Friday 18 May 2012

“አቶ ሥልጣን!”

ዘና ብላችሁ ተቀመጡና አንድ አሪፍ ታሪክ ልንገራችኹ!


                 
                   በአንድ ወቅት የዱር አራዊት ተሰበሰቡና ንጉሥ አንበሳ ለምን ይገዛናል እንዲያውም ከሥልጣኑ ይውረድልን አሉ። ንጉሥ አንበሳም ግልጽነታቸውን ወዶ በሰላም ወረደ። ወዲያው ማን ይንገሥ ብለው አራዊቱ ሸንጎ ተቀመጡ። እንዲያው በአለባበሱ በየዋህነቱ አንገቱን ደፍቶ በመሄዱ በግ ይንገሥልን አሉ። ንጉሥ በግም ሥልጣኑን ተረከበ።

ንጉሥ በግ ከሳምንት በኋላ በሉ በሉ ያንን ጮማ አምጡልኝ አለ። ኹሉም ግራ ገብቷቸው እንዴ ንጉሥ በግ አንተኮ በግ ነህ ሣር ነው የምትበላው አሉት። ንጉሥ በግ ግን ተቆጣ! ከዛሬ ጀምሮ የፈለኩትን መብላት አልችልም? የንጉሥ ትእዛዝ አይከበርም ማለት ነው? በሉ ያን ሥጋ በቶሎ አምጡ ብሎ እየተቆጣ አዘዘ።  እነሱም ይህ ነገር ስላላማራቸው ንጉሥ በግን ከሥልጣን አወረዱት።
ፍየል እንደምንም ታግላ ሥልጣን ላይ ወጣችና ወዲያው ዘባረቀች።  ኧረረረረ……………….…… ያ ሥጋ እንዴት ያስጎመጃል! ኧረረረ…… እያለች የቀን ሕልም ማለም ጀመረች። አራዊቱ ኹሉ ግራ ገባቸው። እሜቴ ፍየል ግን ግራ ቢገባቸው ቀኝ ቢገባቸው ጉዳይዋ አይደለም። በመጨረሻ ችግሩ ከአንበሳ ከበግ ወይንም ከፍየል ሳይሆን ከመቀመጫው ነው! ይህች መቀመጫ ሣር የሚበላውን ሥጋ የምታሳይ ወንበር ናት! አሉና ለመጪው ትውልድ ወንበሩ እንዲመች ለማድረግ ተስማሙ!!!

ቢቢሲ የተባለው ጓደኛችን ነበር ይህችን ታሪክ የነገረን። ቢቢሲ እንዲያው ለአፉ ጅምናስቲክ ካላወራ ዝም ብሎ መቀመጥ አይኾንለትም! አፈር ፈጭተን ውኃ ተራጭተን ያደግን 7 ጓደኛሞች ነበርን። ሁላችንም ስራችንን የሚገልፅ የግብር ስም አለን። አንደኛው ንግግር ከጀመረ ስለማያቋርጥ “ቢቢሲ” አልነው። ሁለተኛዋ ቀልድ ትጀምርና ቀልዱን ሳትጨርስልን ራሷ ስቃ ስለምትጨርሰው “ቀልድ በቴክስት ብለናታል። ይህን ስም የሰጠናት ቀልድሽን ቴክስት አድርጊልን ለማለት አስበን ነው። ሌላኛው ጓደኛችን በጫወታችን መጨረሻ ሁሌ አባባሎችን ጣል ስለሚያደርግልን “አባባሎች ብለነዋል።

ከመካከላችን አንደኛው ሥልጣን በጣም ይወድ ነበር። እንዴት ብዬ ልንገራችሁ ማንኛውንም ሥልጣን ይወዳል። ማን ስልጣንን ይጠላል? እንዳትሉኝ። ሥልጣንን ያልወደዱ የብዙ አበውን ታሪክ ማንሳት እንችላለንና። በእርግጥ ብዙዎቻችን ስልጣንን እንወዳለን።  የጓደኛችን የሥልጣን ፍቅር ግን ልዩና ልዩ ነው። ታዲያ ለዚህ ጓደኛችን ምን የሚል ስም እንናውጣለት? ተባባልን። ከመካከላችን በእድሜ ጠና ስላለ እና ሥልጣን ስለሚወድ    
አቶ ሥልጣንእንበለው ተባለ። ፍቱን ስም ስለተገኘለት ጭብጨባው ቀለጠ። ስለ ሥልጣን ስንነጋገር ልቡ ነግሮት ነው መሰል ሥልጣን የሚወደው ጓደኛችን ወዲያው ከተፍ አለ። ወዲያው አዲስ ስሙንም ለጓደኛችን ነገርነው። አቤት የደስታው ብዛት ….. ኢትዮጲያ የአለም ዋንጫ ብትበላ እንኳን እንደዛ የሚደሰት አይመስለኝም! በቃ! የልቡ ምት እንደ አበበ ቢቂላ እስኪመታ ድረስ ዘለለ! ይህንንም ስም ሻማ አብርተን ድፎ ቆርሰን አፀደቅነው። ግሩም ስም! እያለም እጅግ ተደሰተ።

ፀሐይዋ ጠለቀች ጊዜውም ነጎደ። መቼስ አቶ ሥልጣን” ብለን በገዛ እጃችን ስም ሰጥተነዋልና አንዳች ሥልጣን መስጠት አለብን። ግን ምን? ከብዙ የሐሳብ ልውውጥ በኋላ አንድ መፍትሄ መጣልን። ለምን ዕድር አንከፍትም? አለ ቢቢሲ። ቢቢሲ ሐሳቡን በረጅሙ ለመግለፅ ጉሮሮውን ይጠራርግ ጀመር። እ እ… እ… ጉሮሮው ተሞረደ። ዕድር እንክፈትና አቶ ሥልጣንን ሊቀመንበር እናድርጋቸው። አቶ ሥልጣንን እስቲ በሥልጣን ባሕር እናስዋኛቸው! እስቲ እናስፈንድቃቸው! ይህ ደግሞ ለሀገርም ኾነ ለአቶ ሥልጣን ይጠቅማል ….. እያለ ቢቢሲ ሰፋ ያለ ሐሳቡን ገለፀ።

በሳምንቱ ለሀገር የሚጠቅመው ታላቁ እድር በአቶ ሥልጣን የመክፈቻ ንግግር ተመሰረተ። ስሙንም “የአቶ ሥልጣን እንተባበር ዕድርብለው አቶ ሥልጣን በራሳቸው ሥልጣን ሰየሙት። በዚህ በተከበረ የዕድር መክፈቻ ስነ ሥርአት ላይ ቢቢሲ ተገኝቶ ነበርና ዘገባውን ቀጠለ።

በውኑ ሁላችንም ደስ ብሎናል! ሥልጣን ለሚሰራበት ታላቅ ነው! እነ ማንዴላ ሰሩና ዞር አሉ። ይህ ነው የሥልጣን ጀግና! ሌላው ሥልጣንን ታቅፎ ይሞቃል፤ ጀግኖቹ ግን ሰሩና ዞር አሉ።
[በዚህ ንግግር አቶ ሥልጣን ፈገግ እያሉ አይ ማንዴላ ደጉ” አሉ በልባቸው እያፌዙ] ቢቢሲ ዘገባውን ቀጠለ። ሥልጣን ከቆየ እንደሚፋጅ እሣት ነው፤ ለዚህ እኮ ነው እነ ዋሽንግተን ለአራት አመት ብቻ መርተው ሁሉን አደላድለው ሥልጣንን የናቁት! ለዚህ እኮ ነው እነ ሐዲስ ዓለማየሁ ሥልጣንን እንቢ ያሉት! ለዚህ እኮ ነው እነ ማኅተመ ጋንዲ ሥልጣንን የሸሹት! ለዚህ እኮ ነው እነ ኔሬሬ ሥልጣናቸውን በሠላም አስረክበው ወደ ግብርና የሄዱት! በነገራችን ላይ ታላቁ ኔሬሬ እቅዳችን ታላቅ ነበር በአፈፃፀም ግን ተሳስተናል” ብሎ ከአፍሪካ መሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ እራሱን የወቀሰ የዓለማችን የመጀመሪያው ደኻ መሪ የ400 ብር ደመወዝተኛ ነበር! ለዚህ እኮ ነው እነ ኬኔት ካውንዳ ነጭ መሐረባቸውን እያውለበለቡ በክብር ዓለምን የሚዞሩት! ለዚህ እኮ ነው ጀግኖቹ እነ ማንዴላ የሥልጣን እሣት እንዳያቃጥላቸው ስራቸውን በጊዜ ሰርተው ዞር ያሉት። ይህን ጊዜ አቶ ሥልጣንን ከኋላቸው አንዳች ነገር ገፋፋቸውና ወደ ፊት ሲንደረደሩ በጭንቅላታቸው ሊተከሉ ነበር። ምን ሊናገሩ ይሆን እያልን ዓይን ዓይናቸውን አየን። ማንዴላ” የሚለው ክቡር ስም ብዙም አልተስማማቸውም ነበርና አቶ ሥልጣንን ከኋላ የገፋፋቸው ንዴት ነበር። በእጃቸው እያጨበጨቡ እንደምታውቁት ቢቢሲ ንግግር ከጀመረ ያው ከሥልጣን እስከምወርድ ድረስ ማውራቱን ይቀጥላል። ይህ ደግሞ ዘመናትን ያስቆጥራል! ስለዚህ በአጭሩ እንቅጨው ብለው የተከበሩት አቶ ሥልጣን የቢቢሲን ንግግር በአጭር አስቀሩት። አቶ ሥልጣን ናቸውና በሥልጣናቸው የገባ ማንም አልነበረም።

አሁን አቶ ሥልጣን መስማት የሚፈልጉት ስለ ሥልጣናቸው ብቻ ነው። ቢቻል ሥልጣናቸው በመጪዎቹ ዘመናት እንዴት በአስተማማኝ ኹኔታ ያለ ተቀናቃኝ የሚይዙበትን ዘዴ ቢያማክሯቸው ደስ ይላቸዋል። አቶ ሥልጣን ደስ እንዲላቸው እስቲ ስለ ሥልጣናቸው እንተንትን።

አቶ ሥልጣን ሊቀመንበር የሆኑት በሁለት መስፈርት ነው።

; ሥልጣን እጅግ በመውደዳቸው እጅግ አዝነንላቸው
ለ; በታማኝነታቸው
እውነትም ለመጀመሪያ ጊዜ በዕድራችን ውስጥ ድንኳን የለም ነበር። እድሜ ለአቶ ሥልጣን አሁን ምን የመሰለ ድንኳን አለን! ኩባያ እና አግዳሚ ወንበሮች ተገዝተዋል። አቶ ሥልጣን በሥልጣናቸው ብዙ በቆዩ ቁጥር ግን እየተሰላቹ የመጡ ይመስላል። ከተመረጡ 8 አመታቸው ቢሆንም ሂሣቡን አላስመረመሩም። ምርጫ ይደረግና ያስረክቡ ተብለው ቢነገራቸው እንደ አራስ ነብር ተቆጥተው ነበር ይባላል። የምርጫ ወሬ ያነሱትን ሁሉ ከዕድር በሰበብ በአስባቡ ማባረር ጀምረዋል። ጭምጭምታው ግን ጥሩ አይመስልም። አቶ ሥልጣን ገንዘብ ጎሎባቸዋል ይባላል። ንግድ ብጤ የጀመሩት በዕድር ገንዘብ ነው ተብሎ በሰፊው ይወራል። ምን ያህል ገንዘብ አለን ብሎ ለጠየቃቸው የዕድር አባል ከስድብ በስተቀር ሌላ መልስ የላቸውም።

ሚሥጢሩ ግን እንዲህ ነው፤ አንዱ ወዳጅ መስሎ የተጠጋቸው አጭበርባሪ ሰው አንድ ቀን ቤታቸው በምሽት መጥቶ ያስቀመጡትን የዕድር ገንዘብ ቢያዋጡ እሱም ያለውን ጨምሮ የሽርክና ንግድ እንጀምራለን ብሎ ልባቸውን አሸፈተው። ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል” የሚባልበት ብቸኛዋ ሀገር ኢትዮጲያ ብቻ ናት።
ይህ ውብ ተረታችንን እየሰሙ ያደጉት አቶ ሥልጣንም ያቺን የተቀመጠችውን 50ሺህ ብር ንግድ ላይ አዋሏት። ትርፉ ግን እንዳሰቡት አልነበረም። እንደውም ሸሪካቸው ገንዘባቸውን ወስዶ ከድቷቸዋልም ይባላል። አሁን ከዕድር ሊቀመንበርነታቸው ቢወርዱ ምን ያስረክባሉ? ጭንቁ ይህ ነው። የሥልጣን ጥማታቸውስ እንዴት ክፉኛ ይጎዳ ይኾን? እንደዚያ እንዳልዘለሉ እንዳልቦረቁ እንዴት በቀላሉ እጅ ይሰጣሉ? ሲጀመር የተመረጡት እኮ ታማኝ ተብለው ነበር። ታዲያ በተከበሩበት ሀገር ውርደት? ቱ… ቱ… ቱ ይህስ አይሁንባቸው። ንዴቱ ግን ለጨጓራ ፣ ለደም ብዛት ፣ ለስኳር ዳርጓቸዋል።
ጊዜ ሲነጉድ አቶ ሥልጣን ሕመሙ ጠናባቸው መሰል ተሸፋፍነው አልጋ ላይ ወደቁ። የተጭበረበረችው ገንዘብም መጉደሏ ታወቀ። በዚህም ምክንያት ስማቸው ጠፋ ሕሊናቸውም ታወከ። እንዲህም ሆነው እጅግ የሚያሳስባቸው ጤናቸው ሳይኾን የሥልጣናቸው ጉዳይ ነው! ሥልጣኔን ይነጥቁኝ ይኾን?” ይላሉ ሰው እንዳይሰማቸው በሹክሹክታ። ኦ ኦ ታመሃል ብለው በሰበብ በዐስባቡ ቢያባርሩኝስ?” ይሉና ጤነኛ ለመምሰል እንደምንም ብለው ከአልጋቸው ይነሳሉ። ማንም ሳያያቸው ሰውነታቸውን ያፍታታሉ አንድ ኹለት አንድ ኹለት ኧረ ገና አንድ ፍሬ ልጅ ነኝ” እያሉ ራሳቸውን ያፅናናሉ። አልጋቸው ውስጥ ገብተው በሐሳብ ባቡር ይሳፈራሉ። ማን ይኾን በሥልጣኔ የሚተካው? ይላሉ። ልፋ ያለው በሕልሙ ሸክም ይሸከማል እንዲሉ አቶ ሥልጣን ሕልማቸው ስለ ሥልጣን ነው። ቅዠታቸውም ከሥልጣን አይዘልም። በመጨረሻ አቶ ሥልጣን ታናሹ ሥልጣን የተባለ ልጃቸውን ወልደው እስከወዲያኛው ዐረፉ። ታናሹ ሥልጣንም ለአባቱ እንዲህ የሚል የኀዘን እንጉርጉሮ ገጠመ።

ኢኮኖሚ ቢሞት በሐሳብ ይነሳል
ፖለቲካ ቢሞት በሐሳብ ይነሳል
ሥልጣን የሞተ ዕለት ወዴት ይደረሳል።

እህህህህ……እያለ የአባቱን ሥልጣን ተረከበ! ታናሹ ሥልጣን ልክ እንደ አባቱ የሥልጣን ወዳጅ ነበር። እንዲያውም ብዙ ሥልጣን የሚወዱ ሰዎች እንደሚሉት የሥልጣን ፍቅሩ የአባቱን እጥፍ ነው ይሉ ነበር! እሱም ለአቅመ ሥልጣን በደረሰ ጊዜ ብዙ ሥልጣን የሚወዱ ልጆችን ወለደ። እንደ አባቱ እንዴት አድርገው ሥልጣን መውደድ እንዳለባቸው እየኮተኮተ በሚገባ አሳደጋቸው። እነሆ የሚያማምሩ የአቶ ሥልጣን ዝርያዎች እንደ አሸን በዙ ተባዙ።


ይህን ኹሉ ታሪክ በጥሞና የተከታተለው አባባሎች” የተባለው ጓደኛችንም ይህን አባባሎች ደረደረ።

“ተሸፋፍኖ ቢተኙ ገላልጦ የሚያይ አምላክ አለ

“ሥልጣን ላወቀው ይከብደዋል ላላወቀው ያሳብደዋል

“እንደ ማንዴላ በሥልጣን ጊዜ ሰርቶ መኖር መታደል ነው

ከጥሩ ስምና ከመልካም ሕሊና ጋር የሚሞት ዕድለኛ ነው!