Friday, 6 July 2012

ከባድ ጦርነት ታውጆብናል!



ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት ብለው የተነሱ የዓለማችን ኃያላን መንግሥታት ካልተቧቀስን አናርፍም ብለዋል። ዛሬ ጠዋት በወጣው የቢቢሲ ዜና ለዘመናት የተፈራው ታላቅ ጦርነት እንደሚነሳ ምንጮች እየዘገቡ ነው። የምን መታገስ ነው ሲሰበር ይንሰጠር ያሉም አልጠፉም። ቀን ሲደርስ አንባ ይፈርስ እንዲሉ የጦርነቱ ቀን ደረሰ።

ሥጋ ሠራዊቱን ዘመዶቹን እነ ዘረኝነትን እነ መከፋፈልን ፣ ዝሙትን፣ ቅናትን ፣ ምቀኝነትን አስከትሎ ደረቱን ነፍቶ ልቡን አሳብጦ ውረድ እንዋረድ እያለ ነፍስን ሊወጋ ይሸልል ጀመር። እትዬ ነፍስም በተራዋ ሠራዊቷን አስከትላ ዘመዶቿን እነ ፍቅርን እነ መቻቻልን ፣ ደግነትን ፣ ድንግልናን ፣ ጸሎትን ፣ስግደትን ፣ ጾምን ይዛ እንዲህ እያለች መፎከር ጀመረች።

አንተ ከንቱ በስባሽ አንተ ከንቱ አፈር፤
ሥጋ ለበሬ ነው ና እና በእኔ ተቀደስ።
አልመለስ ብትል ብትደነፋማ
ሞክረኸኝ እየኝ ጀግንነቴን እንካ

አለች እትዬ ነፍስ እየተውረገረገች።

ሥጋ ምድራዊ ነህ ነፍስ ሰማያዊ።

ሥጋ በስባሽ ነህ ነፍስ ዘላለማዊ።

ሥጋ ሟች ነህ ነፍስ ሕያው።

እንዲያው ወፈር ስትል ለዓይን ብትማርክ
ጉራህ አልተቻለ መቀመጫም አጣን።

እያለች ነፍስ ልቧ ቅቤ እስኪጠጣ ድረስ የልብ የልቧን እንደ ጉድ አዘነበችው።

አቶ ሥጋ በበኩላቸው አሸሼ ገዳሜ እሪ ብለው ጮኹ
አንቺ ነፍስ ዋ…. ዋ…. ዋ ዛሬ ጉድ ሳይፈላ
በትዕቢት ታውረሻል ዓይንሽ ይብራ እያሉ አብዝተው ፎከሩ።


እትዬ ነፍስ ለአቶ ሥጋ አንድ ታሪክ እንዲህ ብለው አወጓቸው “ሰውዬው ድንኳን ሰባሪ ነው አሉ። ሁለት ቦታ የአቡዬ ድግስ እንዳለ ይሰማል፡፡ ሰዓቱ ሲደርስ እንደ ተጠራ ሰው የክት ልብሱን ለብሶ ይወጣል፡፡ የሁለቱም ድግስ የተለያየ ቦታ ነበር፡፡ ወደ አንደኛው እየሄደ ሳለ የዚያኛው ድግስ ቢበልጥስ ብሎ ተመለሰ፡፡ ወደዚያም ጉዞ እንደ ጀመረ የዚህኛው ምስር ሆኖ ያኛው ቁርጥ ቢሆንስ ብሎ እንደገና ተመለሰ፡፡ እንዲህ ሲያመነታ ሰዓቱ እያለፈበት ሄደ። በዚህ ጊዜ በመካከለኛ መንገድ ላይ ቆመና በጭንቀት ‹‹አቡዬ የዛሬን ብቻ ለሁለት ይሰንጥቁኝ›› ብሎ ጸለየ ይባላል!”

ዓለምንም እግዚአብሔርንም መያዝ አይቻልም፡፡ ሁለት አባሮም አንድ መያዝ አይቻልም፡፡ ሥጋንም ነፍስንም እሩሩ ማለት አይቻልም አሉ እትዬ ነፍስ አቶ ሥጋን እንደ ሕፃን እሹሩሩ እያሏቸው። ሕፃን ልጅ እናቱን አለቅሽም እያለ ገበያና ሥራ እስኪከለክል እንዳላስቸገረ፣ ሲያድግ ደግሞ እናቱን አትጠብቂኝ እያለ እንደሚፎክር እኛም እንደ ሕፃንኑ መሆን አንችልም አሉ እትዬ ነፍስ እያፌዙ። እዚህ ጋ አቶ ሥጋ አጎረመረሙ። እትዬ ነፍስ ግን አቶ ሥጋን ማናደድ እንደ ትርፍ ጊዜያቸው ያስደስታቸዋልና ማናደዱን እንዲህ ሲሉ ቀጠሉ፦

 “ዓለማዊ ሰዎች ዓለምን ከፍ አድርገው እሽኮኮ ቢሏት በጀርባቸው ቢያዝሏት፣ እሹሩሩ ዓለም ቢሏት አይገርምም። ዓለማዊ ናቸውና ዓለምን ቢወዱ አይገርምም። ዓለም ራስዋ የሚገርማት ግን መንፈሳዊ ተብለን ዓለምን እሽኮኮ እናድርግሽ ስንላት ነው። በጀርባችን እንዘልሽ እሹሩሩ ዓለምዬ እንበልሽ ስንላት ዓለም ራስዋ ከትከት ብላ ትስቅብናለች! በዓለም ውስጥ ብንኖርም ዓለም በእኛ ውስጥ ከኖረች ግን አደጋ ነው! ደብረ ታቦር ላይ ዘምረው ቀራንዮ ላይ የከዱ ብዙዎች አሉአሉ እትዬ ነፍስ እንደ ምሁር ከረቫታቸውን ከፍ ዝቅ እያደረጉ።

ይህን ጊዜ አቶ ሥጋ ቦግ አሉ!! ንዴታቸው እንደ ጉድ ተቀጣጠለ። ወደ እትዬ ነፍስ ተንደረደሩና በያዙት ቢላ ክፉኛ ወግተው ዘነጣጥለው ፣ ዘነጣጥለው ገነጣጥለው ሊለቋቸው አሰቡና ተውት! እትዬ ነፍስን በቢላ ሳይሆን በቅኔ ወጋ ሊያደርጓቸው ፈለጉ። ስለ ሥጋና ነፍስ ግዕዝ ምን እንዳለ አልሰሙም እንዴ?” አሉ አቶ ሥጋ እትዬ ነፍስን በፌዝ እያዩ።

ደግሞ ምን አለ? እትዬ ነፍስ ጠየቁ።

ስለ አንቺና እኔ ግዕዝ እንዲህ ብሏል

“ኢትቀውም ነፍስ ዘእንበለ ሥጋ

ፐ.. ፐ.. ደግሞ ምን ማለት ይኾን? አሉ እትዬ ነፍስ እየተውረገረጉ።

አቶ ሥጋም ነፍስ ያለ ሥጋ አትቆምም ማለት ነዋ” ብለው በረዥሙ ሳቁ። አሁን ደግሞ እትዬ ነፍስ ቦግ አሉ። ቦግ ቦግ ማለት የሥጋና የነፍስ ልማዳቸው ሆነ። አይ ከዚያማ ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት ብለው እንደ ጉድ ተቧቀሱ፣  እንደ ጉድ ታገሉ ፣  እንደ ጉድ ተፋጁ…. 


ቢቢሲ የዘገበው በሥጋና በነፍስ መካከል የተፋፋመውን ይህን ጦርነት ነበር!

ሰው የተፈጠረው ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋ ነው። እነሱም እሳት ፣ ውኃ ፣ መሬት ፣ ነፋስ ናቸው።

አራቱ ባሕርያተ ሥጋ እርስ በእርሳቸው ተቃራኒ መስተፃርራን ናቸው። እሳት በውኃ ይጠፋል። እሳት ውኃን ያሞቃል። ነፋስ መሬትን ያንቀጠቅጣል። መሬት ተራራዎች ነፋስን ያቆማሉ። እንዲህ እርስ በእርሳቸው መስተፃርራን ናቸው። የሰው ልጅ ከነዚህ እርስ በእርሳቸው ተቃራኒ ከሆኑ ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋ ስለተፈጠረ ሰውነቱ የጦርነት ከተማ ነው” ይባላል። ሥጋና መንፈስ የሚዋጉበት ታላቅ የጦርነት ከተማ የሰው ልጅ ነው።

የነፍስ ሽለላ መቆሚያ አጣ
ትዘልፈው ዠመር ሥጋን እንዲህ ብላ

አልሰማህም ወይ አላለበብክም ወይ
ጳውሎስ በኤፌሶን ምን ብሎ እንደነበር?


ቅ/ጳውሎስ በሮማ እስር ቤት ታስሮ እያለ የእስር ቤቱን ጠባቂ እያየ መልዕቱን እንዲህ ብሎ መጻፍ ዠመረ።

የእምነት ጋሻ አንሱ ፤ የመዳንን የራስ ቁር አድርጉ፤ የመንፈስን ሰይፍ ያዙ። እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው።ወገባችሁን በእውነት ዝናር ታጥቃችሁ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ በሰላመ ወንጌል ተጫምታችሁ ቁሙ። ጦርነቱ ከሥጋና ከደም ጋር አይደለም ከዚህ ዓለም ገዥ ከሆነው ከዲያቢሎስ ነው እንጂ ኤፌ [6: 14]


ምርጥ እቃ የተባለው ንዋየ ኅሩይ ቅ/ጳውሎስ የእስር ቤቱን ወታደር በማየት ብቻ ሚስጢር ያለውን መልዕክት ጽፏል።
ሮማዊያን ወታደሮች የሚለብሱት የጦርነት ትጥቅ ዘመናዊ ነበር። የራስ ቁር ማለት ከብረት የተሰራ በራስ ላይ የሚደረግ ሞተረኞች የሚያደርጉት እንደ ሄልሜት ያለ ነገር ነው። ዝናር ማለት ወገብን መታጠቂያ ነው። ጥሩር ማለት ከብረት የተሰራ የደረት መከላከያ ነው።


ይኼ ኹሉ ዝግጅት ጦርነት ስላለ ነው። ጦርነቱም በሥጋና በነፍ መካከል ነው። ሥጋ ሲያሸንፍ መበላላት ፣ መቦጫጨቅ ፣ መለያየት ፣ መነካከስ ፣ ዝሙት ፣ ዘረኝነት ምቀኝነት ጥላቻ ይሰለጥናሉ። ነፍስ እንደምንም ታግላ ተፍጨርጭራ ስታሸንፍ ፍቅር ፣ ሰላም ፣ ትህትና ፣ ትዕግስት ፣ ደግነት ይሰለጥናሉ። ለዚህ እኮ ነው ቅ/ጳውሎስ “ሥጋዬንም ለነፍሴ አስገዛዋለሁ” ያለው። 1ኛ ቆሮ. [9: 26]

       እነኾ የአቶ ሥጋና የእትዬ ነፍስ ጦርነት እስከ አለም ፍጻሜ ይቀጥላል። በመሃል እየገባን የጦርነቱን ዘገባ በትኩሱ እንዘግባለን። ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ሰበር ዜና እንደደረሰን ሥጋ በጦርነቱ ድል እየቀናው ነው። አያሌ ነፍሳት ዳግም እንዳይቆሙ ኾነው ተወግተው ቆስለዋል። የሕክምና ባለሙያዎቹ ካህናትም የቆሰሉትን ነፋሳት ለማከም ደፋ ቀና እያሉ ነው። የቀይ መስቀል ሠራተኞች መምህራንና ዘማርያንም የተቻላቸውን ለመርዳት እየተፋጠኑ ይመስላል። እንዲህ የተረዳችውም ነፍስ እያገገመች ትመስላለች።

ነፍስ ሥጋን ክፉኛ ልትወጋው ተንደረደረች!

አያያያያ ነፍሴ እንዴት ያለ ግሩም ቅጣት ምት ነበረች!

ግን ተስታለች!

ተስፋ

ለለፋ

ትመጣለች

ፊሽካ ሳይነፋ

እያለች ነፍስ አሁንም የሞት ሞትዋን ታግላ ተነሳች።

ማን ያሸንፍ ይኾን? 





ክርስትና እስልምና በኢትዮጲያ

አንድ የእስላም ባለ ሀብት ቤተክርስቲያን ለማሰራት ገንዘባቸውን ሰጡ አሉ። ቤተክርስቲያኑ ከተሰራ በኋላም በየአመቱ ኩንታል ጤፍ እየላኩ በዓላችሁን አክብሩበት ይሉ ነበር! እስላሙ ሕብረተሰብም በጉልበቱ ቤተክርስቲያን ሲሰራ ታይቷል። ክርስቲያኑም እንዲሁ ከእስላም የሃይማኖት መሪዎች ጋር በመሆን መስጊድ ሰርቷል። ይህ ነው ኢትዮጲያዊ ውበታችን!! ይህ ነው ከዓለም የሚለየን ውበታችን!!

ናይጄሪያ ነዳጅ ከማግኘትዋ በፊት ሰላም ነበረች። ነድጅ ስታገኝ የውጪ ኃይል ሰርገው ገቡና ከፋፈሏቸው። አይ ከዚያማ! እንደ ጉድ ተከፋፈሉ! እንደ ጉድ ተባሉ! እንደ ጉድ ተዘነጣጠሉ! እንደ ጉድ አለቁ! ይህን አታሳየኝ አለች ሴትዮዋ ይህንንስ ከኛ ያርቅልን። አንድነታችንና መቻቻላችን የሚፈተንበት ጊዜ አለ። የውጪ ኃይሎች ሰርገው ሲገቡ እንደ ጉድ እንፈተናለን እንደ ጉድ ብንከፋፈል እንደ ጉድ እናልቃለን ፣ እንደ ጉድ አንድ ብንሆን እንደ ጉድ እናድጋለን።

በፌስ ቡክ እና በ you tube ላይ የአክራሪነት መልእክት ያቀነቀኑ አሉ። እንጋደል፣ እናቃጥል፣ እንግደል የሚል ዜማ አውጥተው ነጠላ ዜማቸውን በቅርቡ የለቀቁ አሉ። ቢቻል ኦርጂናል ሲዲውን ካልሆነም ኮፒውን እንድንገዛ ብዙ አስተዋውቀዋል!  እውነተኛይቱ ሃይማኖት ግን እንዲህ አትልም። እውነተኞቹ የእስልምና አባቶች አክራሪነትን ስላልመረጡ ከስራቸው ተባረሩ። ለብዙ ዘመናት በየመስጊድ ጸሎት ሲያሰሙ የነበሩ ኢማም አክራሪ ስላልሆኑ ተባረዋል። እውነተኛቹ የእስልምና አባቶችና የእስላሙ ሕብረተሰብ የዋህ ናቸው። በአክራሪ ስም ቤተክርስቲያንን የሚያቃጥሉና ሰውን የሚገድሉ መጥፎ ፎቶዎችን በሕሊናችን ቀርጸዋል እንጂ የእስላሙ ሕብረተሰብ ማን እንደሆኑ የዋህ የሰላም ሰዎች እንደሆኑ በሚገባ እናውቃለን!

ቅ/ራጉኤል ቤተክርስቲያን ባሰራው ት/ቤት በምማርበት ጊዜ ከጎናችን መስጊድ አለ። ይህ መቻቻል ነው። በሌላው ዓለም ይህን እናድርግ ቢሉ ተባልተው ያልቃሉ እንጂ ይህ አንድነት የላቸውም። ባለሁባት በለንደን ከተማ የእስላም ሰፈር ለብቻው አለ። ክርስቲያኑ ደግሞ በተለየ ሰፈር ይኖራል። ይህ በሀገራችን ያለውን መቻቻል ፍንትው አድርጎ ያሳየናል።

 ሙሐጅር ለማ የሚባል ጓደኛ ነበረኝ። ከልጅነት ጀምሮ አብረን ነው ያደግነው። ትንሣኤ ሲሆን እኛ ቤት አይቀርም። እስላም እንደመሆኑ ለጓደኛዬ ብቻ ተብሎ የሚሰራ ምግብ አለ። የእስላም በዓል ሲሆን ደግሞ ቤታቸው እሄዳለሁ። እናትየው ለእኔ ብቻ ብለው የሰሩትን ምርጥ ምግብ እየደጋገምኩ እበላለሁ። ይህ ነው መቻቻል። ይህ ነው አንድነት። ይህ ነው የኢትዮጲያ ውበት። ክርስቲያኑ ሠርግ ቢደግስ ለእስላሙም ብሎ የተለየ ምግብ ያዘጋጃል። እስላሙም እንዲሁ። ልዩነታችን ውበታችን ነው! እዚህ ጋር እውነቷን መናገር አለብኝ። ስለ እስልምና እምነት ያለኝ አመለካከት የተዛባ ነበር። ለምን ቤተክርስቲያን ያቃጥላሉ፤ ለምን ሰው ይገድላሉ? ለምን? ምን ዓይነት ሃይማኖት ነው? የሚል የሕሊና ጥያቄ ነበረኝ። ይህ አመለካከቴ ግን በፍጹም ትልቅ ስህተት መሆኑ ገብቶኛል። ሃይማኖቱ ይህን አይልምና። እውነተኞቹ የእስልምና ሰዎች እምነታችን ይህ አይደለም እያሉ ኡ ኡ ብለው ሲጮሁ ዓይተናልና። ይህን ሁላችንም መረዳት ዓለብን። አክራሪ ነኝ የሚለ የኢትዮጲያ ጠላት ነውና በክርስቲያኑም ሆነ በእስላሙ ሕብረተሰብ መገለል አለበት።

ሁሉም ዜጋ እንዳይዘናጋ አለች ሴትዮዋ!


ከእስልምና ወደ ክርስትና የተቀየረ አንድ ሰው አውቃለሁ። ይህ ሰው መላ ዘመኑን  አክራሪ በሚባሉ ሰዎች እየተሰደደ ነው። የሃይማኖት ነጻነት የለም እንዴ? አንዱ እስላም ቢሆን እንዴት ብዬ መፎከር የለብኝም። የሰው ልጅ ክቡር ነውና ሃይማኖቴን እንደ ኮምፒዩተር ዳውንሎድ ላደርግበት አልችልም። ሲጀመር ፈጣሪ የሰጠውን ነጻነት የምነፍገው እኔ ማን ነኝ?  ፈጣሪ ከእውነተኛይቱ ሃይማኖት ውጪ ያሉትን ሰዎች ላጥፋ ቢል የእኛን እርዳታ አይፈልግምና!! ብዙ ሰዎች ያልተረዱት ይህንን ነው። ለሃይማኖት ተቆርቋሪ የሆኑ እየመሰላቸው ሃይማኖታቸውን ያስንቃሉ ያስገመግማሉም። ሃይማኖታቸው ስለ ፍቅር እያስተማራቸው እነሱ ግን ሕገ ወጥ ሕግ አስከባሪ ይሆናሉ!

  በየቤቱ ወረቀት እየተበተነ አክራሪ ሁን ማለቱንም የሃይማኖት አባቶች ተቃውመውታል። ይባስ ብሎ ከሃይማኖትህ ውጪ ጓደኛ አትያዝ ማለት የጀመሩም አልጠፉም። አንዳድ ጊዜ ደግሞ የፌስ ቡክ ጦርነትም አለ። በፌስ ቡክ የሚከራከሩ ሰዎች አይገርሟችሁም? አንዱ ይነሳና እኔ እምነቴ ክርስቲያን ነው ይልና ክርስቲያን ያላስተማረውን የሚተርክ አለ። ሌላውም እስላም ያላስተማረውን የሚተነትን አለ። አንዳንዶች ባለማስተዋልም ሆነ ሆን ብለው ሀገርን የሚያጠፋና የማይጠፋ እሳት  የሚያቀጣጥሉ አሉ። እነዚህ ሰዎች የኢትዮጲያና የሰላም ጠላቶች ናቸውና ሊገለሉ ይገባቸዋል። እነዚህ በሕሊና አናሳ የሆኑ ሰዎች ፍቅርን፣ ሰላምን፣ መቻቻልን፣ ሃይማኖትን ንቀዋልና ሊገለሉ ይገባቸዋል!!

ሰው ገድለህ ትድናለህ የሚል ሃይማኖት አልተፈጠረም። ይህን አይነቱ ሰው ሰይጣንም አብደሃል ሳይለው አይቀርም። ምክንያቱም ሰይጣን እንኳን እኔ የማምነውን ካላመንክ ብሎ ሰውን አልገደለምና!! ከሰይጣን እምነት የባሱ ናቸውና ሊገለሉ ይገባቸዋል!! በጎ ሕሊና ላለው ሰው ይህ እብደት እንጂ ጤንነት አይደለምና።

ሰላም ለኢትዮጲያ ይሁን!