋሁ ለእግዚአብሔር እንዲል
ኃጢአት ከበዛች ዘንድ የእግዚአብሔር ጸጋ በዛች። ሮሜ [1: 23] እንዴት ቢሉ በኃጢአቱ ቦታ ጽድቁ
ስለገባ። አንድም ጌታ ሰው መኾኑ በምልአተ ኃጢአት ነው እንጂ በጥንተ አብሶ አይደለምና።/ከአዳምና ከሔዋን ዠምሮ በዘር የሚተላለፍ
ኃጢአት ጥንተ አብሶ ይባላል/ በጥንተ አብሶ ሰው ኾኖ ቢኾን አዳምንና ሔዋንን ብቻ ለማዳን ሰው ኾነ እንጂ እኛስ በመስዋዕታችን
በግዝረታችን በጸሎታችን ዳንን ባልን ነበር። ግዝረቱ መስዋዕቱ እንዳላዳነ ካሳየን በኋላ ከድንግል ተወልዶ ሰው ኾነ።
ኃጢአት ከበዛች ዘንድ
የእግዚአብሔር ጸጋ በዛች! እንዲኽ ከኾነ የእግዚአብሔር ጸጋ ይበዛልን ዘንድ ኃጢአት እንስራ እንላለንን?
ሐሰ።
አንልም።
ቸርነቱን አድንቀን በንስሐ
እንመለሳለን እንጂ።
የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መወለዱ የዓለምን ታሪክ ለሁለት የከፈለ ነው፡፡ ዛሬ በክርስቶስ
የሚያምነውም ሆነ የማያምነው ዓለም ዘመንን ሲቆጥር ከክርስቶስ ልደት በፊት ከክርስቶስ ልደት በኋላ እያለ ይቆጥራል፡፡ ለምን?
ስንል ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለምን ዘመን ለሁለት ስለከፈለው ነው፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊት የነበረው ዘመን ዓመተ ፍዳ፣ ዓመተ
ኵነኔ ሲባል ከክርስቶስ ልደት በኋላ ያለው ዘመን ግን ዓመተ ምሕረት ተብሏል፡፡
ዲያቢሎስ በሥጋ ከይሲ ተሠውሮ ቢያስት ጌታችንም በሥጋ ብእሲ ሥግው
ኾኖ አዳነን! አምስት ሺህ አምስት መቶ
ዓመት ሲፈጸም ከእመቤታችን ያላባት መወለዱ ቅድመ ዓለም ከአብ ያለናት መወለዱን ያስረዳል። ልደት ቀዳማዊ ተዓውቀ በደኃራዊ
ልደት እንዲል። ሰብአ ሰገል በኮከብ እየተመሩ ወደ ቤተልሔም መጡ። ኮከብ የተባለው የማታ ኮከብ ሳይኾን መልአክ ነው። እንዴት
ታወቀ ቢሉ እነኾ ኮከብ በማታ እንጂ በቀን አይታይም። ሰብአ ሰገልን ግን በቀን መራቸው። ኮከብ ወደ ምዕራብ ይሄዳል እንጂ ወደ
ምስራቅ አይመራም። ሰብአ ሰገልን ግን ወደ ምስራቅ መራቸው። ኮከብ ርቀት አለው ሰብአ ሰገልን ግን ከአናታቸው ጥቂት ከፍ ብሎ
መራቸው። ይህስ ኾኖ ለምን መልአኩ በኮከብ ተመሰላቸው ቢሉ ሰብአ ሰገል የኮከብ አጥኚ ወይንም አስትሮኖመርስ ስለነበሩ በለመዱት
ነገር ለመሳብ ነው።
“አውራ ጣቱን አሰረችው”
እመቤታችን ጌታን
በወለደችው ጊዜ የጌታን አውራ ጣት አስራ ነበር። ምሥጢሩ ምን ይሆን ቢሉ እነሆ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ እንዲህ አድርገው ይገንዙሃል
ስትል ነው። አንድም መንፈስ እንዳይደለ ለማሳየት ነው። መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውምና አይታሰርም ነበር። አንድም በጨርቅ
ጠቀለለችው። ይህም ምሥጢሩ አንድ ነው። (የዮሴፍና ኒቆዲሞስ መግነዝ ፣ መንፈስ አለመሆኑን ለማሳየት)
ወደ ምሥራቅ ተመልከቱ፦
ዲያቆኑ
በቅዳሴ ላይ ወደ ምሥራቅ ተመልከቱ ይላል ፤ ሕዝቅኤል በትንቢቱ እንዲህ አንዳለ፦ “በምሥራቅ የተዘጋ ጀጅ አየሁ; ይህች በር ተዘግታ ትኖራለች እንጂ አትከፈትም፤ ሰውም
አይገባባትም ፤ የእስራኤል ቅዱስ ሳይከፍት ገብቶ ሳይከፍት ወቶባታልና” ሕዝቅኤል 44:1
ምሥራቅ እመቤታችን ናት ፤ መናፍቃኑ ግን ይህማ
ስለቤተመቅደስ የተነገረ ነው ይላሉ; ተዘግቶ የሚኖር ቤተመቅደስ አለ
እንዴ? ሰውም የማይገባበት ቤተመቅደስ የለም፤ ይህማ ስለእመቤታችን የተተነበየ
ነው። ከምሥራቅ ፀሐይ እንደሚወጣ ከምስራቋ እመቤታችን ፀሐይ ጌታ ተወልዷልና። አንድም ይህች በር ተዘግታ ትኖራለች እንጂ
አትከፈትም አለ; ድንግል በክልኤት ናትና; በሥጋም በነፍስም ድንግል ናትና ፤ ቅድመ ፀኒስ ወሊድ
ድንግል ፤ ጊዜ ፀኒስ ወሊድ ድንግል ፤ ድህረ ፀኒስ ወሊድ ድንግል ናትና; ወትረ ጊዜ ድንግል ናትና ሲል ነው። አንድም “ሰውም አይገባባትም”
አለ አንድያ ልጇን ብቻ ወልዳለችና። የእመቤታችን ክብርማ መቼ ተነገረና? የእመቤታችን ፍቅርማ መቼ ተነግሮ ይፈጸምና? ስለፍቅሯ
ለመዘመር ለመቃኘት…ሞከሩ ግን መቼ የእናቴ ፍቅር በቀላሉ ይነገርና? መቼ እንዲህ በቀላሉ?
“ይህች ለዘለዓለም
ማረፊያዬ ናት”
እግዚአብሔር ፅዮንን
መርጧታልና፤ ዛቲ ይዕቲ ምዕራፍየ ለዓለም (ይህች ለዘለዓለም ማረፊያዬ ናት) መርጫታለሁና በእርሷም አድራለሁ። መዝ 131:13
ሐዋርያው ዮሐንስ “ቃልም ሥጋ ሆነ” እንዳለ
ጌታችን ከእመቤታችን ሥጋን ነስቶ ተወለደልን። ከእመቤታችን
የነሳው ያ ቅዱስ ሥጋ ወደ ሰማይ ከፍ ከፍ ብሎ ዐረገ።
ክርስቲያን ሆይ ከእመቤታችን የተነሳው ያ ቅዱስ ሥጋ ወደሰማይ ዐርጓል እንጂ
በምድር ተቀብሮ በስብሶ የቀረ እንዳይመስልህ። ይህች ለዘለዓለም ማረፊያዬ ናት እንዲል።
ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ዮሐንስ
እንዲህ አለ፦
በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ … “ቃልም ሥጋ ሆነ” [ዮሐ1:1]
በመጀመሪያ ቃል ነበረ፦ “በመጀመሪያ” የሚለው ቃል “በመጀመሪያ” እግዚአብሔር
ሰማይንና ምድርን ፈጠረ ከሚለው ይለያል፤ [ዘፍ1:1] ሰማይና ምድር ለመፈጠር የተወሰነ ጊዜ ነበራቸው፤ በመጀመሪያ ቃል
ነበረ የሚለው ግን በሰውኛ አገላለፅ እንዲገባን ነው እንጂ የተወሰነ ጊዜን አያመለክትም። ቁጥር እንኳን መጀመሪያና መጨረሻ
የለውም፤ ቃል [ወልድ ዋህድ
ኢየሱስ ክርስቶስም] የመጀመሪያው አልፋ የመጨረሻው ዖሜጋ ነው። ራዕ 22
በመጀመሪያ ቃል ነበረ አዎ
ያም ቃል እግዚአብሔር ነበረ! ሥጋንም ለበሰ፤ ከማን? ከማን ሥጋን ነሳ? ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ በኤፍራታ በቤተልሔም ተወለደ!! ልበአምላክ ዳዊት ናሁ ሰማዕናሁ በኤፍራታ መዝ. [131:6] እነሆ በኤፍራታ ሰማነው እንዳለ ከሀገር ለይቶ በቤተልሔም ከቦታ
ለይቶ በከብቶች ግርግም ከሴቶች ለይቶ ከእመቤታችን ተወለደ። ህጻን ተወልዶልናል ወንድ
ልጅም ተሰቶናል አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል ስሙ ድንቅ መካር ኃያል አምላክ የዘላለም አባት የሠላም አለቃ ተብሎ ይጠራል። ኢሳይያስ 9:6
እንኳን ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አደረሰን!
-
- ይህችን አድራሻ ይጫኑ http://yonas-zekarias.blogspot.com/
- አንዱ ሸረፌ የሚባል ባለጸጋ ነበር። ሹሙን ጠርቶ በቀን በቀን ፩ድ ወቄት ዱቄት ለድኾች ሳትሰጥ አትዋል አለው። ቢሰጥ እየበዛ ሔደ። ከበዛስ ብሎ ከታዘዘው አብልጦ ፪ ወቄት ዱቄት ይሰጥ ዠመር። ባለጸጋው ከቤተ መዛግብቱ ቢገባ ንብብረቱ በዝቶ አገኘው። ሹሙንም ያዘዝኹህን ትተሃል እንዴ? ሲል ጠየቀው። ሹሙም እንዲያውም አብልጬ ሠጠኹ አለው። እንግዲያው አትገምግም እጅህ እንዳነሳ ስጥ ብሎታል።
የተቸገረ ብታይ ከንፈር ከመምጠጥ የቻልካትን ትንሿን አድርግለት! ሐዋርያው “በሥራና በምግባር እንጂ በቃል ብቻ አንዋደድ” እንዲል ለድኾች የቻልነውን እንስጥ! በየበዓላቱ ዶሮ በማይጮኽበት ጢስ በማይጤስበት ቤት ያለችንን ተካፍለን እንብላ! ትዝ ይለኛል ልጅ እያለኹ ዓመት በዓል በኾነ ጊዜ ከክፍል ጓደኞቼ ጋር ዶሮ እያሰራን ለድኾች እናበላ ነበር።
Visit this Blog! http://yonas-zekarias.blogspot.com/ — with Daniel Girma. - ይህችን አድራሻ ይጫኑ http://yonas-zekarias.blogspot.com/
- ይህችን አድራሻ ይጫኑ http://yonas-zekarias.blogspot.com/
- ይህችን አድራሻ ይጫኑ http://yonas-zekarias.blogspot.com/
- ይህችን አድራሻ ይጫኑ http://yonas-zekarias.blogspot.com/
- ይህችን አድራሻ ይጫኑ http://yonas-zekarias.blogspot.com/
- ይህችን አድራሻ ይጫኑ http://yonas-zekarias.blogspot.com/
- ይህችን አድራሻ ይጫኑ http://yonas-zekarias.blogspot.com/
Yonas Zekarias shared Yonas Zekarias's photo.