Saturday, 3 March 2012




ሐዋርያዊት // ቤተክርስቲያን


የሠራዊት ጌታ ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል
“ወደ ተራራ ውጡ እንጨትም አምጡ ቤቱን ስሩ እኔም በሱ ደስ ይለኛል እከበርበታለሁም
ዘሩባቤል ሆይ በርታ ህዝቤ ሆይ በርታ እኔ ከእናንተ ጋር ነኝና ቤተ መቅደሴን ስሩ”
ትንቢተ ሐጌ 1: 7

+++ ስለ ቤተክርስቲያን አበው ብዙ ሰርተው አለፈዋል፤ ብርሐነ አለም ቅ/ጳውሎስም ስለ ቤተክርስቲያን ያልሆነው ነገር የለም ነበር። ይህች የቀደመችው እነ ሐዋርያው ቅ/ጳውሎስ የደከሙላት ፤ ይህች ኖህ ከጥፋት ውሃ የዳነባት ከአለም ወጀብ መጠለያ መርከባቻን ፤ ይህች እነ ዳዊት ሊጠለሉባት የበረጧት መልካም ማረፊያችን ሐዋርያዊቷ ቤተክርስቲያን ናት።


ከቤተመንግስቴ ከአእላፈት ቀን ይልቅ በቤትህ ልጣል ወደድኩ”
መዝ 83(84) ቁጥር 10



+++ ስለ ሐዋርያዊቷ ቤተክርስቲያን በደንብ ጠንቅቀን እንድናውቅ ግዜው ግድ ይለናል፤ ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊት  ትባላለች ምክንያቱም ከሐዋርያት ተያይዞ የመጣ ሥርዓቷን ጠብቃ ስለምትገኝ ነው። እስቲ በቅዳሴው ስለ ሐዋርያዊቷ ቤተክርስቲያን ዲያቆኑ የሚያዜመውን ውብ ዜማ በማስተዋል እንየው፤ ዲያቆኑ እንዲህ ይላል ፦


ፀልዩ በእንተ ሰላመ ቤተክርስቲያን አሐቲ ቅድት ጉባኤ እንተ ሐዋርያት ርትዕት”


[Pray for the peace of the one holy apostolic church orthodox in the Lord]
{ ሐዋርያት ለሰበሰቧት ክብርት ስለምትሆን አንዲት ቤተክርስቲያን ጸልዩ}


ከዜማው እንደምንረዳው አንዲት ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊት ለመሆን 4 ነገሮችን
ማሟላት አለባት፤ የመጀመሪያው ቤተክርስቲያን ላዕለ ኩሉ /ከሁሉ በላይ ናት/ የቤተክርስቲያን ራስ ክርስቶስ ነውና። ኤፌሶን 1:22፤ እስቲ 3ቱን ቀሪዎች ከዜማው በመነሳት አንድ በአንድ እንያቸው፦

1)      አሐቲ፦ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን አሐቲ ወይም አንዲት ናት። በከተማ ትሁን በገጠር; ከአፈር ትሰራ ከወርቅ ፤ በአውሮፓ ይሁን በአሜሪካ; ይህች ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊት ከሆነች አሐቲ ናት ወይም አንዲት ናት። በጸሎተ ሐይማኖት ላይም ሐዋርያት በሰበሰቧት በአንዲት ቤተክርስቲያን እናምናለን ብለን እንደምንጸልየው ማለት ነው።


አንድ ጌታ አንዲት ጥምቀት አንዲት ቤተክርስቲያን እንደሚል”
ኤፌ 4:4










2)    ቅድስትሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን እግዚአብሔር በደሙ ያጸናት ቅድስት ናት።
በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን ጠብቁ እንደሚል” የሐዋ. 20:28
ቤተክርስቲያን ቅድስናዋን ማንም ሊያስቀርባት ወይም ሊያረክስባት አይችልም፤ ለምሳሌ በቤተክርስቲያን የሚቀድሰው ካህን ሰይጣን አስቶት የማይገባ ባሕርይ ቢኖረውና ወደ ቤተክርስቲያን ቢመጣ በካህኑ ምክንያት የሚሰጠው መንፈሳው አገልግሎት ዋጋውን
ሊቀንስው አይችልም፤ ያ ካህን ልክ ቤተክርስቲያን ሲገባ አብሮት የነበረው ዲያቢሎስ ከውጭ ሆኖ ይጠብቀዋል እንጂ ወደ ውስጥ አይገባም፤ ልክ አገልግሎቱን ፈጽሞ ሲወጣ በዛ ባሕርይው ከቀጠለ ያም ዲያቢሎስ አብሮት ይቀጥላል ማለት ነው። ካህኑ ልክ እንደ ስልክ አገናኝ operator ነው፤ ስልክ የምታገናኘን ሴት ባሕሪዋ መልካም ባይሆን እንደምንም ታግሰን አላማችንን እንደምንፈጽመው ማለት ነው። ካህን ዘር እንደሚዘራ ገበሬ ነው ፤ ገበሬ በተበላሸ እጁ ዘር ቢዘራ የዘራው ዘር መብቀሉ አይቀርምና። ወደ ሃሳባችን ስንመለስ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን እግዚአብሔር በደሙ ያጸናት ቅድስት ናት ብለናል; ልብ ብለን ካስተዋልነው ቅዱስ ደሙን በላዕለ መስቀል ላይ ያፈሰሰው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ ቅ/ጳውሎስም ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ መሆኑን ስለሚያውቅ  በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን ጠብቁ ብሎ በሐዋ. 20:28 ተናግሯል።
  
3)     እንተ ሐዋርያት፦
ይህ ክፍል ዋናው የቤተክርስቲያን መሰረት ነው፤ ሐዋርያዊት የሆነች ቤተክርስቲያን ከሐርያቱ ጀምሮ እዚህ የደረሰችበት አመጣጧ እነሆ እንዲህ ነው፦

+++ ጌታ ለሐዋርያት አለቃ እንዲህ አለው; አንተ ጴጥሮስ ነህ በዚህ ዐለት ላይ ቤተክርስቲያኔን እሰራለሁማቴ 16:18፤ ቅ/ ጴጥሮስም ወንጌላዊው ማርቆስን አስተማረው; ቅ/ማርቆስም በግብፅ መንበሩን መሰረተ። ከማርቆስ ቀጥሎ አንያኖስ ከአንያኖስ 20 ፓትርያርክ ቀጥሎም አትናቴዎስ ተተካ፤ ይህ ሐዋርያዊ ቅብብሎሽ ወደ ሃገራችን የመጣው በፍሬምናጦስ ወይም በከሣቴ ብርሐን አባ ሠላማ አማካኝነት ነበር።  

+ የፍሬምናጦስ ታሪክ እነሆ፦ ፍሬምናጦስ ኢትዮጲያዊ አልነበረም ፤ ጌታ ባረገ በ357 ዘመን አንድ ነጋዴ ከኢየሩሳሌም ፍሬምናጦስና ሲድራኮስ የተባሉ ሁለት ልጆችን ይዞ መጣና እንባቆም በተባለ አንድ ገበሬ ቤት ገብተው አደሩ። ከጥቂት ቀናት በሗላ አባታቸው ሞተ፤ ልጆቹም በእንባቆም ቤት መኖር ጀመሩ። ከእለታት በአንድ ቀን ፍሬምናጦስ የኢትዮጲያን ሰዎች ባህልና ሐይማኖታቸውን አደንቃለሁ; ነገር ግን ሥጋ ወደሙን ለምን አትቀበሉም? ብሎ ገበሬውን ጠየቀው; ያም ገበሬ ስንቅ አስይዞ በንጉስ ኢዛና ፈቃድ እስክንድርያ ሄዶ በሊቀጳጳሱ በአትናቴዎስ ተሹሞ ፓፓስ ሆነ። ስሙንም ከሣቴ ብርሃን አባ ሠላማ አለው /ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር የሚያስታርቅ ማለት ነው/ ፍሬምናጦስም በእንዲህ ባለ መንገድ ሐዋርያዊ ቅብብሎሽን ወደ ሃገራችን አምጥቷላ ማለት ነው።

ሐዋርያዊ ቅብብሎሽ” // Apostolic Succession”


ጌታ      ቅ/ ጴጥሮስ        ቅ/ማርቆስ       አንያኖስ        አትናቴዎስ
ፍሬምናጦስ /ከሣቴ ብርሐን አባ ሠላማ/

ለማየት እንደሞከርነው ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊት የምትባለው ከጌታ ጀምሮ በሐዋርያቱ ቅብብሎሽ ስለምትመራ ነው። ይህም በእንግሊዘኛው Apostolic Succession ወይም ሐዋርያዊ ቅብብሎሽ በመባል ይታወቃል።

+++ ሐዋርያዊ ቅብብሎሽ በቅዳሴ፦ እስቲ በሚመጣው እሁድ ወንጌል ከመነበቡ በፊት ካህናቱን ልብ ብለን እንስማ; እንዲህ ይላሉ፤ ገባሬ ሠናዩ ካህን ወይም ዋናው ካህን አስቀድሞ እንዲህ ይላል፦

 His kingdom & his righteousness which he delivers to me I deliver to you
 [ዘአወፈየኒ አወፈይኩከ] ወይም የሰጠኸኝን ሰጠሁህ  

ካህኑ የሰጠኸኝን ሰጠሁህ ብሎ ወንጌሉን ለንፍቅ ካህን ወይም ለሁለተኛው ካህን ይሰጠዋል ፤ ሁለተኛው ካህንም ለዲያቆኑ ይሰጠዋል; ይህ ነው ሐዋርያዊ ቅብብሎሽ የሚባለው; ዋናው ካህን የጌታ ምሳሌ ሲሆን ሁለተኛው ካህን ደግሞ የቅ/ጴጥሮስ ምሳሌ ነው፤ ዲያቆኑም የምዕመናን ሁሉ ምሳሌ ነው ማለት ነው!! ወርቅ የሆኑ አበው ወርቅ የሆነ ሥርአትን ከተግባር ጋር አወረሱን!

+++ ሐዋርያዊ ቅብብሎሽ የቤተክርስቲያን ዋና መሰረቷ ነው። ለምሳሌ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ይህ ሐዋርያዊ ቅብብሎሽ ስለሌላቸው ጥምቀቱም ሆነ ሌላው አገልግሎት ሐዋርያዊ አይደለም ማለት ነው። መንፈሳዊ አገልግሎትን ልንፈጽም የምንችልባቸው ሐዋርያዊት የሆኑ 5 እህትማማቾች ቤ/ተ/ክ ሲኖሩ ከምዕራቡ አለም በሐዋርያዊ ሥርአት ስለሚለዩ ኦሬንታል ወይም ምስራቃዊ ይባላሉ።


        5ቱ ሐዋርያዊት ኦሬንታል ቤተክርስቲያኖች
(በነዚህ ቤተክርስቲያናት መቁረብና መጠመቅ ይቻላል)
 ሐዋርያዊት “ኢትዮጲያና ኤርትራ
      ሐዋርያዊት ግብጽ
      ሐዋርያዊት ሶርያ
      ሐዋርያዊት አርመንያ
      ሐዋርያዊት ህንድ

በድንዃንህ ለዘላለም ልኑር በክንፍህም ልጠለል”
መዝ 60: 4



 ቤተክርስቲያንና // ፈተናዎቿ

+++ የመናፍቃኑ ፈተና፦ መናፍቃኑ ቤተክርስቲያን አያስፈልግም የእኛ ሰውነት ራሱ  ቤተክርስቲያን ነው ይላሉ። ነገር ግን ጌታ በወንጌል ላይ እንዲህ አለ፤
ቤትየ ቤተ ጸሎት ትሰመይ // ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል ማቴ 21:13

+++ የምንደኛ ልጆቿ ፈተና፦ ምንደኛ የሚባሉት ለቤተክርስቲያን ታምኝ ያልሆኑ ልጆቿ ናቸው፤ ሰው እናቱን በገንዘብ ይሸጣል እንዴ? እስከ ዛሬ አልተሰማም; ይሁዳ ብቻ ጌታውን በገንዘብ እንደለወጠ ተጽፏል። ይሁዳ ማለት ታማኝ ማለት ነበር; ነገር ግን እንደስሙ አልታመነም፤ እናቱን ቤተክርስቲያንን በገንዘብ የሚለውጥም ዳግማዊ ይሁዳ ይባላል። አንዳንዶቹ እኛ በሰለጠ አለም ነውና ያለነው ቤተክርስቲያን ትታደስ ይላሉ; በራዕ 15:3 ላይ የሰማይ መላእክት ሱራፌል የዘመሩበት በገና ይቅርና ኦርጋን ይሁን ይላሉ; በውጭው አለም ያሉ አንዳንድ የሰንበት ትምህርት ቤት ዘማርያንም ግማሹ ባለማወቅ ሌላውም እያወቀ አሜን ብለው ተቀብለዋል፤ መንፈስ ቅዱስ ይታደሳል እንዴ ቤተክርስቲያንን እናድሳት የሚሉት? የተፈጥሮ ሳይንስ dynamic ነው ይሻሻላል; ቤተክርስቲያን ግን ትላንትም ዛሬም ነገም አንዲትና ሐዋርያዊት ናት!!!


+++ ቤተክርስቲያንን መሳለም፦ አንዳንድ ሰዎች ቤተክርስቲያንን በእጃችን እያበስን ስንሳለም ሊገርማቸውና ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ እንደሆነ አድርገው ሊቆጥሩ ይችላሉ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ አዘዘው፦ ከድንኳኑ ጀምረህ በውስጡ ያሉትን ንዋያተ ቅድሳትን በሙሉ ቅብዓ ቅዱስ ወይም ሜሮን ቀባና ቀድሳቸው እነሱን የነካም ቅዱስ ይሆናል። ዘጸ 30:22 እኛም የቤተክርስቲያንን ዘርፍ በእምነት የምንዳስሰው በዚህ ምክንያት ነው። 12 አመት ሙሉ ትደክም የነበረችው ሴት እምከመ ገሰስኩ ጽንፈ ልብሱ አሀዩ /በእምነት ሆኜ የልብሱን ዘርፍ ብዳስስ እፈወሳለሁ/ ብላ እንደዳነችው እኛም በእምነት የቤተክርስቲያንን ዘርፍ ብንዳስስ እንፈወሳለን። ጌታ የቤተክርስቲያን ራስ ነውና የልብሱ ዘርፍም ቤተክርስቲያን ናትና!!! ኤፌሶን 1:22

+++ ቤተክርስቲያን ከሙሴ እስከ አዲስ ኪዳን፦ በነሙሴ ዘመን ህንጻ ቤ/ተ/ክ ስላልነበረ ህዝቡ ይገናኝ የነበረው በድንኳን ውስጥ ነበርና የመገናኛ ድንኳን ይባል ነበር። ለመጀመሪያ ግዜ ህንጻ ቤተክርስቲያንን የሰራው ንጉስ ሰለሞን ሲሆን ይህ 46 አመት የፈጀው ቤ/ተ/ክ በአሁኑ ግዜ መስጊድ ተሰርቶበታል!! ከሰለሞን በመቀጠል ዘሩባቤልና ንጉስ ሄሮድስ ሰርተዋል። ከስደት መልስ እነ ሰለሞንንና ዘሩባቤልን ቤቱን እንዲሰሩ የረዳ እኛንም በስደት ሃገር ቤተ መቅደሱን እንድንሰራ የሠራዊት ጌታ ልዑል እግዚአብሔር ይርዳን ፤ አሜን



እኔ ከዝግባ በተሰሩ ቤተመንግስቴ እየኖርኩ የእግዚአብሔር ታቦት ግን በድንኳን ውስጥ ይኖራል። 2ኛ ሳሙኤል 7:2 ፤ ዳዊት ስለእኛ የተናገረው አይመስላችሁም? ምን አልባት እኛ በተመቸ ቤት እንኖር ይሆናል; የእግዚአብሔር ታቦት ግን በድንኳን ውስጥ ይኖራል።

ህዝቤ ሆይ በርታ እኔ ከእናንተ ጋር ነኝና ቤተ መቅደሴን ስሩ”
ትንቢተ ሐጌ 1: 7


ስሜ ለዘለአለም በዚያ ይኖር ዘንድ ይህን ቤተ መቅደስ መርጫለሁ ቀድሻለሁም፤ በቤቴ የሚጸለየውን ጸሎት ዓይኖቼ ያያሉ ጆሮዬም ያደምጣሉ።

2ኛ ዜና 7: 15
በቅድስናው ስፋራ ለእግዚአብሔር ስገዱ
መዝ 28:2
አንተን በመፍራት በመቅደስህ እሰግዳለሁ
መዝ 5:7
ወደ ቤተ እግዚአብሔር እንሂድ ሲሉኝ ደስ አለኝ
መዝ 121(122):1
እግዚአብሔርን በመቅደሱ አመስግኑት
መዝ 150:1
ከተቀደሰው መቅደስህ በረከትን እንጠግባለን
መዝ 64(65):4
ለአይኖቼ መኝታ ለሽፋሽፍቴም ረፍት አልሰጥም ለእግዚአብሔር ስፍራ ለያዕቆብ አምላክ ማደሪያ እስካገኝ ብዬ
መዝ 131:3
የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ መቅደሱ አምጥታቹ ቤተ መቅደሱን ስሩ

1ኛ ዜና 22:19
እግዚአብሔር ለዘላለም ወደ ቀደሰው መቅደሱ ኑ
2ኛ ዜና 30:8
አቤቱ በተቀደሰው መቅደስህ የልመናን ከንፈር ስማ የንስሐን እንባንም ተቀበል
2ኛ ዜና 6:36

ቤቴ ለህዝቦች ሁሉ የጸሎት ቤት ይባላል

ኢሳ 56:7

እለት እለት የሚያስጨንቀኝ የቤተክርስቲያን  ጉዳይ ነው

2ኛ ቆሮ 11:28
ዋዕናቅጸ ሲኦል እይሔይልዋ //
የሲኦል ደጆች አይችሏትም

ማቴ 16:18


+++ መዝሙር እንዘምር፦
ቤተ ክርስቲያን ሆይ ሠላም ላንቺ ይሁን
ሐዋርያዊት የወደዱሽ ጴጥሮስ ወጳውሎስ (2)
ሥብሐት ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ
እናመስግን በአንድነት በቤቱ ሆነን
እንፀልይ በአንድነት ለቤተክርስቲያን

                                                

/ተክለ መድህን/


Tuesday, 28 February 2012

የዕንባ ዘለላ!


ዘና ብላችሁ ተቀመጡና አንድ ታሪክ ልንገራችሁ፤


በአህያ ቆዳ የተሰራ ቤት ይፈርሳል ጅብ የጮኸ እለት” ይላል የሀገሬ ሰው፤ ነገሩ ወዲህ ነው እነሆ በለንደን የምንኖር ሐበሾች በክራይ የምንገለገልበት ቤተክርስቲያን አለ፤ ቤተክርስቲያኑን ከነጮች ጋር በፈረቃ ነው የምንጠቀመው። እሁድ ጠዋት ለቅዳሴ እንገባና ከሰአት ነጮቹ ገብተው የራሳቸውን ፕሮግራም ያካሄዳሉ። ሲፈልጉ ስፖርት ይሰሩበታል ደስ ሲላቸውም ይደንሱበታል! እኛም በየሳምንቱ ለቅዳሴ እየተገለገልንበት እንዲህ እያለ ይቀጥላል። ይህ የእንግሊዝ አብያተክርስቲያናት ጸባይ ነው፤ ድሮ አባቶቻቸው ያወረሷቸው በእየ 7 እርምጃ የተሰሩ ቤተክርስቲያን ነበራቸው፤ አሁን በእየ 3 እርምጃ የተሰሩ የጭፈራ ናይት ክለብ አላቸው፤              ከቤተክርስቲያናቸው ስር /under ground/ የጭፈራ ቤት ተሰርተዋል፤ ዛሬ አውሮፓዊያኑ ከጥንት ነዋሪዎች በስተቀር ቤተክርስቲያን የሚመጣ ህዝብ የላቸውም፤ ስለዚህም ቤተክርስቲያኑ ይሸጥና የጭፈራ ቤት ይሆናል ማለት ነው።


ጨረቃ ብትደምቅ አታሞቅ የሰው ቤት አያደምቅ” ነውና ነገሩ ሰሞኑን በምንገለገልበት ቤተክርስቲያን ውስጥ ያለው ቤተ መቅደስ እንዲፈርስ ጠይቀዋል፤ “ሂድ አትበለው እንዲሄድ አድርገው እንደ ማለት ነው። ቢሯችንም ተዘግቶ አገልግሎቱ ቆሟል። ሰበካ ጉባኤው ሰሞኑን ተሰብስቦ ሌላ ቤተክርስቲያን ፍለጋ እየተሯሯጠ ነው። ሞት ቢዘገይ የቀረ ይመስላል አለች ሴትዮዋ እውነቷን እኮ ነው፤ እኛም ዝምታቸው ሲዘገይ የቀረ መሰለንና ቤተክርስቲያኑ የራሳችን መሰለን፤ በመጨረሻዋ ሰአት ላይም ተረባረብን፤ ይህን ያዩ የለንደን እማ ወራዎችም ሞት ሲደርስ ቄስ ጦር ሲደርስ ፈረስ” ብለው ተረቱ!


በእርግጥ ነጮቹ እስከ ዛሬ ቤተክርስቲያኑን እንድንጠቀም ስለፈቀዱልን ማመስገን ይገባናል፤ ሲጀመር የራሳችን አያያዝ ጥንቃቄ የጎደለው ነበር። ምዕመናንም በንፅህናው ረገድ ችላ ያሉ ይመስላል፤ የሰ/ት/ቤቱ ተማሪዎች በፅዳቱ ቢተጉም በአጠቃላይ አያያዛችን ላይ የጥንቃቄ ጉድለት ነበር፤ አንዳንድ እቃዎች ተሰበሩ፣ በካርፔንት እና በወንበሮች ላይም ሻማ ፈሰሰ፤ ይህን የመሰለ ወዘተ ተረፈዎች ሲደማመሩ ችግሩ ጎላና እነሱም መናገር ጀመሩ፤

*እስከ ሁለት ወር ድረስ ግዜ ተሰጥቶናል፤ ከዛ በኋላስ እንወጣለን ማለት ነው? ወይስ ምን ይመጣ ይሆን? የትንሣኤውን በዓልስ የት ይሆን የምናከብረው? መልካሙን ያሰማን።

ለዚህ ነው “የዕንባ ዘለላ” እናዋጣ የተባለው። ለጸሎት ስትቆሙ እስቲ ስለዚህ ጉዳይ አንዲት አባታችን ሆይ ድገሙ፤ እስቲ ሁላችንም ትንሽ የዕንባ ዘለላ እናዋጣ፤ እስቲ ተሳሉ; እስቲ የዕንባ ዘለላ አዋጡ፤ የእያንዳንዳችን የዕንባ ዘለላ ተጠራቅማ ምን አልባት ታላቅ ስራን ትሰራ ይሆናል ማን ያውቃል? እስቲ አብዝታችሁ ጭኹና ለምኑ፤ ከእልፍ አእላፋት የወፎች ጩኸት መካከል የልጇን ድምጽ ለይታ የምታውቅ ለየት ያለች የወፍ ዝርያ አለች፤ ከመካከላችንም እግዚአብሔር የመረጠው ጩኸቱ ይሰማ ይሆናል ማን ያውቃል?

ለጸሎት በቆማችሁ ግዜ ይህችን ጉዳይ በእግዚአብሔር ፊት አቅርቡ፤ እስቲ እንደ ነብያቱ በዕንባ ዘለላ ጭምር ልመናችንን እናቅርብ፤ የኢየሩሳሌም ቅጥር እና ቤተ መቅደሱ ሲፈርስ ነህምያና ኤርሚያስ ያደረጉት ትዝ እንደሚለን የታመነ ነው። ነህምያ የንጉሥ አስተናጋጅ ነበር፤ በቤተ መንግሥት እየኖረ ይህንንም በሰማሁ ግዜ ተቀምጬ አለቀስኩ” አለ፤የኢየሩሳሌም ቅጥር መፍረሱን፣ ቤተመቅደሱ መፍረሱን፣ሰው ከእግዚአብሔር መራቁን በሰማ ግዜ አለቀሰ፤ ብዙ ግዜም እፀልይና እጾም ነበር ነህምያ [1: 4] እንዲሁ ነብዩ ኤርሚያስም ቤተመቅደሱ መፍረሱን አይቶ አለቀሰ፤ ሰቆ. ኤር. [3: 44]

የሁለቱን እንባ ወደ  እግዚአብሔር ሊያቀርብ ደገኛ የሆነ አንድ የከበረ መልአክ በእግዚአብሔር ፊት ቆመ፤ ይህ መልአክ  እግዚአብሔርን ምን ብሎ ነበር የለመነው? እግዚአብሔርስ ለዚህ ደገኛ መልአክ ምን ብሎ ይሆን የመለሰለት? 
አቤቱ የሠራዊት ጌታ ልዑል እግዚአብሔር ሆይ እነዚህን 70 አመት /እስራኤል በባቢሎን የተወረችበት 70 አመታት/ የተቆጣሃቸውን የኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች የማትምራቸው እስከ መቼ ድረስ ነው፤ እያለ እግዚአብሔርን ለመነ፤ እግዚአብሔርም ደስ በሚያሰኝና በሚያጽናና ቃል ለመልአኩ መልሶለት ለኢየሩሳሌምና ለይሁዳ ከተሞች ምህረትን አደረገ! የኢየሩሳሌም ቅጥር በእነ ነህምያ ተሰራ! ቤተ መቅደሱም በእነ ዘሩባቤል፣ ዘካርያስና ሐጌ አስተባባሪነት ተሰራ! በዚህ ታሪክ ውስጥ የመልአኩን ምልጃ ልብ ይበሉ፤ ትንቢተ ዘካርያስ [1: 12]

የእምነት ጸሎት ኃይልን ታደርጋለች” እንዳለ ሐዋርያው እነሆ የዕንባ ዘለላ ይህን የመሰለ ግዳጅን ትፈጽማለች! 

በስደት ሀገር መስኮቱን ወደ ኢየሩሳሌም ከፍቶ የሚጸልየው ሰው ማን ነበረ? በስደት ሀገርማ ብዙዎች እግዚአብሔርን ይዘው ድንቅ ስራውን አዩ፤ አብርሐም ፣ ሙሴ ፣ ዮሴፍ ፣
እግዚአብሔርን ይዘው ተሰደዱ፤ ነብዩ ዳንኤልም በስደት ሀገር መስኮቱን ወደ ቅድስት ሀገር ከፍቶ ይጸልይ ነበር።

እኛም በስደት ያለን እንደ ነብዩ ዳንኤል መስኮታችንን ወደ ቅድስት ሀገር ኢትዮጲያ ከፍተን የምንጸልይበት ብርቱ ጉዳይ አለ፤ ይህ ብርቱ ጉዳይ “የዕንባ ዘለላ የምናዋጣበት ብርቱ ጉዳይ ነው” እነሆ እንደ ያዕቆብ ልጆች እንጀራን ፍለጋ በምድረ አውሮፓ ወደ ለንደን ተሰደድን፤ ስደትን ለስደተኛ ማን ያስረዳዋል? ወንጌሉ “ማንም ከዛሬ ጀምሮ ጌታን እወቅ ብሎ አያስተምርም፤ ምክንያቱም ከታናሽነት ጀምረው ሁሉም ያውቁኛል” እንደሚል ስደትን ለሚያውቃት ማንም አያስረዳውም።

ስለስደት እንነጋገር ከተባለ ግን ስደት 4 ልጆች አላት፤ ናፍቆት ፣ ብቸኝነት ፣ የሚፈራረቁ ሀዘንና ደስታ ናቸው።

የስደት ልጆችን የምታጽናና አንዲት እናት አለች፤ ይህችም ቤተክርስቲያን ናት።


በስደት ያዘነው ሁሉ በቤተክርስቲያን በርከክ ብሎ አንድ ሁለቴ የሰላም አየር በርጋታ ሲተነፍስ ያኔ የውስጥ ሰላምን ያገኛል! ይህች ቤተክርስቲያን በስደት ሀገር ለስንቱ መጠለያ ሆነች? ስንቱን አጽናናች? ስንቱን የነፍስ ረፍት ሰጠች? ይህን ሳስብ ሁሌ ይገርመኛል! አንድ ታላቅ ሰው “ቤተክርስቲያን ባትኖር ኖሮ ሐበሻ በስደት ሀገር ቆሞ መሄድ አይችልም ነበር” ብለዋል። ይህ በእርግጥ እውነት ነው፤ የእኛ ጸባይ በህብረት መኖር ነው፤ ከሌላው አለም ሲነጻጸርም እኛ ሀዘንን መቋቋም አንችልም። ለዚህ ነው “ቤተክርስቲያን ባትኖር መቆም አንችልም” ያለው። አሁን ግን ይህች መጠለያ ቤተክርስቲያናችን እኔ እንዳቆምኳችሁ እናንተም አቁሙኝ እያለች ነው፤

ይህች ጽሁፍም ዋና አላማዋ ለዚህ ጥሪ አንዳች መልስ እንሰጥ ዘንድ ነውና አንብበን ብቻ ዝም አንበል፤ መንገድ በሀሳብ አይደረስም” እንዲል ማሰብ ብቻ ሳይሆን  አንዳች ነገር በተግባር እንስራ፤ “ስራ የሌለው እምነት ሙት ነው” እንዳለ ሐዋርያው እምነታችን ሕያው እንዲሆን እስቲ አንዳች ነገር እንስራ፤ ጫማ የለም ብለው የሚያጉረመርሙ እግር የሌላቸውን አይተው ይጽናኑ” እንደሚል እኛም ሳናጉረመርም አንዳች ስራን እንስራ፤  ሰው እናቱ ብትራብ ዝም አይልም ከአፉ ነጥቆ ይሰጣታል፤ ምንም የስደት ኑሮ ባይደላም እናት ናትና የሚወጣ ገንዘብ እንኳን እንደየ አቅማችን ብናደርግ ለታሪክ የሚሆን ትንሽ ስራ ሰራን ማለት ነው።



ነህምያ እኛ ባሪያዎቹ እንነሳለን የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል” እንዳለ እስቲ እግዚአብሔር እንዲያከናውንልን እኛ ባርያዎቹ እንነሳ፤ እስቲ እናንተም ያላችሁን ሀሳብ አቅርቡ፤

ከእንግሊዝ ውጪ የምትኖሩ ወገኖቻችንም እስቲ በጸሎት እርዱን፣ በሀሳብ አትርሱን፣ እናንተ ስትጸልዩ እኛ የዕንባ ዘለላን ስናዋጣ የነብያቱን እንባ ያሳረገ መልአክ የእኛንም ያሳርግ ይሆናል ማን ያውቃል?        


 
 የዕንባ ዘለላን አዋጡ!