Friday, 27 December 2013

ኢትዮጲያዊቷ እህታችን ልትታረድ ነው



የአረብ ጋዜጣ እንደተረከው አንዲት የቤት ሰራተኛ የአሰሪዎቿን ልጅ ገደልሽ ተብላ ለመታረድ ቀናትን እየጠበቀች ነው። የቤት ሰራተኛዋ የአሰሪዎቿን ልጅ መግደሏን የሚያሳይ መረጃ ባይናገርም እንደምትገደል ግን ነግሮናል።

ክቡራን ኢትዮጲያዊያን ሆይ! ለሰከንድ አስቡ እስኪ! በእህታችን ፋንታ እናንተ ብትሆኑ ምን ይሰማችሁ ይሆን?

እኛ የክርስቶስን ልደት ልናከብር ቀን እንቆጥራለን፤ እህታችንም የሞትዋን ቀን ትቆጥራለች። እኛ በሬና ዶሮ እናርዳለን፤ እህታችን ደግሞ ራሰዋ ትታረዳለች።

አባቶቻችን እግሬን ለጠጠር ደረቴን ለጦር ብለው የሞቱት ለዛች ክብርት ሀገር መስሎኝ ነበር! የዜግነት ክብር ድሮ ቀረ አሉ እምዬ ሚኒሊክ! ዛሬማ ለአረብ ሸብረክ ብለን ተገዝተናል! ጣልያንን የመከተ ጉልበት ለአረብ ተንበረከከ! እንዴት ቢሉ አባቶቻችን ብርቱ እኛም ገልቱ! የእሳት ልጅ አመድ ይልሃል ይህ ነው!

ተከብረሽ የኖርሽው በአባቶቻችን ደም
እናት ኢትዮጲያ የደፈረሽ ይውደም አሉ!

አንዲት እንግሊዛዊት ተገደለች ቢባል ኖሮ BBC በዘገባው ዓለምን ባዳረሰ ነበር! ETV ሆይ የት ነበርክ? አንድ በትውልድ ህንዳዊ በዜግነት እንግሊዛዊ ሀኪም ኢራን ታግቶ ተገድሎ ነበር። እናማ የለንደን ጋዜጦች ይህንኑ አራገቡ። ለሁለተኛ ዜጋ እንዲህ ክብር ሲሰጥ እኛ ቤት ደግሞ ሁሉም ይሸፈናል። ተሸፋፍነው ቢያድሩ ገላልጦ የሚያይ አምላክ አለ አሉ!

ፖለቲካ ሲባል ብዙም አይደላኝም። ሲጀመር ፖለቲካ ኅጢአት እንዳልሆነ አሳምሬ አውቃለሁ። ስቀጥል ፖለቲካን አለመውደድ የግል መብቴ እንደሆነም አውቃለሁ። ስጨርስም የመንግሥት ደጋፊ አልያም ተቃዋሚ ሳልሆን እኔ የማውቃው "እናት ሀገሬ ኢትዮጲያን" መውደዴን ብቻ ነው! ይህ ግን የሀገርና የህዝብ ፍቅር ጉዳይ ነውና ዝም ማለት አንችልም። አንደበት ዝም ቢል ህሊና ግን እንዴት ዝም ይላል? የእናንተ ህሊና ዝም ይልላችኋልን?

አፍንጫ ሲመታ ዓይን ያለቅሳል ለካ
ወገኔ ሲሰቃይ አልችል አለ አንጀቴ
አንጀቴ ለዓይኔ ምስጢሩን ቢነግረው
ስቅስቅ ብዬ አለቀስኩ ገንፍሎ ስሜቴ
የወገኔ ደም ለሊት እየጮኸ
እንቅልፍ ይነሳኛል ድረሱ እያለ።
የወገኔ ደም በቀን እየጮኸ
ሰላም ይነሳኛል አለቅን ድረሱ ፍጠኑ እያለ።

''ይድረስ ለጠ/ሚ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ''

በዐረብ ሀገር የስንቱ እንባ ፈሰሰ?
እንባስ እንባ ነው ውሃ ጅረት ነው
የስንቱ ደም እንደ ዐባይ ፈሰሰ?
ዓባይ ሊገደብ ነው አሉ
የህዝብ እንባ የህዝቡን ደም የሚገድብ ማን ይሆን?

የኢትዮጲያዊያን ደም በአረብ ምድር እንደ ኣባይ ወንዝ ጎረፈ።

እህታችን ከ 20 ቀን በኋላ በሰይፍ ትቀላለች።

ነፍስ ይማር።