Thursday 11 July 2013

ሕሊናችሁን አትበድሉ!!



ላይኛው ከንፈር ለክርክር ታችኛው ከንፈር ለምስክር አሉ!! 



እስኪ ዘና ብላችሁ ተቀመጡና ዛሬ የታዘብኩትን ላውጋችሁ። አንዳንዶች ለቅዱሳን መስገድ የሚባል ነገር የለም ይላሉ። በብሉይ ኪዳን ብዙዎች ቢሰግዱም ((የመካከለኛው ምስራቅ የሰላምታ ባህል)) እንጂ አምልኮ አይደለም ይላሉ:: ይህን መጨረሻ ላይ እየተረክን እናየዋለን።

አንዳንዶች ደግሞ የአክብሮት ሰላምታ ነው ይላሉ፦ በብሉይ ኪዳን ሰዎች ለሰዎችም ሆነ ሰዎች ለመላእክት የሰጡት ((የአክብሮት ሰላምታ ወይም ስግደት )) አብረዋቸው ለነበሩ ሰዎች ወይም ለተገለጡላቸው መላእክት ነው ይላሉ።

አንዱ ባህል ነው ይላል አንዱ ለአክብሮት ነው ግን ሲገለጡልን ብቻ ነው የምንሰግደው ይላል። ሲጀመር ልብ እውነታን ለመቀበል አልፈለገችምና ምክንያት ፍለጋ አብዝታ ትሮጣለች።

እስኪ ዘመዶቻችንን በሚዛን እንመዝናቸው፦ የሐዋርያት ሥራ 16

25 በመንፈቀ ሌሊት ግን ጳውሎስና ሲላስ እየጸለዩ እግዚአብሔርን በዜማ ያመሰግኑ ነበር፥ እስረኞቹም ያደምጡአቸው ነበር
26 ድንገትም የወኅኒው መሠረት እስኪናወጥ ድረስ ታላቅ የምድር መንቀጥቀጥ ሆነ፤ በዚያን ጊዜም ደጆቹ ሁሉ ተከፈቱ የሁሉም እስራት ተፈታ።
27 የወኅኒውም ጠባቂ ከእንቅልፉ ነቅቶ የወኅኒው ደጆች ተከፍተው ባየ ጊዜ፥ እስረኞቹ ያመለጡ መስሎት ራሱን ይገድል ዘንድ አስቦ ሰይፉን መዘዘ።
28 ጳውሎስ ግን በታላቅ ድምፅ። ሁላችን ከዚህ አለንና በራስህ ክፉ ነገር አታድርግ ብሎ ጮኸ።
29 መብራትም ለምኖ ወደ ውስጥ ሮጠ፥ እየተንቀጠቀጠም ከጳውሎስና ከሲላስ ፊት ተደፋ!

የወኅኒውም ጠባቂ ለጳውሎስና ለሲላስ የሰገደው ለሰላምታ ነው? ዘመዶቻችን ለሰላምታ ነው ሲሉ ነበር፤ እንዲያውም የመካከለኛው ምስራቅ ባህል በደንብ እናቃለን ሲሉ ነበርና አሁን የተሰገደው ለባህል ነው ወይስ ለሰላምታ??

አሁንም ደግመን ዘመዶቻችንን በሚዛን እንመዝናቸው ትንቢተ ዳንኤል 2

45 ታላቁ አምላክ ለንጉሡ አስታውቆታል ሕልሙም እውነተኛ ፍቺውም የታመነ ነው።
46 የዚያን ጊዜም ንጉሡ ናቡከደነፆር በግምባሩ ተደፍቶ ለዳንኤል ሰገደለት፥ የእህሉንም ቍርባን ዕጣኑንም ያቀርቡለት ዘንድ አዘዘ።

እንግዲያውስ አሁን የተሰገደው ለባህል ነው ወይስ ለሰላምታ?? የእህሉንም ቍርባን ዕጣኑንም ያቀርቡለት ዘንድ አዘዘ ማለት ዳንኤልን አምልኩ ማለት ነው? ናቡከደነጾር ዳንኤል ማን እግዚአብሔርም ማን እንደሆነ ያውቃል! አምላካችሁ የአማልክት አምላክ ምስጢርም ገላጭ ነው አለ!! ለዳንኤልም ሰገደ!!

አሁንም ደግመን ዘመዶቻችንን በሚዛን እንመዝናቸው ኦሪት ዘፍጥረት 33

1 ያዕቆብም ዓይኑን አነሣ፥ እነሆም ዔሳውን ሲመጣ አየው፥ ከእርሱም ጋር አራት መቶ ሰዎች ነበሩ ልጆቹንም ከፍሎ ወደ ልያና ወደ ራሔል ወደ ሁለቱም ባሪያዎች አደረጋቸው
2 ባሪያዎችንና ልጆቻቸውንም በፊት አደረገ፥ ልያንና ልጆችዋንም በኋለኛው ስፍራ፥ ራሔልንና ዮሴፍንም ከሁሉ በኋላ አደረገ።
3 እርሱም በፊታቸው አለፈ ወደ ወንድሙም እስኪደርስ ድረስ ወደ ምድር ሰባት ጊዜ ሰገደ።

ሰባት ጊዜ የተሰገደው ለሰላምታ ነው? እንዳላችሁን ይህ ባህላቸው ስለሆነ ሰዎች ሁሉ ሲገናኙ ሰባት ጊዜ ይሰግዳሉ?
ኢየሩሳሌም በሄድን ጊዜ እንደ ባህላቸው ሰባት ጊዜ ለምን አልሰገዱልንም?

ሰዎች ሆይ በሚዛን ተመዘናችሁ። ማኔ ቴቄል ፋሬስ ቴቄል ማለት በሚዛን ተመዘንክ ቀለህም ተገኘህ ማለት ነውና አስተውሉ። ቅዱሳን እና መላዕክት ካልተገለጡልኝ አልሰግድም ማለት ሲጀመር ቢገለጡስ ለመስገድ ፍቃደኛ ናችሁ? ለክርስቶስ የምትሰግዱትስ እየተገለጠላችሁ ነው? ማን ያውቃል ከተገለጠላችሁ እውነቱን ንገሩንና እንገረምባችሁ። ለቅዱሳን እየሰገዳችሁ ፍጡርን እያመለካችሁ ነው ብላችሁ አኩርፋችኋል። ያ በረኛ አምላኬ ጳውሎስ ብሎ ሰገደ? ያ ንጉሥ አምላኬ ዳንኤል ብሎ ሰገደ? አስተውሉ !

ሕሊናችሁን አትበድሉ!! 

No comments: