ቅ/አውግስጢን “እንደ ርግቦች እንጣላለን እንጂ እንደ ተኩላዎች ፈጽሞ አንፋቀርም!!” ብሏል። ርግቦች እርስ በእርስ ይጠባበቃሉ፣ ለመመገብ አንድ ይሆናሉ፤ አንድ ላይም ይበራሉ! አንድም መንፈስ ቅዱስ በርግብ ይመሰላል። ርግብ ኃዳጊተ በቀል በቀልን የማትይዝ ናት። መንፈስ ቅዱስም ኃዳጌ በቀል ነውና። አንድም ርግብ ክንፏን ቢመቱባት ዕንቍላልዋን ቢሰብሩባት ቤቷን ካላፈረሱባት አትሄድም። መንፈስ ቅዱስም ኃጢአት ቢሰሩ ፈጽሞ ካልካዱ በስተቀር አይለይምና በርግብ ተመሰለ።
አንድ የተከበሩ አባት “እንደ ርግብ እንጂ እንደ ግመል አትኹኑ” ማለትን ያዘወትሩ ነበር። ብዙም አልገባኝምና ቀረብ ብዬ አባቴ ሆይ ምን ማለት ይሆን አልኳቸው። ፍግግ ብለው እያዩኝ እንዲህ አሉኝ።
“ልጄ ሆይ ዓለም አቀፍ የሰላም ምልክት ርግብ ናት። ርግብ የዋህና ሰላማዊ ናት። ግመል ግን በቀለኛ ናት። አጥብቆ የመታትን እስከ ስድስትና ሰባት አመት አትረሳም! ቀን ሲመቻት ትረግጠዋለች ስፍራ ሲመቻት ገፍታ ገደል ትጥለዋለች። እኛ ግን ግመልን እንጠቀምባታለን እንጂ ባሕርይዋን አንጠቀምም አንወደውምም” አሉኝ የተከበሩት አባት አሁንም ፍግግ እያሉ። አባባላቸው ማረከኝ። ጠጉሬን እየዳሰሱ ወርቅ አባባላቸውን እንዲህ እያሉ ይመርቁልኝ ዠመር። ልጄ ሆይ “እንደ ርግቦች እንጣላለን እንጂ እንደ ተኩላዎች ፈጽሞ አንፋቀርም!!” ሐሳብ ተለዋውጠው እንደ ጉድ ተወያይተው እንደ ጉድ ተከራክረው በመጨረሻ የሚግባቡ ርግቦች ደስ ይላሉ። ልጄ ሆይ እንደ ተኩላ ከምትፋቀር እንደ ርግብ ያጣላህ አሉኝ። እኔም ጉልበት ስሜ ተሰናበትኳቸውና ይህችን ጽሑፍ መጻፍ ዠመርኩ።
“በኢየሩሳሌም ቆዩ”!
ኢየሩሳሌም ማለት የሰላም ከተማ ማለት ነው። ደቀመዛሙርቱም “ኃይለ መንፈስ ቅዱስን ከሰማይ እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ቆዩ” ተብለው ነበር። ሁለት ደቀ መዛሙርት ግን ይህን ቃል ረሱና ከኢየሩሳሌም ከተማ ወጡ! እነማን ይሆኑ?
እነሆ ሁለት መንገደኞች የጌታችንን ነገረ ሕማሙን የእለተ አርብ የቀራንዮ ውሎውን እየተነጋገሩ ከኢየሩሳሌም 11 ምዕራፍ ወደምትገኘው ወደ ኤማሁስ ይጓዙ ነበር። ጌታችን ያዘዛቸው ግን ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡ ነበር። የኤማሁስ መንገደኞቹ ሉቃስና ቀልዮጳ ይህን ቃል ረሱና ከኢየሩሳሌም ለመውጣት ጉዟቸውን ጀመሩ።
የኤማሁስ መንገደኞቹ በጉዟቸው ላይ ይነጋገሩ የነበረው ስለ ቃለ እግዚአብሔር ነበርና “ቃል” በመካከላቸው ተገኘ። ሁለት ወይም ሦስት ሆናችሁ በስሜ ብትሰበሰቡ በመካከላችሁ እገኛለሁ ያለ ጌታ በመካከላቸው ተገኘ። ልባቸውን ከፈተ። ያን ጊዜም “በኢየሩሳሌም ቆዩ” የሚለው ቃል ትዝ አላቸውና በዛች ሰአት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። ሉቃስ [24: 13-33]
ይህ ወንጌል እኛም እንደ ኤማሁስ መንገደኞች ስለ ነገረ ቤተክርስቲያን እየተነጋገርን ከቤተክርስቲያን እርቃ ወደምትገኘው ወደ ዓለም እንዳንጓዝ ያስተምረናል። በተለያዩ ምክንያት ከቤተክርስቲያን ስንርቅ በሥጋም በነፍስም መጠውለግ ቀጥሎም መድረቅ ይመጣል! ለዚህ እኮ ነው ጌታችን “እየጠወለጋችሁ ስትሄዱ እርስ በእርሳችሁ የምትነጋገሩት ስለምንድን ነው?” ያለው። ሉቃስ [24:16]
“ኢየሩሳሌም”
ጌታችን መከራ መስቀልን የተቀበለው፣ የሞተው፣ የተቀበረው፣ የተነሣውና ያረገው በኢየሩሳሌም ነው። በመሆኑም ለክርስቲያኖች የተቀደሰች ከተማ ናት። ሐዋርያት ጸጋ መንፈስ ቅዱስን እስከሚቀበሉ ድረስ በጸሎትና በጾም የተጉት በኢየሩሳሌም ነው። መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያቱ የወረደው፣ የመጀመሪያዎቹ 3000 ምዕመናን ቤተ ክርስቲያንን የመሰረቱት በኢየሩሳሌም ነው። ቀዳሜ ሰማዕት ቅ/እስጢፋኖስ በድንጋይ ተወግሮ የሞተው፣ ከሐዋርያት የመጀመሪያ ሰማዕት ቅ/ያዕቆብ በሰይፍ የተከለለው በኢየሩሳሌም ነው። የመጀመሪያው ሲኖዶስ የተካሄደውም በዚህች ታሪካዊት ከተማ በኢየሩሳሌም ነው።
ኢየሩሳሌም በዕብራይስ ቋንቋ “ይሩሻሌም” ስትባል የሰላም ከተማ ማለት ነው። በአሁኑ ዘመን ዓረቦች አል-ቁዱስ ብለው ይጠሯታል። የኢየሩሳሌም የመጀመሪያ ስም “ሳሌም” ይባላል። ይህም “ሰላም” ለማለት ነው። ኢየሩሳሌም ተብላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠራችው በመፅሐፈ ኢያሱ 10: 1 ላይ ነው። በሌላ በኩል ኢየሩሳሌም ጽዮን ተብላ ተጠርታለች። ይህም በተመሰረተችበት ተራራ ለመጥራት ሲሆን፣ ሞርያ ደግሞ በሌላኛው በኩል የሚገኘው የተራራዋ ስም በመሆኑ ነው። ይህ ተራራ አብርሐም ይስሐቅን ለመሥዋዕትነት ያቀረበበት፣ በኋላም ንጉሥ ሰለሞን ቤተ መቅደሱን የሰራበት ተራራ ነው።
አማናዊት የሠላም ከተማ ኢየሩሳሌም የተባለችው እመቤታችን ናት፤ ዳዊት በበገናው ዕግትዋ ለጽዮን /ጽዮንን ክበብዋት/ መዝ [47: 12] እንዳለ 72ቱ አርድእት 36ቱ ቅዱሳን አንዕስ 12 ሐዋርያቱ በአጠቃላይ 120ው ቤተሰብ እመቤታችን በመካከላቸው አድርገው ዙሪያዋን ከበው ለጸሎት ይተጉ ነበር፤ ያን ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያቱ ወረደ! ይለናል የሐዋ [1: 14]
“የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ!”
በማርቆስ እናት በማርያም ባውፍልያ ቤት በላይኛው ፎቅ መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያቱ ወረደ፤ የሐዋ [2: 1] መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያቱ ላይ ወረደ ማለት መንፈስ ቅዱስ በአካል በሐዋርያቱ ላይ ወረደ ማለት አይደለም። ብዙዎቻችን ይህ ይመስለናል። ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያቱ ላይ ወረደ ሲባል በአካል ወረደ ማለት ሳይኾን በጸጋ በሐዋርያቱ ላይ ወረደ ማለት ነው። ይበልጥ እንዲገባን ምሳሌ እንይ።
አንዱ የተመረጠው ዲቁና ሊቀበል ቀረበ እንበል። ሕዝቡ በተሰበሰበበት በቤተክርስቲያን ጳጳሱም ተገኝተው ጸልየው እፍ እያሉ ንሳ መንፈሰ ቅዱሰ /መንፈስ ቅዱስን ተቀበል/ ይሉታል። ያ ሰው መንፈስ ቅዱስን ተቀበለ ማለት የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ አደረበት ማለት ነው እንጂ መንፈስ ቅዱስ በአካል መጥቶ አደረበት ማለት አይደለም። ይህማ ከሆነ መንፈስ ቅዱስ በአንድ ሰው ተወሰነ ማለት ይሆናል። ይህ ደግሞ ስህተት መኾኑ ግልጽ ነው። አንድም መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያቱ ላይ በአካል ወረደ ካልን ሐዋርያቱ የጸጋ ሳይኮን የባሕርይ አምላክ ሆኑ ማለት ነውና ይህን ልብ ብለን ልንረዳ ያስፈልጋል። መንፈስ ቅዱስ በሰዎች ላይ የሚወርደው በጸጋው ነው እንጂ በአካሉ አይደለም።
“የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በሐዋርያቱ ላይ የወረደበት ደገኛይቱ ቀን!”
እስራኤላዊያን በአመት አንዴ ለመስገድ ወደ ኢየሩሳሌም ይሄዱ ነበር፤ ኢትዮጲያዊው ጃንደረባ /ባኮስ/ ወደ ኢየሩሳሌም የሄደውም በዚህ በዓል ምክንያት ነው፤ ይህም በዓለ ሰዊት /የእሸት በዓል/ በመባል ይታወቃል። ከየሃገሩ የመጡ እስራኤላዊያን እንዴት ይግባባሉ? ቢባል እነሆ እስራኤላዊያን የሚታወቁበት ጥሩ ባህል አላቸው፤ አራቱ የአይሁድ ወገኖች /ፈሪሳዊያን፣ ሰዱቃዊያን፣ኤሴናዊያንና ቀናዕያን/ የትም ሀገር ቢኖሩ ባህላቸውንና ሃይማኖታቸውን ቢሞቱ አይደባልቁም! አይረሱምም! በፍልስጤም ምድር ቋንቋችንን አንናገርም ያሉ ቀናዕያን የተባሉ አይሁድም ነበሩ። አፍቃሬ ወግ የሆኑ ፈሪሳዊያንም ባህላቸው እንዲነካባቸው አይፈቅዱም፤ ምንም እንኳን እንደ ፈሪሳዊያንና ቀናዕያን እንሁን ባይባልም ባህላችንን በአውሮባ እርሾ እንዳንደባልቅ ግን በአንድም በሌላም ያስተምረናል። ዛሬ በውጭው አለም የሀገሩን ባህል የማያውቅና የሀገሩን ቋንቋ የማይናገር ብሎም ቋንቋውን ጭራሽ የማይሰማ ትውልድ ብቅ እያለ ነው፤ ልጆቻችንን የሀገራቸውን ባህል በሚገባ በማስተማር ከትውልድ ወቀሳ መዳን አለብን።
ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስ፤ እስራኤላዊያኑ ምንም እንኳን በስደት ሀገር ቢኖሩም የራሳቸውን ቋንቋ ልጆቻቸው ጭምር በሚገባ ስለሚያውቁ በትውልድ ቋንቋቸው ማለትም በአረማይክ በዕብራይስጥ እና በዘመኑ ኢንተርናሽናል ቋንቋ በነበረው በግሪክ እርስ በእርሳቸው ይግባቡ ነበር። በአንድ ወቅት ግን ያልተለመደ እንግዳ ነገር ተፈጠረ! ከተለያዩ ሀገራት የመጡት አይሁድ በኢየሩሳሌም በተገኙበት በዛች ደገኛዋ ቀን መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያቱ ወረደ! ሐዋርያቱም አይሁድን በመጡበትን ሀገር ቋንቋ አናገሯቸው! ይህን ጊዜ አይሁድ ጉድ እንግዳ ነገር ብለው እጃቸውን በአፋቸው ላይ ጫኑ! ይህ ነው የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ!
አዳምና እንስሳቱ የሚግባቡባት አንድ ቋንቋ ነበረች፤ አዳም ለእንስሳቱ ስም ያወጣላቸውም ነበር፤ አዳም ሲበድል የሰውና የእንስሳት ቋንቋ ተከፈለ። ባቢሎን ማለት የተደበላለቀ ማለት ነውና ባቢሎናዊያን ሲበድሉም ቋንቋቸው ተደበላለቀ።
ቋንቋ ለሐዋርያቱ የተሰጠበት ምክንያትም በአለም እየዞሩ ወንጌልን እንዲያስተምሩበትና በቋንቋ ምክንያት አገልግሎታቸው እንቅፋት እንዳያገኘው ነው። የሐዋርያው ቶማስ ስብከት እስከ ሩቅ ምሥራቅ ቻይና ድረስ ደረሰ! የቋንቋ ስጦታ ይህን ለመሰለ አገልግሎት ነው እንጂ መግባባት የሚቻልበት ቋንቋ እያለን የማይገባ ቋንቋ እንድንናገር አይደለም።
ጅብ ከጅብ ይግባባል
ወፍ ከወፍ ይግባባል
እንስሳቱ ኹሉ ይግባባሉ
ቋንቋ የሌለው ሕዝብ ፤ ሕዝብ የሌለው ቋንቋ ከቶ አልተፈጠረም።
ትዝ የሚላችኹ ከሆነ ባለፈው ሳምንት ስለበዓለ ዕርገቱ ስናነሳ ጌታችን ሞትን ድል አድርጎ ከተነሳ በኋላ ለ40 ቀናት ለሐዋርያቱ እየተገለጸ ያስተምራቸው ነበር ብለናል
[ሐዋ. 1:3] አርባው ቀናት ሲፈጸም ዓረገ። ባረገ በ10ኛው ቀን መንፈስ ቅዱስን ላከላቸው። እስከዚያው የት ነበር?
እነኾ በ9ኙ ከተማ የነበሩት መላእክት ሚሥጢረ ሥጋዌን ያላወቁ ነበርና ለመላእክቱ ሲያሳውቃቸው ነበር።
“
“መንፈስ ቅዱስ ከጥምቀት እስከ ትንሣኤ ዘጉባኤ”
አንድ ሰው በጥምቀት መንፈስ ቅዱስን ከተቀበለ በኋላ ክህደት ካልፈጸመ በቀር መንፈስ ቅዱስ ከእርሱ ፈጽሞ አይለይም፡፡ ስንሞትም መንፈስ ቅዱስ አይለየንም! ለዚህ ነው መንፈስ ቅዱስ ያልተለየው የነብዩ ኤልሳዕ ዐፅም የሞተውን ያስነሳው 2ኛ ነገሥት [13:21] በነገራችን ላይ የሞተውን ያስነሳው የኤልሳዕ ዐፅም በግብፅ ገዳመ አስቄጥስ ይገኛል። ቅዱሳን ጻድቃን እና ሰማዕታት ምንም ተፈጥሮአዊቱ ነፍስ ከሥጋቸው ብትለይም ከእነርሱ ሰውነት መንፈስ ቅዱስ አድሮ ስለሚገኝ አጋንንት በእነርሱ አስከሬን ፊት ጸንተው መቆም አይቻላቸውም፡፡ ወይም በእነርሱ አካል አድሮ በሚኖረው መንፈስ ቅዱስ ምክንያት ሲጮኽ ይስተዋላሉ፡፡ እንዲሁም በእነርሱ ዐፅም ተዓምራት ሲፈጸም፣ ሕመምተኞችም ከሕመማቸው ሲፈወሱ እንመለከታለን።
መንፈስ ቅዱስ ከትንሣኤ በኋላም አይለየንም! ከትንሣኤ በኋላ ነፍስ ወደ ማደሪያዋ ሥጋ ስትመለስ በእነርሱ ውስጥ መንፈስ ቅዱስ አድሮ ይኖራል፡፡ ከእነርሱ ፈጽሞ አይለይም። ስለዚህም ነው ጻድቃን ነፍሳቸው ከሥጋቸን ስትለይ አረፉ እንጂ ሞቱ የማንለው፡፡
መንፈስ ቅዱስ (ፓራክሊቶስ)
መንፈስ ቅዱስ በጽርኡ ፓራክሊቶስ ፣ ፔንዲኮንዳ ሲባል አረጋጊ አጽናኝ አስደሳች ማለት ነው።
* በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቁ። ማቴዎስ [28:19] በመንፈስ ቅዱስ ስም እንጠመቃለን። ፍጡር ነው ለሚሉት ግን በፍጡር ስም እንጠመቃለን ማለታቸው እንደኾነ ሊረዱት ይገባል።
የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ
የእግዚአብሔር ፍቅር
የመንፈስ ቅዱስም ሕብረት
ከሁላችን ጋር ይኩን። አሜን።
2ኛ ቆሮንቶስ [13: 14] ቅ/ጳውሎስ መንፈስ ቅዱስ የባሕርይ አምላክ መሆኑን ለማስረዳ ይህን የመሳሰሉ ብዙ ጥቅሶችን ጽፋል።
የእግዚአብሔር ቀኝ ኃይልን አደረገች
የእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ አደረገች
የእግዚአብሔር ቀኝ ኃይልን አደረገች
መዝ [117 (118):16] ቃላቱ የተደጋገመበት ምክንያት አለው።
አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስን ሲነግረን ነው።
* መንፈስ ቅዱስ “መንፈስ” ስለተባለ አካል የለውም የሚሉ አሉ። “እግዚአብሔር መንፈስ ነው” ሲል እግዚአብሔር አካል የለውም ማለት አይደለም። ዮሐንስ [4: 24] አንድም ጌታችን ሲጠመቅ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል በራሱ ላይ አርፏል። አካል ባይኖረው በርግብ አምሳል አይገለጽም ነበር። አንድም ጌታችንን አብና መንፈስ ቅዱስ ልከውታልና “እግዚአብሔርና መንፈሱ ልከውኛል” የሚል ቃል አለ። ኢሳይያስ [48:16] “ልከውኛል” የሚለው ቃል ኹለት መኾናቸውን ያሳያል። እነሱም አብና መንፈስ ቅዱስ ናቸው።
ወንጌሉ እንዳለው አንድ ገበሬ ዘር ሊዘራ ወጣ። መልካሙንም ዘር ዘራ። ጠላት መጥቶ እንክርዳዱን ዘራ። ይህም ምሳሌ ነው። መልካሙን ዘር ሐዋርያት ከዘሩ በኋላ ዲያቢሎስ በአርዮስ አድሮ እንክርዳዱን ዘራ። አንድም አርዮስን ካወገዙት አበው በኋላ እነ መቅደንዮስና ንስጥሮስ እነ ሰባልዮስና አርጌንስ እንክርዳዱን ዘሩ። መቅደንዮስ መንፈስ ቅዱስ ፍጡር ነው ብሎ ተነሳ። መንፈስ ቅዱስን የካደ በዚህም ሆነ በወዲያኛው ዓለም ይቅር አይባልም። ማቴዎስ [12:32] ለምን በወዲያኛውም ዓለም ተባለ ልንል እንችላለን። አልቦቱ ለሰብእ ንስሐ እምድኅረ ሞት እንዲል በወዲያኛው ዓለምማ ንስሐ የለም ለምን መጥቀስ አስፈለገ ቢሉ እነሆ ኃጢአትን ለካህን ነግሮ ቀኖና ጀምሮ ቢሞት ሳይጀምረውም ቢሞት መካነ ንስሐ አለ ከዚያ አድርሶ ይወጣልና ይህን ለማሳየት ነው ። መንፈስ ቅዱስን የካደ ግን መካነ ንስሐ አይገባውም። በዚህም ሆነ በወዲያኛው ዓለም ይቅር አይባልምና።
*****************
ይወርድ መንፈስ ቅዱስ በላዕለ ህብስቱ ወወይኑ ሶበ ይብል ካህን “ፀጋ መንፈስ ቅዱስ ፈኑ”
As the priest says let the holy sprite descend,
On this revered Holy of the holies
ፈኑ ፀጋ መንፈስ ቅዱስ ላዕሌነ
Send the grace of the holy sprite upon us
“የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ላክልን”
በሕይወታችን ከክፉ ነገር ሁሉ በመውጣት መግባታችን የሚጠብቀን ፣በአገልግሎታችን የሚረዳንም እነሆ መንፈስ ቅዱስ ነው።
“የመንፈስ ቅዱስ” ፍሬዎችም
ፍቅር
.
.
.
.
.
ትህትና
.
.
.
.
.
ትዕግስት
.
.
.
.
.
ሰላም ፣ ደስታ ፣ ቸርነት ፣ በጎነት ፣ ቅንነት ፣ የዋህነት፣ ራስን መግዛት፣ ታማኝነት ናቸው። ገላትያ 5:22