Thursday 11 July 2013

//ፊደል ይገድላል//


አንዱ ነው አሉ መፅሐፍ ቅዱስ ለማንበብ በግምት አንዱን ገጽ ገለጠ። "ሰላምና ጸጋ ላንተ ይሁን" የሚል ቃል አነበበ። ፀጋ የምትባል ሚስት አለኝ አሁን ሰላም የምትባለዋን መፈለግ አለብኝ አለና አረፈው ይባላል።


ፕሮቴስታንት ዘመዶቻችን የእግዚአብሔርን ቃል እንደወረደ እንቀበላለን ትርጉም አንፈልግም ይላሉ። ይህ ግን ስህተት ይመስለኛል። ዮሐንስ እግዚአብሔርን ያየ ከቶ ማንም የለም ይላል። ነቢዩ ኢሳይያስ ደግሞ እግዚአብሔርን ከፍ ባለና ባማረ ዙፋን ላይ አየሁት ይላል። ጉድ እኮ ነው ዮሐንስና ኢሳይያስ ተጣሉ ማለት ነው? ባለ በገናው ዳዊት ደግሞ ሁል ጊዜ እግዚአብሔርን በፊቴ አየዋለሁ ይላል። መዝ 18፦6 ታድያ ነቢያቱና ሐዋርያቱ ተጣልተዋል ማለት ነው?
አንዱ ወዳጄ መፅሐፍ ቅዱስ ለማንበብ በግምት አንዱን ገጽ ገለጠ። ይሁዳ ታንቆ ሞተ የሚል አነበበ። ኦ ኦ አለና ሁለተኛ እድሉን ሊሞክር ከእንደገና ገለጠ። "በቶሎ አድርገው" የሚል ቃል አነበበ። ከዛን በኋላ ምን እንደተፈጠረ እናንተው ገምቱ።

እኔና አብ አንድ ነን ያለ ጌታ ከእኔ አብ ይበልጣል ብሏል። የክርስቶስ ቃል ተጋጭቷል የሚል እርሱ ማን ነው?
ፕሮቴስታንት ዘመዶቻችን ሆይ የእግዚአብሔርን ቃል እንደወረደ እንቀበላለን ስለምትሉ ከእኔ አብ ይበልጣል
የሚለውን እንደወረደ ለምን አትቀበሉም? ይባስ ብሎ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመላእክ ይልቅ በጥቂት አንሶ ነበር ይለናል፤ ዕብ2፡9 ፕሮቴስታንት ዘመዶቻችን እንግዲያውስ ክርስቶስ ከመላዕክት ያንሳል? ቃሉን ያለ ትርጉም እንዴት እንደወረደ መቀበል ይቻላል? ከመላእክ ይልቅ በጥቂት አንሶ ነበር ማለትስ ምን ማለት ይሆን?

መላዕክትን እንዳይሞቱ አድርጎ ፈጥሮ እርሱ ግን ስለ እኛ ሞተ የማይሞተው ሞተ፤ እነሆ ወልድ በተለየ አካሉ ሞትን ስለቀመሰ ይህ ተብሏል ።

የእግዚአብሔርን ቃል እንደወረደ እንቀበላለን ትርጉም አንፈልግም ማለት ትልቅ ስህተት ነው። በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል ይላልና ማርያም በየትኛው ጦር ሜዳ ነው በነፍሷ ሰይፍ ያለፈው? እውነትና ሕይወት መንገድ እኔ ነኝ የሚለውን ይዘን ክርስቶስን ልክ እንደ ጎዳና ሄደን ሄደን መጨረሻ ላይ አብ ጋ እንደርሳለን እንዴት ማለት ይቻላል? ቃሉ እንደወረደ መንገድ ማለት የምንጓዝበት መንገድ ነው እንዴት ይባላል?

ዮሀንስ 14፡6 እኔ መንገድ እውነት እና ሂዎት ነኝ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም የሚለውም እውነት እንደሆነና በኢየሱስ ክርስቶስ የጥል ግድግዳው እንደተናደ ተናግረናል እንጂ የላከኝ አብ ከሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም ዮሀ 6፡44 ማለት አብ አማላጅ ነው ማለት እንዳልሆነ ሁሉ ይህም እንዲሁ ነው!

እንግዲህ ምን እንላለን? ቃሉን እንደወረደ እንቀበል ማለት ከዓለማችን ታላቁ ስህተት እንደሆነ እንወቅ።

"ሁሉ ከተገዛለት በኋላ ግን እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ ይሆን ዘንድ በዚያን ጊዜ //ልጁ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ይገዛል// 1ኛቆሮ15፡24-28 " ይህን ወስዳችሁ ወልድ ለአብ ተገዢ ነው ብላችሁ እንዴት ማስረዳት ይቻላችኋል? እንግዲያውስ ምን ይሻለናል? ልጁ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ይገዛል ማለት ምን ማለት ይሆን?

በመሰረቱ የዚህ ጥቅስ መልዕክት ስለ ሞት ነው 24-25. በኋላም፥ መንግሥቱን ለእግዚአብሔር ለአባቱ አሳልፎ በሰጠ ጊዜ አለቅነትንም ሁሉና ሥልጣንን ሁሉ ኃይልንም በሻረ ጊዜ፥ ፍጻሜ ይሆናል። ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ በታች እስኪያደርግ ድረስ ሊነግሥ ይገባዋልና።+++++ስለ እለተ ምፅዓት ይናገራል
26. የኋለኛው ጠላት የሚሻረው ሞት ነው፤++++ ሚሻረው ሞት ነው ይለናል
27. ሁሉን ከእግሩ በታች አስገዝቶአልና። ነገር ግን። ሁሉ ተገዝቶአል ሲል፥ ሁሉን ካስገዛለት በቀር መሆኑ ግልጥ ነው።++++ሞት ሁሉን ገዝቷል ነገር ግን እንዲገዛ ያረገው እግዚአብሄር ነው ይላል+
28. ሁሉ ከተገዛለት በኋላ ግን እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ ይሆን ዘንድ በዚያን ጊዜ ልጁ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ይገዛል።+++++እግዚአብሄር ወለድ ለሞት ይገዛል ይለናል አውነት ነው ኢየሱስ 3ማዓልት እና 3ሌሊት ሞት ይዞት ነበርና፡፡

ልጁ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ይገዛል ማለት ኢየሱስ 3ማዓልት እና 3ሌሊት ስለ ሰው ልጅ ፍቅር ሞቶ ነበርና ለሞት ተገዛ ተባለ። ይሁን እንጂ ሞት ሥልጣን አልነበረውምና ሞት ሆይ መውጊያህ የት አለ ተባለ። ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ ተነስቷልና!

እንግዲያውስ ቃልን መተርጎም እንደሚገባ ልብ ያለው ልብ ይበል!

ሐራ ጥቃ የሚባሉ ሰዎች ቀዳሚሁ ቃል ሥጋ ኾነ /በመጀመሪያ ቃል ነበረ ቃልም ሥጋ ኾነ/ የሚለውን ብቻ ይዘው አካላዊ ቃል ተለውጦ ሥጋ ኾኖ በማህፀነ ድንግል ማርያም አደረ ብለው ያምናሉ። የቃና ዘገሊላው ውኃ ተለውጦ ወይን እንደኾነ ፣ የሎጥ ሚስት ተለውጣ የጨው ሃውልት እንደኾነች ቃልም እንዲሁ ተለውጦ ሥጋ ኾነ አሉ። ይህ ግን የምንፍቅና ትምህርት ነው። ሐራ ጥቃ በመጀመሪያ ቃል ነበረ ቃልም ሥጋ ኾነ የሚለውን ብቻ ሲያዩ ወኃደረ ላዕሌለ /በእኛም አደረ/ ያለውን አላዩም። ልብ በሉ! ወንጌላዊው ዮሐንስ ምዕራፍ 1 ቁጥር 1

በመጀመሪያ ቃል ነበረ

ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ

ቃልም እግዚአብሔር ነበረ

“ቃልም ሥጋ ሆነ”

ወንጌላዊው “ቃልም ሥጋ ኾነ” አለን እንጂ “ቃልም ወደ ሥጋ ተለወጠ” አላለንም። ቤተክርስቲያናችንም ይህንኑ አምና ቃል በተዋህዶ ከእመቤታችን ሥጋን ነሳ በድንግል ማርያም ማህጸንም አደረ ብላ ወንጌልን ታስተምራለች።
ንስጥሮስም ቀዳሚሁ ቃል /በመጀመሪያ ቃል ነበረ/ የሚለውን ሳይመለከት ወኃደረ ላዕሌነ /በእኛም አደረ/ የሚለውን ብቻ አየና ኃደረ በብእሲ /ከሴት ዘንድ አደረ/ ብሎ እመቤታችን ወላዲተ አምላክ አይደለችም አለ። ፊደል ይገላል እንዲሉ ፊደሉን በቁሙ ብቻ ካየነው ቆመን እንቀራለን። ቆመን ብንቀርስ በተሻለ ነበር ከዚህ የከፋው እንዳንነሳ ሆነን መውደቃችን ነው። ብዙዎች ፊደል ብቻ አይተው ወድቀዋልና። እለ አርዮስ እለ መቅደንዮስ እለ ንስጥሮስ እለ መርቅያን …… እነዚህ ኹሉ የቆመውን ፊደል አይተው ቆመው የቀሩ ናቸው።

በከመ ይቤ ቅዱስ ጳውሎስ “እስመ መፅሐፍ ይቀትል ወመንፈስ ያሐዩ” ፪ኛ ቆሮንጦስ [፫: ፯] እንዲል ፊደል እንደ አርዮስ ፣ እንደ ንስጥሮስ እንደ ሐራ ጥቃ ይገላል፤ መንፈስ ቅዱስም ሕይወትን ይሰጣል።




No comments: