Friday 14 December 2012

“ጨረቃ ብትደምቅ አታሞቅ!”




በመዲናችን
 አዲስ አበባ ፩ድ ቤትዋ የፈረሰባት እናት አቤቱታ ስታቀርብ አንዱ ፖሊስ እናቲቱን እመታለሁ ብሎ ልጂቱን መትቶ ገደለ አሉ። ይህም አነሰና በሐዘንዋ ላይ ልቅሶ እንዳትቀመጥ ተደረገ። ይህች እናት ስሟ ራሔል ይባላል። ይህን የሚያነቡ ዐይኖች ሁሉ በታላቁ መፅሐፍ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች የተባለውን ልብ ይበል።

 

/“የራሔል እንባ በራማ ተሰማ”/ 

 

«እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የኀዘን የልቅሶና የጩኸት ድምጽ በራማ ተሰማ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች የሉምና ስለ ልጆችዋ መጽናናትን እንቢ አለች [ኤር. 3115] የእንባ ሰው ራሔል ሮቤልም ስምዖንም የሚባል ባል ሞቶባት ሐዘንተኛ ነበረች። እርሱ ሲሞት ነፍሰ ጡር ብትሆንም « በእርሱ ምትክ ኖራ ውቀጪ ጭቃ ርገጪ፤ » ተባለች። መንታ ፀንሳ ነበርና ደም ፈሰሳት ሕፃናቱም ወጥተው ወጥተው ከጭቃው ወደቁ። ደንግጣ ብትቆምምን ያስደነግጥሻል? የሰው ደም የሰው ሥጋ ጭቃውን ያጸናዋል እንጂ ምን ይለዋል ብለሽ ነው? ርገጪውአሏት። በዚህን ጊዜ ነው « ኢሀሎኑ በዝ ሰማይ አምላከ እሥራኤል በውኑ በዚህ ሰማይ የእስራኤል አምላክ የለምንብላ እንባዋን ያፈሰሰችው። ይኽንንም እንባ በእፍኟ እየሰፈረች ወደ ላይ ረጨችው። እንባዋ ወደ ምድር አልተመለሰም ከመንበረ ጸባዖት ደረሰ እንጂ « ወዐበየት ተናዝዞ ወነጊፈ ላህ ልቅሶ መተውን መጽናናትን እንቢ አለች።» ምክንያቱም ግፉ ያሳዝናልና የሕፃናቱ ሞት የፃር ነውና ሐዘን በየደጁ ኹኗልና፡፡ « እስመ ኢኮንዋ ውሉዳ ውሉደ ልጆቿ ልጆች አልሆኗትምና » ሙተዋልና ባሌ ቢሞት በልጆቼ እጽናናለሁያለችው ከንቱ ኹኖባታልና። ይኽንን ነው ነቢዩ ኤርምያስየኀዘን የልቅሶና የጩኸት ድምፅ በራማ ተሰማ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰችያለው።


እነዚህ ትንሽ ጆሮና  ዐይን የማያዩትና የማይሰሙት የለም። ሰሞኑን ጆሯችን የሰማው ወሬ ልባችንን አሳዝኖታል። ሐና ማርያም በተባለ አካባቢ ቤቶች ፈርሰው ሕዝቡ ውጪ መኖር ጀመረ አሉ። “ጌታዋን ያመነች በግ ላትዋ እውጭ ያድራል” እንዲሉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችም መንግሥታቸውን አምነው ውጪ አደሩ። እናላችሁ ሕዝቡ “ኑሮ ካሉት ፍሪጅም ይሞቃል” ብሎ መኖር ጀመረ። ፍሪጅ ግን እንዲያሞቅ ታስቦ አልተሰራምና ብርዱ ሲጠናባቸው የት እንሂድ ብለው ጠየቁ። “የኢትዮጵያ ሕዝብ ውጪ ነው የሚኖረው” የሚል ምላሽ ተሰጣቸው አሉ። “ራቁቱን ለተወለደ ጥብቆ መች አነሰው” አለ የሀገሬ ገበሬ። ይህ የሞራል ድቀት ነው። ይህ ለኢትዮጵያዊነታችን ሃፍረት ነው። ይህ የዜግነት ክብር ሳይሆን የዜግነት ውርደት ነው። ግማሾቹ “ሁሉን ቢናገሩ ሆድ ባዶ ይቀራል” ሲሉ “ዜግነታችን ይቀየር” ያሉ ዜጎችም አሉ። ሌሎቹም “ማወቅ እናውቃለን ብንናገር እናልቃለን” ብለው ዝምታን መርጠዋል። “መናገር መልካም ነው ማዳመጥ ይበልጣል ቢባልም ብዙ ዝምታ ይሆናል በሽታ ያለኝን ወዳጄን አልረሳውም።

እስኪ ያለሁበትን የስደቱን መንግሥት ላውጋችሁ።

የእንግሊዝ መንግሥት ለስደተኛው ሁሉ ቤት ሰጥቶ ያኖረናል። ስራ እስክንይዝ ድረስ ድቃቂ ፍራንክ እንከፍላለን እንጂ መንግሥት ነው የቤት ኪራዩን የሚችለው። ስራ እስክንጀምር  በየሳምንቱ የምግብ ይችለናል። የትራንስፖርት ቅናሽ ያደርጋል። ይሄ ሁሉ ደግነት ከማናውቀው መንግሥት የመጣ ነው። ይህ ሁሉ መንግሥት ዜጋዬ ለማይላቸው የሚያደርገው ነው። የማናውቀው መንግሥት ቤት ሲሰጠን የኛ ደግ ቸሩ መንግሥት ደግሞ ቤታችንን ያፈርሳል! ይህ እኮ ነው “ሕገ ወጥ ሕግ አስከባሪ” ማለት።


“ጨረቃ ብትደምቅ አታሞቅ!”


አዲስ አበባችን እንደ ጨረቃ ፏ ብላ ደምቃለች አሉ“ጨረቃ ብትደምቅ አታሞቅ!” እንዲሉ እንደ ጨረቃ የደመቀችው አዲስ አበባችን ካልሞቀችን ጥቅሙ ምኑ ላይ ነው? የአዲስ አበባ 125ኛ ዓመት ሲከበር ከአንድ ወዳጄ የልደት በዓል ጋ ተገጣጠመ። ሁለት ጊዜ ነው የዶሮ ልደት አንዱ በእንቁላል ሌላው በጫጩት” እያለች ልጅቱ  በዓመት ሁለት ጊዜ ነው ልደትዋን የምታከብረው። እኛም ይሁንልሽ ብለን አደመቅንላት። እናላችሁ ይህች አንድ ፍሬ ልጅ በአዲስ አበባ ጎዳና ፎቶዬ ካልተሰቀለ ብላ መንግሥትን እየወተወተች ነው አሉ። ለምን? ስትባል አዲስ አበባ እንደ ስሟ ውብ ከተማ ስለሆነች በጣም አምራኛለች አለች አሉ። እውነትም በጣም ዘመናዊ ሆና ያደገችው አዲስ አበባችን ፏ ብላ በፎቶ ላይ እናያታለን። የቤቶቹ ማማር፣ የመንገዱ መጥመዝመዝ ፣ በቅርቡ የሚሰራልን አዲሱ ባቡራችን ኧረ የቱን አንስቼ የቱን ልጣል? እንደው በሞቴ እስኪ ያያችሁትን ሁሉ በሕሊናችሁ ሳሉት። (ስዕል መሳል አልችልበትም እንዳትሉኝ ብቻ) ይሁንና ምድሪቱ ገነት ሆና ሕዝቡ ሲዖል እንዲኖር ከተፈረደበት እድገት ሳይሆን ቅዠት ነው! ላም አለኝ በሰማይ ወተትዋን የማላይ አስመሰለው እኮ። ሕዝቡ የላሟን ወተት ነው የሚፈልገው። አንዳንዴ ከራሴ ጋ አጠር ያለች ስብሰባ አድርጌ ስለ አዲስ አበባችን መሽቀርቀር ሳስብ የቁንጅና ውድድር ያለባት ይመስለኛል። ሕዝቡ ግን “ወዛም ሆደ ባዶ” እንዳይሆን ያሰጋኛልአዲስ አበባ በዓለም ከሚጎበኙ አሥር ከተሞች አንዷ ሆና ሕዝቡን ግን የኑሮ ውድነት የሚጎበኘው ከሆነ “ሕገ ወጥ ሕግ አስከባሪ” የነገሰበት ጊዜ ነው ማለት ነው። አንድም ማንም ባልደፈራት በተከበረችው ሀገር ባልና ሚስትን አዋርዶ ዕርቃናቸውን እንዲሄዱ ማድረግ ሕገ ወጥ ሕግ አስከባሪነት ነው።  ቤት እየሰሩ ከቤት ማፈናቀል ደግሞ ትልቅ ሕገ ወጥ ሕግ አስከባሪነት ነው።

ሐሰቱ ሲበዛ እውነት ሆነ ዋዛ አሉ እቴሜቴ። እውን ሀገራችን ኢትዮጵያ አድጋለች? ሽንጣቸውን ይዘው አዎ አድገናል” የሚሉ ይኖራሉ። ሌሎቹም “ልክ ነው ወደታች አድገናል” የሚሉም አይጠፉም። የነዋሪው ህይወት ሲያድግና ሲለወጥ ነው አፋችንን ሞልተን አድገናል የምንለው። ልጅ እያለሁ ሁል ጊዜ ማታ ማታ ከሸምሱ ሱቅ በ50 ሣንቲም ዳቦ ስገዛ ጦም ከማደር ዳቦ መቀርቀር” ይለኝ ነበር። ዛሬስ ከሸምሱ ሱቅ የሚገዛው ዳቦ ስንት ገብቶ ይሆን? መቼስ ተከፈት ያለው ጉሮሮ ጦም አያድርም እንጂ ሕዝቡ ኑሮ ከበደኝ” ሲል መንግሥት ደግሞ “ሀገሪቱ አድጋለች እኮ” ይላል። የተጠየቀው ሌላ የተመለሰው ሌላ። በቅሎ አባትህ ማነው ቢሉት እናቴ ፈረስ ነች አለ አሉ”



እትዬ ጣይቱ አንድ ሙድ አላቸው። ድምፁን አጥፍተው ETV ከፍተው ያዩና ESAT እየሰሙ ከቆዩ በኋላ እህህ እያሉ ነገር መብላት ይጀምራሉ። አፋቸውን እንደ ጉድ ያሽሟጥጡና  “ግራ እኮ ገባን ለነገሩ ሕዝቡ ግራ ቢገባው ቀኝ ቢገባው ማን ይጨንቀዋል” ይላሉ። እኛም እንደ እትዬ ጣይቱ በተመሳሳይ ሰአት ESAT እየሰማን ETV እያየን እንኖራለን!

ይህን ስንል “መጥፎ ወሬ ይበራል መልካሙ ይተኛል” የሚሉ አይጠፉም። ይህን ስንል ግን ዐይናችንን ጨፍነን ሁሉ ነገር ከንቱ እያልን አይደለም። ወንዶች ጎንበስ ብለን ሴቶች እልል ብለው ደግ ደጉን አመስግነናል። የእናት ሀገሩን እድገት የሚጠላ ከቶ ማንም የለም። የሕዝብ እንባ ጎርፍ ነውና ደግ ደጉን ስሩ፣ ሕዝቡንም አክብሩ ለማለት ያህል ነው። መንግሥት ህዝቡን ጥሎ ብቻውን የሚሮጥ ይመስላል። ብቻውን የሚሮጥ አይቀድምም” አሉ እትዬ ጣይቱ።

በስተመጨረሻ እትዬ ጣይቱ የገጠሙትን ግጥም ልጋብዛችሁና ልሰናበት

ኑሮ ንሮ”

ሐያት በቁንጅና ሐይሌ በእግሮቹ
ቴዎድሮስ በጀግንነት ቴዲ በግጥሞቹ
ሁሉም ቢወደዱ እንደየስራቸው
ስለታመነ ነው እንደሚገባቸው
እኔ ግን ያልገባኝ ስኖር በዚህች ሀገር
ኑሮ የተወደደው ምን አድርጎ ነበር?

========================================================================


የልጅ ዮናስ ብሎግ አባል ይሁኑ!!