Saturday 16 June 2012

የሰማዩ ቤተ መንግሥት!

በሕንድ የማላባር ግዛት ይኖር የነበረ ንጉሥ ጎንዶፓረስ በኢየሩሳሌም ይኖር ስለነበረው የሰለሞን ቤተ መንግሥት ዝና እየሰማ እርሱም በግዛቱ ያን ዓይነት ቤተ መንግሥት መሥስራት ይፈልግ ነበርና ነጋዴዎች በየሀገሩ ሲጓዙ የታወቀ ግንበኛ እንዲያመጡለት አዟቸው ነበር። ነጋዴዎቹም በሀገሩ ሕንፃ በማነፅ ኑሮውን ይገፋ የነበረውን ሐዋርያው ቶማስን ለንጉሡ አመጡለት። ንጉሡ ቶማስን ከከተማው አጠገብ ወደሚገኘው ጫካ ወሰደውና ቤተ መንግሥቱ የሚሰራበትን ሰፊ መሬት አሳየው።     


ከጥቂት ጊዜ በኋላ ንጉሥ ጎንዶፓረስ ለቤተ መንግሥቱ ማሰሪያ ይኾን ዘንድ ለሠራተኛ መቅጠሪያ ፣ ለድንጋይና ዕብነ በረድ ፣ ለብርና ለወርቅ ፣ ለብረትና እንጨት መግዣ” እያለ ያለ የሌለውን ገንዘብ ለቶማስ ይልክለት ጀመር። ቅ/ቶማስ ገንዘቡን ሲያገኝ የተጓዘው ወደ ገብያ ወይም ሠራተኛ ፍለጋ ሳይኾን ወደ ድኾች መንደር ነው። በዚያም ለተራቡ ምግብ ለታረዙ ልብስ በየቦታው ለወደቁ መጠለያ እየገዛ ማደል ጀመረ። 

ንጉሥ ጎንዶፓረስ አይደርስ የለ ደርሶ ባየኹት” እያለ ቤተመንግሥቱን ለማየት ጉዞውን በጉጉት ጀመረ። ቤተ መንግሥቱ ይሰራበታል በተባለበት ቦታ ላይ ሲደርስ ንጉሡ ክው አለ። ጫካው አልተነካም። ሰማይ ጠቀስ ፎቅ ቀርቶ የወደቀ ድንጋይ የለም። ንጉሡ የልቡ ምት ጨመረ። በዚያ በኩል የሚያልፍ አንድ መንገደኛ ጠራና ቶማስ የት አለ”? ብሎ አፈጠጠበት። 

ቶማስ የተራቡትን እያበላ ፣ የተጠሙትን እያጠጣ ፣ የታረዙትን እያለበሰ በድኾች መንደር ይገኛል ብሎ መንገደኛው መለሰ።

“እርሱ ባልከፋ ታዲያ የሰራልኝ ቤተ መንግሥት የት አለ”? ንጉሡ መንገደኛው ላይ እንዳፈጠጠ ጠየቀው።

“በድንጋይ የተሰራ ቤተ መንግሥት ላያዩ ይችላሉ ጌታዬ፤ ነገር ግን በሕዝቦ ገጽታ ላይ ደስታና ፈገግታ ማንበብ ይችላሉ አለው መንገደኛው።

በዚህ ጊዜ ንጉሡ ያ ሁሉ ገንዘቡ እንደባከነበት መጠርጠር ጀመረ። ወዲያው ወታደሮቹ ቶማስን ፍለጋ አካባቢውን አጥለቀለቁት።

ቅ/ቶማስ ተይዞ እንደመጣ “ቤተ መንግሥቴን ለምን አልሰራህልኝም”? አለው ንጉሡ።

“ሠርቻለሁ ጌታዬ” ቶማስ መለሰ።

“የታለ? ጫካው እንኳን መች ተነሣ?”

“በእርግጥ ምድር ላይ የድንጋይ ቤተ መንግሥት ላያዩ ይችላሉ፤ እኔ ግን በሰማይ ላይ ቤተ መንግሥት ሠርቼልዎታለሁ” አለው ቶማስ ለንጉሡ። ይህን ጊዜ ንጉሡ ተቆጣ! ቶማስን እጅ እግሩን እየቆራረጡ እንዲያሰቃዩት አዝዞ ወደ እስር ቤት አወረደው።


በዚያች ለሊት የንጉሡ ወንድም የሆነው ልዑል ጋድ በድንገተኛ በሽታ መጣደፍ ጀመረ። ሊነጋጋ ሲልም ነፍሱ ወጣች። የጋድ ነፍስ በመላእክት ታጅባ ወደ ሰማያት ወጣች። ካጀቧት  ቅዱሳን መላዕክት አንዱ ብዙ አብያተ መንግሥታትን እያሳያት “ትኖሪበት ዘንድ ደስ ያለሽን ምረጪ” አላት። የጋድ ነፍስም ውብ የኾነውን ቤተ መንግሥት መረጠች። “ይህ ቤተ መንግሥት የአንቺ አይደለም ቶማስ ለንጉሥ ጎንዶፓረስ የሠራለት ሰማያዊ ቤተ መንግሥት ነው” አላት። በዚህች ሰአት የልዑል ጋድ ነፍስ ከሥጋው ጋር ተዋሐደች። ጋድ ሊቀብሩት በተሰበሰቡት ሰዎች መካከል ከእንቅልፉ እንደሚነቃ ሰው ተንቀሳቀሰ። ከዚያም አፈፍ ብሎ ተነሣ። ልዑል ጋድ በዚያች ቅጽበት የተመለከተውን ለንጉሥ ጎንዶፓረስና ለተሰበሰቡት ሁሉ ነገራቸው።

ንጉሡ ይህን ሲሰማ በቶማስ ላይ በሰራው ግፍ ሁሉ አዘነ። ተፀፀተም። ያ-ያሰበው ቤተ መንግሥት መሰራቱን ሲሰማ ቶማስን ከእስር ቤት አወጣው። እርሱና ቤተሰቡም ክርስቶስን አምነው ተጠመቁ። ንጉሥ ጎንዶፓረስ “ሌላም ቤተመንግሥት ስራልኝ” እያለ ያለውን ሁሉ ገንዘብ ለቶማስ ይሰጠው ጀመር።  

************
“የለንደኑ ንጉሥ ጎንዶፓረስ ማን ይሆን?

አሁን ለቤተክርስቲያናችን የሚያስፈልገን ንጉሥ ጎንዶፓረስን የመሰለ ልብ ነው። አሁን የለንደን ቅ/ሥላሴ ቤተክርስቲያን ብዙ ንጉሥ ጎንዶፓረስን የመሰሉ ሰዎች ያስፈልጋታል። የንጉሡን ያክል ሀብት ሳይሆን የንጉሡን ያክል ልብ ያስፈልገናልና።

      በለንደን ቅ/ሥላሴ በተደረገው ጉባኤ ዲ/ምንዳዬ ቃል ገባ። ለዚህች ታዳጊ ቤተክርስቲያን አንድ የመዝሙር ሲዲ ሰርቼ ገቢው ለቤተክርስቲያኑ ማሰሪያ ይኹን” አለ። እንዳለውም በቅርቡ ለንደን ገብቷል። የመዝሙር ካሴቱንም በቅርቡ ያስመርቃል።

       የለንደን ቅ/ሥላሴ ቤተክርስቲያን የተመሰረተበትን 6ኛ ዓመት በቅርቡ አክብሮ ነበር። ይኽ በአጭር ጊዜ በፍጥነት ያደገ ቤተክርስቲያን ነው። ቤተክርስቲያኑ በየዓመቱ በሚያደርገው ጉባኤ ብዙ የባዘኑ ነፋሳት ረፍት አግኝተዋል ቢባል ማጋነን አይኾንም። ይኽ ቤተክርስቲያን የዛሬ 6 ዓመት በአባታችን በአቡነ ሙሴ ሲመሰረት የመጀመሪያ የመባዕ ገቢው 20 ፓውንድ ነበር። አኹን ግን ምዕመናኑ በቁጥር በዝተዋል። የአገልግሎቱ አድማስም እየጨመረ ነው። 6 አመት ተንስኡ ለፀሎት ያለው ወንድማችን በቅርቡ ሰላም ለኩልክሙ ብሎ ሥልጣነ ክህነትን ተቀብሎ ቀስስ ቴዴ ተብሏል!
  
ይኽን ቤተክርስቲያን የምንገለገለው በክራይ ነውና ካሕናቱ ለቅዳሴ መሯሯጥ ግድ ይላቸዋል። ቦታውን በተሰጠችን አጭር ጊዜ መልቀቅ አለብንና ረጋ ብሎ መቀደስ አይታሰብም። ሰፋ ያለ ትምህርት መስጠት አይታለምም። መዘምራን 3 መዝሙሮችን ለመዘመር ቢያጠኑም ሰአት የለምና መዝሙራችን በአጭሩ ትቀራለች። ሕጻናቱን ማስተማር ማዘመር ወዘተ ተረፈዎች በጊዜ እጥረት አናስባቸውም። ከብዙ በጥቂቱ ከረጅሙ በአጭሩ የዘወትር አገልግሎታችን ይህ ነው።

 የራሳችንን ሕንጻ ቤተክርስቲያን ለምን አንሰራም ተባለ። “አንድ ሺህ ለአንድ የሚል ንድፍ ተነደፈ። እያንዳንዳችን አንድ ሺህ ብር አዋጥተን አንዲት ብሎኬት ብንገዛ ሙሉው ቤተክርስቲያን ይሰራል ተባለ።

ቤተክርስቲያናችን ንጉሥ ጎንዶፓረስ የመሰለ ብዙ ሰዎችን ትፈልጋለች ብለን ነበር፤ ይህ ንጉስ ባለው ፀጋ ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን ሰርቷል። እኛም እንደ አቅማችን ትንሹ ንጉሥ ጎንዶፓረስ መኾን ይገባናል። ልብ በሉ! የዚህ ስራ መሰረቱ ልብ እንጂ ገንዘብ አይደለምና ልብ ሲሰጥ እጅም ይሰጣል።

አንድ ብሎኬት ብቻዋን ብትቀመጥ ለምንም አትጠቅምምና ብቸኝነት ይሰማታል። አንዱ የራሱን ብሎኬት ሲያስቀምጥ ሌላውም በዚያ ላይ ሲደርብ ቀጣዩ ሲቀጥል ቀስ እያለ እስከ ጣራው ይደርሳል። አራቱም መአዘን ይገጣጠሙና የፍቅር ቤት ይሰራል። በሕብረትና በፍቅር ስንሰራው ፍቅር ያለበት ቤት ትኾናለች። ብዙዎች ሕንጻ ኖሯቸው ፍቅርና አንድነት የሌላቸው አሉና ይኽን በሕብረት መስራቱ ዋጋ አለው። ይኽ ሚሥጢር እንደምን ያለ ሚሥጢር ነው! ይኽ ሕብረት እንደምን ያለ ሕብረት ነው! ወርቃማው የኢትዮጲያዊያን አባባል እንዲኽ ይላል። “ግድግዳ እርስ በእርሱ ካልተደጋገፈ አይቆምምይኽ እውነት ነው። ለመቆም መደጋገፍ ያስፈልጋልና። ቀብሩን ለቀባሪ ሳይሆን ለሟች አረዱ እንዲል ይህችን ታላቅ ስራ ሳይደጋገፉ መስራት አይቻልም።


ይህች አንዷ ብሎኬት የፍቅር ምሳሌ ናት!

ይህች አንዷ ብሎኬት የሕብረት ምሳሌ ናት!

ይህች አንዷ ብሎኬት ታላቅ ዋጋ አላት!

“ግንበኛ የናቀው ድንጋይ የማዕዘን ራስ ይኾናል ተብሎ ተፅፋልና ይህች አንዷ ብሎኬት የቤተክርስቲያን ራስ የኾነው የጌታ ምሳሌ ናት!