Friday 6 April 2012

ዘና ብላችሁ ተቀመጡና አንድ ታሪክ ልንገራችሁ


”ጥርስና ምላስ”
አንድ ቀን ነው አሉ አቶ ጥርስ ልክ እንደ ወፍጮ ያገኘውን ሁሉ ይፈጫል ያደቃል ይከካል፤

ይህም የአቶ ጥርስ መደበኛ ሥራ ሆኖ ቀረ አሉ። ጉረቤቶቹ እነ ጨጓራና ትርፍ አንጀት “አድቃቂው” የሚል የማዕረግ ስም እስከሚሰጡት ድረስ ስሙ ከፍ ከፍ አለ። አቶ ጥርስም ስራው ፍሬያማ በመሆኑ እነሆ ደስተኛ ኾነ።

ከእለታት በአንደኛው ቀን ግን ችግር ተፈጠረ፤ አቶ ጥርስ እንደለመደው ያገኘውን ሁሉ ሲፈጭ ሲያደቅ ሲከካ ሳያስበው እትዬ ምላስን ቀረጠፋት!

ምላስም እስከምትቆስል ድረስ እጅግ ተጎዳች። እትዬ ምላስ አቶ ጥርስን እየተቆጣች “ትንሽ ምላስ ጫካን ታቃጥላለች የተባለልኝ እኔ እንዴት እደፈራለሁ” እያለች እሪሪሪ ብላ ጮኸች፤  ጮኻም አልቀረች የሰውነት ክፍሎችን ሁሉ እነ ዓይን ፣ አፍንጫ፣ ጨጓራ፤ ትርፍ አንጀትማንንም ሳታስቀር ሰበሰበችና ከዛሬ ጀምሮ ጥርስ የሚባል ነገር አያስፈልገንም! ፀባዩም ከእኛ ለየት ይላል፤ እስቲ እዩት እኛ ስስ እሱ ጠንካራ፤ እኛ ሥጋ እሱ… አለችና ከምን እንደተሰራ ሲጠፋት እሱ ሁሉ ነገሩ ከእኛ ይለያል፤ በቃ ይወገድልን! አለች እትዬ ምላስ ምርር ብላ!

ሁሉም እጃቸው እስከሚላጥ አጨበጨቡ፤ ልክ ነው አቶ ጥርስ ይወገድልን እያሉም ጮኹ! ………..
መቼም አስተዋይ ሽማግሌ አያሳጣን፤ የተከበሩት ሽማግሌው ጨጓራ ተነሱና እስቲ እስከ አሁን ድረስ ዝም ያሉት እነ ዓይን የሚሉትን እንስማ” አሉ፤ ዓይንም ማወቅ እናውቃለን ብንናገር እናልቃለን” ብላ እጥር ያለች መልስ ሰጠችና ተቀመጠች! አቶ ጨጓራ በዓይን መልስ በጣም ተገረሙ። የራሳቸውንም ኀሳብ ሰጡ፤ “የምትናገሩትን አስተውሉ! በአንድ ወቅት አይሁድ “ሆሣዕና እያሉ እንዳልዘመሩና እንዳላመሰገኑ በሳምንቱ  ግን ስቀለው ስቀለው እያሉ ጮኹ! ሽባን ቢፈውስ ለምፅን ቢያነፃ አጋንንትን ቢያስወጣላቸው በቸርነት ፋንታ ይሰቀል ይሰቀል እያሉ ጮኹ!” …..

አዬ ዬ… ላይኛው ከንፈር ለክርክር ታችኛው ከንፈር ለምስክር!” አሉ፤ እናንተም እኮ ከእነርሱ ምንም አልተማራችሁም። አንድ ሰሞን አድቃቂው!” ብላችሁ እንዳላሞገሳችሁት በሳምንቱ “ይወገድልን” እያላችሁ ጮኻችሁ! ይህ እኮ ነው ተረፈ አይሁድ መሆን፤ አቶ ጥርስን አመድ አፋሽ አደረጋችሁት! ጥርስ ባደቀቀው እናንተ ያለችግር ትጠቀማላችሁና አስተውሉ! እኛ እኮ ኑሯችን እንደ ሠንሰለት ነው፤ “ልብ ያሰበውን አፍ ይናገራል ዓይን ያየውን እጅ ይሰራል! አለች ሴትዮዋ እውነቷን እኮ ነው፤ አንድነት መልካም ነው! መፅሐፉም በሶስት የተገመደ ገመድ በቀላሉ አይበጠስም! ስለሚል በአንድነታችን እንበርታ! ለላም ቀንዷ አይከብዳትም” ሲባል አልሰማችሁምን? እኛ የራሳችን ቀንድ እየከበደን እኮ ነው! አሉና በልባቸው መናገር መልካም ነው ማዳመጥ ይበልጣል!” ብለው የተከበሩት ጨጓራ ዝም አሉ።


ወዲያው ግን የእነ ምላስ ጩኸት ቀጠለ፤ ልፋ ያለው በህልሙ ሸክም ይሸከማል” እንዲሉ ያ ሁሉ የአቶ ጨጓራ ንግግር ከንቱ ኾነ።
የእትዬ ምላስንና የአቶ እጅን ከንቱ ወሬ አስቀድመው የሰሙት እነ ዓይንም በጩኸቱ ተባበሩ! እንዲያውም በእነሱ ብሶ እኛ ብዙ ማውራት አንፈልግም፤ ብቻ አቶ ጥርስ ይወገድልን! አሉ፤ ለእባብ እግር የለው ለሞኝ መላ የለው” እንዲሉ መላ ከመፈለግ ይልቅ በችግር ላይ ተደመሩ! መጀመሪያ ጆሮ የገባን ከንቱ ወሬ የ 10 አመት ትምህርት አይለውጠውም የሚባለው ለዚሁ ነው፤ ለማርያም መግደላዊት ፣ ለእነ ሉቃስና ቀልዮጳ ጌታችን ዳግም እንደሚነሣ 3 አመት ከ3 ወር አስተምሯቸው ነበር እኮ፤ ሐሰቱ ሲበዛ እውነት ሆነ ዋዛ!” እንዲሉ የአንድ ቀን የአይሁድ ተሰርቋል” የሚለው ከንቱ ወሬ ትምህርቱን ሁሉ በረዘባቸው። አስቀድማ ትንሣኤውን ያየችው ማርያም መግደላዊት ጌታዬን ወስደኸው እንደሆነ አሳየኝ” ያለችው መጀመሪያ በሰማችው ከንቱ ወሬ ምክንያት ነበር። አዬ መጀመሪያ የተሰማች ከንቱ ወሬ! መጥፎ ወሬ ይበራል መልካሙ ይተኛል” ይባል የለ፤ መጥፎ ወሬ ክንፍ አለው ይበራል፤ መልካሙ ወሬ ግን እንቅልፋም ነውና ይተኛል።

አቶ እጅም ድንገት ተነሳና “ባጎረስኩ እጄን ተነከስኩ” ይላል ሰው የተባለ ፍጡር፤ እናም አቶ ጥርስ እጅ የተባልኩትን እኔን ስለነከሰኝና ስራው ያገኘውን ሁሉ መክተፍ ብቻ ስለሆነ ምርር ብሎኛል! ሁሉን ቢናገሩ ሆድ ባዶ ይቀራል” አሉ፤ እኔም እትዬ ምላስን እደግፋታለሁ! ብሎ ለራሱ አጨበጨበ!  እጅ ነውና ለእራሱ ቢያጨበጭብ ማንንም አላስገረመም!


“መከራው ያላለቀለት በሬ ቆዳው ለነጋሪት ይጠፈራል” እንዲሉ የአቶ ጥርስ መከራም እንዲሁ በዛ። በዚህ ሁኔታም አቶ ጥርስ ከሰውነት ክፍል ተነቀሉና ተወገዱ! እነ ምላስና እጅም በሁኔታው ተደሰቱ  .   .     .      .

ብዙም ሳይቆይ ጨጓራ መጮ ጀመረ፤ እየተንጉራደደ “የደቀቀውን ምግብ አምጡልኝ እንጂ” እያለ ያጓራ ጀመር። አቶ ጥርስ ተወግዷልና ምላስ ለጨጓራ የምትልከውን አጣች። አቶ እጅም ጥርስ ይወገድ! እያለ ለራሱ ያጨበጨበውን በሳምንቱ እረሳና ምን የሚያክል አጥንት ይዞ የሚግጥለትን የሚዘነጥልለትን የሚያደቅለትን መፈለግ ጀመረ፤ ለመስራት ያፈረ ለመብላት ደፈረ!

ችግሩ እንዲህ እያለ ተባባሰ፤ የጨጓራ ጩኸትም ቀጠለ…… እትዬ ምላስና አቶ እጅም እዬዬ እያሉ ምርር ብለው ማልቀስ ጀመሩ፤ ሆድ ሲሞላ ፍቅሩ ሌላ ሆድ ሲጎድል ሰው ያጋድል” እንዲሉ በመጨረሻ እርስ በእርሳቸው ተጣሉ; ሽማግሌው ጨጓራም እንዲህ ብሎ ገጠመባቸው፦

በፊት ነበረ እንጂ በሕብረት መደቆስ
አሁን ምን ያደርጋል ጥርስን ጥሎ ማልቀስ!

የሚያደቀውንም ፈልጋችሁ ፉከራውንም ወደዳችሁ፤ ሁለት ወዳችሁ እንዴት ይኾናል? ሁለት አይወዱ ከመነኮሱ አይወልዱ” አሉና መናገር ብር ነው ዝምታ ወርቅ ነው”    አሉ አቶ ጨጓራ እንደለመዱት በልባቸው!



አቶ ጥርስ ይህን ችግራቸውን ሁሉ አየና አዘነላቸው፤ ለረዥም መንገድ አትሩጥበት ለረዥም ነገር አትቸኩልበት!” እንዲሉ ምን ማድረግ እንዳለበት ለራሱ ግዜ ሰጥቶ አሰበበት፤ ወዲያው ፩ መፍትሄ መጣለት፤ እንዲህም አላቸው ምንም ብትበድሉኝ አብረን ሰርተናል፣


ብዙ ትዝታዎችንም አሳልፈናል ሆደ ሰፊ  ይሻላል ከአኩራፊ” ስለሚባል በስራችሁ አልቀየምም አብሮ የበላና የጠጣ ሰው እስከ መጨረሻው አይቀያየምም” ሲባል ሰምቻለሁ። አሁንም አብረን እጅና ጓንት ሆነን መስራት አለብን” ሲል አቶ እጅ ስሙ ስለተነሳ ደስ አለውና በረጅሙ አጨበጨበ…..      አዬ የእጅ ነገር እንዲያው በተገኘው ነገር ሁሉ ማጨብጨብ…  እራሱ ተናግሮ ለእራሱ ያጨበጭባል፤ ሌላውም ሲናገር እንዲሁ፤ እሱ እቴ ምን አለበት ሰው ግራ ይግባው ቀኝ ይግባው አይመለከተውም በቃ! ማጨብጨብ ብቻ …








አቶ ጥርስ በእጅ ባህሪ ቢገረሙም “አብሬያችሁ ልሰራ ፈቃደኛ ነኝ ሁለተኛ ጥፋት ቆሞ ማንቀላፋት” ስለሚባል አስቀድመን ግን ውል መፈራረም አለብን አሉ፤ እነሱም “እርሶ የፈለጉትን ያድርጉ አጥንቱም ሥጋውም የእርሶ ነው፤ ሁሉ ተፈቅዶሎታል” አሉ።  አቶ ጥርስም እነሆ ውሉ ይህ ነው “ሁላችሁም እድሜ ልካችሁን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳትሉ ትሰራላችሁ። እኔ ግን የአገልግሎት ዘመኔ ሲፈፀም ጡረታ መውጣት እችላለሁ” አሉ። ግዜያዊ ችግራቸው ብቻ ስለታያቸው “ይኹን ይደረግ” ብለው ተስማሙ። አቶ ጥርስም በሉ ከዛሬ ጀምሮ ጡረታ እስከምወጣበት ቀን ድረስ አብረን “እናደቃለን እንፈጫለን እንከካለን” ብለው በታላቅ ሞራል ተናገሩ!



ይህ ሁሉ ክርክር የተከናወነበት ሰውዬ ነገሩን ሁሉ በጥሞና ይከታተል ነበር። አይ ምላሴና ጥርሴ! ለካ ይህ ሁሉ ታሪክ አላችሁ! እያለ ያወጣና ያወርድ ጀምር። በድንገት በአቶ ጨጓራ ንግግር ሰውዬ እስኪንዘፈዘፍ ድረስ ጭብጨባው ቀለጠ!

 ከሁሉም ጭብጨባ ግን የአቶ እጅ ለረጅም ግዜ ሳያቋርጥ ቀጠለ!

ለተወሰኑ አመታት አቶ ጥርስ ፣ እጅና እትዬ ምላስ አብረው ሰሩ።

አቶ ጥርስ ጡረታ መውጫቸው ግዜ ደረሰ።

እነሆ ሰው ሲያረጅ ጥርሱ የሚያልቀው ከዛሬ ብዙ አመታት በፊት በተደረገው የውል ስምምነት ነው!