Friday, 13 January 2012

”ጥርስና ምላስ”

አንድ ቀን ነው አሉ አቶ ጥርስ ልክ እንደ ወፍጮ ያገኘውን ሁሉ ይፈጫል ያደቃል ይከካል፤

ይህም የአቶ ጥርስ መደበኛ ሥራ ሆኖ ቀረ አሉ። ጉረቤቶቹ እነ ጨጓራና ትርፍ አንጀት “አድቃቂው” የሚል የማዕረግ ስም እስከሚሰጡት ድረስ ስሙ ከፍ ከፍ አለ። አቶ ጥርስም ስራው ፍሬያማ በመሆኑ እነሆ ደስተኛ ሆነ።

ከእለታት በአንደኛው ቀን ግን ችግር ተፈጠረ፤ አቶ ጥርስ እንደለመደው ያገኘውን ሁሉ ሲፈጭ ሲያደቅ ሲከካ ሳያስበው እትዬ ምላስን ቀረጠፋት!

ምላስም እስከምትቆስል ድረስ እጅግ ተጎዳች። እትዬ ምላስ አቶ ጥርስን እየተቆጣች “ትንሽ ምላስ ጫካን ታቃጥላለች የተባለልኝ እኔ እንዴት እደፈራለሁ” እያለች እሪሪሪ ብላ ጮኸች፤  ጮኻም አልቀረች የሰውነት ክፍሎችን ሁሉ እነ ዓይን ፣ አፍንጫ፣ ጨጓራ፤ ትርፍ አንጀትማንንም ሳታስቀር ሰበሰበችና ከዛሬ ጀምሮ ጥርስ የሚባል ነገር አያስፈልገንም! ፀባዩም ከእኛ ለየት ይላል፤ እስኪ እዩት እኛ ስስ እሱ ጠንካራ፤ እኛ ሥጋ እሱ… አለችና ከምን እንደተሰራ ሲጠፋት በቃ እሱ ሁሉ ነገሩ ከእኛ ይለያል፤ “በቃ ይወገድልን አለች እትዬ ምላስ ምርር ብላ! ሁሉም እጃቸው እስከሚላጥ አጨበጨቡ፤ ልክ ነው አቶ ጥርስ ይወገድልን እያሉም ጮኹ! ………..
መቼም አስተዋይ ሽማግሌ አያሳጣንና የተከበሩት ሽማግሌው ጨጓራ ተነሱና እስኪ እስከ አሁን ድረስ ዝም ያሉት እነ ዓይን የሚሉትን እንስማ” አሉ፤ ዓይንም ማወቅ እናውቃለን ብንናገር እናልቃለን” ብላ እጥር ያለች መልስ ሰጠችና ተቀመጠች! አቶ ጨጓራ በዓይን መልስ ተገረሙና የራሳቸውን ሃሳብ ሰጡ፤ “የምትናገሩትን አስተውሉ! በአንድ ወቅት አይሁድ ሆሳዕና እያሉ እንዳልዘመሩና እንዳላመሰገኑ በሳምንቱ  ግን ስቀለው ስቀለው እያሉ ጮኹ! ሽባን ቢፈውስ ለምፅን ቢያነፃ አጋንንትን ቢያስወጣላቸው በቸርነት ፋንታ ይሰቀል ይሰቀል እያሉ ጮኹ!” …..

አዬ ዬ… ላይኛው ከንፈር ለክርክር ታችኛው ከንፈር ለምስክር!” እናንተም እኮ ከእነርሱ ምንም አልተማራችሁም፤ አንድ ሰሞን አድቃቂው ብላችሁ እንዳላሞገሳችሁት በሳምንቱ ይወገድልን እያላችሁ ጮኻችሁ! ይህ እኮ ነው ተረፈ አይሁድ መሆን፤ አቶ ጥርስን አመድ አፋሽ አደረጋችሁት! ጥርስ ባደቀቀው እናንተ ያለችግር ትጠቀማላችሁና አስተውሉ! እኛ እኮ ኑሯችን እንደ ሠንሰለት ነው፤ “ልብ ያሰበውን አፍ ይናገራል ዓይን ያየውን እጅ ይሰራል! አለች ሴትዮዋ እውነቷን እኮ ነው፤ አንድነት መልካም ነው! መፅሐፉም በሶስት የተገመደ ገመድ በቀላሉ አይበጠስም! ስለሚል በአንድነታችን እንበርታ! ለላም ቀንዷ አይከብዳትም” ሲባል አልሰማችሁምን? እኛ የራሳችን ቀንድ እየከበደን እኮ ነው! አሉና በልባቸው መናገር መልካም ነው ማዳመጥ ይበልጣል!” ብለው የተከበሩት ጨጓራ ዝም አሉ።

ወዲያው ግን የእነ ምላስ ጩኸት ቀጠለ፤ ልፋ ያለው በህልሙ ሸክም ይሸከማል” እንዲሉ ያ ሁሉ የአቶ ጨጓራ ንግግር ከንቱ ኾነ።
የእትዬ ምላስንና የአቶ እጅን ከንቱ ወሬ አስቀድመው የሰሙት እነ ዓይንም በጩኸቱ ተባበሩ! እንዲያውም በእነሱ ብሶ እኛ ብዙ ማውራት አንፈልግም፤ ብቻ አቶ ጥርስ ይወገድልን! አሉ፤ ለእባብ እግር የለው ለሞኝ መላ የለው” እንዲሉ መላ ከመፈለግ ይልቅ በችግር ላይ ተደመሩ! መጀመሪያ ጆሮ የገባን ከንቱ ወሬ የ10 አመት ትምህርት አይለውጠውም የሚባለው ለዚሁ ነው፤ ለማርያም መግደላዊት ፣ ለእነ ሉቃስና ቀልዩጳ ጌታችን ዳግም እንደሚነሣ 3 አመት ከ3 ወር አስተምሯቸው ነበርኮ፤ ሐሰቱ ሲበዛ እውነት ሆነ ዋዛ!” እንዲሉ የአንድ ቀን የአይሁድ ተሰርቋል” የሚለው ከንቱ ወሬ ግን ትምህርቱን በረዘባቸውና ጌታዬን ወስደኸው እንደሆነ አሳየኝ እያሉ አስቀድማ ትንሣኤውን ያየችው ማርያም መግደላዊት ተናገረች። አዬ መጀመሪያ የተሰማች ከንቱ ወሬ! መጥፎ ወሬ ይበራል መልካሙ ይተኛል” ይባል የለ፤ መጥፎ ወሬ ክንፍ አለው ይበራል፤ መልካሙ ወሬ ግን እንቅልፋም ነውና ይተኛል።

አቶ እጅም ተነሳና “ባጎረስኩ እጄን ተነከስኩ” ይላል ሰው የተባለ ፍጡር፤ እናም አቶ ጥርስ እጅ የተባልኩትን እኔን ስለነከሰኝና ስራው ያገኘውን ሁሉ መክተፍ ብቻ ስለሆነ ምርር ብሎኛል! ሁሉን ቢናገሩ ሆድ ባዶ ይቀራል” አለና እኔም እትዬ ምላስን እደግፋታለሁ! ብሎ ለራሱ አጨበጨበ! 
እጅ ነውና ለእራሱ ቢያጨበጭብ ማንንም አላስገረመም!

“መከራው ያላለቀለት በሬ ቆዳው ለነጋሪት ይጠፈራል” እንዲሉ የአቶ ጥርስ መከራም እንዲሁ በዛ። በዚህ ሁኔታም አቶ ጥርስ ከሰውነት ክፍል ተነቀሉና ተወገዱ፤ እነ ምላስና እጅም በሁኔታው ተደሰቱ  .   .     .      .

ብዙም ሳይቆይ ጨጓራ መጮ ጀመረ፤ “የደቀቀውን ምግብ አምጡልኝ እንጂ” እያለ ይጮኽ ጀመር። አቶ ጥርስ ተወግዷልና ምላስ ለጨጓራ የምትልከውን አጣች። አቶ እጅም ጥርስ ይወገድ! እያለ ለራሱ ያጨበጨበውን በሳምንቱ እረሳና ምን የሚያክል አጥንት ይዞ የሚግጥለትን የሚዘነጥልለትን የሚያደቅለትን መፈለግ ጀመረ፤ ለመስራት ያፈረ ለመብላት ደፈረ!

ችግሩ እንዲህ እያለ ተባባሰ፤ የጨጓራ ጩኸትም ቀጠለ…… እትዬ ምላስና አቶ እጅም እዬዬ እያሉ ምርር ብለው ማልቀስ ጀመሩ፤ ሆድ ሲሞላ ፍቅሩ ሌላ ሆድ ሲጎድል ሰው ያጋድል” እንዲሉ እርስ በእርሳቸው ተጣሉ; ሽማግሌው ጨጓራም እንዲህ ብሎ ገጠመባቸው፦

በፊት ነበረ እንጂ መጥኖ መደቆስ
አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ፤

የሚያደቀውንም ፈልጋችሁ ፉከራውንም ወደዳችሁ፤ ሁለት ወዳችሁ እንዴት ይኾናል? ሁለት አይወዱ ከመነኮሱ አይወልዱ” አለና መናገር ብር ነው ዝምታ ወርቅ ነው”    አለ እንደለመደው በልቡ!

አቶ ጥርስ ይህን ችግራቸውን ሁሉ አየና አዘነላቸው፤ ለረዥም መንገድ አትሩጥበት ለረዥም ነገር አትቸኩልበት!” እንዲሉ ምን ማድረግ እንዳለበት ለራሱ ግዜ ሰጥቶ አሰበበት፤ ወዲያው ፩ መፍትሄ መጣለት፤ እንዲህም አላቸው ምንም ብትበድሉኝ አብረን ሰርተናል፣ ብዙ ትዝታዎችን አሳልፈናል ሆደ ሰፊ  ይሻላል ከአኩራፊ” ስለሚባል በስራችሁ አልቀየምም አብሮ የበላና የጠጣ ሰው እስከ መጨረሻው አይቀያየምም” ሲባል ሰምቻለሁ፤ አሁንም
አብረን እጅና ጓንት ሆነን መስራት አለብን” ሲል አቶ እጅ ስሙ ስለተነሳ ደስ አለውና በረጅሙ አጨበጨበ…..      አዬ የእጅ ነገር እንዲያው በተገኘው ነገር ሁሉ ማጨብጨብ…  እራሱ ተናግሮ ለእራሱ ያጨበጭባል፤ ሌላውም ሲናገር እንዲሁ፤ እሱ እቴ ምን አለበት ሰው ግራ ይግባው ቀኝ ይግባው አይመለከተውም በቃ ማጨብጨብ ብቻ …

አቶ ጥርስ በእጅ ባህሪ ቢገረምም “አብሬያችሁ ልሰራ ፈቃደኛ ነኝ ሁለተኛ ጥፋት ቆሞ ማንቀላፋት” ስለሚባል አስቀድመን ግን ውል መፈራረም አለብን አላቸው፤ እነሱም “አንተ የፈለከውን አድርግ አጥንቱም ሥጋውም ያንተ፤ ሁሉ ተፈቅዶልሃል” አሉት። አቶ ጥርስም እነሆ ውሉ ይህ ነው “ሁላችሁም እድሜ ልካችሁን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳትሉ ትሰራላችሁ እኔ ግን የአገልግሎት ዘመኔ ሲፈፀም ጡረታ መውጣት እችላለሁ” አላቸው። ግዜያዊ ችግራቸው ብቻ ስለታያቸው “ይሁን ይደረግ” ብለው ተስማሙ። አቶ ጥርስም በሉ ከዛሬ ጀምሮ ጡረታ እስከምወጣበት ቀን ድረስ አብረን “እናደቃለን እንፈጫለን እንከካለን” ብሎ በሞራል ተናገረ፤

ጭብጨባው ቀለጠ ከሁሉም ጭብጨባ ግን የአቶ እጅ ለረጅም ግዜ ሳያቋርጥ ቀጠለ ….

ለተወሰኑ አመታት አቶ ጥርስ ፣ እጅና እትዬ ምላስ አብረው ሰሩ፤ አቶ ጥርስ ጡረታ መውጫው ግዜ ደረሰ፤

እነሆ ሰው ሲያረጅ ጥርሱ የሚያልቀው ከዛሬ ብዙ አመታት በፊት በተደረገው የውል ስምምነት ነው!