Friday 21 September 2012

“አስገራሚው የለንደን ታሪክ”


ያለመከራ አይገኝም እንጀራ ትለኝ ነበር እናቴ እንጀራ ባጎረሰችኝ ቁጥር። አንድ ወንድሜ እንጀራን ፍለጋ ስደት የተባለውን ባህር አቋርጦ ለንደን ገባና ቀን ከሌት ለፍቶ 150 ሺሕ ፓውንድ አጠራቀመ። ይህን 150 ሺሕ ፓውንድ ያስቀመጠው ግን ባንክ ሳይሆን ከሚተኛባት ፍራሽ ስር ነበር። ሞት በእንቅልፍ ይለመዳል እንዲሉ ይህ ወንድሜ ብሩን ባስቀመጠበት ፍራሽ ላይ እንደተኛ በዛው እስከወዳኛው አንቀላፋ። ወዲያው ፖሊሶች መጡና ቤቱን ፈተሹ። ከፍራሹ ስር 150 ሺሕ ፓውንድ ተገኘ። ይህ ብር ለማን ይሰጥ? የሚለው ጥያቄ ግን መልስ አጣ። ምክንያቱም ኢትዮጵያዊው ወንድሜ አለኝ የሚለው አንዳች ወገን የለውም ነበርና ነው። በመጨረሻም ብሩ የመንግሥት ገቢ መሆን አለበት ተባለና የመንግሥት ገቢ ሆነ!! 150 ሺሕ ፓውንድ ማለትም 4,200,000 ብር የመንግሥት ንብረት ሆነ።

ሁለት ቀን ለመኖር አራት ቀን አትጨነቅ” ትላለች እናቴ። እንዲህ ለሚጠፋ ብር ይህ ወንድሜ ብዙ ተጨንቆ ነበር። ወንጌሉም እየደጋገመ ስለ ጠፊ አላፊ ነገር ከቶ አትጨነቁ ይለናል። ልብ በሉ አትጨነቁ ተባልን እንጂ አታስቡ አልተባልንም። መጨነቅና ማሰብ እጅግ ይለያያሉና። ሞት ታላቅ መፅሐፍ ነው፤ ነገር ግን የሚያነበው የለም ይባላል። እስኪ ይህን ታላቅ መፅሐፍ እናንብበው። እስኪ ከዚህ ወንድማችን ታላቅ ነገር እንማር።

ወንድሜ ሆይ በስደት ያላረፈች ነፍስህ በመንግሥቱ ዘለዓለማዊ ረፍትን ታግኝ፤ አሜን።



 አሁን ደግሞ ኛውን አስገራሚ የለንደን ታሪክ ላውጋችሁ። ነገር ያሻ ዳኛ አምጡ ይላል የዶሮ ሻኛ እንዲሉ አንዱ ወዳጄ የዶሮ ሻኛ ካላመጣሽ በሚል ዓይነት ክርክር በአዲስ ዓመት ከሚስቱ ጦርነት ከፈተ። ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት ብለው የተከበሩት ባልና ሚስት በተከበረች ጎጇቸው ጦርነት ከፈቱ። አዲሱን ዓመት ይህን በመሰለ የፍቅር መግለጫ ሞቅ ደመቅ ባለ አቀባበል ተቀበሉት። ባለፈው አመትም ልክ እንደዚሁ በፍቅር ነበር አዲሱን ዓመት የተቀበሉት። የተከበረው ባል የተከበረችውን ሚስቱን ስለሚሳሳላት ደፍሮ በሙሉ ዓይኑ አያያትም ነበር። ስትናገር እንዳይደክማት ብሎ እንደ ባህታዊ አርምሞ ዝምታ ያበዛ ነበር። ጎጇቸው ገዳም እስኪመስል ድረስ ዝምታ በዛበት። ሚስት ብዙ ዝምታ ይሆናል በሽታአለች በልቧ። ሰዎችምፊት ነሳትብለው አሙት። ሚስት ደግነቱ የሰው ፊት አለመፋጀቱ አለች አሁንም በልቧ። ሁለቱም ከፍቅራቸው የተነሳ ዓመቱን ሙሉ ሲጨቃጨቁ ሲከራከሩ ሲደባደቡ ኖረው ይኸው ለአዲሱ ዓመት ደረሱ። የዛሬው ክርክር ለዓመት በዓሉ ድምቀት ሞቅ ደመቅ ብሎ ነበርና ሰውነታቸው ዝሎ በያሉበት ተዘርረው አደሩ። አይነጋ የለ ነጋ። አቶ ባል በለሊት ተነስቶ ከተወደደች ሚስቱ 30 ሺሕ ፓውንድ ደብቆ ከሶፋው ውስጥ አስቀመጠና ሀገር ቤት ለረፍት ሄደ። እባብ አፈር ያልቅብኛል ብሎ ሲሰስት ይኖራልአሉ እቴጌ ጣይቱ። ከሚስት ተደብቃ የተሰሰተችው ገንዘብ ለባልም አትሆንም። ከጊዜ በኋላ ሚስት ባሌ ሲመጣ ይደሰት ብላ የቤቱን ቀለም ቀይራ ቤቱን ! አደረገችው። የቤቱ እቃ በሙሉ ተቀየረ። አሮጌ እቃዎች ተጥለው በአዲስ ተተኩ። ያቺ አሮጌ ሶፋም 30 ሺሕ ፓውንድ ጋር ገደል ገባች። የተከበረችው ሚስት እንዲህ አድርጋ ቤቷን ካሳመረች በኋላ በአዲሱ ሶፋ ላይ ዘና ብላ ተቀመጠችና ይህች ናት ሚስት ማለት አለች በልቧ!! አቶ ባል ከረፍታቸው ተመልሰው ቤታቸውን አንኳኩ። ሚስት ፈካ ብላ በፈገግታ በሩን ከፈተች። ገና በሩ እንደተከፈተ ሶፋውስ? ሶፋውስ? ብለው አቶ ባል እየደጋገሙ መጠየቅ ጀመሩ። ሚስትምየኔ ጌታ በጣም ናፍቀኸኛል እስኪ መጀመሪያ ልቀፍህአለች ሻንጣውን እየተቀበለች። አቶ ባልም በቅሎ አባትህ ማነው ቢሉት እናቴ ፈረስ ነች አለ አሉ የጠየቅኩሽን መልሺልኝብሎ አፈጠጠባት። ሚስት ባልዋ ቅኔ ቤት ውሎ የመጣ መስሏት በተረቱ ሳቀችናያረጀው ሶፋ ተጥሎ አዲስ ሶፋ ተገዝቷልአለች አሁንም ፈገግ እያለች። አቶ ባል ክው ብለው ቀሩ። 30 ሺሕ ፓውንድ ማለትም 840,000 ብር ገደል ስለገባ ሰውየው ግማሽ ፓራላይዝድ ሆኑ። 



ግልጽነት የጎደለው ትዳር ትርፉ ይህ ነው። መግባባት ሳይኖር መጋባት ግራ መጋባት ነው!” ትለኛለች እናቴ። ኧረ ለመሆኑ ሁለት ቀን ለመኖር አራት ቀን የምንጨነቀው ግን ለምን ይሆን? መልሱ ለሁላችንም ትምህርት ነው። በፍራሽና በሶፋ ውስጥ ያሉ ታሪኮችም እጅግ ብዙ ናቸው። የሰይጣንን አመጣጥ የማያውቅ አይመንኩስ ይባላልና የጋብቻን ምሥጢር የማያውቅ የሰይጣንን ሸር ያልተረዳ ለአቅመ ጋብቻ አልደረሰም ማለት ነው ትለኛለች እናቴ ስለ ጋብቻ ምክሯን ስትለግሰኝ። ምክሯን በልቤ ጽፌይቀጥላል …. ብዬ ቀና ስል እውነተኛ ሚስት ባልዋን ትወልዳለች እንዲሉ አንተን የሚቀማብኝ እንዳይመጣ ብቻ ብላ ተነበየች። እናት ለልጅዋ ነቢይ ናትይባል አይደል!! እኔም በልቤእውነትም እውነተኛ ሚስት ባልዋን ትወልዳለችብዬ የልቤን ደብዳቤ ካቆሙኩበት ቀጠልኩና እንደለመድኩት የሴት ምክር የሾህ አጥር በሚል መዝጊያ የእናቴን ምክር የልቤን ደብዳቤ በአራት ነጥብ ዘጋሁት። 


አሁን ደግሞ ኡኡ የሚስብለውን አስገራሚውን የለንደን ታሪክ ላውጋችሁ። በጥንታዊቷ በለንደን ከተማ ሲያዩት ግርማ ሞገስ ያለው መንፈስን የሚያድስ የቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን አለ። ይሁንና በስም ብቻ ኢትዮጵያዊ የሆኑፖለቲከኞችተነሱናቤተክርስቲያኒቷ ካምፓኒ መሆን አለባትአሉ! ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም አይደል ተረቱ። እናማ በመጪው እሑድ መስከረም 6 2005 . ስብሰባ ተጠርተናል። በስብሰባው ላይ ልበ ደንዳና ፖለቲከኞቹ እና ስደተኛው ሕዝብ ይፋጠጣሉ! ቤተክርስቲያኒቷ በሕዝቡ ገንዘብ ስለተገዛችና ወጪ ስለሌለባት የምዕመኑ የሙዳይ ምጽዋት ሁሉ የፖለቲከኞቹ ኪስ ማሞቂያ ነበር። ይህም አልበቃ ሲል ጭራሹን ዐይን ያወጣ ጥያቄ ጠየቁ። ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይቀርም አይደል ተረቱ። ይህች ቤተክርስቲያን ያለፉት ፓትርያርክ የአቡነ ጳውሎስን ስም በቅዳሴ ላይ አንጠራም በሚሉ ምክንያቶች ከቅዱስ ሲኖዶስ አባልነት ራስዋን አግልላ ነበር። በዚህ ምክንያት በለንደን ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን የምናገለግል የሰ//ቤት መዘምራንና ካህናት /ሥላሴ ቤተክርስቲያን ማገልገል ጀመርን። አሁን የቅ/ሥላሴን ቤተክርስቲያን የምንጠቀመው በክራይ ነው /ሥላሴ ቤተክርስቲያን ሕንጻ አጥቶ ሲቸገር /ማርያም ቤተክርስቲያን ደግሞ ሕንጻው ካምፓኒ ይሁን ተባለ! 


አሁን ደግሞ የመጨረሻውን አስገራሚውን የለንደን ታሪክ ላውጋችሁ። የማይዘልቅ ማህበር በጠጅ ይጀመራልእንዲሉ ባልና ሚስቱ የማህበር ኑሯቸውንጋብቻብለው ለመኖር ተስማሙ። መቼስ ይህን የመሰለ ማህበራዊ ጋብቻ አመሌ አወጣኝ ከማህበሬማስባሉ አይቀርም። የማይተማመን ባልንጀራ በየወንዙ ይማማላልእንዲሉ ባልና ሚስቱ በየቀኑ እየተማማሉም መኖር ጀመሩ። ሚስት ደጓ ቀን ከሌት ለፍታ ገንዘቧን ለባልዋ ታስረክባለች። አቶ ባል ደላቸውና ቁጭ ብለው ፓውንዳቸውን ሲቆጥሩ ላያቸው የባንክ ሰራተኛ ይመስሉ ነበር። እናማ ኪስ ሲሞላ አቶ ባል ብራቸውን ይዘው ጠፉ። ሚስትም ሰውን ማመን ገደለኝ እኔን እየመሰለኝ ብላ ታሪኳን አወጋችኝ። ሰውን አትመኑ አብዷል ዘመኑብንል ደገኛ ሰዎችን መበደል ይሆንብናል። ብሩን ይዘው የጠፉት አቶ ባል ሌላ ሀገር ሄደው ተሸፋፍነው መኖር ጀመሩ። ተሸፋፍነው ቢተኙ ገላልጦ የሚያይ አምላክ አለ የሚለውን ተረት ማን በነገራቸው! እናንተዬዋ የለንደን ታሪክ ብዙ ነው ለካ። ያልሞተና ያልተኛ ብዙ ይሰማልአሉ። እኔማ ሁሉን ዘክዝኬ ልነግራችሁ አሰብኩና ሁሉን ቢናገሩ ሆድ ባዶ ይቀራልአለኝ የገዛ ሆዴ። የቀበሮ ባህታዊ ከበጎች መሃል ይጸልያል የሚያስብሉ ብዙ ታሪኮች አሉ። ይሁንና እንኳን ሁሉን ተርኬ ጥንትም አንዳንድ ሰዎች ስለ ጋብቻ ሲያነቡ አልያም ሲሰሙ ከፍራቻ የተነሳምነው ጋብቻ ቢቀርስይላሉ። ወዳጄ እኛ መስማት ያለብንኮ የሚያስፈልገንን ነው እንጂ መስማት የምንወደውን ብቻ አይደለም። የትኛው ወታደር ነው ሳይለማመድ ጦርነት የሚወጣው? የጦር ነገር ከፈሪ ጋር አትማከርእንዲሉ የምናማክረውም ሰው ይወስነዋል። ስለ ጋብቻ ጋብቻን ከሚፈሩ ሰዎች ጋር መማከር ውኃን መውቀጥ ነው። እሳት መጣብህ ቢሉት እሳር ውስጥ ገብቻለሁ አለ አሉ። በትዳር ውስጥ ፈተና አለ ማለት ትዳርን ረግሞ ራስን ለፈተና ይበልጥ ማጋለጥ አለብን ማለትኮ አይደለም ጎበዝ! የትኛው ስፖርተኛ ነው ሳይለማመድ ስኬታማ የሆነው? የቅርብ ጊዜ ጀግኖቻችን ጥሩነሽም ሆነች መሰረት ለወርቅ የሚሆን ልምምድ አድርገው ነው ወርቅ ያገኙት። ወርቅ ለማግኘት ወርቅ ይዞ መነሳት አለች ጥሩነሽ! ወዳጄ ሆይ ልምምድ ፈርቶ ወርቅ የተሸለመ ሯጭ አላየንም።

====================================

አዲሱ ዓመት ለተጋባችሁ ሁሉ የመተማመን የርህራሄ የፍቅር የሰላምና የመቻቻል ትዳር ይሁንልዎ።

ክፉ ዘመን አይምጣ ዘመድ እንዳላጣአሉ እቴጌ ጣይቱ። አዲሱ ዘመን ለእርዎ እና ለውድ ቤተሰብዎ ዘመነ ፍስሃ ዘመነ ንስሃ ይሁንልዎ። ዐውደ ዓመቱ የምህረት የፍቅር የሠላምና የአንድነት ዘመን ይሁንልዎ።

አዲሱ ዓመት ለእናት ቤተክርስቲያን ለእናት ሀገራችን ዘመነ ሠላም ዘመነ ፍስሃ ይሁን፤ አሜን።

====================================


    የልጅ ዮናስ ብሎግ አባል ይሁኑ!!


Like ·  ·