Saturday, 25 February 2012

“ሃይማኖትህን ጠይቅ፣ እወቅ፣ ደግሞም ጠብቅ”

“ኪዳነ ተካየድኩ ምስለ ኃሩያንየ”
/ከመረጥኳቸው ጋር ቃል ኪዳኔን አደረኩ/
መዝ 89:3

እውነት በእውነት ይህ ትንቢት ግሩም ነው! ከደገኞቹ ነብያት አንዱ የሆነው ነብዩ ኢሳይያስ ስለ እመቤታችን እንዲህ አለ፦ ወሶበ አኮ እግዚአብሔር ፀባኦት ዘአትረፈለነ ዘርአ ከመ ሰዶም እምኮነ ወከመ ገሞራ እመሰልነ፤
/የሠራዊት ጌታ ልዑል እግዚአብሔር ዘር ባያስቀርልን ኖሮ
እንደ ሰዶም በሆንን እንደ ገሞራም በጠፋን ነበር!/ኢሳ [1:9]
ፅድቃችን እንደ መርገም ጨርቅ ነው በተባለበት በዛ በጨለማው ዘመን ከአዳም በዘር የሚተላለፈው ኃጢአት /ጥንተ አብሶ/ ወይም original sin እንዳይደርስባት መንፈስ ቅዱስ ከማህፀን ጀምሮ የጠበቃት ንፁህ ዘር እመቤታችን ነበረች! ለዚህም ነው ታላቁ ነብይ እግዚአብሔር ዘር ባያስቀርልን ኖሮ እንደ ሰዶም በሆንን እንደ ገሞራም በጠፋን ነበር ብሎ የተነበየው”

ጽድቃችን እንደ መርገም ጨርቅ ነው ኢሳ [64:6] በተባለበት ዘመን እመቤታችን ግን ጸጋን የተመላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ የሚል ቃል ሰማች፤ ምልዕተ ፀጋ መትህተ ፈጣሪ ናትና፤ ከፍጡራን ሁሉ በላይ ከፈጣሪ በታች ፀጋን የተመላሽ ምልዕተ ፀጋ!

ደገኞቹ መላዕክት አመሰገኗት፣ ባለበገናው ዳዊት በገናውን እየደረደረ ጽዮን ሆይ እያለ ዘመረ፣ ነብያት ተነበዩ፣ እነዚያ 12ቱ ደገኞች ሐዋርያትም እመቤታችንን በመካከላቸው አድርገው ለጸሎት ቢተጉ መንፈስ ቅዱስ በመካከላቸው ወደረ ይለናል የሐዋ [1:14]

የእነዚህን ደገኞች ትንቢትና ሥራ ክርስቲያን ሁሉ በተረደ ነገር ሊያውቀው አይገባምን? በእርግጥ እነዚህ ሁለቱ ጥቅሶች በቃል ጭምር ሊታወቁ ይገባል፤

*ኢሳ 1:9፣ የሐዋ [1:14]

አንቺ ሴት ከአንቺ ዘንድ ምን አለኝ”

ጌታ ለእመቤታችን አንቺ ሴት ከአንቺ ዘንድ ምን አለኝ አላት፤ ይህም ግሩም የሆነ ሚስጢርን በውስጡ ይዟል; እስቲ ቃሉን ለሁለት ከፍለን እንየው፦

+++ “አንቺ ሴትይህን ቃል ለመጀመሪያ ግዜ የተጠቀመው አዳም ነበርአዳም በግብረ ሥላሴ ከህቱም ድንግል መሬት (ከአፈር) ተፈጠረ፤ ከባድ እንቅልፍ ተኝቶ ሳለ ከግራ ጎን አጥንቱ ሔዋን ተፈጠረች። አዳም ከእንቅልፉ ነቅቶ ሔዋንን ከጎኑ ቢያት ይህች ሥጋ ከሥጋዬ ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት ሲል ሴት አላት” ጌታችንም እመቤታችንን ከሥጋሽ ሥጋ ከነፍስሽ ነፍስ ነስቼ ከአንቺ ተወልጄ ዓለምን ኹሉ አዳንኩ ሲል //አንቺ ሴት// አላት። አንድም አዳም ከህቱም ድንግል መሬት ወይም ከአፈር መፈጠሩ እመቤታችን በህቱም ድንግና ጌታን የመውለዷ ምሳሌ ነው። አንድም ከአዳም ጎን አጥንት ሲነቀል አዳም ህመም አለመሰማቱ እመቤታችን ያለ ህመም ጌታን የመውለዷ ምሳሌ ነው። አንድም እግዚአብሔር አዳምን ከፈጠረ በኋላ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ አለ፤ ይህም አዳምን ሳይሆን እመቤታችንን ነው; እንዴት? ቢሉ ወልድ ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ከሶስቱ አካል አንዱ ስለሆነ ነው።

+++ ከአንቺ ዘንድ ምን አለኝ፦ መፅሐፉ አጋንንት ያምናሉ ይንቀጠቀጣሉም ይላል; ነገር ግን ጌታን ከአንተ ዘንድ ምን አለን” አሉት፤ አጋንንት ይህን ሲሉ ጌታን ንቀውት እንዳልሆነ ግልፅ ነው። አንድም ሱናማዊቷ ሴት ልጇን ከሞት እንዲያስነሳላት ነብዩ ኤልዕን ጌታዬ ሆይ “ከአንተ ዘንድ ምን አለኝ” አለችው። አንድም ዳዊት ልጁን አቤሴሎምን ሊገድሉበት ሲሉ እናንተ ሰዎች “ከእናንተ ዘንድ ምን አለኝ” አላቸው። ይህም የአክብሮት እንጂ የመናቅ ንግግር አለመሆኑ ግልጽ ነው።


በእንተ “ስማ ለማርያም


+++ መፅሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ ፀሐይን ተጎናጽፋ ጨረቃንም ተጫምታ በራስዋ ላይ 12 ከዋክብት ያለበት አክሊል የተቀናጀች አንዲት ሴት ነበረች ራዕይ 12:1; የእመቤታችን ክብር እንዲህ ይነበባል። እስቲ እያንዳንዱን ቃል በቃል እንየው;

ፀሐይን ተጎናጽፋ፦  ፀሐይ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ  ነው። አነ ብርሐኑ ለአለም /እኔ የአለም ብርሐን ነኝ እንዳለ/
ጨረቃን ተጫምታ፦ ጨረቃ ቅዱሳን : ጻድቃን ሰማእታት ናቸው። በሳይንሱ ጨረቃ የራሱ የሆነ ብርሐን አለው እንዴ? የለውም ነገር ግን ከፀሐይ ብርሐን reflect ወይም አንፀባርቆ በማታ ያበራልናል። ቅዱሳኑም ብርሐንን ፀሐይ ከሆነው ከጌታ ለጨለማዋ አለም ያበራሉ። ብርሐነ አለም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደምንል። እኔ የአለም ብርሐን ነኝ ያለው ጌታ ፃድቃንንም አንትሙ ብርሐኑ ለአለም
/ እናንተ የአለም ብርሐን ናቹህ/ ብሏቸዋልና። በአንድ ጨለማ ክፍል ያለን ሻም ብናጠፋው ጨለማው የሚብሰው ባጠፋነው በራሳችን ላይ ነው፤ መናፍቃንም እንደሻማ እየቀለጡ የሚያበሩትን ጻድቃንን ቢቃወሙ ጨለማው የሚብሰው በራሳቸው ላይ ነው ማለት ነው።  
ጨረቃን ተጫምታ፦ አንድም ጨረቃ የእመቤታችን የክብሯ መገለጫ ነው። አንድም እመቤታችን የፃድቃን የሰማእታት ሞገሳቸው ክብራቸው ናትና ጨረቃን ተጫምታለች።

 12 ከዋክብት ያለበት አክሊል የተቀናጀች፦ የእመቤታችንን ቅዱስ ሥዕል ስንመለከት በራስዋ ላይ 12 ከዋክብት ያለበት አክሊል አለ; አሥራ ሁለቱ ከዋክብት ብርሐነ አለም የሆኑት የአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ምሳሌዎች ናቸው። እመቤታችን የሐዋርያቱ ሞገሳቸው ናትና፤

አንቲ ውእቱ እህቶሙ ለመላእክት ትንቢቶሙ ለነብያት ሞገሰ ክብሮሙ ለሐዋርያት እሞሙ ለሰማእታት እንዲል

እመቤታችን የመላእክት እህት የነብያት ትንቢት የሐዋርያት ሞገስ የጻድቃን እናታቸው ናትና!!!








*ሃይማኖትህን ዕወቅ!
አማን አማን እብልክሙ ዐብይ ወግሩም ይዕቲ ሃይማኖት! እውነት በእውነት ይህች ሃይማኖት የፀናች ፅኑ ናት!
እነ ቅ/ገብርኤል ፀንተን እንቁም ብለው የፀኑባት ሃይማኖት እውነት በእውነት ይህች ሃይማኖት ድንቅ ናት! ሐዋርያዊ ቅብብሎሽን ጠብቃ የኖረችው የቀደመችቱ ሃይማኖት!
በእውነት ያለ ሐሰት ይህች ሃይማኖት ድንቅ ናት! ነብያት በደም ጻድቃን በሰማእትነት የጠበቋት፤ እውነት በእውነት ይህች ሃይማኖት ግሩም እፁብ ድንቅ ናት! ሐዋርያት ዞረው የሰበኳት! ከደገኞቹ ሐዋርያ አንዱ የሆነውም እንዲህ አለ፦
“ሩጫዬን ፈጽሜያለሁ ይማኖቴን ጠብቄያለሁ
የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል” 2ኛ ጢሞ. 3:4


ሀገረ ጥበብ የሆነችውን ይህችን ቤተክርስቲያን አልፎ አልፎ ሳይሆን ሁሌ እንደሚጠያየቁ ጓደኛሞች ምን ጎደለ? ብለን ልንጠይቃት ይገባል ፤ ከስር ከመሰረቱ አውቀን ልንረዳም ይገባል። በሚገባ ላወቃት እውነት በእውነት ይህች ሃይማኖት ድንቅ ናት!

“ሃይማኖትህን ጠይቅ፣ እወቅ፣ ደግሞም ጠብቅ”