Saturday, 11 February 2012

                        “እናታችንን ለሁለት እንካፈላት!”




ዘና ብላችሁ ተቀመጡና አንድ ታሪክ ልንገራችሁ፤








በነገሥታት ዘመን ነው አሉ አንዲት ደግ እናት ሁለት ወንድ መንታ ልጆችን ወለደች፤ ሁለቱም ካደጉ በኋላ አንደኛው ልጇ እጅግ ደግና ታዛዥ ሆነ፤ “የእናት ሆድ ዥንጉርጉር እንደ ነብር ፀጉር” እንዲል ሁለተኛው ልጇ ግን ከንቱ ልጅ ሆነ። ይህን ግዜ ያቺ ደግ እናት በጣም ተጨነቀች፤ እናት ናትና በሕጻንነቱ እንደምታደርገው ፀጉሩን እያሻሸች ያንን ከንቱ ልጅ ብዙ መከረችው፣ አስመከረችውም። ያ ልጅ ግን የከንቱ ከንቱ ሆኖ ቀረ። ከፍ ሲልም በወንድሙ ላይ ተነሳሳ፣ እናቱንም ጠላት። ከዕለታት በ፩ኛው ቀን ተነሳና “ሩቅ ሀገር መሄዴ ነው፤ እናቴን ግን ማጣት አልፈልግምና በሰይፍም ቢሆን ተቆርጣ ከወንድሜ ጋር ለሁለት እንካፈላት”! አለ፤ የሰፈሩ ሰዎች ጉድ እንግዳ ነገር ብለው እጃቸውን በአፋቸው ላይ ጫኑ፤ ሽማግሌዎችም ነገሩ አስጨነቃቸው፤ ትዕቢተኛንና ወራጅ ውሃን ቆመህ አሳልፍ እንዲሉ ጉዳያቸውን ወደ ንጉሡ አስተላለፉት፤ ንጉሡም እንደ ንጉሥ ሰለሞን ጠቢብ ነበርና ይህችን ደግ እናት ለደጉ ልጇ እንድትሆን ፈርዶ ያ ከንቱ ልጅ ግን ልብ እስከሚገዛ ድረስ እንዲቀጣ ትዕዛዝ አስተላለፈ።

ይህች ደግ እናት ቤተክርስቲያን ናት፤ ደጉ ልጅ ታማኝ ክርስቲያኖች ሲሆኑ እናታችንን ለሁለት እንካፈላት ያለው ልጅ ደግሞ ተሐድሶ” ናቸው፤



 እናታችንን ለሁለት እንካፈላት!

ተሐድሶዎች የሕንድ ቤተክርስቲያንን ለሁለት ለመክፈል የተጠቀሙበት ታክቲክ እጅግ ግሩም ነው! ይህንኑ ስልት አውሮፓዊያኑ በተሐድሶ ስም በኢትዮጲያ ቤተክርስቲያን ላይ ለመድገም እነሆ ደፋ ቀና እያሉ ነው። ለእኔ ብለህ ስማ እንዲሉ በሕንድን ቤተክርስቲያን ታሪክ የተሐድሶን እንቅስቃሴ እናያለን፦


ተሐድሶዎች በሕንድ ቤተክርስቲያን ተመሳስለው ገቡና ብዙ ደጋፊዎችን አፈሩ፤ ከጳጳሳት ፣ ከካህናት፣ከሰባኪያን ፣ከዘማሪያን፣ ከምዕመናን ግማሽ የሚያህለውን በራሳቸው እጅ አስገቡ። ድምጻቸውን አጥፍተው ውስጥ ለውስጥ ተስፋፉ። “ልብ ያሰበውን አፍ ይናገራል፤ ዓይን ያየውን እጅ ይሰራል እንዲሉ እያደር የተሐድሶን ስራቸውን በግልጽ መስራት ጀመሩ፤ በመጨረሻም የሚገርም ጥያቄ ጠየቁ፤ እኛ ተሐድሶን እንፈልጋለንና የሕንድ ቤተክርስቲያንን ከኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ጋር ለሁለት እንካፈላት!” ብለው ጮሁ፤ በየቤተክርስቲያኑም ረብሻ ፈጠሩ። ይህን ግዜ መንግሥት የሕንድ ቤተክርስቲያንን ንብረት ቆጠረ፣ ስንት ቤተክርስቲያን እንዳሉ፣ ስንት ገዳማት፤ ስንት ጥሬ ገንዘብ እንዳላቸው ቆጠረና እንዳለ ለሁለት ከፍሎ አከፋፈላቸው!

እንግዲህ ይህች ቢላዋ ናት በኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንም ላይ እየተሳለች ያለችው! ይህች ቢላዋ ስትሳል አልሰማችሁምን? ካልሰማችሁ ጥሩ ጥሩ የተሳሉ ቢላዎች አሉና በመቀጠል እናያቸዋለን፤

ተሐድሶ ልክ በሕንድ ቤተክርስቲያን ላይ በተጠቀሙት ፎርሙላ መሰረት የራሳቸውን ግሩፕ ከሰበሰቡ በኋላ ከቀሪው የኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ጋር መለየታቸውን በግልጽ ያሳውቃሉ፤ ከዛም የኢትዮጲያ ቤተክርስቲያን ትገባኛለች እያሉ ይጮሃሉ ማለት ነው! በሕንድ ቤተክርስቲያን ላይ እንዳደረጉት ሁሉ መንግሥት ቤተክርስቲያኒቷን ለሁለት እንዲያካፍላቸው ታላቅ ምኞታቸው ነው!


ከዚህ በተጨማሪ ተሐድሶ የሚጠቀሙበት ስልት ቤተክርስቲያንን ከሁለት አቅጣጫ ለመሳብ ሁለት ኃይሎችን በመጠቀም ነው፤
ይህም ከውጭ ወደ ውስጥ /በግልፅ ተሐድሶ ያስፈልጋል እያሉ የሚናገሩ ኃይሎች ሲሆን/ ሁለተኛው ኃይል ደግሞ ከውስጥ ወደ ውጭ /ተመሳስሎ በውስጥ የሚያገለግሉ ኃይሎች ናቸው/
ለዚህ ነው የትግሉን ሜዳ ቤተክርስቲያን ውስጥ ማድረግ አለብን፤ ከቤተክርስቲያን መውጣት ቀረ” እያሉ የሚፎክሩት።

እናታችንን ለሁለት እንካፈላት!

ይህን የረጅም አመት ሕልማቸውን እውን ለማድረግ ብዙ ድርጅቶችን በኢትዮጲያ ከፍተዋል፤ ከነዚህ ውስጥ የተወሰኑትን ማወቅ ግዜው ግድ ይለናል፦

/1/ ሐይማኖተ አበው፦ ይህ ማህበር የተቋቋመው በ1951 ዓ.ም ሲሆን እስከ 1963 ዓ.ም ድረስ የመናፍቃንን ስራ ሲቃወም የቆየ በጎ ማህበር ነበር፤ ይህን ስራውን ያዩ ተሐድሶዎች ግን ማህበሩን የዓለም ክርስቲያን ተማሪዎች /World Christian students federation/ አባል እንዲሆን አደረጉት፤ ቀስ እያሉ ሙሉ በሙሉ ወደ ራሳቸው አላማ አሰጠሙት!  ብዙ ጥፋት ካጠፉ በኋላ በ1980 ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሐይማኖት ሰብሳቢነት ቅዱስ ሲኖዶስ ተሰብስቦ ማህበሩን ዘጋው፤ በ1983 ለውጡን ተከትሎ ዘው ብሎ ወደ ቤተክርስቲያን ገባ፤ ቅዱስ ሲኖዶስ የዘጋውን በራሱ ፈቃድ እንዴት እንደገባ ሲጠየቅ ችግሬን አስተካክያለሁ ብሎ ነበር። ነገር ግን የተሐድሶን ልብስ ባለመቀየሩ ምክንያት በ1984 ዓ.ም በድጋሚ በሲኖዶስ አዛዥነት ተዘጋ። ዛሬስ? ይህ ሁለት ግዜ በሲኖዶስ የተዘጋ ማህበር ዛሬም የተሐድሶ ልብሱን እንደለበሰ በ2000 ዓ.ም በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ 50ኛ ዓመቱን እንዲያከብር ተፈቅዶለታል፤ የጋዜጣ ቢሮና የሚዲያ ሽፋን እንዲያገኝ ተደርጓል።

/2/ የመነኮሳት ማህበር፦ በ1990 ዓ.ም በኤግዚቢሽን ማዕከል ቆባቸውን እንደ ኮፍያ እያውለበለቡ በዘለሉት የስም መነኮሳት የተመሰረተ ነው። በኋላ መበታተን ቢያጋጥማቸውም አሁን ግን በአሜሪካ ቤተክርስቲያንን የመከፋፈል ስራቸውን በፍጥነት እያቀላጠፉት ይገኛሉ።

ብዙ የተሐድሶ ማህበራት ቢኖሩም ከብዙ በጥቂቱ ከረጅሙ በአጭሩ እነዚህ ናቸው፦ ማሕበረ በኩር፤ጮራ፣ፍኖተ ሕይወት ማህበረ መድኃኔ ዓለም፣የምሥራች አገልግሎት በኢትዮጲያ፣ ከሣቴ ብርሃን ….

እነዚህን የተሐድሶ ማህበራት በበላይነት ይዤ በአጭር ግዜ ውስጥ የኢዮጲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን በእጄ አስገባታለሁ! እያለ የሚፎክር የእንግሊዝ ፕሮቴስታንት ድርጅት ብቅ ብሏል!ይህ ድርጅት የሕንድ ቤተክርስቲያንን በመክፈል ሰይጣናዊ ልምድ ያለው ነው።



መርፌ የራሷን ቀዳዳ ሳታይ የሌላውን ቀዳዳ ትጠቅማለች!

አውሮፓዊያኑ ግብረ ሰዶማዊነት ኃጢአት አይደለም የሚባልበትንና ሰይጣን የሚመለክበትን ሃገር ይዘው ወደ ኢትዮጲያ መጡና ቤተክርስቲያን ትታደስ አሉ! ይህ ነው መርፌ የራሷን ቀዳዳ ሳታይ የሌላውን ቀዳዳ ትጠቅማለች! የሚያሰኘው። መጽሐፍ ቅዱስን ለድሃ ሃገራት በነጻ የሚያድሉትስ ለመጽደቅ ነውን? ይህ “ኦ ዓቃቤ ሥራይ ፈውስ ርእሰከ” ያሰኛል፤ ሉቃስ [4: 23] ለራሳቸው ጽድቅና ኩነኔ አለ ብለው የማያምኑ ሲሆን ከገንዘባቸው ከፍለው ለእኛ ሐዋርያ የሚልኩልን እነሱ የማያምኑበትን ጽድቅ ለእኛ ከየት አስበው ሊያሰጡን ይሆን? ይህን ማሰብና መጠየቅ ያለባቸው እነሱ ሳይሆን እኛ ነን፤ እነሱማ ስራቸውን እየሰሩ ነው።


“የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በአፍሪካዊያን”
የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በአፍሪካዊያንና በካረቢያን እጅግ እየተፈለገች ነው፤

አውሮፓዊያኑ በሃይማኖት ስም አፍሪካዊያንን ወደ ሃገራቸው በመውሰድ ስቃይ ስላበዙባቸው አፍሪካዊያን በአውሮፓዊያኑ ላይ ጥላቻ አድሮባቸዋል፤ በዚህ ምክንያት አፍሪካዊያኑ የአባቶቻቸውን እምነት ፍለጋ ሲባዝኑ ኖሩ፤ የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሐዋሪያዊ ቅብብሎሽን ጠብቃ የቆየች ጥንታዊት መሆኗን ስለሚያውቁም መብራት እያበሩ ኢትዮጲያን ፍለጋ መጡ!
እኔ ባለሁበት በለንደን ከተማ እንኳን የካረቢያን ወገኖቻችን ወደ ኢትዮጲያ በመሄድ ዋልድባ ገዳም ገብተው ሥርአተ ቤተክርስቲያንን ክህነትንና ዲቁናን ተምረው የመጡ ብዙ ሰዎች አሉ፤ እነዚህ ወገኖቻችን በቅዱስ ሲኖዶስ ፍቃድ በእንግሊዝ ሃገር ቤተክርስቲያን ተመስርቶ ብዙ ወገኖቻቸውን እያስተማሩ ነው።  ካህናቱና ዲያቆናቱ ድምጻቸው እንኳን ሲሰማ ግሩም የቤተክርስቲያን ጣዕም አለው!


የኢትዮጲያ ቤተክርስቲያን ከጠነከረች አፍሪካዊያን በጥላዋ ይጠለላሉ፤ ስለዚህም ይህችን ተስፋ የተጣለባትን ቤተክርስቲያን አውሮፓዊያኑ ተረባርበው ማጥፋት ይመኛሉ፤ ይህንንም ለመፈጸም እየሰሩ ነው። IMF ውስጥ ለ12 አመታት በከፍተኛ ኃላፊነት ሲሰራ የነበረው ቡድሆ የተባለ አንድ ሰው የሰራቸውን ስራዎች እንዲህ ገልጾታል፦
I may hope to wash my hands of what in my mind eye is the blood of millions of poor people; the blood is so much; you know it runs in rivers. Sometimes I feel that there is not enough soap in the whole world to clean me.
/New york new Horizons press, 1990/

/በሚሊዮን ለሚቆጠሩ አፍሪካዊያን ላይ ያለኝ ደም እንደ ወንዝ ይፈሳል እጅግም ቡዙ ነው፤ አንዳንዴ ሳስበው ይህን ደም ከእጄ ለመታጠብ በአለም ላይ ያሉ ሳሙናዎች የሚበቁ አይመስለኝም/

+++ ከእኛ ምን ይጠበቃል? ድርሻችንስ ምንድን ነው? +++

/1/ ዋናው የተሐድሶ አላማ የሕንድን ታሪክ በኢትዮጲያ ቤተክርስቲያን ላይ መድገም ነው፤ ይህን ለማድረግም ከላይ እንዳየነው ብዙ ደጋፊዎችን በማሰባሰብ ቤተክርስቲያኒቷ ትገባኛለች ብለው ለሁለት እንድትከፈል እጅግ ይጎመጃሉ፤ ስለዚህም የሰባኪ ደጋፊ ፣የመዘምራን ደጋፊ በአጠያላይ የግለሰብ ደጋፊ መሆን እንደሌለብን ከምንግዜውም በላይ ልናውቅ ይገባናል!

/2/ ይህን የተሐድሶ አላማ በሚገባ ነቅቶ መከታተልና በሚገባ ተገንዝቦ ለሌሎችም ማሳወቅ! /ለምሳሌ ይህችን ጽሁፍ በኢሜልም ሆነ በፌስ ቡክ ላይ ሼር ማድረግ እንደ ምሳሌ ሊታይ ይቻል ይሆናል/

/3/ ተሐድሶዎች ቤተክርስቲያንን እንዳይከፍሏት ነቅቶ መጠበቅ! ምንም አይነት እድልም አለመስጠት።

/4/ ሰ/ት/ቤቶችንና ጉባኤዎችን በቅርብ መከታተል፤ በፌስ ቡክ የምናነባቸውን የግለሰብ ጽሁፎች የተሐድሶ አንደበት እንዳልሆኑ ለይቶ ማወቅ፤ ሥጋ በል ዕጽዋት አሉና ነቃ ብሎ ማየት!

/5/ የእምነት ጸሎት ኃይልን ታደርጋለች እንዲል ስለቤተክርስቲያን ሠላምና አንድነት፤ ከፈተናም እንድትጠበቅ አጥብቆ መጸለይ! በአጠቃላይ እያንዳንዱ የቤተክርስቲያኒቷ ታማኝ ልጆች በሙሉ በዚህ ወሳኝ የፈተና ወቅት ሁሉንም የሥራ ድርሻ ለመስራት ቆርጦ መነሳት፤

ለቤተክርስቲያናችን “ሰላም ክብርና ሞገስ
ለዘለዓለም ይሁን አሜን!!!
-//-