Wednesday 21 August 2013

የቅዱሳን በረከት ይህ ነው!





ነቢዮ ኤልሳዕ ከመመረጡ በፊት 12 ጥማድ በሬዎችን የሚያጠምድ ሀብታም ገበሬ ነበር። ብዙ አገልጋዮችም ነበሩት። የኤልያስ መጎናጸፊያ በኤልሳዕ ላይ አረፈች። እነሆ ኤልሳዕ ለአገልግሎት ተጠራ፤ ሀብት ንብረቱን ጥሎ እናት አባቱን ተሰናብቶ የኤልያስ አገልጋይ ሆነ።

እነሆ ኤልያስ ለኤልሳዕ ከአንተ ተለይቼ ወደ ቤቴል እሄዳለሁ ጠብቀኝ አለው። ኤልሳዕ ግንበህያው ነፍስህ እምላለው አልለይህም አለው። ያዕቆብ ካልባረከኝ አልለቅህም እንዳለ ኤልሳዕም አልለይህም አለ። እግዚአብሔር እያለ ኤልያስ ምን ያደርግለታል? ኢየሱስ ክርስቶስ እያለ ኤልያስ ምን ታደርግልኛለህ አላለም። በረከትን እንደሚያገኝ ያውቃልና!

ኤልያስም ከአንተ ከመለየቴ በፊት ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ? አለው። ወደ እግዚአብሔር ለምን /ልለምንልህ እንዴት አላለውም? እግዚአብሔር ሲያደርግ ኤልያስ አደረገ ተባለ። አንዳንዶች ግን ጻድቁ እንዲህ አደረገልኝ ስንል ይቆጣሉ።

እነሆ ኤልሳዕ የኤልያስን መጎናጸፊያ ይዞ አምላከ ኤልያስ ወዴት ነው! አለና ዮርዳኖስን ከፈለበት። እኛም እንዲሁ አምላከ ጊዮርጊስ ወዴት ነህ እንላለን። የቅዱሳኑ አምላክ የእኛም ፈጣሪ ድንቅን ስራ ይሰራልና!

ከአንተ ከመለየቴ በፊት ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ? ኤልሳዕም መንፈስህ ሁለት እጥፍ ሆኖ ይደርብኝ አለው። ኤልያስም እነሆ በሠረገላ ስነጠቅ እኔን ብቻ እይ ያን ጊዜ መንፈሴ እጥፍ ሆኖ ያድርብሃል አለው። አንዳንዶች ኢየሱስ እንጂ ኤልያስን ብቻ ለምን እናያለን ብለው ይቆጡን ነበር። እነሆ እንዲህም ሆነ። የኤልያስ መንፈስ እጥፍ ሆኖ በኤልሳዕ ላይ አደረ! ጠቢቡ ሰለሞን በረከት በጻድቅ ራስ ላይ ነው እንዲል ይህ ነው የቅዱሳን በረከት! ይህ ነው ከቅዱሳን በረከት መቀበል!

የኤልያስ መንፈስ እጥፍ ሆኖ በኤልሳዕ ላይ ማደሩን ያዩ 50 ነቢያትም ለኤልሳዕ ሰገዱ!

ይህ ነው የቅዱሳን ክብር! ይህ ነው የአክብሮት ስግደት!

ኤልያስ አንድ ሙት አስነሳ፤ ኤልሳዕ 2 ሙት አስነሳ
ኤልያስ አንድ ጊዜ ዮርዳኖስን ከፈለ ፤ ኤልሳዕ ሁለት ጊዜ ከፈለ
ኤልያስ በህይወቱ ሙት አስነሳ፤ ኤልሳዕ ከሞተ በኋላ ሙት አስነሳ!
ይህ ነው የቅዱሳን በረከት! ይህ ነው ከቅዱሳን በረከት መቀበል!

http://yonas-zekarias.blogspot.com/


Unlike ·  ·