Saturday, 28 April 2012

ዘና ብላችሁ ተቀመጡና አንድ አሪፍ ታሪክ ልንገራችኹ!

የክረምቱ ዝናብ እንደ ጉድ ይረግጠዋል!

በረዶው ሳያዳላ ኹሉንም በኩርኩም እየመታ ሰው ኹሉ እንደ ጉድ ይሮጣል!

ይህ በረዶ የፈነከተኝ እስከ አሁን አልተሻለኝም!

መብረቁ እንደ ጉድ ይጮኻል!

የደላው ዝናብ እንደ ጉድ ሿሿሿሿ…… ይላል!

ትዝ ይለኛል በልጅነቴ የክረምቱ ዝናብ ከጣራው ጋር እየተጋጨ የሚሰጠው ድምፅ በጣም ደይ ይለኝ ነበር።
ሿ ሿ ሿ …… የሚለው ውብ ድምፅ እንዴት ደስ ይላል! ዝናቡ ሲጮኽ እኔም አልጋዬ ላይ እየዘለልኩ ስጮኽ እናቴ ጩኸት የለመደ ዐባይ ዳር ቅበሩን ይላል” እያለች ትተርትብኝ ነበር!


በልጅነቴ የምወደው ዝናብ ዛሬም በረዶ ቀላቅሎ እኔና ጓደኞቼን እያዝናናንና እየኮረኮመን ፤ እያሯሯጠ የአገልግሎ ኮርስ የምንወስድበት ክፍል አደረሰን። እኛም ግባ እንጂ ሻይ ቡና በል አልነው። ኧረ እኔ የማሯሩጠው ብዙ ሰው አለኝ ብሎ አልገባም አለን። ብዙ ብንለምነውም እንቢ ስላለን በሩ ላይ ትተነው ወደ ውስጥ ገባን።

ወደ ውስጥ እንደገባን የአገልግሎት ኮርስ የሚሰጡን አንድ የተከበሩ አባት ደስ በሚል ፈገግታ ተቀበሉን። ልብሳችን በውኃ ርሶ አዩንና የልጅ ነገር ኹለት ፍሬ አንዱ ብስል አንዱ ጥሬ” ብለው ፈገግ አስባሉን። ከዝናብ ጋር ከምትጣሉ ለምን አባርታችኹ አልመጣችኹም? ለአገልግሎት ያላችኹን ፍቅር ግን አደንቃለኹ ብለው አበረታቱን። ትንሽ ፍግግ አሉና ዓይን ዓይናችንን እያዩ ብረትን መቀጥቀጥ እንደ ጋለ ነው!” በአገልግሎት ዝለት ሳትመጡ እንዲህ በትኩሱ አገልግሉ አሉን።

የአገልግሎት ኮርሱም ተጀመረ።

የተከበሩት አባት እንዲህ ብለው ጠየቁ፤

መላእክት እንደ ሰው የሚታጠፍ እና የሚዘረጋ እግረ ሥጋ የላቸውም፤ ታዲያ መላኩ ቅ/ገብርኤል እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው” ገብርኤል ነኝ ሲል ምን ማለቱ ነው?? ሉቃስ [1: 19]


ይህች ጥያቄ ያለንበትን ክፍል ዝም አስባለች። ኹላችንም በልባችን ለምን ይኾን? እያልን መጠየቅ ጀመርን።
  
የተከበሩት አባት መልሱን እንዲኽ እያሉ አስረዱን፤ በእርግጥ ግሩም ጥያቄ ነው፤ መላእክት መንፈስ ናቸውና እግረ ሥጋ የላቸውም፤ አይቀመጡም አይነሱም አይቆሙምም! ሊቀ መላእክት ቅ/ገብርኤል እኔ በእግዚአብሔር ፊት “የምቆመው” ገብርኤል ነኝ ማለቱ ምህረትን ጠያቂ አማላጅ ነኝ ሲል ነው አሉን።

በክፍላችን ውስጥ የነበሩ የሌላ እምነት ተከታዮች ነበሩና  አሁን ማን ይሙት ይኼ ከአማላጅነት ጋር በምን ይገናኛል?” አሉ በልባቸው። ይኽን ሐሳባቸውን የተከበሩት አባት ስለገባቸው ፍግግ አሉ። እንዴት ማለት ጥሩ ነውና እንዴት? እንበል አሉን። እንዴት አልን በልባችን። እንዲህ ብለው ቀጠሉ፦



ይህን እንድንረዳ ልበ አምላክ ዳዊት የዘመረውን አብረን እንይ፤  የተመረጠው ሙሴ በእግዚአብሔር ፊት ባይቆም” ኖሮ ሕዝበ እሥራኤላዊያን በቅጽበት በጠፉ ነበር ይለናል መዝ. [105:23] ሙሴ ቀጥ ብሎ ስለ ቆመ አይደለም እስራኤላዊያን ምሕረት ያገኙት፤ ሕዝቡን ከምታጠፋ ሥሜን ከሕይወት መጽሐፍ ላይ ደምስስ!!! እያለ የለመነው ልመና ነው እስራኤላዊያንን ያስማራቸው ዘፀአት [32:32]

ስለዚህም “መቆም” ማለት ቀጥ ብሎ መቆም ብቻ ሳይሆን  መለመን ፣ ማማለድ እንደሆነ ባህረ ጥበብ የሆነች ቤተክርስቲያናችን እንዲህ ከመጽሐፍ ቅዱስ እያበሰለች ትመግበናለች!

የተከበሩት አባት በግርማ ሞገሳቸው ጎርደድ እያሉ “እስኪ በአንድምት እንምጣ” አሉ። አንድም ስለ ሕዝቡ የሚቆመው” ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሳል ዳንኤል [12:1] ቅ/ሚካኤል እግረ ሥጋ የለውም፤ ስለ እኛ ምህረትን ይለምናል እንጂ። አንድም መላዕክትም በእግዚአብሔር ፊት “ለመቆም” መጡ፤ ሰይጣንም በመካከላቸው ነበር። ኢዮብ [1:6] ሰይጣን ከሳሽ ስለሆነ ቆመ አልተባለም መላዕክቱም ቆሙ የተባሉት ቀጥ ብለው ቆሙ ለማለት አይደለም፤ ሊለምኑ መጡ ለማለት ነው እንጂ። አንድም እግርህ በድንጋይ እንዳይመታ “በእጆቻቸው ያነሱሃል” ይላል፤ መዝ. [90: 11] መላዕክት እንደ ሰው እጅ የላቸውም መንፈስ ናቸውና፤ ነገር ግን ሎጥን ከሰዶም እሣት እጁን ይዘው እንደወጡ ፈጥነው ደራሽ መሆናቸውን ሲያስረዳን ነው።



አንድም መላዕክት እንደ ሰው የሚያዩበት ዓይነ ሥጋ የላቸውም፤ መንፈስ ናቸውና፤ በወንጌል ግን ጌታችን እንዲህ አለ፦ ከታናናሾቻችሁ ማንንም እንዳትንቁ ተጠንቀቁ ጠባቂ መላእክቶቻቸው ዘወትር የአባቴን ፊት “ያያሉና” ማቴ. [18:10] “ያያሉና” ማለት መላዕክት በዓይናቸው እግዚአብሔርን ያያሉ ለማለት አይደለም; መላዕክት ዓይነ ሥጋ የላቸውም ተብሏልና “ያያሉ ማለት ይለምናሉ” ለማለት ነው፤ አንድም እግዚአብሔርን ያየ ከቶ ማንም የለም ይለናል፤ 1ኛዮሐ.[4: 12]  ያያሉ” ማለት ይለምናሉ ማለት እንደሆነ አየህን?

አንድም “ጠባቂ መላእክቶቻቸው” የሚለውን ስንመለከት “ጠባቂ” የሚለው ቃል መላዕክት ጠባቂ እንደሆኑ አይነግረንምን? አንድም “መላእክቶቻቸው” የሚለው ቃል እያንዳንዱ ሰው ፪ ዑቃቢ መልአክ /ጠባቂ መልአክ/ እንዳሉት አይነግርህምን? ፩ዱ በቀን ሲጠብቅህ ፩ዱ በለሊት እንደሚጠብቅህ አታውቅምን? አሉ የተከበሩት አባት በማይጠገብ ፈገግታቸው እያዩን። ይህችንም ማስታወሻ ሰጡን፦ “የጥቅስ ጥናት ዘዴ”

የቅ/ሚካኤል በዓል የሚውለው በ 12 ነው ስለዚህ ዳንኤል [12:1]
የቅ/ገብርኤል በዓል የሚውለው በ 19 ነው ስለዚህ ሉቃስ [1: 19]


የተከበሩት አባት ውድ ልጆቼ ሆይ ይህን ሁሉ ባሕረ ጥበብ ቤተክርስቲያን ታስተምረናለችና ይህች ቤተክርስቲያን ግሩም ድንቅ ናት!” አሉን። ይህን ሲሉ ለመጻፍ የማይቻል አንዳች የመንፈስ ደስታ ይታይባቸው ነበር።

ይህች ቤተክርስቲያን ግሩም ድንቅ ናት!”  አሉ በድጋሚ፤ እኛም ይህች ቤተክርስቲያን ግሩም ድንቅ ናት!” አልን በልባችን።


ንዋየ ኀሩይ ቅ/ጳውሎስ እንዳለው “እለት እለት የሚያስጨንቀኝ የቤተክርስቲያን ጉዳይ ነው” የሚለውን ጥቅስ አነበቡልንና
የተከበሩት አባት ትንሽ ዝም አሉ። በዚህች ትንሿ ዝምታ ውስጥ ግን ብዙ ነገር ነበር።

“የቀበሮ ባሕታዊ በበጎች መካከል ይፀልያል” አዎ ብዙዎች ተሐድሶ የሚባል የበግ ለምድ ለብሰው በቤተክርስቲያን ውስጥ አሉና ከውስጥም ከውጪም የሚያናውጧት ሞልተዋል። በጥባጭ ካለ ማን ጥሩ ይጠጣል” እንዲሉ የጠራውን የሕይወት ውኃ እንዳንጠጣ ኾነ። ቤተክርስቲያን ይህን አለፍኩ ስትል አንዱ ይተካል፤ አንዱ ሲያልፍ ሌላው ይቀጥላል። ዘመነ ሰማዕታት ያለፈ መስሎን ነበር ግና ዛሬ አክራሪ ነኝ በሚሉ በእሳት ትጋያለች። “በካብ ላይ ብሰራ እባብ መከራ ፣ በዛፍ ላይ ብሰራ አሞራው መከራ ፣ በምድር ብሰራ እረኛው መከራ የት ውዬ የት ልደር አለች ወፍ!” ልክ እንደዚህች ወፍ ሠላም አጥታ የተቸገረች አንዲት ነገር አለች። ይህችውም ቤተክርስቲያን ናት። ዘመኑ ለቤተክርስቲያን የከፋ ዘመን ኾኗልና የተከበሩት አባት ፈገግታቸው ጨለም አለ። ይህች ኀዘናቸው ግን ወዲያው ከፊታቸው ጠፋች። የፊታቸው ኀዘን  በልባቸው ቀርቷልና ያስለመዱንን ፈገግታ አሳዩን። የዚህች ቀን የመጨረሻ ንግግራቸው ይኽ ነበር፦
ለቤተክርስቲያናችን

ሠላም

ክብርና

   ሞገሥ ይኹን።

ይህች ቤተክርስቲያን ግሩም ድንቅ ናት!”
************
ይህን የመሳሰለውን ማንበብ ከወደዱ ይኽን አድራሻ ይጎብኙ!