Saturday 23 June 2012

“ይድረስ ለኢትዮጲያ ሀገሬ // የዛሬ አበባዎች የነገ ፍሬዎች”




       
      “ልጅ ለእናትዋ ምጥ አስተማረቻት” ቢሉ ማን ያምናል? ሕጻናትን ሳይንከባከቡ ፍሬውን መጠበቅም እንዲሁ ነው። “አለሽ መስሎሻል ተበልጠሽ አልቀሻል” አለች እምዬ ኢትዮጲያ። ፊት ለፊቴ አንድ ትንሽ ብላቴና ኳሷን እንደ ጉድ እያንከባለለ ትንፋሹ ቁርጥ እስክትል ድረስ እንደ ጉድ ይሮጥ ነበር። “የዛሬ አበባዎች የነገ ፍሬዎች አሉ አባባ ተስፋዬ! የዛሬ አበባዎች ናቸው ለነገ ፍሬ የሚሆኑት” አለኝ ሕሊናዬ። ዛሬ ሕጻናት አበቦችን በስስት ሳንንከባከብ ፣ የተስፋ ውኃ ሳናጠጣ ፣ በስጦታ ሳንኮተኩት፣ ፀሐይ ጊዜያችንን ሳንሰጣቸው ምን ዓይነት ፍሬ ይሆን የምንጠብቀው? አለኝ ሕሊናዬ ደገመና። “አሁን ገና በራልኝ አለች እብድ ቤቷን አቃጥላ!”


   ከልጅነት ጓደኞቼ ጋር ኳስ ለመጫወት አንድ የሚገርም ኮድ አለን። በለሊት ቀድሞ የነቃ ለዘመናት ዝናብና ፀሐይ ያደከመው ቆርቆሮ ላይ ድንጋይ ይወረውራል። ያኔ ሆዳቸውን የባሳቸው አያሌ የሰፈራችን ቆርቆሮዎች እዬዬ ብለው ብሶታቸውን ያሰማሉ። ድንጋይ ውርወራው የኛ የብልጦቹ “ኮድ” ነው። ለቆርቆሮዎቹ ያዘነ ደግሞ ድንጋይ መወርወር ትቶ ያፏጫል። ልክ ያቺ ድንጋይ ቋ ቋ ቋ ስትል አልያም ፉጨቱ ሲሰማ ኮድ ነውና ሁላችንም ብንን እንላለን።         

     እንደዚህ የኳስ ፍቅር ያለን ልጆች በደንብ ብንያዝ ኖሮ ዛሬ ከመካከላችን አንዱ ለሀገር የሚበቃ ኮኮብ በሆነ ነበር። “ብረትን መቀጥቀጥ እንደጋለ ነው” ይላል የአንጥረኞች መፈክር። በጋለው የልጅነት ፍላጎታችን ትንሽ ድጋፍ ቢገኝ የት በተደረሰ ነበር። ባለሁበት በለንደን ከተማ ለሕጻናቱ ያላቸው የጋለ ድጋፍ ይደንቀኛል። ገና በማህፀን እያሉ ለአንድ ክለብ ይፈርማሉ።  እስከ ሰባት ዓመት ሲሞላቸው አሰልጣኝ ተቀጥሮ እንደ ጉድ ውድድር ይደረጋል። እንደ ጉድ ሕዝቡ ይደግፋቸዋል። እንደ ጉድ ሀገራቸውን ያስጠራሉ። እንደ ጉድ ኮኮቦች ይሆኑና እንደ ጉድ ያበራሉ!

         “ልጅህንም አባትህንም ስታጎርስ ለአንዱ ታበድራለህ ለሌላው ትከፍላለህ” እንዲሉ እስኪ ለልጆቻችን ሞራል እናበድራቸው። ለሕጻናቱ ትኩረት መስጠት በኛ ሀገር እንደ ሕልም ነው የሚታየው። የኛ ነገር “ሞት ሲደርስ ቄስ ጦር ሲደርስ ፈረስ” ሆነብንኮ ሰዎች! የልጆች አስተዳደግ ፣ ፍላጎት፣ ዓላማ ወዘተ ተረፈዎች ለኛ ትርፍ ነገር ናቸው። በመንፈሳዊም ሆነ በዓለማዊ ሕይወት አንዳች ድጋፍ አናደርግላቸውም። “በአባቶችሽ ፋንታ ልጆች ተወለዱልሽ” የሚለው ቃል ተረስቶ “በአባቶችሽ ፋንታ ልጅ የሚወልድልሽ ጠፋ” እንዳይሆንብን ያሰጋል። የሰለጠነው ዓለም ግን ልቡና ዓይኑ በታዳጊዎች ላይ ነው ያለው። ሩኒ ፣  ጄራርድ ፣ መሲ እና ሮናልዶ ከሰማይ የወረዱ አይደሉም። እነዚህ ፍሬዎች ሁሉ በዓላማቸው ላይ ከጎናቸው በቆሙ ወላጆችና በሕብረተሰቡ ታቅፈው ያፈሩ የወይን አትክልቶች ናቸው። ይህ ሁሉ እኛ ቤት ቢዘገይም እስከ መጨረሻው ግን አይቀርም። “ሞት ቢዘገይ የቀረ ይመስላል” አለች ሴትዮዋ። እስኪ ሁላችንም ሕጻናቱን በፍላጎታቸው እንደግፋቸው። ሴቷ ስትሮጥ ዘላል ወንዱ ኳስ ሲያንከባልል ዱርዬ ከማለት እስኪ የአስተሳሰብ ለውጥ እናምጣና እናበረታታቸው። ያኔማ በርቱ ብለን ብናሞግሳቸው አልፎም ስጦታ ብንሰጣቸው በሞራልና በራስ መተማመን ያድጋሉ። በሞራልና በድፍረት ያደገችው ሴቷ ብትሮጥ መሰረት ደፋር ትሆናለች!


      “ቁንጫ መሔድ ሳትማር መዝለል ተምራለች” እንዲሉ ኳስ ማንከባለል ሳናስተምር በኃይለኛው ለግቶ ግሩም ግብ እንዲያገባ እንጮኻለን። ሌላው ቀርቶ ደጋውን ሲወጡ ቆላውን ሲወርዱ ሲሮጡ ሲደክሙ ላባችሁን መተኪያ ብለን ውኃ እንኳን ሳንገዛላቸው ማራቶኑን ፣ 10ሺውን ፣ 5ሺውን እንዴት በኬንያና በቻይና ተበላን ብለን እዬዬ እያልን እንጮኻለን። “ባትዋጋ እንኳን ተሰለፍ” ይላል የወታደሮች መፈክር። እኛ ባንዋጋ እንኳን በሞራል እንሰለፍ እንጂ ጎበዝ!

አልሰማችሁም እንዴ? አልሰማን ግባ በለው አሉ። (ሉሲዎቹ) የኢትዮጲያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ለ8ኛው የአፍሪካ ዋንጫ አለፉ! ሴቶቻችን ታንዛኒያ ዳሬሰላም ገሥግሠው ውድ ልጃችን “ብሩክታይት” ጎሉን እንደ ጉድ አግብታ በድል ተመልሰዋል!! ይህ ውጤት ከየት መጣ? ልብ በሉ አንዳች የሴቶች ውድድር በሌለበት ሀገር ነው ይህን ውጤት ያመጡት። ዋልያዎቹ (የኢትዮጲያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን) ቤኒን ገሥግሰው “አዳነ ግርማ” ጎሉን አግብቶ 1 ለ 1 በመውጣት ተጋጣሚውን ጥሎ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፏል። ከ15 ቀን በኋላ ዕጣ ይወጣና ከአንድ ቡድን ጋር ተመድበን በደርሶ መልስ ካሸነፍን ከ35 ዓመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ እናልፋለን ማለት ነው! ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያም ምድባችንን እየመራን ነው! ይህ ግሩም ድንቅ ውጤት ነው። ሌሎቹ በአውሮፓ ፕሪሚየር ሊግ የሚጫወቱ ሲሆን የኛዎቹ ግን ሙሉ በሙሉ በሀገርቤት የሚጫወቱ ናቸውና።
ቅ/ጴጥሮስ ካስተማረ በኋላ ሕዝቡ “ምን እናድርግ?” አሉ። እስኪ እኛም “ምን እናድርግ?” እንበል። ለጀግኖቹ ደማቅ አቀባበል ማድረግ ፣ የወንዶቹንም የሴቶቹንም ቡድን በአንድላይ አድርጎ ልዩ ብሔራዊ ቀን በማወጅ ማበረታታት ፣ መሸለም ፣ ማድነቅ ፣ ማወደስ ብሎም ቀጣዩ ዋና ስራ ምን መሆን እንዳለበት መወያየት ከኛ ይጠበቃል። የሴት ብሔራዊ ቡድናችን የተከበሩት አሰልጣኝ 15 ሺህ ፣ ምክትል አሰልጣኞች 10 ሺህ ተጫዎቾቹ ደግሞ እያንዳንዳቸው 15 ሺህ ብር ተሸልመዋል።

“እርሻው ሲያምር ዳቦው ያምር” አለች ዳቦ ጋጋሪዋ እውነቷን እኮ ነው። ልጆችን ስንኮተኩታቸው የሚገመጡ ዳቦ ይሆናሉ። “የልጅ ነገር ሁለት ፍሬ አንዱ ብስል አንዱ ጥሬ” እንዲል እኛም ታዳጊዎችን ብንኮተኩት ያልበሰለው በስሎ የበሰለው አምሮ ቢታይ የሚያጓጓ ቢበላ የሚያረካ ፍሬ ይሆናሉ። የዛሬ አበባዎቹ የነገን ፍሬ ያፈራሉ! “የዛሬ አበባዎች የነገ ፍሬዎች አሉ አባባ ተስፋዬ” ይህ ሁሉንም ሕብረተሰብ ይመለከታል። እስኪ ቃል እንግባ። እስኪ ሁላችንም በቤታችን ያሉትን ሕጻናት ቢያንስ በሳምንት አንድ ቀን ቀርበን ለአበባዎቹ የሚያስፈልጉትን ሁሉ እናድርግላቸው! እስኪ በአካባቢያችን ያሉትን ሕጻናት ኮትኩተን ኢትዮጲያን የሚያኮሩ ከዋክብት እናድርጋቸው! “ኮከብ እም ኮከብ ይኄይል በክብሩ” እንዲል አንዱ ኮከብ ከሌላው ይበልጣንና እስኪ ለጎበዞቹ ስጦታ እየሰጠን እናበርታቸው። እነሱን አይተው ብዙ ከዋክብት ይወጣሉና።
እዚህ ጋር እውነታኛ ታሪኬን ላውጋችሁ። ኳስ በጣም ስለምወድ በየሳምንቱ ቅዳሜ በጠዋት ለመነሳት እንቅልፍ አይወስደኝም ነበር። “አምራለሁ ብላ ተኩላ ዓይኗን አጠፋችው ቸኩላ” እንዲል ለሊቱ ይነጋልኝ ዘንድ እቸኩል ነበር። ታዲያ አንድ ቀን ሳፈጥ አመሸሁና በለሊት ተነሳሁ። ብጠብቅ ኮዱ የለም። ድንጋይ አይወረወርም። ብጠብቅ ከወፍ በስተቀር የሚያፏጭ የለም። ጥለውኝ ሔዱ ማለት ነው ብዬ ተናደድኩና ከምሽቱ 9 ሰአት ላይ በሩን ከፍቼ ወደ ኳስ ሜዳ ገሠገሥኩ። ሜዳ ላይ ደረስኩ። አንዳች ፍጥረት የለም። ደነገጥኩ። በልቤ “ሹሩባ ልትሰራ ሔዳ ጸጉሯን ተላጭታ መጣች” የሚለው ተረት ተፈጸመብኝ ማለት ነው እያልኩኝ በመጣሁበት እግሬ እየሮጥኩ ቤቴ ተመልሼ አንኳኳሁ። የሚከፍትልኝ ጠፋ። ከወንድምና እህቶቼ ጋር በተለየ ክፍል ነው የምናድረውና አባ ወራና እማ ወራ ይህን ኹሉ ጉድ አያውቁም። በሩን ብደበድብ ሁሉም እያንኮራፉ ይገለባበጣሉ እንጂ የሚከፍትልኝ ጠፋ። ተስፋ ቆርጬ በሩን ደገፍ ብዬ እንደቆመኩ እንቅልፍ ሸለብ አደረገኝ። ወዲያው ግን “ሁለተኛ ጥፋት ቆሞ ማንቀላፋት” ብዬ መላ መፈላለግ ጀመርኩ። ዞር ስል አንደኛው ቤት ወለል ብሎልኛል። ቁልፉ የት እንዳለ ስለማውቅ ከፈትኩና ገባሁ። ማዕድ ቤት ነበር። ዶሮዎቹ እንተኛበት እንጂ እያሉ በልሳነ አእዋፍ እንደ ጉድ ጮሁብኝ። ምን ላድርግ ብዬ ጸምሩን ዘረጋግቼ ፣ ድንጋዩን ተንተርሼ ፣ ዶሮዎቹን ታቅፌ ማንኮራፋት ጀመርኩ። “ልፋ ያለው በሕልሙ ሸክም ይሸከማል” እንዲሉ የዛች ለሊት ሕልሜ ለሕልም ፈቺውም ሕልም ሆኖበት ነበር። ሕልሜን ብነግራችሁ ደስ ባለኝ ነበር። ሁሉን ቢናገሩ ሆድ ባዶ ይቀራል እንዲሉ ይለፈኝ። ያቺ ለሊት ግን እንደ ጉድ  አስተምራኛለች። “ሌሊት የምክር እናት” ትል ነበር እናቴ።

ወቅቱ የዓለም ዋንጫ የሚካሔድበት ጊዜ ነበር። ያኔ በቴሌቭዥን ያየነውን ኮከብ እኛም ለመሆን ወዲያው ኳስ ለማንከባለል ወንዝ እንወርዳለን። እናንተዬዋ አይጣል ነውኮ! አሁን ኳስ ለመጫወት ወንዝ መውረድ ምን ይሉታል? እንስራዋን ጥላ ወንዝ ወረደች አሉ! በሰፈራችን አንዳች የመጫወቻ ሜዳ የለምና ወንዝ መውረድ አለብን። ሰፈር ብንጫወት ሰምተነው የማናውቀው የእርግማን ዓይነት ይወርድብናልና ሜዳ ፍለጋ ወንዝ መሻገር አለብን። ወንዙ ደግሞ ድልድይ የለውም። ረዥሙ ወንዝ በረዥም እንጨቶች ድልድይ ተሰርቶላቸዋል። እኛም ያቺን ኳስ ክብልል ለማድረግ ይህን ወንዝ ማቋረጥ ግድ ይለናል። ያ- ለዘመናት ጡረታ ልውጣ እያለ በልሳነ ዕጽዋት እዬዬ ያለው እንጨት ሲጢጢጢጢ ቋቋቋቋቋ ሲል የልጅነት ልባችንም አብሮ ፈራ ተባ ይላል። ቀስ ብለን ማገሩን ይዘን ተራ በተራ ለማለፍ ስንሞክር ከፍ ዝቅ እያለ ኪሏችንን ይቀንሰዋል። አንድ ቀን ያቺ እንጨት ብትቀነጠስ ስንት ሕጻናት ይሆኑ የሚያልቁት?

የሀገር ያለህ ፣ የሀገር ያለህ ፣ የሀገር ያለህ! ይድረስ ለኢትዮጲያ ሀገሬ። ይህ ሁሉንም ሕብረተሰብ ይመለከታል!!
ጆን ደብልዩ ሎረንስ የተባለ ፀሐፊ በመጽሐፉ እንዲህ ብሏል፡-
ልጅ እየተወቀሰ ካደገ ማውገዝን ይማራል፡፡
ልጅ በጥላቻ አካባቢ ካደገ መደባደብን ይማራል፡፡
ልጅ እየተፌዘበት ካደገ ዓይነ አፋርነትን ይማራል፡፡
ልጅ በሐፍረት ካደገ ጥፋተኝነትን ይማራል፡፡
ልጅ በመቻቻል ካደገ ትዕግሥተኝነትን ይማራል፡፡
ልጅ በመበረታታት ካደገ በራስ መተማመንን ይማራል፡፡
ልጅ በመሞገስ ካደገ ማድነቅን ይማራል፡፡
ልጅ በአግባብ ካደገ ፍትሕን ይማራል፡፡
ልጅ ዋስትና ባለው ኑሮ ካደገ ሰውን ማመን ይማራል፡፡
ልጅ በተቀባይነትና በወዳጅነት ካደገ በአጠቃላይ ዓለም ፍቅርን ማግኘት ይማራል፡፡

ከተበላሸ ወተት ጥሩ እርጎ አይገኝምና ሕፃናትን ሀገር ወዳድ አድርገን እናሳድጋቸው!

****-//-****

“የዛሬ አበባዎች የነገ ፍሬዎች አሉ አባባ ተስፋዬ” ይህ ሁሉንም ሕብረተሰብ ይመለከታል!! እስኪ አስተያየታችሁን በነጻ ለግሱ።
እስኪ በአካባቢያችን ያሉትን ሕጻናት ኮትኩተን ኢትዮጲያን የሚያኮሩ ከዋክብት እናድርጋቸው!! እስኪ ሕጻናቱን ለመኮትኮት በተከበረችው በሀገራችን በኢትዮጲያ ሥም ቃል እንግባ!!

Tuesday 19 June 2012

"እንኳን ለቅ/ሚካኤል ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ"


ዘና ብላችሁ ተቀመጡና አንድ አሪፍ ታሪክ ልንገራችኹ!

የተከበሩት አባት እንዲህ ብለው ጠየቁ፤

መላእክት እንደ ሰው የሚታጠፍ እና የሚዘረጋ እግረ ሥጋ የላቸውም፤ ታዲያ መላኩ ቅ/ገብርኤል እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው” ገብርኤል ነኝ ሲል ምን ማለቱ ነው?? ሉቃስ [1: 19]


ይህች ጥያቄ ያለንበትን ክፍል ዝም አስባለች። ኹላችንም በልባችን ለምን ይኾን? እያልን መጠየቅ ጀመርን።
  
የተከበሩት አባት መልሱን እንዲኽ እያሉ አስረዱን፤ በእርግጥ ግሩም ጥያቄ ነው፤ መላእክት መንፈስ ናቸውና እግረ ሥጋ የላቸውም፤ አይቀመጡም አይነሱም አይቆሙምም! ሊቀ መላእክት ቅ/ገብርኤል እኔ በእግዚአብሔር ፊት “የምቆመው” ገብርኤል ነኝ ማለቱ ምህረትን ጠያቂ አማላጅ ነኝ ሲል ነው አሉን።

በክፍላችን ውስጥ የነበሩ የሌላ እምነት ተከታዮች ነበሩና  አሁን ማን ይሙት ይኼ ከአማላጅነት ጋር በምን ይገናኛል?” አሉ በልባቸው። ይኽን ሐሳባቸውን የተከበሩት አባት ስለገባቸው ፍግግ አሉ። እንዴት ማለት ጥሩ ነውና እንዴት? እንበል አሉን። እንዴት አልን በልባችን። እንዲህ ብለው ቀጠሉ፦



ይህን እንድንረዳ ልበ አምላክ ዳዊት የዘመረውን አብረን እንይ፤  የተመረጠው ሙሴ በእግዚአብሔር ፊት ባይቆም” ኖሮ ሕዝበ እሥራኤላዊያን በቅጽበት በጠፉ ነበር ይለናል መዝ. [105:23] ሙሴ ቀጥ ብሎ ስለ ቆመ አይደለም እስራኤላዊያን ምሕረት ያገኙት፤ ሕዝቡን ከምታጠፋ ሥሜን ከሕይወት መጽሐፍ ላይ ደምስስ!!! እያለ የለመነው ልመና ነው እስራኤላዊያንን ያስማራቸው ዘፀአት [32:32]

ስለዚህም “መቆም” ማለት ቀጥ ብሎ መቆም ብቻ ሳይሆን  መለመን ፣ ማማለድ እንደሆነ ባህረ ጥበብ የሆነች ቤተክርስቲያናችን እንዲህ ከመጽሐፍ ቅዱስ እያበሰለች ትመግበናለች!

የተከበሩት አባት በግርማ ሞገሳቸው ጎርደድ እያሉ “እስኪ በአንድምት እንምጣ” አሉ። አንድም ስለ ሕዝቡ የሚቆመው” ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሳል ዳንኤል [12:1] ቅ/ሚካኤል እግረ ሥጋ የለውም፤ ስለ እኛ ምህረትን ይለምናል እንጂ። አንድም መላዕክትም በእግዚአብሔር ፊት “ለመቆም” መጡ፤ ሰይጣንም በመካከላቸው ነበር። ኢዮብ [1:6] ሰይጣን ከሳሽ ስለሆነ ቆመ አልተባለም መላዕክቱም ቆሙ የተባሉት ቀጥ ብለው ቆሙ ለማለት አይደለም፤ ሊለምኑ መጡ ለማለት ነው እንጂ። አንድም እግርህ በድንጋይ እንዳይመታ “በእጆቻቸው ያነሱሃል” ይላል፤ መዝ. [90: 11] መላዕክት እንደ ሰው እጅ የላቸውም መንፈስ ናቸውና፤ ነገር ግን ሎጥን ከሰዶም እሣት እጁን ይዘው እንደወጡ ፈጥነው ደራሽ መሆናቸውን ሲያስረዳን ነው።



አንድም መላዕክት እንደ ሰው የሚያዩበት ዓይነ ሥጋ የላቸውም፤ መንፈስ ናቸውና፤ በወንጌል ግን ጌታችን እንዲህ አለ፦ ከታናናሾቻችሁ ማንንም እንዳትንቁ ተጠንቀቁ ጠባቂ መላእክቶቻቸው ዘወትር የአባቴን ፊት “ያያሉና” ማቴ. [18:10] “ያያሉና” ማለት መላዕክት በዓይናቸው እግዚአብሔርን ያያሉ ለማለት አይደለም; መላዕክት ዓይነ ሥጋ የላቸውም ተብሏልና “ያያሉ ማለት ይለምናሉ” ለማለት ነው፤ አንድም እግዚአብሔርን ያየ ከቶ ማንም የለም ይለናል፤ 1ኛዮሐ.[4: 12]  ያያሉ” ማለት ይለምናሉ ማለት እንደሆነ አየህን?

አንድም “ጠባቂ መላእክቶቻቸው” የሚለውን ስንመለከት “ጠባቂ” የሚለው ቃል መላዕክት ጠባቂ እንደሆኑ አይነግረንምን? አንድም “መላእክቶቻቸው” የሚለው ቃል እያንዳንዱ ሰው ፪ ዑቃቢ መልአክ /ጠባቂ መልአክ/ እንዳሉት አይነግርህምን? ፩ዱ በቀን ሲጠብቅህ ፩ዱ በለሊት እንደሚጠብቅህ አታውቅምን? አሉ የተከበሩት አባት በማይጠገብ ፈገግታቸው እያዩን። ይህችንም ማስታወሻ ሰጡን፦ “የጥቅስ ጥናት ዘዴ”

የቅ/ሚካኤል በዓል የሚውለው በ 12 ነው ስለዚህ ዳንኤል [12:1]
የቅ/ገብርኤል በዓል የሚውለው በ 19 ነው ስለዚህ ሉቃስ [1: 19]


የተከበሩት አባት ውድ ልጆቼ ሆይ ይህን ሁሉ ባሕረ ጥበብ ቤተክርስቲያን ታስተምረናለችና ይህች ቤተክርስቲያን ግሩም ድንቅ ናት!” አሉን። ይህን ሲሉ ለመጻፍ የማይቻል አንዳች የመንፈስ ደስታ ይታይባቸው ነበር።

ይህች ቤተክርስቲያን ግሩም ድንቅ ናት!”  አሉ በድጋሚ፤ እኛም ይህች ቤተክርስቲያን ግሩም ድንቅ ናት!” አልን በልባችን።