Friday, 13 July 2012

…….“እናት ቤተክርስቲያን ለመናፍቃን የማያዳግም መልስ አላት” …….



……. ያመነ የተጠመቀ ይድናል ይላልና ሳያምኑ እንዴት ማጥመቅ ይቻላል? ……. ሕጻናትን ሳያምኑ ሳይማሩ ነፍስ ሳያውቁ ለምን እየተጣደፋችሁ ታጠምቃላችሁ? ……. ለመጠመቅ’ኮ ማመን አለባቸው” ብላ አንድ ወዳጄ ጥቅሱን ጠቅሳ ጥያቄ ደራርባ ጠየቀችኝ ……. ማር [16:16]  

……. እህት ዓለም ጌታችን በወንጌል  ሕጻናትን ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ አትከልክሏቸው ብሏል……. ይህ ማለት ምን ማለት ነው? ብዬ ጠየኳት……. ልጅቱ ከማሰብ በስተቀር መልስ አጣች…….

እህት ዓለም ሕጻናትን ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ አትከልክሏቸው ማለት’ኮ አይጠመቁ እያላችሁ መንግሥተ ሰማያት እንዳይገቡ አትከልክሏቸው ማለት ነው!! አልኳት።

ሕጻናት አይጠመቁ የሚሉ ሁሉ ይህንን እውነታ አውቀው ይፈሩ! አንድም ጌታችን ለሐዋርያቱ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቁ አላቸው እንጂ እድሜ እየጠየቃችሁ 30 ዓመት የሞላቸውን ብቻ አጥምቁ አላለም። አንድም ሐዋርያቱ እድሜ እየጠየቁ የልደት ካርድ እያዩ አላጠመቁም። እንዲያውም ቅ/ጴጥሮስ የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ ነው ብሎ ሰበካቸውና 3 ሺህ ሕዝብ አጠመቀ። ሐዋ [2:38] እዚህ ጋ ከ 3 ሺህ ሕዝብ መካከል ሕጻናት አልተጠመቁም ማለት ቅ/ጴጥሮስን ማቃለል ነው። ሐዋርያቱ እነ ቅ/ጴጥሮስ ይህን አያደርጉምና። “ሕጻናትን ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ አትከልክሏቸው ብሎ ጌታ አስተምሯቸዋልና ቅ/ጴጥሮስ ሕጻናት አይጠመቁ ብሎ መንግሥተ ሰማያት እንዳይገቡ አልከለከላቸውም!!

ከወዳጄ ጋ ይህን የመሳሰለውን ከተነጋገርን በኋላ በመኃል ሕጻናት አይጠመቁ ስትሉ under age መንግስተ ሰማይ አይገቡም እንዴ?” አልኳት ትንሽ ፈገግ እንድትል ብዬ። ሐሳቤ ተሳክቶ ፈገግ አለችና እንዲህ ብላ ተረተች።

አሁን ገና በራልኝ አለች እብድ ቤቷን አቃጥላ ብላ ወዳጄ ነገሩ ሁሉ ፍንትው ብሎ ገባኝ አለችኝ።


እስኪ ዘና ብላችሁ ተቀመጡና አንድ በጣም የገረመኝን ገጠመኝ ላውጋችሁ።

አንዲት እናት ልጇን ክርስትና ለማስነሳት በለሊት ቤተክርስቲያን መጣች። ይህ ምን ይገርማል? በሉኛ። ይህስ ባልከፋ የገረመኝ ወዲህ ነው። ጌታችን ሐዋርያቱን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቁ እንዳላቸው ካህናቱ ተሰበሰቡና

አጠምቀኪ በሥመ አብ
አጠምቀኪ በሥመ ወልድ
አጠምቀኪ በሥመ መንፈስ ቅዱስ

እያሉ ታናሽዋን ልጅ ማጥመቅ ጀመሩ።  ሚሥጢር ከተግባር ጋር አስማምታ ወንጌልን የምታስተምረን እናት ቤተክርስቲያን እንዴት ደስ ትላለች! ይህ ሁል ጊዜ ሲደንቀኝ በአንደኛው ሰንበት ደግሞ እጅግ የደነቀኝን ነገር አየሁ። እናትየው ልጇን ክርስትና ካጠመቀች በኋላ በቅዳሴ ላይ ወንጌሉን መሳለም ጀመርን። ይህን ጊዜ የክርስትና እናት ተብየዋ ወንጌሉን አልሳለምም አለች። የክርስትና እናትኮ ነሽ ወንጌሉን ለምን አትሳለሚም ብለን ጠየቅናት። ወይ ፍንክች ብላ አይሆንም አለች። እኛም ግራ ገባን። ግራ ቢገባን ቀኝ ቢገባን ልጅቱ አያስጨንቃትም። በመጨረሻም በቃ እኔ የሌላ እምነት ተከታይ ነኝ” አለችን። ክው ነበር ያልነው። ልጅቷ ጴንጤ ነበረች! የክርስትና እናት ጴንጤ ተጠማቂዋ ልጅ ደግሞ ክርስቲያን መሆኗ ነው!

ይድረስ ለካህናት”

ይህ የሚያስተምረን ሁለት ዐቢይ ነገሮች አሉ። ካህናቱ ሲያጠምቁ የክርስትና እናትና አባቶችንም የራሳቸውን የክርስትና ስም በመጠየቅ ማንነታቸውን ጠንቅቀው ማወቅ አለባቸው። አንድም ወላጆች ጥምቀት ማለት ዝምድናን ለማጥበቅ መዛመቻ ሳይሆን ሚሥጢር መሆኑን መረዳት አለባቸው። ሚሥጢረ ጥምቀት መባሉ ከንቱ አይደለምና! የሰው መሰረቱ እናትና አባቱ” እንዲል ወላጆች፣ የክርስትና አባትና እናት ኃላፊነታቸውን በሚገባ መወጣት ይኖርባቸዋል። መልካም ላባ ከመልካም ወፍ ይገኛልና ለልጆቻችን ክርስትናን በሚገባ ማስተማር አለብን።

ይህ ደንቆኝ ሳያባራ የሚጠየቀው ጥያቄ ደግሞ አስደመመኝ። ልጅቷ ሚሥጢረ ጥምቀትን እናስተምራችሁ እያለች እሪሪሪ…. ብላ ስታለቅስ በመገረም እጄን በአፌ ላይ ጫንኩኝ። እንዲህ አለችና በጥያቄ አፋጠጠችኝ። ጌታችን የተጠመቀው በ30 ዘመኑ ነው። እናንተ ወንድ በ 40 ቀን ሴት በ 80 ቀን የምትሉት ለምንድን ነው። ለምን? እንዴት? ወዴት? እያለች ጥያቄዋን አዘነበችው።

እህት ዓለም ብዙ ጠይቀሽኛልና እኔ አንድ ጥያቄ ብቻ ልጠይቅሽ አልኳት። ባትደሰትም ጭንቅላቷን በእሺታ ላይና ታች አወዛወዘችው።

አይበለውና 30 ዓመት ሳይሞላኝ ብሞት እጣ ፋንታዬ ምንድን ነው? ቅድም አንቺው ባመጣሽው ጥቅስ ያላመነ ያልተጠመቀ ይፈረድበታል” ይላልኮ አልኳት። ማር [16:16]

ይህን ጊዜ ልጅቱ ለአርምሞ እንደዘጋ ባህታዊ ዝምታዋ በዛ።ለደቂቃዎች ዝም ብላ ቆመች። “አንቺው ታመጪው አንቺው ታሮጪው” ይላሉ የሀገሬ እማ ወራ። ጥቅሱን ያመጣችው እሷ እራስዋ ነበረች። በዝምታዋ ደቂቃዎች እሮጡ። መልስ ፍለጋ መሆኑ ስለገባኝ እስክትናገር ጠበኳትና አንችዬ ተናገሪ እንጂ አልኳት። አስባ አስባ መልሱ ቢጠፋት ሌሎቹን እጠይቃለሁ ብላ ከአጠገቤ እየበረረች ሔደች።

በሳምንቱ ከበፊቱ በዝተው መጡና አልተሸነፍንም ለማለት ጥያቄዎችን እንደ ጉድ ማውረድ ጀመሩ። ጥያቄያቸው በሙሉ እንደ ጉድ ተመለሰላቸው።

የኛ ተራ ደረሰና እኛም ጥያቄ መጠየቅ ጀመርን።


ጌታችን ለሐዋርያቱ “በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም” አጥምቁ ብሎ አዘዛቸው። ማቴ. [28:19] ቅ/ጴጥሮስ ግን ሕዝቡን ካስተማራቸው በኋላ “ምን እናድርግ? ሲሉት በኢየሱስ ክርስቶስ ስም” ተጠመቁ አላቸው። ሐዋ [2:38]

እስኪ ጥያቄ እናንሳ!

ጌታችን “በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም” አጥምቁ እያላቸው ቅ/ጴጥሮስ እንዴት በኢየሱስ ክርስቶስ ስም” ተጠመቁ አለ? የሐዋርያት አለቃ ነኝ ብሎ የጌታን ትዕዛዝ ሽሮ ይሆን እንዴ? ወይስ ያን ሁሉ ሕዝብ ሲያስተምር ድክምክም ብሎት ይሆን እንዴ? ወይስ ጌታ ያዘዘውን ረስቶ ተሳስቶ ይሆን እንዴ? ለምን ይመስላችኋል እንዲህ ያለው? ብለን ጠየቅናቸው። አንዳች መልስ ጠፋ። አሁንም እንደ ባህታዊ ዝምታቸው በዛ።


እኛው ጠይቀን እኛው መለስነው።

ቅ/ጴጥሮስ የጌታን ትዕዛዝ ሽሮም አይደል ፣ ደክሞት አልያም ተሳስቶም አይደል። ሐዋርያቱ ያጠመቁት መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ነውና መንፈስ ቅዱስ ስለሚመራቸው ተሳስተው አይደለም። ደም ከደም ስር ጋር እንደማይጋጭ ሁሉ የሐዋርያቱም ትምህርት ከጌታችን ትምህርት ጋር አይጋጭም። ይህ ሚሥጢር ስላለው ነው እንጂ!


“በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም” ማጥመቅ እና በኢየሱስ ክርስቶስ ስም” ማጥመቅ አንድ ነው። በአገዛዝ ፣ በፍርድ ፣ በሥልጣን በአምላክነት አንድ ናቸውና!  ቅ/ጴጥሮስ ለዚህ እኮ ነው “በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም” ተጠመቁ ማለት ሲችል በኢየሱስ ክርስቶስ ስም” ተጠመቁ ያለው!


አንድም ጌታችን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ “ስም አጥምቁ አላቸው እንጂ “ስሞችአላላቸውም። በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ብሎ ሦስትነታቸውን” ስም ብሎ “አንድነታቸውን” ተናገረ!


ጥምቀት ኃጢአትን ያነጻል?


በጸሎተ ሐይማኖት ላይ ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት ለስርየተ ኃጢአት” እንላለን።


ትርጉም፦ ኃጢአት በሚሰረይባት በአንዲት ጥምቀት እናምናለን። ይህም ጥምቀት ኃጢአትን እንደሚያስተሰርይ ያስረዳናል። እንዴት? ቢሉ ቅ/ጴጥሮስ ኃጢአታችሁ እንዲሰረይላችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ ብሏልና ጥምቀት ኃጢአትን ያስተሰርያል። ሐዋ [2:38] አንድም ሐይማኖተ አበው በአንዲት ጥምቀት እናምናለን እንዲል ጥምቀት አንዲት ናት አትከለስም አትደገምም ኤፌሶን [4:4] አንድም ንጹሕ ውኃ እረጫችኋለሁ፤ እናንተም ትነጻለችሁ። የድንጋዩን ልብ አውጥቼ የስጋን ልብ እሰጣችኋለሁ እንዲል ጥምቀት ኃጢአትን ያስተሰርያል። ሕዝቅኤል [36:25]


ጥምቀት ከኃጢአት እንደሚያነጻ አይተናል። ሕጻናቱ የሚጠመቁት ግን ኃጢአትን ሰርተው ሳይኾን ከአዳም ጀምሮ በዘር የሚተላለፈውን ኃጢአት /ጥንተ አብሶ/ original sin ለማስተሰረይ ነው። “በአንድ ሰው ምክንያት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ” እንዲል የአዳም ኃጢአት በሁላችንም አለ። ሮሜ [5:12] ሕጻናቱ ከዚህ ኃጢአት የሚነጹት በጥምቀት ነው!! የዘመናችን ሰዎች ልጆቻቸው እንዴት ይሆን ከዚህ ኃጢአት የሚነጹት? ኧረ ባካችሁ ሕጻናት መንግሥተ ሰማያት ይገቡ ዘንድ አትከልክሉ። 


አንድም ሕጻናት ሲጠመቁ ልብ ብላችሁ ካያችሁ ካህኑ ሕጻኑን ሦስት ጊዜ ውኃ ውስት ብቅ ጥልቅ ያደርገውና በሦስተኛው እንደወጣ ይቀራል። ይህ ግሩም ሚስጢር አለው። ሦስት ግዜ ብቅ ጥልቅ ማለቱ ጌታችን በመቃብር የማደሩ ምሳሌ ነው። ሕጻኑ በሦስተኛው እንደወጣ ይቀራል፤ ይህም የጌታችን ትንሳኤ ምሳሌ ነው። ቅ/ጳውሎስም ሞቱን በሚመስል ሞት ከሱ ጋር ከተቀበርን ትንሳኤውን በሚመስል ትንሳኤ ከሱ ጋር እንነሳለን ብሏል። ሮሜ [6:3] ፣ ቄላስይስ [2:11] ቤተክርስቲያናችን ወንጌሉን እንዲህ ተርጉማ በተግብር ታስተምራለች!


ሰባቱ ሚሥጢረ ቤተክርስቲያን ስማቸውንና ትርጉማቸውን ለማወቅ የሚያረዳ ግሩም ዘዴ አለ። እስኪ ይህን ዘዴ ኤፍራታ በምትባል ሕፃን በምሳሌ አብረን እንይ።

1. ጻን ኤፍራታ ገና እንደተወለደች በሰማንያ ቀኗ ትጠመቃለች። (ሚሥጢረ ጥምቀት)

2. ከጥምቀት በኋላ ወዲያው ሜሮን ትቀባለች (ሚሥጢረ ሜሮን)

3. በመቀጠል ትቆርባለች (ሚሥጢረ ቁርባን)

4. ከፍ ስትል በኃጢአት ብትወድቅ ንስሐ አለ። (ሚሥጢረ ንስሐ)

5. ንስሐ ለነፍስ ነው፤ በሥጋ ስትታመም በቀሳውስት የምትቀባው ቅዱስ ቅባት አለ (ሚሥጢረ ቀንዲል)

6. ከዚህ ሁሉ በኋላ ኤፍራታ ለጋብቻ ስትደርስልን ታገባለች። (ሚሥጢረ ተክሊል)

7. ወይዘሪት ኤፍራታ ይህንን ሁሉ ሚሥጢራት የፈጸመውን ካህን በሠርጓ ላይ ትጠራዋለች። (ሚሥጢረ ክህነት)


ሕጻናት አይጠመቁ የሚሉ ሁሉ ይህንን እውነታ አውቀው ይፈሩ! …….“እናት ቤተክርስቲያን ለመናፍቃን የማያዳግም መልስ አላት” …….