Saturday 4 January 2014

ምክረ አበው!


ቀን ከሌት ለፍታ ዳገት ወጥታ ሽቅብ ወርዳ ባልዋን አውሮፓ ያመጣች አንዲት ሴት ነበረች። “ደግነቱ የሰው ፊት አለመፋጀቱ አሉ” እያለች የሰው ፊት እያየች ክቡር ባልዋን አውሮፓ ላይ ከች አደረገችው። ለብዙ ዘመናት ስለተለያዩ በሃሳብ መግባባት አቃታቸው። “መግባባት ሳይኖር መጋባት ግራ መጋባት ነው” እንዲልህ እነሆ ግራ ተግባቡ። እናማ 3ኛው የዓለም ጦርነት በቤታቸው ውስጥ ተከፈተ። ጠዋትና ማታ “እኝኝ” ብቻ ሆነ። ባል ዞር እጥፍ ብለው ሴቶችን ማማገጥ ጀምረው ልጆችን ማስከተል ጀመሩ። ምሽት እርር ድብን አሉ።

ጊዜው የገና በዓል ነበር። ምሽት ሀበሻ ልብሰዋን ሽክ ብላ አዲስ ህይወት ለመጀመር ባልዋን በፍቅር ለመግዛት መቀነትዋን አሰረች! ጸጉራቸውና ጽህማቸው በረዶ የመሰለ ዘካርያስ የተባሉ ሽማግሌን ለበዓሉ ጋብዛ ተፍ ተፍ ትላለች። ዶሮ ወጡንና ድፎውን አሳምራ ቡናውን አፍልታ ፋንዲሻውን አሰናድታ ቤቱን ሞቅ ደመቅ አደረገችው። ሆኖም ድንገት ሳታስበው እንባዋ እንደ ዓባይ ፈሰሰ። ለካስ ለብዙ ሰዓታት እንባዋን አምቃ ይዛ ኑሯል ፍንቅል አለና ስቅስቅ እያለች አለቀሰች። ትዳርዋና ኑሮዋ ስደቱ ተባብረው አስለቀስዋት።

ልጄ ምን ሆንሽብኝ አሉ እንያ ሽማግሌ

አባቴ ሰንካላው ትዳሬ ሰባራው እድሌ ነው የሚያስነባኝ አለቻቸው እንባዋን በነጠላዋ እያበሰች።

የሚዋደዱ ሰዎች ሲጣሉ ከኩርፊያ በኋላ ፍቅራቸው እየታደሰ እየሞቀ ይመጣና ይበልጥ ይተሳሰባሉ። የማይዋደዱ ሰዎች ሲጣሉ ግን ልባቸው ይበልጥ እየሻከረ ይበልጥ እየተጠላሉ ይመጣሉ አሉ ሽማግሌው በፍቅር እያይዋት።

አዬ የኔስ ነገር ለጉድ ነው ይተዉኝ አባቴ። እስኪ ይተዉኝ…….. የአረብና የነጭ እሳት ሲያቃጥለኝ ኖሬ ሰባራ ትዳር ጠበቀኝ አለች በተሰበረ ልብ።

ሽማግሌውም እንዲህ ብለው ተረቱላት።

ልጄ ሆይ!

“ፋንዲሻ ለምንድን ነው እንዲህ ዓበባ የመሰልሽው ቢሏት እሳቱን ስለታገስኩት ነው አለች አሉ!”


“ልጆቼ ሆይ ትእግስታችሁ ሰማይ ፍቅራችሁ መንገድ ይሁንላችሁ” ብለው በረዶ ጽህማቸውን እንደ ጉድ እየዠረገጉ በረዶ ጥርሳቸውን ብልጭ አድርገው የተረቱበትን ፋንዲሻ ዘግነው ወጡ!


ምሽትም በምክሩ ጥበብ ተደንቃ እንደፋንዲሻው እሳቱን ታግሳ ፈክታ ዓበባ የመሰሉ ልጆችን ወልዳ ዓበባ የመሰለ ህይወት መኖር ጀመረች!