Saturday, 31 December 2011

እንተዋወቅ ስም፦ ሐዋርያው ቅ/ጳውሎስ እባላለሁ

እንተዋወቅ

ስም፦ ሐዋርያው ቅ/ጳውሎስ እባላለሁ
ሀገር፦ መንግስተ ሰማያት
ዜግነት ፦ ክርስቲያን
ስራ፦ እግዚአብሔርን አመልካለሁ

+++ ይህ ስም ክቡር ነው! “ብርሐነ ዓለም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ”

የመጀመሪያ ስሙ ሳውል የተባለው ይህ ምርጥ እቃ “ሰርግዮስ ጳውሎስ” ለተባለ ሃገረ ገዢ ብርኀን ወንጌልን ያስተምረው ነበር፤ ነገር ግን የሙሴን በትር እንደተቃወሙት ሁለቱ ጠንቋዮች /ኢያኔስና ኢያንበሬስ/ ሳውልንም የሚቃወም “ኤልማስ” የተባለ ጠንቋይ ነበር፤

ይህ ኤልማስ የተባለው ጠንቋይ ሳውል ወንጌልን ለሃገረ ገዢው /“ለሰርግዮስ ጳውሎስ”/ እንዳይሰብክለት ትልቅ እንቅፋት ሆነበት፤ ሳውልም ለጠንቋዩ ኤልማስ “አንተ ጨለማ ሆነህ በእውነት ብርኀን ወንጌልን ተቃውመሃልና እነሆ በጨለማ ትመታለህ” አለው። ጠንቋዩ ኤልማስም ወዲያውኑ ጨለማ ወረሰውና ዓይኑ ተያዘ፤ ሃገረ ገዢው ሰርግዮስ ጳውሎስም የኤልማስ ዓይነ ሥጋ ሲጨልም፣ የራሱም ዓይነ ልቡና ሲበራ አየና ለሳውል “ስምህ ሳውል አይሁን "ጳውሎስ" ማለት ብርኀን ማለት ነውና አንተም ዓይነ ልቡናዬን በወንጌል ብርኀን አብርተሃልና ስምህ //ጳውሎስ// ይባል ብሎ የራሱን ስም ሰጠው። [ሐዋ. 13: 7]

ጳውሎስ! ይህ ስም ክቡር ነው! እነሆ “ጳውሎስ” ማለት “ብርኀን” ማለት ነውና “ብርኀነ ዓለም ሐዋርያው ቅ/ጳውሎስ” ብለን ጠራነው። ስሙ በራሱ ብርኀን ማለት ሲሆን ከስሙ አስቀድመን "ብርኀነ ዓለም" ብለን እኛም እንደ ሃገረ ገዢው እንደ ሰርግዮስ ጳውሎስ ስንጠራው የፃፋቸው መልዕክቶችም ብርኀን ሆነው ይነበባሉ!

ለህፃናት የምናወጣላቸውን ስሞች እንዲህ ትርጉም ሲኖራቸው መልካም ነው፤ ይህን በተመለከተ በአንድ ወቅት ያጋጠመኝን እውነተኛ ታሪክ ልንገራችሁ፤

ባለሁበት በለንደን ከተማ አንዲት እናት ለሴት ልጇ ደስ ይላል ያለችውን ስም አወጣችላት፤ ምን የሚል ስም መሰላችሁ? የልጅቷ ሥም “ሜልኮል” የሚል ነበር። ስሙን ስንሰማ ገረመንና እንዴት ልጅሽን “ሜልኮል” ብለሽ ጠራሻት? አልናት። እናትየውም የዳዊት ሚስት ናት ሲባል ስለሰማሁና ስሙን ስሰማ ስለወደድኩት “ሜልኮል” ብዬ ጠራኋት አለችን። “ሜልኮል” እኮ ልጅ እንዳትወልድ ማህፀንዋን እግዚአብሔር የዘጋባት ሴት ናት ብለን እነሆ “ሜልኮል” የተባለችው ቆንጅዬ ልጅ ቤተልሔም የሚል አዲስ ስም ወጣላት።

+ ዕራቁታቸውን የሮጡት 7ቱ ሰዎች፦
ወይወስዱ እምፅንፈ ልብሱ ወያነብሩ ዲበድውያን ወየሃይው ወአጋንንት እኩያን ይወፅኡ እንዲል የቅ/ጴጥሮስ ጥላ በሽተኞችን ሲፈውስ የቅ/ጳውሎስ የልብሱ ቁጨት ደግሞ አጋንንትን አወጣ! [ሐዋ. 5 ፤ 19:12]

ቅ/ጳውሎስ አጋንንትን ሲያወጣ ብዙ ሰዎች ተዓምሩን አዩ፤ የካህናቱ አለቃ የአስቄዋ 7 ልጆች ግን “ጳውሎስ በሚሰብከው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ውጡ” እያሉ አጋንንትን ለማስወጣት ሞከሩ። አጋንንትም ኢየሱስን ዐውቀዋለሁ ጳውሎስንም ዐውቀዋለሁ እናንተ ግን እነማን ናችሁ? ብለው ዘለው ያዙዋቸው! በሰዎቹም ላይ እጅግ ስለበረቱባቸው ቤቱን ጥለው ዕራቁታቸውን ሮጡ ይለናል!! [የሐዋ. 19:12]

+++ ቤተክርስቲያንና ቅ/ጳውሎስ፦
ሐዋርያው ቅ/ጳውሎስ ለቤተክርስቲያን እጅግ ይቀና የነበረ ሐዋርያ ነው። ቅ/ጳውሎስና ቤተክርስቲያን የአንድ ዕርግብ ሁለት ክንፍ እንደማለት ናቸው!! ሁለቱም አይለያዩምና; በቀዝቃዛ እስር ቤት እያለ ቅ/ጳውሎስ ያስብ የነበረው ለቤታክርስቲያን ነበር። አብዛኛውን መልዕክታቱንም የፃፈው ከምድር በታች ባለች ቀዛቃዛ እስር ቤት ውስጥ ነበር። 2ኛው የጢሞቴዎስ መልዕክት የተፃፈውም በቀዛቃዛዋ እስር ቤት ነበር!!!

ቅዱስ ጳውሎስ መልእክታቱን የጻፈባቸው ቀዝቃዛ እስር ቤት ይህን ይመስላል;
ልእ እንደ ለንደን ባቡር መሄጃ / /under ground/ ሲሆን ካታኮምቦ /ግበበ ምድር/ ይባላል።

+++ ሐዋርያዊ ስራዎቹ፦ ይህ ታላቅ ሐዋርያ ከሐዋርያት ሁሉ ብዙ መንገድ በእግሩና በባህር በመጓዝ የደከመና በጉዞው ህይወቱን ለአደጋ ያጋለጠ ሲሆን ለአህዛብ ወንጌልን ለመስበክ በመመረጡ 16 መልዕክታትን ጽፋል፤ ሁለቱ ጠፍተው በመጽሐፍ ቅዱስ ያለው 14ቱ መልዕክታቱ ናቸው።

+++ ዕውቀትን ከትህትና ጋር ደርቦ የያዘ ነበር፦
በእየሩሳሌም በሚገኘው በታላቁ የአይሁድ ት/ቤት ከሊቁ ከገማልያል እግር ስር ቁጭ ብሎ ብሉይን የተማረና አዲስ ኪዳንን አበጥሮ የሚያቃት ቢሆንም በእውቀቱ አልተመካም፤ እኔ ጭንጋፍ ነኝ እስከማለትም ደርሶ ነበር። 1ቆሮ. 15:8

+++ ሥራ ወዳድ ነበር፦
ሌት ተቀን በወንጌል ቢደክምም ለምዕመናን እንዳይከብዳቸው ድንኳን እየሰፋ እራሱን ይችል ነበር!!!

+++ እጅግ ትዕግስተኛ ነበር፦
ብዙ ግዜ ቢታሰርም በረሃብ ቢደክምም መልዕክቱን በትዕግስት ሆኖ በደስታ ይጽፍ ነበር፤ በጌታ ደስ ይበላቹ ደግሜ እላለሁ ደስ ይበላቹ እያለ በመልዕክቱ ያጽናና ነበር።

+++ ተግባቢ ነበር፦
ቅ/ጳውሎስ ሰውን እንዴት መቅረብ እንዳለበት ያውቅ ነበር። ከተራ ሰዎች እስከ ነገስታት በፍቅር እየሳበ ክርስቲያን አድርጓል። በመልዕክቱ መጨረሻ የቤተክርስቲያንን ልጆች ስም እየጠራ ሰላምታ ማቅረብ የዘወትር ተግባሩ ነበር።

+++ ጥበበኛ ነበር፦
የቤተክርስቲያን አበው ቅ/ጳውሎስን መዶሻ ይሉታል። መዶሻ ማዕድናቱን ቀጥቅጦ አንድ እንደሚያደርግ ሐዋርያውም አህዛብንና ሕዝብን/እስራኤል ዘሥጋን/ አንድ ስላደረገ ነው። በጉዞው ቲቶንና በርናባስን አስከትሎ ነበር; ቲቶ ግሪካዊ አህዛብ ሲሆን በርናባስ ደግሞ አይሁዳዊ ነበር።

+++ በመጀመሪያ የቤተክርስቲያን አሳዳጅ ነበር፦
ቅ/ጳውሎስ በ32 አመቱ ክርስቲያንን ለማጥፋት ከሊቀ ካህናቱ ቀርቦ የፍቃድ ደብዳቤ ከተቀበለ በሗላ የሶርያ ዋና ከተማ ወደሆነችው ወደ ደማስቆ ሊደርስ ጥቂት ሲቀረው ነበር ከሰማይ የወረደው ብርሃን አካባቢውን ሞላውና “ሳውል ሳውል ለምን ታሳድደኛለህ" የሚል ድምጽ የሰማው። በመቀጠልም ለሐዋርያነት ተጠራ።

+++ ታላቅ ሰማዕትነትን ተቀብሏል፦ በዘመኑ የነበረው ጨካኙ ንጉስ ኔሮን በጥጋቡ የሮማ ከተማ ስትቃጠል ማየት እፈልጋለሁ ብሎ አቃጠላት; የሮም ሕዝብ በክርስቲያን ላይ አሳበቡ፤ በዚህም ክርስቲያኖች ሰማዕት መሆን ግድ ሆነባቸው። ቅ/ጳውሎስም ለሁለት ዓመት ከስድስት ወር በጨለማ እስር ቤት ታስሮ ከቆየ በሗላ በ74 ዓመቱ በሮማ ከተማ በኦስትያ መንገድ አንገቱን ተሠይፎ ሐምሌ 5 67 ዓ.ም በሰማዕትነት ዐረፈ።

ብርሐነ አለም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ
ሰማእትነትን እንደተቀበለ
“ሩጫዬን ፈጽሜያለሁ ሐይማኖቴን ጠብቄያለሁ
የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል” 2ኛ ጢሞቴዎስ 3:4

የእግዚአብሔርን ቃል የተናገራችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ; የእምነታቸውንም ፍሬ እየተመለከታቹ በህይወታቸው ምሰሏቸው ዕብራዊያን 13:7። ታላቁ ሐዋርያ ቅ/ጳውሎስ እንዲህ እንዳለው መላው ህይወቱ ትምህርት ትሁነን፤ አሜን። -//-

እንተዋወቅ

ስም፦ ሐዋርያው ቅ/ጴጥሮስ እባላለሁ
ሀገር፦ መንግስተ ሰማያት
ዜግነት ፦ ክርስቲያን
ስራ፦ እግዚአብሔርን አመልካለሁ

+++ ቅ/ጴጥሮስ ለሐዋርያነት ከመጠራቱ በፊት፦ ቅ/ጴጥሮስ የመጀመሪያው ስሙ ስምኦን ሲሆን የተወለደውም በጥብርያዶስ ባህር ዳር በምትገኘው በቤተሳይዳ ነበር። የአባቱ ስም ዮና ይባላል፤ ከአምስት አመቱ ጀምሮ ከወንድሙ ከእንድርያስ ጋር ሆኖ በታላቋ ጥብርያዶስ ባህር መረባቸውን ዘርግተው አሳ ማጥመድ ጀመሩ። ይሄኔ ነበር ጌታ ወደ ወንድማማቾቹ ጠጋ ብሎ ቅ/ ጴጥሮስን ተከተለኝ ያለው። ታላቁ ሐዋርያ ቅ/ጴጥሮስ ለሐዋርያነት ሲጠራ ዕድሜው 55 ዓመት ነበር።

ቅ/ጴጥሮስና ቅ/እንድርያስ አሳ እያጠመዱ // ለሐዋርያነት ሲጠሩ

+++ ድንቅ ሐብተ ፈውስ በቅ/ጴጥሮስ፦ እግዚአብሔር የፀጋ ስጦታ ለቅዱሳኑ ሰቷቸው ድንቅ ተዓምራትን ይሰሩ ነበር። ቅ/ጴጥሮስ ጥላው ድውያንን ሲፈውስ ቅ/ጳውሎስ ደግሞ የልብሱ ቁጨት አጋንንትን አወጣ የሐዋ.5:15 ፤ 19:12

+++ ንስሐ ቅ/ጴጥሮስ፦ በቤተክርስቲያናችን በንስሐ ከሚታወቁት መካከል ቅ/ጴጥሮስና ልበ አምላክ ዳዊት ቀደምት ናቸው ፤ ሁለቱም "ንስሐ አበው" በመባል ይታወቃሉ። ቅ/ጴጥሮስ ምንም እንኳን በፍራቻ ጌታውን ቢክድም ከካህናቱ ግቢ ወቶ ሥቅስቅ ብሎ አልቅሷል። የቅ/ጴጥሮስ ዕንባ ልክ እንደ ጅረት ወንዝ ያለ ታላቅ የንስሃ ዕንባ ነበር። በንስሃ የታወቀው ክቡር ዳዊትም እንዲህ አለ፦

“ለሊቱን ሙሉ አልጋዬን አጥባለሁ፤ መኝታዬንም በለቅሶዬ አርሳለሁ
አቤቱ በሂሶጵ እርጨኝ እነጻማለሁ” መዝ 6:6 እና መዝ 50

ንስሃ ዳዊት ወጴጥሮስን የተቀበለ የኛንም የንስሃ ልቅሶ ይቀበለን፤ አሜን። ቅ/ጴጥሮስ ጌታን 3 ግዜ ክዶት ነበርና ጌታም 3 ግዜ ትወደኛለህን ብሎ ጠየቀውና ክርስቲያኖችን በመንፈሳዊ ደረጃቸው ከፍሎ ግልገሎቼን ጠብቅ; ጠቦቶቼን ጠብቅ; በጎቼን ጠብቅ ብሎት 3 ግዜ ደጋግሞ አዘዘው፤ ንስሃውንም ተቀበለ። በጣም የሚደንቀው ቅ/ጴጥሮስ መጀመሪያ በተጠራባት በጥብርያዶስ ባህር ጌታ ዳግም ተገልጾ እንዴት ትክደኛለህ ብሎ አዳች አለማስታወሱ ነው ፤ እኛም በንስሃ ስንመለስ "ትላንት ምን ነበርክ? ትላንት ምን ነበር ስራሽ"? ብሎ አንዳንች ሳያነሳ እንዲሁ እጆቹን ዘርግቶ የሚቀበል ሃዳጌ በቀል / በቀልን የሚተው/ አምላክ ክብርና ምሥጋና አምልኮትና ውዳሴ ለእግዚአብሔር ይሁን፤ አሜን።

+++ የቅ/ጴጥሮስ ድንቅ አማናዊ አባባል በቂሣሪያ፦ በእነ ቅዱስ ጴጥሮስ ዘመን የነበሩ ሰዎች ጌታን ግማሹ ከነብያት አንዱ ነው ሲል ሌላው ኤልያስ ነው ደግሞም ሙሴ ነው ይሉ ነበር ፤ እናም ጌታ ሐዋርያቱን “ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል” ብሎ ጠቃቸው; ቅ/ጴጥሮስም እንዲህ አለ፦ አንተ ውእቱ ወልደ እግዚአብሔር ሕያው / አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ/ ብሎ ለአይሁድ ሊቃውንት የተሰወረውን ምስጢረ ተዋህዶ ገልጦ በመመስከሩ ጌታችን “አንተ ጴጥሮስ ነህ” ብሎታል ፤ ጴጥሮስ በላቲን ቋንቋ ፔትራ ሲባል ዐለት ማለት ነው። በአራማይክ ደግሞ ኬፋ ይባላል።

+++ የቅ/ጴጥሮስ ድንቅ አማናዊ አባባል በቅፍርናሆም፦ በቅፍርናሆም ጌታችን ምሥጢረ ቁርባን ሲያስተምር አይሁድ ስላልገባቸው ወደሗላ አፈገፈጉ። ብዙ ግዜ ጌታ በምሳሌ ያስተምርና ካልገባቸው ምሳሌውን ይተረጉምላቸው ነበር ፤ ለምሳሌ ከአይሁድ እርሾ ተጠበቁ ሲላቸው ሐዋርያቱ ዳቦ ስላልያዙ የተነገራቸው መስሏቸው ነበር; ጌታም ተዐቀቡኬ እም ሐሳውያን ነቢያት ፤ /ከሐሰተኞች መምህራን ተጠበቁ / ብሎ አስረዳቸው። ይህን ያመጣንበት ምክንያት አለ፤ ይህም ጌታ ስለ ምሥጢረ ቁርባን ሲያስተምር አይሁድ እንዴት ሥጋዬን ብሉ ይለናል? እንዴትስ ለእኛ ለሁላችን ይበቃናል? ብለው አጉረምርመው ነበር። ይህ ግን ምሳሌ ሳይሆን አማናዊ ሚስጢር ነውና ከላይ እንዳየነው እንደ እርሾው ምሳሌ አልተተረጎመላቸውም፤ ወርቁም ሰሙም ይህ ነውና “ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው” ዩሐንስ 6:54።

ልብ በል ከርእሴ አልወጣሁም; ቅ/ጴጥሮስ ያለውን ለማምጣት ነው፤ አይሁድ ወደኋላ ሲመለሱ ጌታችን ሐዋርያቱን “እናንተ ደግሞ ልትሄዱ ትወዳላቹ?” ብሎ ጠየቃቸው ፤ በዚህን ግዜ ቅ/ ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ ወደማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም የሕይወት ቃል አለህ። እኛስ አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ እንደሆንክ እናምናለን” በማለት ሐዋርያትን ወክሎ የመሰከረው እርሱ ነው። ዩሐ. 6:66። ቅ/ ጴጥሮስ በቂሳሪያ እንደመሰከረ በቅፍርናሆም ደግሞ ሐዋርያቱን ሁሉ ወክሎ የመሰከረ የሐዋርያት አለቃ ነው።

የቅ/ጴጥሮስ ሰማዕትነት፦
በሰማዕትነት ያለፈው በሮሜ ከተማ ሲሆን በዛች ከተማ ለ25 ዓመታት እንዳስተማረ የሮማ ሰዎች ይናገራሉ፤ ከጌታ ጋር 3 ዓመት ከ3 ወር; ዙሮ በማስተማር ደግሞ ለ27 ዓመታት ቆይቷል። የዘመኑ ጨካኝ ንጉስ ኔሮ ቅ/ጳውሎስን እንዲሰየፍ በማድረጉ ክርስቲያኖች ቅ/ጴጥሮስን ባይሆን አንተ ትረፍልን ብለውት በከተማዋ ግንብ በገመድ አስረው በቅርጫት በማውረድ ቅጽረ ሮማን ለቆ እንዲወጣ አደረጉት ፤ በሸመገለ ጉልበቱ እያዘገመ ሲጓዝ ጌታን በመንገድ ላይ አገኘው; ቅ/ጴጥሮስም ጌታዬ ወዴት እየተጓዝህ ነው? አለው ጌታም
“ዳግም በሮማ ልሰቀል” አለው። ቅ/ጴጥሮስም አዘነና ወደ ሮማ ተመልሶ እንደ ጌታዬ ልሰቀል አይገባኝም ብሎ ቁልቁል እንዲሰቅሉት ለመነ!!

ዳግም በሮማ ልሰቀል ነው // እንደ ጌታዬ ሳይሆን ቁልቁል ስቀሉኝ

“እስመ ፀላኢክሙ ጋንኤን ይህጥር ከመ አንበሳ ዘይሃስስ ዘይውሃጥ"
"ንቁ ጠላታቹ ዲያቢሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ በዙሪያቹ ይዞራል”
1ኛ ጴጥሮስ 5:8 -//-

እንተዋወቅ

ስም፦ ሐዋርያው ቅ/ማቴዎስ እባላለሁ
ሀገር፦ መንግስተ ሰማያት
ዘር ፦ ደግ ክርስቲያን
ስራ፦ እግዚአብሔርን አመልካለሁ

ከሐዋርያት ሁሉ በሀገራችን ያስተማረው ሐዋርያው ማቴዎስ ሲሆን ከነብያት በሀገራችን ለ2 አመት በእግሩ የተጓዘው ደግሞ ነብዩ ኢሳያስ ነው። ኢሳ. ምዕ 20:3

Ethiopia stretching out her hands onto God
ኢትዮጲያ ታበጽህ እዴሃ ሐበ እግዚአብሔር
መዝ 67:31

+++ ማቴዎስ ለሐዋርያነት ከመጠራቱ በፊት ፦ የመጀመሪያው ስሙ ሌዊ ሲሆን ማቴዎስ የሚለውን ስም ያወጣለት ጌታ ነው ፤ ትርጉሙም የተመረጠ ማለት ነው። ማቴዎስ የቀድሞ ስራው ቀራጭነት /tax collector/ ሲሆን ይሰራበት የነበረበትም ቦታ በገሊላ ባህር በምትገኘው በደማቋ በቅፍርናሆም ከተማ ነበር። በዚህች ከተማ ሱቅ ከፍቶ ነጋዴዎችን ቀረጥ ያስከፍል ነበር። ጌታችንም ወደ ማቴዎስ ጠጋ ብሎ ተከተለኝ አለው፤ ማቴዎስም ሁሉን ትቶ ተከተለው።

ማቴዎስ ቀረጥ ከሚሰበስብበት ቦታ ሲጠራ

ቅ/ማቶዎስ የሚያገኘው አልበቃ ብሎት ከአቅም በላይ ገንዘብ እየቀረጠ ነጋዴዎችን እንዳላስመረረ ድኾችን በነጻ የሚያበላ ድውያንን በነጻ የሚፈውስ ሲያገኝ ተገርሞ ስራውን ርግፍ አድርጎ ተከተለው። አበው ቅ/ማቴዎስን የቁም ተዝካሩን አውጥቶ ጌታን የተከተለ ሐዋርያ ነው ይሉታል; ምክንያቱም ለሐዋርያነት ሲጠራ በቤቱ ድግስ ደግሶ ነዳያንን ጠርቶ ጌታን ጋብዞታልና ነው።

+++ ሐዋርያው ይኖርባት የነበረችው ከተማ በጥቂቱ፦ ማቴዎስ ይኖር የነበረው በቅፍርናሆም ከተማ ሲሆን "ቅፍርናሆም" ማለት የናሆም ከተማ ማለት ነው፤ በዚህች ከተማ ጌታ በመዋዕለ ሥጋዌው ከ 11 በላይ ታላላቅ ተዓምራትን አድርጓል። በማቴዎስ የትውልድ ከተማ; በቅፍርናሆም በሚገኘው በጥብርያዶስ ባህር አሳን አበርክቶ አበላቸው ፣ በባህር ላይ ተረማመደ ፣ ጎባጣ ተቃና ለምጽ ነጻ እነ በጥለሚዎስ እውራኑ ሁሉ ብርሐናቸውን አገኙ። ወንጌል ዘማቴዎስ ምዕ 20:34 ፤ ማር 10:46። ከሚበላው አሳን አበርክቶ አበላቸው ከሚታየው ህሙማንን ፈወሰ፤ ነገር ግን የቅፍርናሆም ነዋሪዋች በእምነታቸው እጅግ ቀዝቃዛ ነበሩ፤ ጌታም በዚህች ከተማ ብዙ ተዓምራትን ሊሰራ አልፈቀደም፤ ጌታ በወንጌል ላይ በእምነት ምክንያት ሁለት ግዜ ተደነቀ ተብሎ ተጽፋል፦

አንደኛው በቅፍርናሆም ነዋሪዎች በእምነታቸው ጎዶሎነት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በቅፍርናሆም ከተማ ይኖር በነበረውና “ቃል ብቻ ተናገር ልጄም ይፈወሳል” ባለው በሮማዊው ወታደር በእምነቱ ጽናት ነበር። በማቴዎስ ወንጌል ልጁ ታሞ ሲል በሉቃስ ወንጌል ደግሞ አገልጋዩ ይለዋል; ይህም ወንጌላቱ ተሳስተው ሳይሆን እንደ ልጁ የሚወደው አገልጋዩ ነው ይላሉ አበው። ወንጌል ዘምቴዎስ ምዕ 8:5 ፤ ሉቃስ 7:1።

ወደ ቀደመው ስንመለስ እምነት ወሳኝ ነውና ጌታም ሮማዊውን ወታደር በእምነቱ አድንቆታል; ሐዋርያው ቅ/ጳውሎስም “እምነትና በጎ ሕሊና ይኑርህ” እንዳለ መልዕክተ ሐዋርያው ቅ/ጳውሎስ ሀበ ጢሞቴዎስ 1ኛ ጢሞ. ምዕ 1:19። እኛንም በእምነት በዝማሬው ቀዝቃዛ ከመሆን ይጠብቀን፤ አሜን።

ስለ እምነት ዕብራዊያን ምዕ 11 ላይ ብዙ ተጽፋልና ልናነብ እንችላለን። ወደ ቀደመው ሃሳባችን ስንመለስ ሐዋርያው ማቴዎስ የተጠራው እምነተ ጎዶሎ ከሆነችው ከቅፍርናሆም ከተማ ነበር። የእግዚአብሔር አጠራር ልዩ ልዩ ነውና; አብርሐምን ከጣዖት አምላኪ ቤተሰብ የጠራ እነ መጥምቁን ዩሐንስን ደግሞ ከማህጸን ጀምሮ መረጣቸው፤ ቅ/ ጳውሎስን ከደማስቆ የጠራ ማቴዎስንም ከቅፍርናሆም ጠራ። እኛስ ከየት ነበር የተጠራነው? እንደ ናትናኤል ከበለስ ዛፍ ስር ወይስ እንደነ ቅ/ጴጥሮስ በአለም አሳን ለማጥመድ ስንደክም? አዎ ከተለያየ ቦታ ተጠራን፤ የጠራን ከእናታችን ከቅድስት ቤተክርስቲያን አንድ ያደረገን ያለየን ልዑል እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን ፤ አሜን

“ከቤተመንግስቴ ከአእላፈት ቀን ይልቅ በቤትህ ልጣል ወደድኩ”
መዝ 83(84) ቁጥር 10

“ወንጌል ዘማቴዎስ”

+++ የማቴዎስ ወንጌል ከማርቆስ በኋላ በሁለተኛነት ተጽፎ እያለ የመጀመሪያውን ተርታ ያገኘው ለብሉይና ለሐዲስ ኪዳን ድልድይ ስለሆነና የብሉይ ኪዳን ምሳሌ በሐዲስ ኪዳን መፈጸሙን ስለሚያሳይ ነው።

+++ ሐዋርያው ወንጌሉን የፃፈው ለአይሁድ በመሆኑ ከ150 በላይ የብሉይ ኪዳንን ጥቅሶች አቅርቧል፤ በዚህም የብሉይ ኪዳንን ጥቅስ አብዝቶ በመጥቀስ ከሌሎች ወንጌሎች ይበልጣል። ከ 1068 ቁጥሮቹ መካከል 644ቱ የጌታ ትምህርቶች ናቸው። ይህም ከወንጌሉ 60% ማለት ነው።

+++ የማቴዎስ ወንጌል በመናፍቃኑ ዓይን፦ ማቴ 17:14፤
አንድ ሰው በጣም የሚወደው ልጁን አጋንንት ያሰቃይበት ነበር፤ አንዴ እሣት ላይ ደግሞም ወደ ባሕር እየወሰደው በጣም አሰቃየው; ይህ አጋንንት ከልጅነቱ ጀምሮ ከልጁ ጋር ስላደገ ዝንቱ ዘመድ ይባላል /አብሮ አደግ አጋንንት እንደማለት ነው/ ሰውየውም ልጁ እንዲማርለት ወደ ሐዋርያቱ አምጥቶ ለመናቸው፤ እነሱም ገና እምነታቸው ለጋ ነበርና አጋንንቱ ሊወጣላቸው አልቻለም ነበር፤ ሰውየውም ወደ ጌታ አመጣው; የድንግል ማርያም ልጅ ገባሬ ተዓምር ኢየሱስ ክርስቶስም ያን ልጅ ፈወሰው; ሐዋርያቱም ለምን ለእኛ አቃተን አሉት; ጌታም ይህ አጋንንት ያለ "ፆምና ያለ ፀሎት" አይወጣም አላቸው!!! ማቴ 17:21። ፆም አጋንንትን ለማውጣን እንደሚጠቅም አስተማራቸው፤ ይህ ክፍል ስለጾም ስለሚናገር መናፍቃኑ "ቀላል አማርኛ" በሚሉት መፃህፋቸው የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 17 ቁጥር 21 ላይ ያለውን ቃል ዘለውታል; ቁጥሩ እንዳለ የለም፤ የእንግሊዘኛውን መፃህፍ ቅዱስ ስንመለከት ለምሳሌ Good news የሚለውን ብናይም ይህ ቁጥር የለውም!!

+++ የሐዋርያው ማቴዎስ ሰማዕትነት፦ ሐዋርያው ማቴዎስ በሃገራች አስተምሯል ብለናል፤ ብዙ ሐዋርያት ባስተማሩበት ሐገር ሰማዕትነትን መቀበል ግድ ሆኖባቸው ነበር; ሐዋርያው ማቴዎስ ግን በሃገራችን ሰማዕትነትን አልተቀበለም፤ ሃገራችን ልዩ የሚያደርጋትም ክርስትናን የተቀበለችው የአንድም ሐዋርያ ደም ሳታፈስ ይኩንኒ /ይሁልኝ/ ብላ በመቀበሏ ነው። ጤዛ ልሰው; ዳዋ ጥሰው; ዋዕይ ቁሩንም ታግሰው በየበረሃው የሚጸልዩ ፃድቃን አሉን፤ ሃገራችን ብትታረስ የሚበቅሉ ብዙ ቅዱሳን ጻድቃን አሏትና። ማቴዎስ ጥቅምት 12 ቀን ዐንገቱን ተሠይፎ ዐርፏል።

+++ አዋልድ መጽሐፋና ማቴዎስ፦ አዋልድ መጽሃፍ ማለት ከመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ያልወጡ ቅዱሳን መጽሐፍት ናቸው። መናፍቃኑ ከመፅሐፍ ቅዱስ ውጪ ምንም አይነት አዋልድ መጽሐፍትን አይቀበሉም። ለምን ሲባሉ ከዚህ መጽሐፍ አንዳች የሚጨምር ወይም የሚቀንስ ፍርድ ይጠብቀዋል የሚለውን የራዕየ ዩሐንስን የመጨረሻ ምዕረፍ ይጠቅሳሉ ራዕ ምዕ 22:18 ፤ እኛ ተሳስተናል ማለት ነው እንዴ? ካልተሳሳትን እንዴት እንዲህ ተብሎ ተጻፈ?

መናፍቃኑ መጽሐፍ ቅዱስን ቅንጭብ ቅንጭብ አድርገው ስለሚያነቡ ይስታሉ፤ ጌታም አስቀድሞ መፃህፍትን ስለማታውቁ ትስታላቹ እንዳለ፤ ወደ መልሱ እንመለስ; መናፍቃኑ መፅሐፍ ቅዱስን ልክ እንደ ስምንተኛ ክፍል የሳይንስ መጽሐፍ ያዩትና ዘፍጥረትን ምዕራፍ አንድ ራዕይን ደግሞ የመጨረሻ ምዕራፍ አድርገው ይቆጥሩታል፤ ይህ ግን የተሳሳተ ሐሳብ ነው። መፅሐፍ ቅዱስ የተጻፈው በአንድ ወቅትና በአንድ ሰው አይደለም; መጀመሪያም አንድ ጥራዝ አልነበረም ፤ ሐዋርያው ዩሐንስም በዚህ መጽሐፍ መጨመርም ሆነ መቀነስ እንደማይገባ የነገረን ለራዕዩ ነው እንጂ አዋልድ መፅሐፍትንማ ሐዋርያቱም በመፅሐፍ ቅዱስ ተጠቅመዋል እኮ!!! ልብ በል ከርዕሴ አልወጣሁም ከማቴዎስ ጋር እየተዋወቅን ነው፤ እስቲ ሐዋርያው ማቴዎስ ስለ አዋልድ መፅሐፍት ምን እንዳለ እንይ፦

+++ ለምሳሌ ማቴዎስ 2:23፦

“በነብያት ናዝራዊ ይባላል የተባለው ይፈፀም ዘንድ ናዝሬት ወደምትባል ከተማ ገብቶ ኖረ”

እስኪ መናፍቃን ይመልሱ; በነብይ ናዝራዊ ይባላል ተብሎ የተጻፈው ትንቢት በመፅሐፍ ቅዱስ የተፃፈው የቱ ጋር ነው? ከዘፍጥረት እስከ ራዕይ ብንፈልግ ይህን ትንቢት አናገኝም፤ ነገር ግን ሐዋርያው ማቴዎስ በወንጌሉ ፃፈው; ከየት አግኝቶ ጻፈው ቢሉ ይህ ትንቢት በነብያት ተነግሮ በምርኮ ግዜ በጠፉት መጻሕፍት የነበረ ሲሆን መጻሕፍቱ ቢጠፉም በቃል ለሐዋርያት ደርሷል፤ እናም ይህች ትንቢት በማቴዎስ ወንጌል ተጻፈች!!! ሐዋርያዊት የሆነችው ቤተክርስቲያናችን አዋልድ መጻሕፍትን የምትጠቀመው ሐዋርያቱ እነ ማቴዎስና ቅ/ጳውሎስ እንዳስተማሯት ነው ማለት ነው።
“በእግዚአብሔር መንፈስ የተፃፈ መጽሐፍ ሁሉ ለተግሣጽና ለትምህርት ይጠቅማል” 2ኛ ጢሞቴዎስ 3:16

የሐዋርያት ሥራ /acts of the apostles/ ወይም ግብረ ሐዋርያት ማለት ሐዋርያቱ የሰሩት ተጋድሎ ማለት አይደል እንዴ? እነ ሐዋርያው ያዕቆብ በሰይፍ ሲገደሉ በገድለ ሐዋርያት ተጽፏል የሐዋ. 12:1 ፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰማዕትነቱ የተጻፈለት ሐዋርያ ቅ/ያዕቆብ ብቻ ነው፤ ታዲያ የሌሎች ሐዋርያት ሰማዕትነትን መቀበል የለብንም ማለት ነው? መናፍቃኑ እንዲህ ካሰቡ “ሁለት ዓይን አለኝ ሁለቱም በደንብ ያያሉ ነገር ግን በአንዱ ዓይኔ ብቻ ነው ማየት የምፈልገው እንደማለት ይሆንባቸዋል!” ዩሐንስ በወንጌሉ እንዲህ አለ፦ “ጌታ ያደረገውን ተዓምራት ሁሉ ልጻፍ ቢሉ ለተዓምራቱ መጻፊያ አለም ባልበቃም ይመስለኛል” የዩሐ. 21:25 ፤ ጌታ ያደረጋቸው ተዓምራት ብዙ ናቸውና; በተዓምረ ኢየሱስ ላይም የተፃፈው ይህ እውነታ ነው። ጌታ ያደረገውን ተዓምር ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ አላምንም ማለት ደጎሞ “ሁለት ዓይን ነበረኝ አሁን ግን እንደ በጥለሚዎስ እውር ሆንኩኝ” ማለት ይሆናል ማለት ነው። በጥለሚዎስስ የዳዊት ልጅ ሆይ ማረኝ ብሎ የዓይን ብርሐኑን አግኝቷል። እኛንም ዓይነ ልቦናችንን ለቃሉ ያብራልን፤ አሜን

ወ ሥ በ ሐ ት ለ እ ግ ዚ አ ብ ሔ ር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር ፤ አሜን

ይህን የመሳሰለውን ማንበብ ቢፈልጉ ይህን ይመልከቱ
http://yonas-zekarias.blogspot.com/

Friday, 30 December 2011

“ታናሽዋ ደመና”




“ታናሽዋ ደመና”  
 ከአ.አ - ለንደን ኤርፖርት

 “አሁን ባላችሁበት ዘና ብላችሁ ተቀመጡና አንድ ታሪክ ልንገራችሁ”

 አውሮፕላን ውስጥ ነው ያለነው፤  ከሩቅ የምናየውን ደመና እያሳየን ጓደኛዬ ዘካርያስ ታሪክ እየነገረን ነበር፤  እኛም ትንሽ ደክሞን ስለነበር ደስ አለን … /፤/

ግዜው የፈረንጆቹ አዲስ አመት ነበር፤ እነሆ ከኢትዮጲያ አየር መንገድ ተነስተን ጉዞ ወደ ለንደን ጀመርን። እኔና ጓደኛዬ ዘካርያስ አውሮፕላኑ ውስጥ እንደገባን ትንሽ አረፍ አልንና ለረጅሙ መንገድ ያዘጋጀነውን መፅሐፍ አውጥተን ማንበብ ጀመርን፤

ለትንሽ ግዜ ካነበብን በኋላ ከአጠገባችን የተቀመጠችው አንዲት ልጅ ለመግባባት ብላ “ ሔርሜላ እባላለሁ የምታነቡት መፅሐፍ ምንድን ነው?” ብላ ጠየቀችን በጨዋ ፈገግታ፤ እኔ የማነበው ነገረ ማርያም /Mariology/ የሚል ነው አልኳት ገፁን ለማሳየት እየሞከርኩ፤ ዘካርያስም የእኔ ደግሞ “ቤተክርስቲያንህን እወቅ” ይባላል አላት።
እርስ በእርስ ለመተዋወቅ ብዙ አልፈጀብንም፤ ሶስታችንም በስደት ሃገር ስለምንኖር ስለሃገር ቤት ናፍቆት ብዙ ተነጋገርን።

ደኛዬ አሁን ባላችሁበት ዘና ብላችሁ ተቀመጡና አንድ ታሪክ ልንገራችሁ” አለን እኛም ትንሽ ደክሞን ስለነበር ደስ አለን፤ ያለንባትን መቀመጫ ወደኋላ አመቻችተን ተቀመጥንና በል ንገረን አልነው፦

ከሩቅ የሚታየውን ደመና ሳይ አንድ ታሪክ ትዝ አለኝ አለንና ትረካውን ቀጠለ /1ኛው ታሪክ/



በነገሥታት ዘመን ነበር፤ ነብዩ ኤልያስ ሰማይን በፀሎቱ ለ31/2 ዓመት ዘጋ; ዝናብም አልዘነበም ነበር፤ እነሆ አንድ ታናሽ ብላቴና ይዞ ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ወጣና እስኪ ዝናብ እንደሚዘንብ ወደ ተራራው ጫፍ ሂድና አይተህ ና ብሎ ላከው። ያም ህፃን ከሄደበት ተመልሶ መጣና አባቴ ኤልያስ ሆይ ሰማዩ ደመና የለው መሬቱ ደረቅ ነው ምንም ዝናብ የለም” አለው። ኤልያስም ተመልሰህ ሂድና እይ አለው፤ ታናሽ ብላቴናው እንዲህ እያለ ፯ ግዜ ተመላለሰ። ይህ ታናሽ ብላቴና ካደገ በኋላ ነብዩ ዮናስ ሆነ ይላሉ አባቶቼ።

ነብዩ ዮናስ በ፯ኛው የምስራች ዜና ይዞ ወደ ኤልያስ መጣና አባቴ ኤልያስ ሆይ እነሆ ገና ከሩቅ እጄን የምታክል “ታናሽ ደመና” ትታየኛለች አለው፤ ያቺ ደመና ወደ ሰማይ ወጥታ ዝናብን አመጣች! እነሆ ይህች ታናሽዋ የኤልያስ ደመና የእመቤታችን ምሳሌ ናት! አለን ዘካርያስ።

እንዴት? አልነው እኔና ሔርሜላ

እንዲህ ብሎ ቀጠለ፦

እነሆ ያቺ ታናሽ ደመና ወደ ሰማይ ወጥታ ዝናብን እንዳመጣች ሁሉ እመቤታችንም ገና የ15 አመት ታናሽ ገሊላዊት ብላቴና ስትሆን “የተጠማ ቢኖር የሕይወትን ውሃ ይጠጣና ይርካ” ያለውን ጌታን ወልዳለችና፤ አንድም ታናሽዋ ገሊላዊት ብላቴና ሰማየ ሰማያት የማይችሉትን ጌታን በማሕፀንዋ ተሸክማለችና “ታናሽዋ ብላቴና በታናሽዋ የኤልያስ ደመና ትመሰላለች አለንና ሙሉውን ታሪክ አነበበልን [1ኛ ነገሥት 18: 43]

ይህ መዝሙርስ ትዝ አይላችሁም? አለን

ክብረ ቅዱሳን ይእቲ /2/ ሙዳዬ መና ግሩም /2/
የቅዱሳኑ ክብር ነሽና
እንሰጥሻለን ቅኔ ምስጋና
የወለድሽልን የሕይወት መና
ዝናብ ያለብሽ ታናሽ ደመና”
የእኛ መዝሙር እንዲህ ትርጉም ያለው ሲሆን መልካም ነው፤ ባህረ ጥበብ ቤተክርስቲያን ገና ብዙ ያልተነካ ሚስጢራት አሏትና! እኛ ግን ሚስጢሩ ገና ሳይገባን ትታደስ የሚል መዝሙር ልናወጣ ግጥም እንገጥማለን! አዬ ከንቱ “ፍራሽ አዳሽ  ለነገሩ ጥበብ የገባው ሰለሞን በመፅሐፈ መክብብ መግቢያው ከንቱ ከንቱ የከንቱ ከንቱ ያለው የራሱ ምክንያት ቢኖረውም በዘመናችን ከንቱ ሰዎች እንደሚነሱ ታይቶት ቢሆንስ ማን ያውቃል? አለንና በረጅሙ ተነፈሰ ዘካርያስ ኡህህህ

ወደ ታናሽዋ ደመና ልመልሳችሁ”አለ ከሃሳቡ መለስ እያለ፤

ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም በህሊናው ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ወጣና እንደ ነብዩ ዮናስ ያቺን ታናሽ ደመና አያት፤ እንዲህም ብሎ ዘመረ፦
ኦ ርህርተ ህሊና እንተ ኤልያስ ደመና ……

/ነብዩ ኤልያስ በቀርሜሎስ ተራራ ታናሽዋን ደመና እያየ/


ይህ ታሪክ  ታላቅ ነው! አለና እነሆ ዘካርያስ ትረካውን ቀጠለ፦

የፍጥረታት መጋቢ የሆነውን የድንግልና ወተትን አጥብታዋለችና ይህ ሚስጢር ታላቅ ነው! በሳይንሱ አንዲት ሴት ለልጇ የሚሆነውን ወተት የምታዘጋጀው በፀነሰች ግዜ ነው። ሴት ልጅ የድንግልና ወተት የላትም፤ እመቤታችን ግን የድንግልና ወተትን /ሐሊብ ወተትን/ በድንግልና አዘጋጀች! አሁንም ደግሜ እለዋለሁ ይህ ሚስጢር ታላቅ ነው!   እሣታዊያን የሚሆኑ መላዕክት የማይዳስሱትን በጀርባዋ አዝላ እናትነትን ከድንግልና አስተባብራ ይዛለችና! ይህ ሚሥጢር በእርግጥ ግሩም እፁብ ድንቅ ነው!

ሌላ ትረካ ትፈልጋላችሁ? አለን ዘካርያስ እንዳንደክምበት እያሰበ
እኛም ይሁን ይጨመርልን አልነው፤ የዘካርያስ 2ኛው አዲስ ታሪክም ቀጠለ፦

ሔርሜላ በእጇ ላይ የያዘችው መፅሐፍ “አንቺ ሴት” የሚል ነበር፤ መናፍቃኑ የፃፉት ነው።  ለእሷም እንድታነበው ሰው ነው የሰጣት፤
 እንደ መግቢያ የተፃፈው ንባብ “ጌታችን ማርያምን አንቺ ሴት ብሎ ስም አወጣላት” ይላል ዘካርያስ “አንቺ ሴት” ብሎ ርዕሱድ በድጋሚ በማስተዋል አነበበልንና ይገርማችኋል ለመጀመሪያ ግዜ “አንቺ ሴት“ ያለው የመጀመሪያው ሰው አዳም ነው፤ እነሆ አዳም ከህቱም ድንግል መሬት ወይም ከአፈር ተፈጠረ፤ እግዚአብሔር አምላክም በአዳም ላይ ከባድ እንቅልፍ ጣለበትና ከግራ ጎኑ አንዲት ዐጥንት ተነቅላ ሔዋን ተፈጠረች።  አዳምም ዞር ብሎ ሔዋንን አያትና ይህች ሥጋ ከሥጋዬ ይህች ዐጥንት ከዐጥንቴ ናት ሲል “ሴት” አላት [ዘፍ. 2: 23] ጌታችንም እመቤታችንን አንቺ ሴት ሲላት ከሥጋሽ ሥጋ ከነፍስሽ ነፍስ ነስቼ የተወለድኩብሽ “አንቺ ሴት” ሲላት ነው!
አንድም አዳም ከህቱም ድንግል መሬት መፈጠሩ እመቤታችን በህቱም ድንግልና ጌታን የመውለዷ ምሳሌ ነው! አንድም ከአዳም የግራ ጎን ዐጥንት ሲነቀል አዳምን አላመመውም ነበር ይህም እመቤታችን ጌታን በወለደች ግዜ ህመም እንዳላገኛት ሲያስረዳን ነው!  
ይህ ትርጉም ግሩም ነው! ባህረ ጥበብ ቤተክርስቲያን እንዲህ ታስተምራለችና! ቤተክርስቲያንህን እወቅ የሚለውን መፅሐፍ የማነበው ለዚሁ ነው አለንና ዘካርያስ ታሪኩን ወደመጨረሱ መሆኑን አሳወቀን።

አሁን ደግሞ ከደመና ወደ ፀሐይና ወደ ጨረቃ ልውሰዳችሁ” ሲለን ሔርሜላ ሳቅ እያለች ወደ ሰማይ ቀረብ ስትል Astronomers መሆን አማረህ እንዴ? አለችው፤ ዘካርያስ ሳቅ አለና የጨረቃውን ታሪክ ለነ ዩሪ ጋጋሪን ልተውላቸውና ለዛሬ የእኔን ታሪክ ልንገራችሁ” ብሎ ይህችን ታሪኩን ነገረን፦
 ፀሐይን ተጎናጽፋ ጨረቃንም ተጫምታ በራስዋ ላይ 12 ከዋክብት ያለበት አክሊል የተቀናጀች አንዲት ሴት ነበረች” [ራዕይ 12:1] የእመቤታችን ክብር እንዲህ ይነበባል። እስኪ እያንዳንዱን ቃል በቃል እንየው አለን ዘካርያስ; እኛም ለመስማት ተዘጋጀን። እርሱም ቀጠለ፦

ፀሐይን ተጎናጽፋ፦  ፀሐይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  ነው። አነ ብርሐኑ ለአለም /እኔ የአለም ብርሐን ነኝ እንዳለ/
ጨረቃን ተጫምታ፦ ጨረቃ ቅዱሳን ፣ ጻድቃን ሰማእታት ናቸው። በሳይንሱ ጨረቃ የራሱ የሆነ ብርሐን አለው እንዴ? የለውም ነገር ግን ከፀሐይ ብርሐን reflect ወይም አንፀባርቆ በማታ ያበራልናል። ቅዱሳኑም ብርሐንን ፀሐይ ከሆነው ከጌታ ለጨለማዋ አለም ያበራሉ። ብርሐነ አለም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደምንል። እኔ የአለም ብርሐን ነኝ ያለው ጌታ ፃድቃንንም አንትሙ ብርሐኑ ለአለም
/ እናንተ የአለም ብርሐን ናቹህ/ ብሏቸዋልና። በአንድ ጨለማ ክፍል ያለን ሻም ብናጠፋው ጨለማው የሚብሰው ባጠፈነው በራሳችን ላይ ነው፤ መናፍቃንም እንደሻማ እየቀለጡ የሚያበሩትን ጻድቃንን ቢቃወሙ ጨለማው የሚብሰው በራሳቸው ላይ ነው ማለት ነው። 
ጨረቃን ተጫምታ፦ አንድም ጨረቃ የእመቤታችን የክብሯ መገለጫ ነው። አንድም እመቤታችን የፃድቃን የሰማእታት ሞገሳቸው ክብራቸው ናትና ጨረቃን ተጫምታ እያለ የራዕዩ ፀሐፊ ያወድሳታል።

 12 ከዋክብት ያለበት አክሊል የተቀናጀች፦ የእመቤታችንን ቅዱስ ሥዕል ስንመለከት በራስዋ ላይ 12 ከዋክብት ያለበት አክሊል አለ; አሥራ ሁለቱ ከዋክብት ብርሐነ አለም የሆኑት የአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ምሳሌዎች ናቸው። እመቤታችን የሐዋርያቱ ሞገሳቸው ናትና፤
ባለበገናው ዳዊትም በገናውን እየደረደረ እግትዋ ፅዮን /ፅዮን ክበብዋት/ ብሎ ዘመረ [መዝ. 47: 12] ፅዮን ማለት አምባ መጠጊያ ማለት ነው፤ እመቤታችን ስሟን ጠርተን ምርኩዛችን ሆናለችና! ሐወርያቱም የበገናውን መዝሙር ወደዱት መሰል እመቤታችንን በመካከላቸው አድርገው ዙሪያዋን ከበው ለፀሎት ይተጉ ነበር! ያን ግዜ መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያቱ ወረደ! ይለናል [የሐዋ. 1: 14]


ነብዩ ኢሳያስ ስለ ፅዮን /ስለእመቤታችን/ ዝም አልልም እያለ በቤተልሔም ኤፍራታ ተገኘና
የመላዕክቱን የእረኞቹን ዝማሬ ሰማና
ናሁ ድንግል ትፀንስ እነሆ ድንግል በድንግልና ትፀንሳለች አለና
የጌታን ልደት በዓይኑ ሊያይ ናፈቀና ትንቢቱ ከመፈፀሙ ከ700 ዓመታት በፊት አስቀድሞ ተነበየ፤ የዘመኑ ሰዎች አልታደሉምና እንዴት ድንግል በድንግልና ትፀንሳለች አሉና መጋዝ አመጡና ኢሳያስን ያዙና እነሆ ሥጋውን ለሁለት በመጋዝ ቆራረጡት!

“ነገር  ይፀናል በሶስት” እንዲሉ ሶስተኛውን ታሪክ ልንገራችሁና ልፈፅም አለን። እኛም ተስማማንበት፤ ፫ኛውና የመጨረሻውንም ታሪክ ቀጠለ፦
ከነብዩ ኢሳያስ ተነስተን ኤርምያስን አልፈን ሕዝቅኤልን እናገኛለን
ነብዩ ሕዝቅኤልም እንዲህ አለ፦ “በምሥራቅ የተዘጋ ደጃፍ አየሁ፤ ይህች በር ተዘግታ ትኖራለች እንጂ አትከፈትም ሰውም አይገባባትም፤ የእሥራኤል ቅዱስ ሳይከፍት ገብቶ ሳይከፍት ወጥቶባታልና”[ሕዝ. 44:1]

መናፍቃኑ ይህማ ስለ ቤተመቅደስ የተነገረ ነው ይሉናል፤ ተዘግቶ የሚኖር ቤተመቅደስ አለ እንዴ? ሰውም የማይገባበት ቤተመቅደስ የለም። ይህማ ስለእመቤታችን የተተነበየ ነው፤ ትንቢቱን ልብ ብለን ስናነበው  ምን ይላል? “ይህች በር ተዘግታ ትኖራለች እንጂ አትከፈትም” //በህቱም ድንግልና ጌታን ወልዳለችና//
ቅድመ ፀኒስ ወሊድ፣ ግዜ ፀኒስ ወሊድ፣ ድህረ ፀኒስ ወሊድ ድንግል ናትና፤ ወትረ ግዜ ድንግል ናትና ሲለን ነው።

አባ ሕርያቆስም በቅዳሴው ጎሳ ልብየ ቃለ ሰናየአለና
ከልቡ ምንጭ ውዳሴውን አፈለቀና “የማይናገር በግ የክርስቶስ እናቱ ገነት ደስ ይላታል”አለና ቅዳሴውን ቀደሰና አመሰገነ በግሩም ምሥጋና! የማይናገር በግ የተባለው ጌታችን ነው፤ በሸላቾቹ ፊት ዝም እንደሚል በግ አፉን አልከፈተም እንደተባለ [ኢሳ.53:7] በግ የተባለው ጌታችን ነው፤ የማይናገር በግ የክርስቶስ እናቱ ገነት” የተባለችው ደግሞ እመቤታችን ናት፤ ይህን በተመለከተ ጠቢበኛውም በጥበቡ እንዲህ አለ፦
እኅቴ ሙሽራዬ የታጠረች “ገነት የታተመች የውሃ ጉድጓድ ናት
[መሓ 4:12] “ገነት” የተባለችው እመቤታችን ናት ብለናል፤ እነሆ እነዚህ ሁሉ እናትነትን ከድንግልና ጋር አስተባብራ ስለያዘችው ስለ “ታናሽዋ የኤልያስ ደመና” የሚናገሩ ናቸውና ግሩም ናቸው! አለን ዘካርያስ አስተናጋጅዋ እንድትታዘዘን በዓይኑ እያሳየን፤ የአውሮፕላኑ አስተናጋጅ ሴትም ምን ልታዘዝ ብላ ጠየቀችን የራሳችንን ምርጫ ነገርናት፤ ምግቡ መጥቶ ከተመገብን በኋላ ለአንድ ሰአት ያህል አረፍ አልን።

This is London Heathrow airport አለን ፓይለቱ፤
 እኛም ሻንጣችንን ይዘን ወረድን። -//-

በሚቀጥለው ሳምንት “የዓለም እረኛ በግ ሆኖ ተወለደ” በሚል ርዕስ የጌታችንን ልደት በትርጓሜ እንመለከታለን
ወሥበሐት ለእግዚአብሔር