Saturday, 4 August 2012

“እውነትም ጥሩነሽ”


ሩነሽ እውነትም ጥሩ ነሽ
ጫን አስተማርሽ አፈትልከሽ ሮጠሽ!
ይ ተደሰቺ ባንዲራውን ይዘሽ
ልማትሽ ይህ ነው ለፈሰሰው ላብሽ!

ጥሩነሽ እውነትም ጥሩ ነሽ
እጅግ ይደሰቱ የወለዱ እናትሽ!
ጥሩነሽ እውነትም ጥሩ ነሽ
ይህን ድንቅ ስምሽ ማን ይሆን የሰጠሽ!

ጥሩነሽ እስኪ ልጠይቅሽ
ምነው ቪቪያን ጥለሽ ብቻሽን ገሠገሥሽ!?
እልልልል እኛን ደስ ብሎናል
እጅግ ይደሰቱ የወለዱ አባትሽ!
ጥሩነሽ እውነትም ጥሩ ነሽ
ወርቅ ይዘሽ መጣሽ ለእናት ሀገርሽ!!


የዕንባ ሳቅ”

“ላይፈሩ ቁጣ ከእብደት አንድ ነው ትል ነበር ንግሥት ጥሩነሽ! ቪቪያን ጥሩነሽን አልፈራትም ወርቁም የኛ ነው ጨፍሩ” ብላ ሳይኮሎጂ ተጠቅማ ነበር። ለአፍ ዳገት የለውም” አሉ እትዬ ጣይቱ። ንግሥት ጥሩነሽ ግን ሩጫ የአፍ ስፖርት ሳይሆን የሜዳ ላይ ፍልሚያ መሆኑ ስለገባት ብዙ ኃይል አላባከነችም። 

ቪቪያን “ጥሩነሽን አልፈራትም” ስትል ንግሥት ጥሩነሽ ከትከት ብላ ሳቀችና ድብድብ አይደለም በሜዳ ላይ እናያለን” ብላ በሜዳ ላይ ንግሥትነቷን አሳየችን! ብዙ የፎከረችው ቪቪያን አፍዋ ጀግና ቢሆንም እግሯ ከዳት። አፍና እግር አልጣጣም አሉ። ይህን ጊዜ ንግሥት ጥሩነሽ ከአፍ ወለምታ የእግር ወለምታ ይሻላል” አለችና ከአጠገብዋ አፈትልካ ገሠገሠች። ቪቪያን አንዳች ማድረግ አትችል ነገር ንግሥቷን ከሩቅ እያየች አይ አፌ ጉድ ሰራኝ የአፍ ወለምታ በቅቤ አይታሽም“ አለች። ንግሥት ጥሩነሽም ቀበል አድርጋ ልጅ ለእናትዋ ምጥ አስተማረቻት” ብላ ሩጫን ለቪቪያን ጥሩ አድርጋ አስተማረቻት!

ይድረስ ለንግሥት ጥሩነሽ፦ ሩጫው ሲጀመር ልቤም በፍርሃት ይመታ ጀመር።ወርቁ በእጃችን ገብቷልና መጨፈር ትችላላችሁብላ እኮ ነበር ኬንያዊቷ ቪቪያን። ይህ ደግሞ ፍራቻውን ጨመረ። ኢትዮጲያዊያን በሙሉ ልባቸው በያሉበት ይመታ ነበር። ንግሥት ጥሩነሽ እግሮቿ ሲፈተልኩ ልቧ ሲመታ እኛም በያለንበት ልባችን ይመታ ነበር። መቀመጥ አቅቶኝ ቆሜ አብሬያት በመንፈስ እሮጥ ነበር። ሳይታሰብ አፈትልከሽ ስትቀድሚ ዕንባዬም ሳላስበው ቀደመኝ። በእውነት እየዘለልኩ በዕንባ አሳቅሽኝ። የዕንባ ሳቅ ልበለው። አዎ! ንግሥት ጥሩነሽ ዲባባ ይህ ይገባሻል።

“ወርቅ ለማግኘት ወርቅ ይዞ መነሳት” ትል ነበር ንግሥት ጥሩነሽ። እውነትም ወርቅ የሆነችውን “ንግሥት ወርቅነሽን” ይዛ ተነሳች። “ንግሥት ወርቅነሽ ኪዳኔ” እውነትም ወርቅ ናት። ጥርሷን ነክሳ ለሀገርዋ የተፋለመች ታላቅ ወርቃችን ወርቅነሽ ኪዳኔ ናት። አደራ በሰማይ በምድር ዋናው ሞተር ንግሥት ወርቅነሽ እንዳትረሳብን። ወርቅነሽ ወርቁ የአንቺና የሀገርሽ ልጅ የጥሩነሽ ዲባባ ነው!


አማትባ ተነሳች ወርቅ ይዛ ንግሥት ሆነች። ንግሥት ጥሩነሽ ጥሩ አድርጋ የከፈተችው በር ለብሔራዊ ቡድኑ ጥሩ ማነቃቂያ ነው። አሁንም እንደተለመደው ቆሜ ንጉሥ ቀነኒሳን አያለሁ። ሌሎቹም እንዲሁ በዕንባ ያስቁናል! የዕንባ ሳቅ!!”




Thursday, 2 August 2012

==>“ጾመ ፍልሰታ”<==



  
በደገኛዋ በዘመነ ሐዋርያት ጊዜ አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ለአገልግሎት የሚመላለሱት በደመና ተጭነው ነበርበአንድ ወቅት ከደገኞቹ ሐዋርያት አንዱ የሆነው ቅ/ቶማስ በደመና ተጭኖ ከሀገረ ስብከቱ ከሕንድ ወደ ኢየሩሳሌም ይጓዝ ነበር። በዚህ የደመና ጉዞ ላይ እመቤታችን ወደ ገነት ስታርግ አገኛት። ቶማስከዚህ በፊት የልጅሽን ትንሣኤ ሳላይ ተጠራጣሪ ሆንኩ፤ ያንቺንም ትንሣኤ ላላይ ነበር” ብሎ በጣም አዝኖ ከደመናው ላይ ሊወድቅ ፈለገ። እመቤታችንም ከአንተ በቀር ማንም ዕርገቴን አላየም ብላ አጽናናችውና የተገነዘችበትን የወርቅ ጨርቅ ወይም ሰበናዋን ሰጠችው። ቶማስም የእመቤታችንን ሰበና ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ገሠገሠ። የእመቤታችንን ሰበና ለደገኞቹ ሐዋርያት አሳያቸው። ሐዋርያቱም ለቶማስ እንደታየሽ ለእኛም ተገለጪ ብለው ጾመው ሱባኤ  ይዘው እመቤታችን ለደገኞቹ ሐዋርያት ተገልጣላቸዋለች። ይህም ፍልሰታ” ብለን የምንጾመው ልጅ አዋቂው የሚወዳት ጾም ናት።

   
እንኳን “ለጾመ ፍልሰታ” በሰላም አደረሳችሁ


“ፍልሰታ” ማለት ፈለሰ ከሚለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ማዛወር የነበሩበትን ሀገር ለቆ ወደ ሌላ ሀገር መሰደድ መፍለስ ማለት ነው፡፡ ጾመ ፍልሰታ ሲባልም የእመቤታችን ሥጋ ከጌቴሰማኒ ወደ ገነት መፍለስን በኋላም በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር ከነበረበት መነሣቱን ለማመልከት የሚነገር ነው፡፡


የእግዚአብሔር መልአክ የእመቤታችን ሥጋ ከሐዋርያው ዮሐንስ ጋር ተድላ ደስታ ወደ አለባት ገነት በመንፈስ ቅዱስ ተነጠቁ፡፡ ጌታም የእመቤታችንን ሥጋ ታወጣ ዘንድ ምድርን እንዲጠሩዋት ሰባቱን የመላእክት አለቆች አዘዛቸው፡፡ እነርሱም ትወጪ ዘንድ እግዚአብሔር አዞሻል አሏት፡፡ ያን ጊዜም ከዕፅ ሕይወት በታች ካለ መቃብር የእመቤታችን የማርያም ሥጋዋ ወጣ፡፡ ጌታችንም ዘላለማዊ ወደሆነ መንግሥተ ሰማያት መላእክት እና ሰማዕታት እየሰገዱላት አሳረጓት፡፡ ንጉሥ ዳዊት “በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋ ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች” እንዳለ፡፡ /መዝ 44:9/

ወንጌላዊ ዮሐንስም ከእርሷ በረከትን ተቀብሎ ተመልሶ ከሰማይ ወረደ፡፡ ሐዋርያት ተሰብስበው ስለ እመቤታችን ሥጋ ፈጽሞ ሲያዝኑና ሲተክዙ አገኛቸው፡፡ እርሱም እንዳየ እንደሰማ ሥጋዋም በታላቅ ክብር ማረጉን ነገራቸው፡፡ ሐዋርያትም ዓመት ሙሉ ቆዩ የነሐሴም ወር በባተ /በገባ/ ቀን ዮሐንስ እንዲህ አላቸው፦ የእመቤታችንን ሥጋዋን ለማየት ኑ፤ ሁለት ሱባኤ በመጾም እንለምን አለ፡፡ በጾም በጸሎት ሱባኤ ያዙ፤ ጌታም የእመቤታችንን ሥጋ አምጥቶ ስለሰጣቸው በታላቅ ዝማሬ፣ በውዳሴና በጽኑ ምሕላ ወስደው ቀድሞ በተዘጋጀው መካነ እረፍት በጌቴሴማኒ ቀበሯት፡፡

የእመቤታችን የቀብር ሥነ ሥርዓት በተፈጸመ ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ቶማስ አልነበረምና ከሀገረ ስብከቱ በደመና ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ እመቤታችን በተቀበረች በሦስተኛው ቀን እንደ ልጅዋ ትንሣኤ ተነሥታ ስታርግ ያገኛታል፡፡ ትንሣኤዋን ሌሎቹ ሐዋርያት አይተው ለእርሱ የቀረበት መስሎት ተበሳጭቶ “በመጀመሪያ የልጅሽን ትንሣኤ አሁን ደግሞ የአንቺን ትንሳኤ ሳላይ ቀረሁ ብሎ ከማዘኑ የተነሣ ከደመናው ተወርውሮ ሊወድቅ ቃጣው፡፡ እመቤታችንም ከእርሱ በቀር ሌሎቹ ሐዋርያት ትንሳኤዋን እንዳላዩ ነግራው አጽናንታው ሄዶም ለሐዋርያት የሆነውን ሁሉ እንዲነግራቸው አዝዛው ምልክት ይሆነው ዘንድ ሰበኗን /መግነዟን/   ሰጥታው ዐረገች፡፡

ሐዋርያው ቶማስም ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ እመቤታችንን እኮ ቀበርናት ብለው ነገሩት። እርሱም “ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር እንዴት ይሆናል?” አላቸው፡፡ “አንተ የጌታን ትንሣኤ ተጠራጠርክ አሁንም አታምንምን?” ብለው በቅዱስ ጴጥሮስ መሪነት ወደ እመቤታችን መካነ መቃብር ይዘውት ሄደው መቃብሩን ቢከፍቱ ሥጋዋን አጡት፡፡ ደነገጡም። ቶማስም “አታምኑኝም ብዬ እንጂ እመቤታችን ተነሥታ ዐርጋለች” ብሎ የሆነውን ሁሉ ነገራቸው፡፡ ለማረጋገጫ ምልክት እንዲሆን የሰጠችውን ሰበኗን አሳያቸው፡፡ ሰበኗን /መግነዟን/ ለበረከት ቆራርጠው ከተከፋፈሉ በኋላ ወደየአህጉረ ስብከታቸው ሄደዋል፡፡ (ዲያቆኑ ከመስቀሉ ጋር የሚይዘው ጨርቅ የእመቤታችን ሰበና ምሳሌ ነው)

ሐዋርያትም ትንሣኤሽን ቶማስ አይቶ እኛ እንዴት ይቀርብናል ብለው ከነሐሴ አንድ ቀን ጀምረው ሱባኤ ገቡ፡፡ በሱባኤው መጨረሻ በነሐሴ አሥራ ስድስት ቀን ጌታችን ጸሎታቸውን ተቀብሎ እመቤታችንን መንበር፣ ቅዱስ ጴጥሮስን ንፍቅ /ረዳት/ ቄስ፣ ቅዱስ እስጢፋኖስን ገባሬ ሰናይ /ዋና/ ዲያቆን አድርጐ ቀድሶ ሁሉንም ከአቆረባቸው በኋላ የእመቤታችንን ዕርገቷን ለማየት አብቅቷቸዋል፡፡

ቤተክርስቲያናችንም ሥርዓት ሠርታ ከሰባቱ ዓበይት አጽዋማት ተርታ አስገብታ ይህን ታላቅ የበረከትና የምሥጢር መግለጫ ጾም እንድንጾም አድርጋናለች፡፡ ሐዋርያት ያዩትን ድንቅ ምሥጢር የእመቤታችንን ትንሳኤና ዕርገት ለማየትና ከሐዋርያት አበው በረከት ለመሳተፍ ጌታችን “ልጆቼ” ይላቸው ለነበሩ ሐዋርያት አምሳል ሕፃናትና ወጣቶች፣ ሴቶችና ወንዶች፣ አረጋውያንም የጾመ ፍልሰታን መድረስ በናፍቆት እየጠበቁ በየዓመቱ በጾም በጸሎት ያሳልፉታል፡፡

የእመቤታችን ትንሣኤና ዕርገት መታሰቢያ /በጾመ ፍልሰታ/ ወቅት ብዙዎች ከቤታቸው ተለይተው፤ አልጋና ምንጣፍ ትተው፣ በመሬት ላይ ተኝተው ዝግን ጥሬ እፍኝ ውኃ እየቀመሱ በጾምና በጸሎት በመትጋት በታላቅ ተጋድሎ ይሰነብታሉ፡፡ በሰሙነ ፍልሰታ ምእመናን ለእመቤታችን ያላቸውን ጽኑና ጥልቅ ፍቅር የሚያሳዩበት ነው፡፡

ጌታችን ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሰ መቃብር ቆይቶ ሙስና መቃብር ሳያገኘው፣ መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል በሥልጣኑ እሑድ በመንፈቀ ሌሊት እንደተነሣ ሁሉ እርሷም በተቀበረች በሦስተኛው ቀን ማኅደረ መለኮት ናትና ሙስና መቃብር ሳያገኛት መግነዝ ፍቱልኝ፣ መቃብር ክፈቱልኝ ሳትል የልጅዋ ሥልጣን ኃይል ሆኗት መነሣቷን ትንሣኤዋ “ከመ ትንሣኤ ወልዳ፤ እንደ ልጅዋ ትንሣኤ” ነው ተብሎ ሲከበርላት ይኖራል፡፡

እመቤታችን ጥር 21 ቀን ዕረፍት በሆነበት ዕለት ሐዋርያት የእመቤታችንን ሥጋ ለማሳረፍ ወደ ጌቴሰማኒ መካነ ዕረፍት /የመቃብር ቦታ/ ይዘው ሲሄዱ አይሁድ በቅንዓት መንፈስ ተነሣሥተው “ቀድሞ ልጅዋን በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተነሳ፡፡ በአርባኛው ቀን ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡ እንደገናም ተመልሶ ይህን ዓለም ለማሳለፍ ይመጣል እያሉ በማስተማር ሕዝቡን ፈጽመው ወስደውታል፡፡ አሁን ደግሞ ዝም ብለን ብንተዋት እርሷንም እንደ ልጅዋ ተነሣች ዐረገች እያሉ በማስተማር ሲያውኩን ሊኖሩ አይደለምን፤ ኑ ተሰብሰቡና በእሳት እናቃጥላት ብለው ተማክረው መጥተው ከመካከላቸው “ታውፋኒያ” የተባለው ጐበዝ አይሁዳዊ ተመርጦ ሄዶ የእመቤታችንን ሥጋ የተሸከሙትን አልጋ ሽንኮር ያዘ፡፡ የአልጋውን ሽንኮር በያዘ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ በእሳት ሠይፍ ሁለት እጁን ስለ ቆረጣቸው ከአልጋው ሽንኮር ላይ ተንጠልጥለው ቀሩ፡፡ ታውፋንያ በፈጸመው ድርጊት ተጸጽቶ ወደ እመቤታችን ስለተማጸነ በኅቡዕ ተአምር የተቆረጡ እጆቹን እንደ ቀድሞ አድርጋ ፈውሳዋለች

እመቤታችን ከእናትና ከአባቷ ዘንድ ሦስት ዓመት፣ በቤተ መቅደስ 12 ዓመት፣ መድኃኔዓለምን በማህጸንዋ ጸንሳ ዘጠኝ ወር ፤ከልጅዋ ከወዳጅዋ ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ 33 ዓመት ከሦስት ወር፣ ከዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድ ዘንድ 14 ዓመት ከዘጠኝ ወር ጠቅላላ ድምር 64 ዓመት ሲሆናት ጥር 21 ቀን በ49 ዓመተ ምሕረት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች፡፡ ነቢያት አስቀድመው ስለ እመቤታችን እረፍትና ትንሳኤ በምሥጢር ተናግረዋል፡፡ ነቢዩ ዳዊት በመዝሙር /መዝ 131:8/ “አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ አንተና የመቅደስህ ታቦት” ብሎአል፡፡ ፈጣሪዬ ሆይ ምእመናንን ወደምታሳርፍበት ወደ መንግሥተ ሰማያት የመቅደስህን ታቦት ድንግል ማርያምን ይዘህ ተነሥ ሲል ነው፡፡ ይህም እመቤታችን እንደ ልጅዋ ትንሣኤ መነሣቷን የሚያመለክት ነው፡፡ ታቦት ያላትም ማደሪያው ስለሆነች ነው፡፡



ሰላም ለፍልሰተ ሥጋኪ መካነ ፍሥሐ ምጡቀ ፤

በአእባነ ባህርይ ዘተነድቀ፤

ማርያም ደብተራ እንተ ኢትትከደኒ ሠቀ  ፤                         


ትርጉም፦ እመቤቴ ማርያም ሆይ ምጡቅና ሩቅ ወደሚሆን የደስታ ቦታ ላረገ ሥጋሽ ሰላምታ ይገባል። ይኸውም ኅብሩ ሊመረምሩት በማይቻል ዕንቊ የታነፀ ሕንፃ ይገኝበታል (መልክአ ማርያም)

ለደገኞቹ ሐዋርያት ለደገኞቹ አባቶቻችን ለአባ ሕርያቆስ ለቅዱስ ኤፍሬም ፤ለቅዱስ ያሬድ ፤ ለአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የተገለጸች መቤታችን እኛንም በበረከት እና በረድኤት ትጎብኘን። ከልጅዋ ከወዳጅዋ ከመድኃኔዓለም ዘንድ ታማልደን። ጾሙን ጾመ ሥርየት ፤ጾመ መድኃኒት ያድርግልን- አሜን ፡፡