Saturday, 9 June 2012

“እስኪ እንደ ሰዎች እንኑር”



ዘና ብላችሁ ተቀመጡና አንድ አሪፍ ታሪክ ላውጋችሁ!

የጫካ ንጉሥ እየተባለ የሚጠራው አንበሳ አስፈሪ ድምጹን ሲያስተጋባ ብዛት ያላቸው ወንድ ፣ ሴቶችና ግልገል አናብስት በፍጥነት ወደ እርሱ ተሰበሰቡ።

ንጉሥ አንበሳም አሁን የጠራዋችሁ በሕልሜ አንድ ነገር ስላየሁ ነው! አላቸው።

ምን? ምን ? አሉ ሁሉም ለመስማት እየጓጉ፤

“እስኪ እንደ ሰዎች እንኑር!” አለ በሕልሙ ያየው እንደ ሰው መኖር ነበርና። ከአናብስቱ መካከል ሕልም ፈቺ ተጠራና ሕልሙን እንዲፈታ ታዘዘ።

እንዲህ ብሎ መላምቱን ጀመረ “ልፋ ያለው በሕልሙ ክብደት ይሸከማል!”  አሁን ማን ይሙት እንዴት እንደ ሰው መኖር እንችላለን? እኛ እርስ በእርሳችን አንዋጋም፤ እርስ በእርሳችን አንበላላም። ከአራዊት መካከል እርስ በእርሱ የሚጣላ ማን ነው? አስባችሁበት ታውቃላችሁ? አናብስቱ እርቧቸዋል መሰል እያዛጉ ኧረ ማንም የለም” አሉ። ቀጠለች ሁለተኛይቱ ደቦል፤ “እኛ ሁሉን ነገር የምናደርገው በሕብረት ነው። የጣልናቸውን ግዳዮቻችንን ተካፍለን ነው የምንመገበው። ከእኛ ጋር ባይደክሙም ለታላላቆቻችንና ለታመሙት፣ ለግልገሎቻችንም እናካፋላቸዋለን አለች እየተኩራራች። ይህን ውይይታቸውን ከቅርብ ኾኖ የሚሰማው አያ ጅቦ “ጅብ እንዃን ጓደኛውን ይጠራል እንዲል ስንበላ እንካፈላለን” ብሎ ጓደኞቹን ሰብስቦ የዕለቱን ምርጥ እራት ያነክት ጀመር። “ሰው የተባለው ፍጡር ግን እንጃ! በተለይ ከሀገሩ ሲወጣ ብዙ ይታማል አለ አያ ጅቦ የያዘውን አጥንት እየዘነጣጠለ።

ይኽን ሲወያዩ ከሩቅ ኾኜ እሰማቸው ነበርና አንድ ነገር ትዝ አለኝ። ባለሁበት በለንደን ከተማ በአንድ ሱፐርማርኬት ውስጥ ማናጀር ኾኖ የሚሰራ ሐበሻ ነበር። አንዲት ልጅ ስራ መስራት እንደምትፈልግ በዚሁ ሱቅ ለምትሰራው ለስፔናዊቷ ሴት ትጠይቃታለች። ስፔናዊቷም ማናጀሩኮ የሀገርሽ ሰው ነውና ጠይቂው አለቻት። ልጅቷም ይኽን ተስፋ ይዛ የሀገራን ሰው ስራ ጠየቀችው። የሀገሯ ሰው ግን ፊቱን እንደ ፎጣ አጣጥፎ ስራ የሚባል የለም” ብሎ ጥሏት ሄደ። “ጅብ እንዃን ጓደኛውን ይጠራል” የሚለው የአያ ጅቦ ተረት ትዝ አለኝ። ቢችል ስራውን ቢያስገባት ባይችል ሴት ናትና አክብሮ ቢያነጋግራትና ሌላ የስራ ቦታዎችን ቢያሳያት ምን አለበት? እስኪ በለንደን ወዳለው ቻይና ታውን ሂዱ፤ ቻይናዊያን እንደመብዛታቸው ቻይና የገባችኹ ይመስላችኋል። እኛ ቤት ግን ይኽ ኹሉ ኪሳራ ነው!      

አንበሳው ሲያጋሳ ከዚህ ሐሳቤ ነቃኹ።

ንጉሥ አንበሳ እያጋሳ የሚያስፈራውን ሳውንድ ትራኩን በረጅሙ ለቀቀና “በሉ ተነሱ አኹን! እንደ ሰው ለመኖር በተለያዩ ብድኖች ውስጥ እንከፋፈልና እርስ በእርሳችን በመዋጋት እርስ በእርሳችን እንበላላ!” አለ። አናብስቱ ኹሉ “ሰማይ አይታረስ ንጉሥ አይከሰስ” ብለው የንጉሥ አንበሳን ትዕዛዝ ለመፈጸም እንደ ሰውም ለመኖር ሆ ብለው ተነሱ።


አይ ከዚያማ! አናብስቱ እንደ ጉድ ተከፋፈሉ! እንደ ጉድ አጋሱ! እንደ ጉድ ተባሉ! እንደ ጉድ ተዘነጣጠሉ! እንደ ጉድ አለቁ!

እስኪ እንደ ሰዎች እንኑር!” የምትለዋ የንጉሥ አንበሳ ሕልም ይህን ኹሉ ወዘተ ተረፈ ችግሮችን አስከተለ። ለነገሩ ሕልም ፈቺውም ኾነ ሌሎቹ አናብስት ቢሆኑ እንደ ሰው መኖር እንደማይችሉ አስቀድመው ተናግረውኮ ነበር!

የኾነው ይሁንና እንደ ሰው ለመኖር አስበዋልና እንደ ሰው ለማንበብ ታላቁን መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ ጀመሩ፤ በአንድ ወቅት የአናብስት ሸንጎ ተጠራና ንጉሥ አንበሳ ሊያነብላቸው ተነሳ፤ የንጉሥ አንበሳ ዓይን በመጀመሪያ ያረፈው
ገላትያ 5:15 ላይ ነበር፦

“እርስ በእርሳችሁ የምትነካከሱና የምትበላሉ ከሆነ እርስ በእርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ!!

ይህችን ቃል ደግሞ ላነበባት ትገርማለች!

ንጉሥ አንበሳ ይህ ቃል ገረመው! ራሱንም በአግራሞት ነቀነቀ። አሁንም ታላቁን መጽሐፍ ገለጥ አደረገ። የንጉሥ አንበሳ ዓይን ያየው ይህችን መልዕክት ነበር።

“የፍቅር የአንድነት ባለቤት እግዚአብሔር ሰይጣንን በእጃችሁ ጭብጥ በእግራችሁ እርግጥ አድርጎ ያጥፋላችሁ
ሮሜ [16:20] ይህች ቃል ደግሞ ላነበባት ትገርማለች!

“ዲያቢሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ በዙሪያችሁ ይዞራል” 1ኛ ጴጥሮስ [5: 8] የሚለውን ሲያነብ አቶ አንበሳ እጅግ ተናደደ። ዲያቢሎስ በስሜ ነገደብኝ ብሎ የተለመደውን ሳውንድ ትራክ ለቀቀ። እንደ ጉድ ደነፋ ተቆጣም። ቢችል በክርኑ ደቁሶ በመንጋጋው አድቅቆ ድራሹን ቢያጠፋው ደስ በተሰኘ ነበር።

አንድነት ያገባል ገነት!”

እናቴ ይህችን አባባል ትወዳት ነበር። አንድነት ያገባል ገነት!

ትዝ አይላችሁም የቆሮንቶስ ነዋሪዎች? በአንዲት እናት ቤተክርስቲያን እየኖሩ በአራት ግሩፕ ተከፍለውኮ ነበር።

አነ ዘጳውሎስ ወአነ ዘአጵሎስ ወአነ ዘኬፋ ወአነ ዘክርስቶስ
እያሉ እንደ አንቤማ ተከፋፈሉ።



1ኛው ግሩፕ መጀመሪያ ያስተማረን የጳውሎስ ተከታይ ነን ይሉ ነበር።

2ኛው ግሩፕ ደጋግሞ ያስተማረን የኦሪት ሊቅ የኾነው የአጵሎስ ተከታይ ነን አሉ።

3ኛው ግሩፕ የሐዋርያት አለቃ ለኾነው የጴጥሮስ ተከታይ ነን አሉ።

4ኛው ግሩፕ ከነአበዛሽ ማን ይገዛሽ እንዲል የክርስቶስ ተከታይ ነን አሉ። ክርስቶስን ከሐዋርያት ደምረው ተከታዩ ነን አሉ።


ቅ/ጳውሎስም ይህን መለያየትና መከፋፈል አይቶ እንዲህ እያለ የቆሮንቶስ ክታቡን ጻፈላቸው፦ ለመሆኑ ሐዋርያት ዓለምን ዕፃ በዕፃ ተከፋፍለው ሲያስተምሩ ልባቸው ተከፍሎ ነበርን? አንድነታቸውስ ተከፋፍሎ ነበረን? አሥራ ኹለቱ ሐዋርያት ዓለምን ዕፃ በዕፃ ተከፋፍለው ሲያስተምሩ ክርስቶስ 13ኛ ኾኖ አስተምሯልን? ታዲያ ክርስቶስን እንደ ሐዋርያት ቆጥራችሁ እኔ የእገሌ እኔ የእቶኔ የምትሉ ወፌ ወለፌ ማለቱን ከየት ተማራችሁት” ብሎ ክታቡን ላከላቸው።  የቆሮንቶስ ነዋሪዎችም እርስ በእርሱ ያልተደጋገፈ ግድግዳ አይቆምም” ብለው መለያየትን ናቁ። አንድነትን መረጡ። በአንድ ቃል ተናጋሪ በአንድ ልብ መስካሪ ኾነዋል።


በስተመጨረሻ አቶ አንበሳ ይህን አጭር ንግግር አደረገ። “ከንቱ ሕልም አልሜ ከንቱ ጥፋት አጥፍቼያለሁና ይቅር በሉኝ፤ ከዛሬ ጀምሮ እስኪ እንደ ሰው  እንኑር የምትለው አዋጅ ይሰረዝልን፤ በምትኩ እንደ አመላችን ፣ እንደ ጸባያችን ፣ እርስ በእርሳችን ሳንዋጋ እርስ በእርሳችን ሳንበላላ እንደ አንበሳነታችን እንኑር!” አለ።

ጭብጨባው እንደ ጉድ ቀለጠ።

የአቶ አንበሳ ተፈጥሯዊ ሳውንድ ትራክ እንደ ጉድ ተለቀቀ።

ሌሎቹም እንደ ጉድ ተቀበሉት።

ግርማ ሞገስ ያለው የአናብስቱ ግሳት ጫካዋን በአንድ እግሯ አቆማት።  

ከዚህች ቀን ጀምሮ እንደ ሰው ሳይሆን እንደ አንበሳ መኖር ጀመሩ!