Saturday 30 June 2012

ጻድቃን ከሞቱ በኋላ እኛ የምንለምናቸውን ልመና እንዴት ይሰማሉ??

ጻድቃን ከሞቱ በኋላ እኛ የምንለምናቸውን ልመና እንዴት ይሰማሉ??

“Righteous From paradise  የቅዱሳን ምልጃ ከገነት”

አንድ ወንድሜ ጻድቃንን ከሞቱ በኋላ  ለምኑልን ጸልዩልን የምትሉት እኛ የምንሰራውን ስራ በምን ያውቃሉ? እንዴትስ ይሰሟችኋል? ብሎ ጠየቀኝ።  ወንድሜ የጠየቀኝን ጥያቄ እኔ ሳልሆን መፅሐፍ ቅዱስ መልሶለት ለሕሊናው ጥያቄ መልስ አግኝቶበታል። ለመሆኑ ጻድቃን ከሞቱ በኋላ እኛ የምንለምናቸውን ልመና እንዴት ይሰማሉ??

አብርሐም፦ በሉቃስ ወንጌል የተጻፈ አንድ ታሪክ አለ። ኃጥኡ ነዌ በሲኦል እያለ ከሩቅ አብርሐምን አየውና አብርሐም አባት ሆይ እኔ በሲኦል እሣት እጅግ እየተሰቃየሁ ነውና እባክህን ምላሴን በቀዝቃዛ ውኃ እንዲያርስልኝ አላዛርን ላክልኝ አለው። አብርሐምም በኛና በእናንተ መካከል ታላቅ ገደል አለ ብሎ መለሰለት። ነዌም እንግዲያው በዓለም የሚኖሩ 5 ወንድሞች አሉኝና እባክህን አላዛርን ላከው አለ። አብርሐም የሚገርም ቃል ተናገረ ለነሱ ሙሴና ነብያት አሏቸው” አለ። ይገርማል አብርሐም ሙሴን የት አየው? መቼ ተገናኘው? አብርሐምና ሙሴ በዓለም አልተገናኙም ነገር ግን አብርሐም በአካለ ነፍስ ሆኖ ሙሴ እንደመጣ፣ መጽሐፍትን እንደጻፈ፣ ተዓምራትን እንደሰራ፣ የኤርትራን ባሕር እንደከፈለ ያውቅ ነበር!! አዎ በአካለ ነፍስ ያሉ ቅዱሳን በዓለም የሚከናወነውን ሁሉ ከእኛ በላይ ያውቃሉ። ስለእኛም ይለምናሉ። በሲኦል ያለው ነዌ ስለ ወንድሞቹ ከለመነ በገነት ያሉት ጻድቃንማ እንዴት ስለእኛ አይለምኑ?? አብርሐም በአካለ ነፍስ” ሆኖ አላዛርና ነዌ በዓለም ምን እንደሰሩ ያውቅ ነበር። አላዛር አንተ ችግርን ሁሉ ታገስክ; ነዌ አንተም ምቾትን ሁሉ ተቀበልክ” ያለው አብርሐም በአካለ ነፍስ  ሆኖ ምን እንደሰሩ ስለሚያውቅ ነው። አንዳንድ የዘመኑ ሰዎች ጻድቃን በአካለ ነፍስ ሆነው እንዴት ያውቃሉ ይላሉ አይደል? ወንጌሉ ይገለጥና ይነበባ። እውነትን ፍንትው አድርጎ በደንብ ያስረዳናል [ሉቃስ 16:19]

ነዌ አብርሐምን አነጋገረአብርሐምም መለሰለት። አብርሐም መናገር መቻሉ ሕያው መሆኑን ያስረዳናል” ጌታችንም እኔ የሕያዋን የአብርሐም የይሥሐቅ የያዕቆብ አምላክ እንጂ የሙታን አምላክ አይደለሁም” ያለውም ለዚሁ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ አለ አሁን በመስታወት እንደሚያይ በድንግዝግዝ እናያለን ያን ጊዜ ግን ፊት ለፊት እናያለን” [1ኛ ቆሮ13:12]



አዎ ቅዱሳኑ ስለ ሀገራችን ስለ ዓለም ስለ ቤተክርስቲያን ስለ ራሳችን ለምኑልን ስንል ይሰማሉ፤ ቅ/ጳውሎስ እንዳለው ቅዱሳኑ ሁሉን ፊት ለፊት በግልጽ ያያሉና!!


በር እና ቁልፉ፦ መድኃኒተ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል ላይ እውነተኛ የበጎች በር እኔ ነኝ” ብሏል። መልካም እረኛ እኔ ነኝ እንዳለ የበጎች በር ጌታችን ነው። በር ካለ ቁልፍ አለ ማለት ነው። የበሩ ቁልፍ የት ነው ያለው?

የበሩ ቁልፍማ በቅ/ጴጥሮስ እጅ ነው ያለው! ጴጥሮስ አንተ ዐለት ነህ። በዚህች ዐለት ላይ ቤተክርስቲያኔን እሰራታለሁ። የሲኦል ደጆች አይችላትም (የሲኦል ደጅ ጠባቂ አጋንንት አይችሏትም) “የመንግሥተ ሰማያትን መክፈቻ እሰጥሃለሁ [ማቴ. 16:17]

የበሩን ቁልፍ ሳይዝ በሩን ለመክፈት የሚታገል ካለ መቼስ ምን እንላለን? ቁልፉን ሳይዙ በሩን ለመክፈት የሚታገሉ ሰዎችኮ በመፅሐፍ ቅዱስ ላይ ታሪካቸው ተተርኳል! ትዝ አይላችሁም የሰዶምና ገሞራ ሰዎች የሎጥን ቤት ሲደበድቡ? የበሩ ቁልፍ ያለው ግን በሎጥ እጅ ነበር። የበሩ ቁልፍ ያለው በቅ/ጴጥሮስ እግር በተተኩት ምርጥ እቃዎች በቅዱሳኑ ዘንድ ነው። የበራችንን ቁልፍ ስናይ ፣ በራችንን ስንከፍት ይህ ትዝ ሊለን ይገባል። የበሩ ቁልፍ ያለው በአካለ ነፍስና በአጸደ ነፍስ ባሉ በቅዱሳኑ እጅ ነውና። ዐለት የተባለውን የሐዋርያት አለቃን ስለ እምነታችን ፅናት እስኪ እንለምነው “ከሞቴ በኋላ ስለ እምነታችሁ ፅናት ስለእናንተ እተጋለሁ[2ኛ ጴጥሮስ 1:15]

ይህን በተመለከተ እስኪ ቤተክርስቲያናችን በቅዳሴ የምታዜመውን አብረን እንይ።ተውህቦ መራሁት ለአቡነ ጴጥሮስ” ወድንግልና ለዮሐንስ ወመልዕክተ ለአቡነ ጳውሎስ እስመ ውእቱ ብርኃና ለቤተክርስቲያን።

ትርጉም፦ ለአባታችን ለጴጥሮስ የመንግሥተ ሰማያት መክፈቻ ፣ ለዮሐንስ ድንግልና ለቅ/ጳውሎስም መልእክት ተሰጠው። [ማቴ. 16:17]

    
 ሙሴ ፦ከሞተ ዘመናት ያለፉት ሙሴ ከኤልያስ ጋር በደብረ ታቦር በተገለጸ ጊዜ ኤልያስና ሙሴ ከጌታ ጋር ይነጋገሩ ነበር። ስለ ኢየሩሳሌምም ትንቢት ተናገሩ እንዲል ሉቃስ [9:30] ሙሴ መናገር መቻሉና ትንቢት መተንበዩ ሕያው መሆኑን ያስረዳናል

 ደመ ሰማዕታት [Martyrdom]፦ ሰማዕታት ማለት ሰማ መሰከረ ሰማዕት ምስክር ማለት ነው። ደመ ሰማዕታት በታላቅ ድምጽ እየጮሁ ደማችንን በከንቱ ያፈሰሱትን የማትበቀለው እስከመቼ ድረስ ነው?” አሉ [ራዕ 6:9] “በታላቅ ድምጽ መጮህ መቻላቸው ሕያዋን መሆናቸውን ያስረዳናል። ደማችንን በከንቱ ያፈሰሱትን የማትበቀለው እስከመቼ ድረስ ነው? ማለታቸው ደማቸውን በከንቱ ያፈሰሱት እነ ዲዮቅልጥያኖስና ሌሎችም ገና እንዳልተቀጡ ስለሚያውቁ ነው። ጌታም ሌሎች ሰማዕታት ስላሉ እንዲታገሱ ነግሯቸው የንጽህና ምልክት የሆነውን ነጭ ልብስ ሰጣቸው። ሰማዕታት ደማቸውን በከንቱ ስላፈሰሱት ፍርድን ሲጠይቁ ስለ እኛ ደግሞ ይለምናሉ


“ዙሪያ ጥምጥም

እዚህ ጋ ከላይ እንዳየነው ወንድሜ የጠየቀው ጥያቄ ትዝ አለኝ። ቅዱሳን ከሞቱ በኋላ እኛ የምንሰራውን ስራ በምን ያውቃሉ? ብሎ ነበር የጠየቀኝ። የአብርሐምና የነዌ ታሪክ መልሶለታል [ሉቃስ 16:19] ወዳጄ ጥያቄውን እንዲህ እያለ ቀጠለ። እኛ ራሳችን እግዚአብሔርን በቀጥታ መለመን ስንችል ለምን በተዘዋዋሪ ዙሪያ ጥምጥም መጓዝ አስፈለገ? ብሎ ጠየቀኝ።

ጌታችን ለምጻሙን ሰው ከፈወሰው በኋላ ወደ ካህን ሔደህ ራስህን አሳይ ለምን አለው? እሱ ራሱ ካየው አይበቃም ነበር? እግዚአብሔር ቅ/ገብርኤልን ወደ እመቤታችን ለምን ላከው? እሱ ራሱ ለምን በቀጥታ አላነጋገራትም ብለን ልንጠይቅ እንችላለን? ብዬ ጠየኩት። ወጃጄ ነገሩ ሁሉ እየገባው መጣ።

ዳዊት፦ ንጉሥ ሰናክሬም ንጉሥ ሕዝቅያስን እጅግ ያስጨንቀው ነበር። በአንድ ወቅት ሰናክሬም የትዕቢት ደብዳቤ ጽፎ በንጉሥ ማሕተም አትሞ ሥጋህን ቆራርጬ ለአሞራ አጥንትህን ፈጭቼ ለነፋስ እሰጠዋለሁ እያለ ለሕዝቅያስ ላከበት። ንጉሥ ሕዝቅያስም ደብዳቤውን ይዞ ወደ ቤተክርስቲያን ገሠገሠ። ወዲያው ደብዳቤውን በእግዚአብሔር ፊት ዘረጋው። አቤቱ ይህን ሁሉ ተመልከት፣ አቤቱ የጭንቅ ደብዳቤውን አንተ እይ እያለ ለመነ። እግዚአብሔርም የንጉሡን ጩኸት ሰማ። እስኪ የሚያስጨንቀንን ነገር ከቤቱ ገብተን እንደ ንጉሥ ሕዝቅያስ ደብዳቤ በፊቱ እንዘርጋው። የከበደው ቀሎ፣ የጨለመው በርቶ አስጨናቂው ለሊት ሲነጋልን በዓይናችን አይተናልና!! በቤቱ እጁን ዘርግቶ ማን ባዶውን ይመለሳል? ጌታችን ሆይ በቃላት ስለማይነገረው ስጦታህ ሁሉ እናመሰግንሃለን።

ንጉሥ ሕዝቅያስ ደብዳቤውን በእግዚአብሔር ፊት ከዘረጋ በኋላ መልክተኞችን ወደ ነቢዩ ኢሳይያስ ላከ። ነቢዩ ኢሳይያስ የነገሥታት አማካሪ ነበር። ኢሳይያስ ንጉሥ ሕዝቅያስንና ንጉሥ ዖዝያንን ያማክር ነበር። ዛሬ ቅዱሳንን የሚያማክር ከየት ይገኛል? ንጉሥ ሕዝቅያስ የነቢዩ ኢሳይያስን መልስ በተስፋ እየተጠባበቀ ነበር። እግዚአብሔርም መልሱን በነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ብሎ ላከለት። ልበ አምላክ ዳዊት ከሞተ ከብዙ ዘመን በኋላ ስለ ዳዊት ስል ኢየሩሳሌምን ከጥፋት እጋርዳታለሁ” አለ [2ኛ. ነገ19:34]

ስለ ዳዊት ስል ኢየሩሳሌምን እምራታለሁ እንዳለ ስለ አቡነ ተክለሐይማኖት ፣ ስለ አቡነ አረጋዊ ፣ ስለ ቅ/ጊዮርጊስ ስትል ሀገራችንን ማር ብንል ስህተቱ ምኑ ላይ ነው? የዘመኑ ሰዎች ለምን ስለ ዳዊት አልክ ብለው ፈጣሪንም ተሳስተሃል ይሉ ይሆን?

ንጉሥ ሕዝቅያስና ንጉሥ ዖዝያን ነቢዩ ኢሳይያስን እንደሚያማክሩ አይተን ነበር። ነቢዩ ኤልሳዕም እንዲሁ የእስራኤል ንጉስን ያማክር ነበር። ትዝ ካላችሁ የሶርያው ንጉሥ እስራኤልን ለመውረር ብዙ ሲሞክር ነቢዩ ኤልሳዕ በእስራኤል ሆኖ በሶርያ ቤተመንግሥት ውስጥ የሚመከረውን እያንዳንዷን ምክር ያውቅ ነበርና ሚሥጢሩን ለእስራኤል ንጉሥ ያቀብል ነበር። ኤልሳዕ ልክ እኛ በ CCTV እንደምናየው ሁሉን ያይ ነበር። የሶርያው ንጉሥ ግራ ገባውና ተጨነቀ። በመጨረሻም ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት ብሎ ወደ እስራኤል ገሠገሠ። የተዋጋው ግን ንጉሡን ወይንም የንጉሡን ሠራዊት ሳይሆን ኤልሳዕን ነበር። ኤልሳዕ ከጠፋ እስራኤል ጠፋች ማለት ነውና። ይህኮ በኛ ቤትም እየተሰራበት ነው። ቅዱሳኑ ከጠፉ ኢትዮጲያን ማጥፋት ቀላል ነው የሚሉ ብዙ የዘመናችን ሰዎች አሉና። እስኪ ልብ በሉ።

ፕሮቴስታንቱ ቢነሳ በኛ
ካቶሊኩ ቢነሳ በኛ  
ተሐድሶ ቢነሳ በኛ
እስላሙ ቢነሳ በኛ
ፖለቲከኛው ቢነሳ በኛ

አንዱ አንዱን ላጥፋ አይልም። ከውጪውም ሆነ ከሀገር ውስጥ ሁሉም ዓይኑ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ላይ ነው።

ቅድስቲቱን ከተማ ሃገራችንን ቤተክርስቲያናችንን ከጠላት እንዲጠብቅልን በአካለ ሥጋና በአካለ ነፍስ ያሉ ጻድቃን ሰማዕታትን እንለምን። በአካለ ሥጋና በአካለ ነፍስ ያሉ የቅዱሳኑ ምልጃ ከእኛና ከሃገራችን ከኢትዮጲያና - ኤርትራ” አይለይ አሜን! /7-2-2010/


በቅዱሳን ላይ በትዕቢት የሚናገር አንደበት ዲዳ ይሁን! [መዝሙረ ዳዊት 30:18]



ነብያትን ይስሙ [ሉቃስ 16:19]

ነዌ ባለጠጋው ሃብቱን አከማችቶ
እለት ከእለት ባለም ተመቻችቶ
ይኖር ነበር አምላክን ረስቶ
ደሃው አላዛርም በደጁ ተኝቶ
አንድ ቀን ጌታዬ ያዝንኛል ብሎ
ቀን ይቆጥር ነበር በቁስል ተወርሶ
ቁራሽ ፍርፋሪን አገኛለሁ ብሎ።

ባለጠጋ በልቡ ሳይራራ
በንቀት አየው ሲወጣ ሲገባ
ቀኑ ደረሰና ደሃ ተጠራ
በአብርሃም እቅፍ መልካም ቦታ አገኘ
ነዌ ባለጠጋ ሃብቱ መች ጠቀመው
ቀኑ ሲደርስ እርሱም ሞት አገኘው
መልካም ስላልነበር በምድር የሰራው
በሲኦል ክፉ ሆኖ አገኘው
በስቃይ ሳለ አሻቅቦ አብርሃምን አየው
አላዛርንም በእቅፉ ቢያየው
የጣቱን ጫፍ በውሃ ውስጥ ነክሮ
ምላሴን ቢያርሰው
አብርሃም አባት ሆይ አላዛርን እባክህን ላከው
ብሎ አላዛርን ሻተ በምድር ለናቀው።
አብርሃም መልሶ
አንተ በምድር ሳለህ መልካምን ተቀበልክ
አላዛርም ደግሞ እንዲሁ ክፉውን
ሁሉን ተቀብሏል አሁን ግን ይፅናናል
በኛና በናንተ ታላቅ ገደል ሆኗል።
ነዌ ይህን ግዜ 5 ወንድም አሉኝ
እነርሱም ደግሞ እንደኔ እንዳይሆኑ
አላዛርን ላከው ሁሉን ይንገርልኝ፤
ሙሴና ነብያት ለነርሱ አሏቸው
እነርሱንም ይስሙ መንገድ ይሁኗቸው
ሰምተው ቢፈፅሙት ህይወት ይሁናቸው
ብሎ መለሰለት እኛ እንድንሰማቸው።


/ተክለ መድህን/ 

በቅዱሳን ላይ በትዕቢት የሚናገር አንደበት ዲዳ ይሁን! [መዝሙረ ዳዊት 30:18]