Saturday 12 May 2012

“አንቺ ሴት ከአንቺ ዘንድ ምን አለኝ”


ጌታ ለእመቤታችን አንቺ ሴት ከአንቺ ዘንድ ምን አለኝ አላት፤ ይህም ግሩም የሆነ ሚስጢርን በውስጡ ይዟል; እስቲ ቃሉን ለሁለት ከፍለን እንየው፦

አንቺ ሴት

ይህን ቃል ለመጀመሪያ ግዜ የተጠቀመው አዳም ነበርአዳም በግብረ ሥላሴ ከህቱም ድንግል መሬት (ከአፈር) ተፈጠረ፤ ከባድ እንቅልፍ ተኝቶ ሳለ ከግራ ጎን ዐጥንቱ ሔዋን ተፈጠረች። አዳም ከእንቅልፉ ነቅቶ ሔዋንን ከጎኑ ቢያት “ይህች ሥጋ ከሥጋዬ ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት ሲል ሴት አላት። ጌታችንም እመቤታችንን ከሥጋሽ ሥጋ ከነፍስሽ ነፍስ ነስቼ ከአንቺ ተወልጄ ዓለምን ኹሉ አዳንኩ ሲል “አንቺ ሴት” አላት። አንድም አዳም ከህቱም ድንግል መሬት ወይም ከአፈር መፈጠሩ እመቤታችን በህቱም ድንግና ጌታን የመውለዷ ምሳሌ ነው። አንድም ከአዳም ጎን ዐጥንት ሲነቀል አዳም ህመም አለመሰማቱ እመቤታችን ያለ ህመም ጌታን የመውለዷ ምሳሌ ነው። አንድም እግዚአብሔር አዳምን ከፈጠረ በኋላ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ አለ፤ ይህም አዳምን ሳይሆን እመቤታችንን ነው; እንዴት ቢሉ ወልድ ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ከሶስቱ አካል አንዱ ስለሚሆን ነው”


ከአንቺ ዘንድ ምን አለኝ፦

መፅሐፉ አጋንንት ያምናሉ ይንቀጠቀጣሉም ይላል; ነገር ግን ጌታን “ከአንተ ዘንድ ምን አለን” አሉት፤ አጋንንት ይህን ሲሉ ጌታን ንቀውት እንዳልሆነ ግልፅ ነው። አንድም ሱናማዊቷ ሴት ልጇን ከሞት እንዲያስነሳላት ነብዩ ኤልዕን ጌታዬ ሆይ “ከአንተ ዘንድ ምን አለኝ” አለችው። አንድም ዳዊት ልጁን አቤሴሎምን ሊገድሉበት ሲሉ እናንተ ሰዎች “ከእናንተ ዘንድ ምን አለኝ” አላቸው። ይህም የአክብሮት እንጂ የመናቅ ንግግር አለመሆኑ ግልጽ ነው።
******** // ********

ሐዋርያዊ ቅብብሎሽ “Apostolic Succession”

የቤተክርስቲያን ራስ ጌታ ነው። ከጌታ ቀጥሎ
“እስከ ዘመናችን” ያሉትን አባቶች በቅደም ተከተል አብረን እንያቸው!!



 የሐዋርያት አለቃ ቅ/ጴጥሮስ ነው።

ከቅዱስ ጴጥሮስ ቀጥሎ ቅ/ማርቆስ።

ቅ/ማርቆስ ግብጽ ሄዶ መንበሩን በግብጽ አደረገ።

ከቅ/ማርቆስ ቀጥሎ አንያኖስ ነው።

ከአንያኖስ ቀጥሎ 20 ፓትርያርክ አሉ። 20ኛው አትናቴዎስ ነው።

ከአትናቴዎስ ቀጥሎ ከሳቴ ብርኅን አባ ሰላማ /ፍሬምናጦስ/ ይህን ሐዋርያዊ ቅብብሎሽ ወደ ሀገራችን አመጣልን።

ፍሬምናጦስ ኢትዮጲያዊ አይደለም። አንድ ነጋዴ ሲድራኮስ እና ፍሬምናጦስ የሚባሉ ሁለት ልጆቹን ይዞ አንድ ነጋዴ ቤት ገብቶ መኖር ጀመረ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ነጋዴው ሞተ። ልጆቹም በገበሬው ቤት መኖር ጀመሩ። ፍሬምናጦስም የኢትዮጵያዊያንን እምነትና ባህል አደንቃለሁ። ለምን ሥጋ ወደሙን አትቀበሉም? ብሎ ገበሬውን ጠየቀው። ገበሬውም ካህናት ስለሌሉን ነው አለው። ፍሬምናጦስም በኢዛና እና ሳይዛና ፈቃድ ግብጽ ሄዶ ፕትርክናን ከአትናቶዎስ ተቀበለ።


የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ፍሬምናጦስ ነው።

ከዚህ ጊዜ በኋላ ለብዙ ዘመናት ኢትዮጵያ በግብጽ ፓትርያርኮች ስትመራ ቆይታለች።

የመጀመሪያው አራቱ ኢትዮጲያዊያን ጳጳሳት በ1921 ተሾሙ! 

አቡነ ሚካኤል
አቡነ ጴጥሮስ
አቡነ አብርሐም
አቡነ ይሥሐቅ ናቸው።

ከዚህ ጊዜ በኋላ በግብጽና በኢትዮጲያ መካከል ለሃያ አመታት ያክል ሀገራችን ኢትዮጵያዊ ጳጳስ ያስፈልጋታል አያስፈልጋትም በሚል ሽኩቻ ውስጥ ነበሩ።

ይህ እልህ አስጨራሽ ሽኩቻ አለፈና በ1940 ሌሎች አራት ጳጳሳት በግብጻዊው ፓትርያርክ በአቡነ ዮሳብ ተሾሙ።

አቡነ ሚካኤል
አቡነ ያዕቆብ
አቡነ ባስልዮስ
አቡነ ጢሞቴዎስ ናቸው።

ከእነዚህ ጳጳሳት አቡነ ባስልዮስ የመጀመሪያው ኢትዮጲያዊ ሊቀ ጳጳስ ኾነው ተሾሙ!! በዚህች እለት 21 ጊዜ መድፍ ተተኮሰ! ታላቅ ደስታ ነበርና! ጊዜውም በ1943 ዓ.ም ሲኾን ለአቡነ ባስልዮስ ሊቀ ጵጵስናውን የሰጡት የግብጹ ፓትርያርክ አቡነ ዮሳብ ነበሩ።
ከ1951-1963 ዓም ድረስ የመጀመሪያው ኢትዮጲያዊ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ባስልዮስ የመጀመሪያው ኢትዮጲያዊ ፓትርያር ኾኑ!!

በርግጥ ከአቡነ ባስልዮስ በፊት አቡነ አብርሐምና አቡነ ዮሐንስ የሚባሉ ሌሎች ሁለት ፓትርያርክ ነበሩ። ነገር ግን የኢጣልያው መንግስት ስለሾማቸው ቤተክርስቲያናችን ሕጋዊ ፓትርያርክ አድርጋ አትቀበላቸውም። የመጀመሪያው ሕጋዊ ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ አቡነ ባስልዮስ ናቸው።

ከአቡነ ባስልዮስ ቀጥሎ ፓትርያር አቡነ ቴዎፍሎስ ናቸው።

ከአቡነ ቴዎፍሎስ ቀጥሎ አቡነ ተክለሐይማኖት ናቸው።

ከአቡነ ተክለሐይማኖት ቀጥሎ አቡነ መርቆርዮስ ናቸው።

ከአቡነ መርቆርዮስ ቀጥሎ አቡነ ጳውሎስ ናቸው።

በነብያትና በሐዋርያት መሰረት ላይ ታንጻችኋል! የማዕዘኑ ድንጋይም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ኤፌ [2: 20] እንዲል የቤተክርስቲያን ራስ ጌታ ነው! በነብያትና በሐዋርያት መሰረት ላይ ስለታነጽን ሐዋርያዊ ቅብብሎሽን በሚገባ ማወቅና መረዳት አለብን። ፍትሕ መንፈሳዊ በአምስተኛው አንቀጽ ቁጥር 164 በሚያዝዘው መሠረት ቅዱስ ሲኖዶስ በዓመት ሁለት ጊዜ መደበኛ ስብሰባ ያካሂዳል፡፡ የመጀመሪያው ጉባኤ በየዓመቱ ጥቅምት 12 ቀን ሲኾን የሁለተኛው ጉባኤ ደግሞ ትንሣኤ በዋለ 25ኛው ቀን /በርክበ ካህናት/ የሚካሄደው ነው፡፡




Monday 7 May 2012

ይህች ሀገር ክቡር ናት!

ዘና ብላችሁ ተቀመጡና አንድ አሪፍ ታሪክ ልንገራችኹ!

ይህች ሀገር ክቡር ናት!

ኢትዮጲያ

“ሐሰቱ ሲበዛ እውነት ሆነ ዋዛ” አለች እምዬ ኢትዮጲያ እውነቷን እኮ ነው። ምን ታድርግ ደረሰባታ! ይህች ሀገር ደሃ ናት ብላችሁ የምትስቁ ታሪክን ጠይቁ። ይህች ሀገር ስሟን በዲክሽነሪያችሁ “ደሃ” ብላችሁ የፃፋችሁ ታሪክን ጠይቁ። በየዜናችሁ የምትሳለቁ ታሪክን ጠይቁ። አዎ! ማን ናት? በሉና ታሪክን ጠይቁ።         “ያየ ልናገር ቢል የሰማ ላውራ አለ” አለች እምዬ ኢትዮጲያ!  እስኪ ያየውን ታሪክን ጠይቁ።

አንድ ቀን ነው አሉ አቶ ታሪክ በድንገት ተነሱና በቃ! ታሪክን ጠይቁ ተባላችሁ አይደል እንዴ? ጠይቁኛ! አፍናችሁ ጨነቀኝኮ! እስኪ ልተንፍስና በዓይኔ ያየሁትን ልናገር። “ጆሮ የሰማውን ዓይን ለማየት ይንከራተታል” አለች እምዬ ኢትዮጲያ!

እውነቱ ይኽ ነው። እምዬ ኢትዮጲያ የተባለች ታላቅ ሀገር ነበረች። አውሮፓዊያን ጣኦት ሲያመልኩ ይህች ክቡር ሀገር ግን የተከበረውን የክርስትና ሃይማኖት የተቀበለች ታላቅ ሀገር ናት! መካከለኛው ምስራቅ የእስልምናን እምነት ከመቀበላቸው በፊት እስልምናን የተቀበለች ታላቅ ሀገር! የማናግራችሁ ታሪክ ነኝና አልዋሻችሁም። የዛሬዋ ኃያል ሀገር አሜሪካ አንዴ እንኳን ስሟ ሳይጠራ ይህች የከበረች ሀገር ግን ከ40 በላይ በመፅሐፍ ቅዱስ የተጠራች ኃያል ፣ ክቡር ፣ ሃይማኖተኛ ሀገር ናት! እውነቱን እንድታውቁ መርምሩ፤ ዳኞች ከመረመሩ ይናገራል ምድሩ” አለች እምዬ ኢትዮጲያ!

የጥበብ ሀገርዋ ወዴት ነው? ኢትዮጲያ አይደለችምን?  የቀደሙት አባቶቻችን ለሥልጣኔ መች ይተኙ ነበር! ይህን ያውቁ ኖሯል? በዐፄ ኀይለ ሥላሴ ትዕዛዝ የተሰራ 40 ኪ.ግ የሚመዝንና 972 ገፅ ያሉት 250 የበግ ቆዳ የፈጀ የብራና መፅሐፋ ያላት ባሕረ ጥበብ ኢትዮጲያ ናት!!

በአለም ለመጀመሪያ ጊዜ ጥምቀጥን የተጠመቀው ኢትዮጲያዊው የሃይማኖት ሰው ነው! በአለም ለመጀመሪያ ጊዜ በገንዘብ ላይ መስቀልን ያሳተመች የሥልጣኔ ሀ ሁ የቆጠረችው እምዬ ኢትዮጲያ ናት!

ታሪክ! እውነቱን እውነት ሐሰቱን ሐሰት ነውና የምለው ልብ ብላችሁ ስሙኝ። የምትጠጡት ቡና መገኛ ይህች ድንቅ ሀገር ናት! የታላቁ የዓባይ ወንዝ መመንጫ ይህች ሀብታም ሀገር ናት! የተፈጥሮ እናት የ 13 ወር የፀሐይ መውጫ ይህች ውብ ሀገር ናት። የአክሱም ፣ የላሊበላ ፣ የጎንደር አብያተ መንግሥት ፣ የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ፣ የጥያ ትክል ድንጋይ ፣ የአዋሽ ሸለቆ ፣ የጀጎል /የሐረር ግንብ/ ስምንቱ አለም አቀፋዊ የቅርስ ወደብ እምዬ ኢትዮጲያ ናት!
ይህችን ሀገሬንማ አትንኩብኝ! አዎ እምዬ ኢትዮጲያንማ አትንኩብኝ!

ወይ ሐቀኛው ታሪክ!
አሜሪካ እስከ 1776 ድረስ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት እኮ ነበረች፤ ይህች ታላቅ ሀገር ግን በማንም አልተደፈረችም! ለዚህ ነው ይህች ሀገር ክቡር ናት የምላችሁ! ከአፍሪካ በቅኝ ግዛት ያልተንበረከከችው ብቸኛዋ የጀግኖቹ ሀገር ይህች ክቡር ሀገር ናት! የአፍሪካ እናት የነፃነት ማማ የክብር ኮከብ ታላቅዋ ሀገር ማን ናት አላችሁ? አዎ ኢትዮጲያ ናት በሉ! አሜሪካ ገና 300 አመትዋ ነው፤ ይህች ሀገር ግን 3000 አመታትን አዘምናለች። የዚህችን ታላቅ ሀገር አየር የተነፈሰ ታላቅ ነው፤ ከአፍሪካዊያን ለመጀመሪያ ጊዜ የኦሎምፒክ አሸናፊው የዚህች ሀገር ሰው ነበርና። ከዓለማችን የራሳቸው ፊደልና ቁጥር ካላቸው 10 ሀገራት አንዷ ኢትዮጲያ ናት! ከአፍሪካ የራስዋ ፊደልና ቁጥር ያላት ብቸኛዋ ሀገር ማን ናት አላችሁ? አዎ የአፍሪካ የሥልጣኔ በር ኢትዮጲያ ናታ!

ይህች ናት ኢትዮጲያ!

የፃፋችሁትን ሰርዙ ደልዙ።

ኢትዮጲያ ይህች ናትና!

መቼም አቶ ታሪክ ስለ ኢትዮጲያ አውርተው አይጠግቡም። እጃቸውን በከዘራቸው ደገፍ ብለው በሐሳብ ባቡር ተሳፈሩና አቶ ታሪክ ታሪካቸውን ቀጠሉ፦ ጆን ፓርከንስ የተባለ ፀሐፊ የአሜሪካ ኢንፓየር ሚሥጢራዊ ታሪክ” በተባለ መፅሐፉ ውስጥ ጆርጅ ሪች የተባለ ጂኦሎጂስት ስለ ኢትዮጲያ የነገረውን እንዲህ ብሎ ፅፏል፦ ሕይወቴን በሙሉ ያሳለፍኩት በጂኦሎጂ ጥናት ነው የምነግርህ ተራራ ሙሉ ቤንዚን /ዘይት/ በዚህ እንዳለ ነው። እመነኝ ይህ አካባቢ በሕይወት እያለህ የቤንዚን ጦርነት ቀጠና ሲሆን ታያለህ” አለኝ ብሎ ፅፏል!!

አቶ ታሪክ እንግዲህ ምን እንላለን? አሉ ከሐሳብ ባቡራቸው እየወረዱ። ኢትዮጲያ እንደ ናይጄሪያ የቤንዚን ባሕር ብትሆን ሳናስተውል እንፈነድቃለን ወይስ ጦርነት ይመጣብናል ብለን የፍራቻ ዜማ እናዜማለን? “እንቁላል እንደያዙት ነው” በቸልታ ከያዝነው ይሰበራል በጥንቃቄ የያዙት እንቁላል ግን ተጠብሶ ይበላል! ይህ ኹሉ ግን ገና በእጃችን አልገባምና “ነብር ሳይገድል ቆዳውን ያስማማል” የሚለው ተረት እንዳይሆንብን ለዛሬ በዚሁ ይብቃን አሉ አቶ ታሪክ በከዘራቸው መሬቱን እየመቱ። ለተወሰነ ጊዜ ዝም አሉ። የቁጭትና የኀዘን ፊት ይታይባቸዋል። የአሁኗ ኢትዮጲያ በልባቸው ካለችው ኢትዮጲያ ጋር ስላልተመሳሰለላቸው ክፉኛ አዝነዋል። አቶ ታሪክ በድንገት ፈገግ አሉና ያዩትንና የዳሰሱትን ሁሉ መናገር ቀጠሉ፦

ይህን ያውቁ ኖሯል? ታላቁ ማንዴላ ገና የ 17 አመት ወጣት እያለ ነፃነትን ከማን ነበር እያየ ያደገው? ከኢትዮጲያዊው መሪ አልነበረምን!?

The legendary ruler who had inspired Mandela as a boy of 17 when he first heard he stood firm against Mussolini’s invading force. Selassie was neither a social nor a capital, but he ruled over the one African nation that had always been independent! 

ይሄ ኹሉ ታሪክ የት ደረሰ? አሉ አቶ ታሪክ ታሪክን መለስ ብለው እያስተዋሉ። ሌሎቹ ሀገራት ፈረስ ላይ ወጡና ጋለቡ ሸመጠጡ መጠቁ! እኔ የምለው ፈረሰኛ ሲሮጥ እግረኛ ምን አቆመው? ወርቅ የያዘ ሳጥን በወርቅ አይለበጥም ስለሚባል ይሆን የወርቁን ሳጥን በአሮጌ ጨርቅ የጠቀለላችሁት? አሉ አቶ ታሪክ በግርማ ሞገሳቸው እየተንጉራደዱ። እንዲህ እያሉም ታሪካቸውን ቀጠሉ፦



አንድ ሊቅ አንድ ጊዜ እንዲህ ብለው ጠይቀው ነበር፡፡
«ሰው ነው በሀገር ውስጥ የሚኖረው ወይንስ ሀገር ነው በሰው ውስጥ የሚኖረው?»
አንዳችን ይህንን ሌሎቻችን ደግሞ ያንን መለስን፡፡
እርሳቸው ግን እንዲህ አሉን «መጀመርያ ሰው በሀገር ውስጥ ይኖራል፡፡ ይህ ቀላሉ ነገር ነው፡፡ የመወለድ ጉዳይ ነው፡፡ የፈቃድ ጉዳይ ነው፡፡ የአሠራር ጉዳይ ነው፡፡ የመታወቂያ ጉዳይ ነው፡፡ ዋናው ከዚያ በኋላ የሚመጣው ነው፡፡»
«ከዚያ በኋላ ምን ይመጣል
«ከዚያ በኋላ ግን ሀገር በሰው ውስጥ ትኖራለች፡፡ ይህችን ሀገር በሰው ልብ ውስጥ የሚተክላት ፍቅር ነው፣ ባህል ነው፤ ቤተሰብ ነው፤ እምነት ነው፤ ታሪክ ነው፤ ከዚያም በላይ ደግሞ አንዳች ሁላችንም የማናውቀው ኃይል ነው፡፡ እውነተኛ ዜጎች በሀገራቸው ውስጥ የሚኖሩ አይደሉም፡፡ ሀገራቸው በእነርሱ ልብ ውስጥ የምትኖር ናቸው፡፡ እነዚህ ዜጎች የትም ይኖራሉ፡፡ ሀገራቸው ግን በልባቸው ውስጥ ናት፡፡ ታላቁ አባት አትናቴዎስ ከባዛንታይናውያን በደረሰበት

ጥቃት በተደጋጋሚ የእስክንድርያን መንበር እየተወ ተሰድዶ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ሮም ተገኝቶ በነበረ ጊዜ የሮሙ ሊቀ ጳጳስ ከእስክንድርያ በመባረሩ ማዘናቸውን ገለጡለት፡፡ እርሱም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው «እኔን ከእስክንድርያ ማስወጣት ቀላል ነው፡፡ ከባዱ እስክንድርያን ከእኔ ልብ ውስጥ ማስወጣት ነው፡፡ እስክንድርያ ሩቅ አይደለችም፡፡ እስክንድርያ እኔ ልብ ውስጥ ናት፡፡ እኔ የማዝነው ከእስክንድርያ ሲያስወጡኝ አይደለም፡፡ እስክንድርያ ከእኔ ልብ ውስጥ ከወጣች ነው» ነበር ያለው፡፡ መቼስ የአቶ ታሪክ ጨዋታ የአህያ ጆሮ ያቆማል! አቶ ታሪክ ስለ ታሪክ ሲናገሩ ውለው ቢያድሩ አይሰለቻቸውም። አንዳንዴ በውጭ ሀገር ለተወለዱ ኢትዮጲያዊያን አማርኛ ማንበብ ካልቻሉ እንግሊዘኛም ጨመር እያደረጉ ሀገራቸውንና ማንነታቸውን  እንዲያውቁ ያደርጉ ነበር። እንግሊዝ ተወልዳ ላደገች አንዲት ኢትዮጲያዊ ስለ ሀገርዋ እንዲህ ብለው አስረዷት።



Set back & relax! Let me tell you one Great History.

ETHIOPIA!

The only African nation never been colonized!

First Africans to win Gold in Olympics!

The country that practice Christianity before Europeans & accepted Islam before Middle East!

The country with the flag colors that everyone rocks with out even knowing it!

The country mentioned in the bible over 40 times!

The country that is the origin of Coffee you drink!

The only African nation with its own alphabets!
(ሀ ሁ ሂ ሃ ሄ ህ ሆ)

The only African nation with its own numbers!
1 2 3 4 5 (፩ ፪ ፫ ፬ ፭)

The country with so much culture & spirituality that you can’t even comprehend!

Can the Ethiopian change his skin or the leopard his spots? Jer 13: 23

በውኑ ኢትዮጲያዊ መልኩን ወይስ ነብር ንጉርጉሩነቱን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን? ኤር ፲፫ ፳፫
አቶ ታሪክ ታሪካቸውን ለመጨረስ አንዲት አባባል በእንግሊዘኛ ጣል ለማድረግ አሰቡና ነገር ቢበዛ በአህያ አይጫንም” እስኪ ታሪኬን ልጨርስ አሉ። አባባልሉን ግን በእንግሊዘኛ መተርጎም ስላቃታቸው አለፏት።    በመጨረሻም አቶ ታሪክ ስለ ታሪካቸው ስለ እምዬ ኢትዮጲያ እንደ ኳስ ተጫዋች ቀኝ እጃቸውን በደረታቸው ላይ አድርገው እንዲህ ብለው ገጠሙ፦

ሰማነው አየነው ሁሉን በየቅሉ
ታዲያ ይሄ ሁሉ ታሪክ ምነው ሕልም መምሰሉ?!  
ይኽው ትታያለች ለህዝብ በይፋ፣
ጥቁር ተከናንባ ጥቁር ተጎናጽፋ።
እኔስ መስሎኝ ነበር ዘመድ የሞተባት፣
የእናት ሞት የአባት ሞት፣
የልጅ ሞት ያጠቃት፣
ለካ እሷስ ኖራለች ዘመን የሞተባት።

እምዬ ኢትዮጲያ ይህን ጊዜ ልቧ ተነካ። ለምን አይነካ? ያመነችው አቶ ታሪክ እንኳን ሕልም መሰልሽ ሲሏት እንዴት አትከፋ?

እምዬ ኢትዮጲያም በተራዋ አሰብ አደረገችና ይህን ግጥም ገጠመች፦



በዚህ ሁሉ ታሪክ በዚህ ሁሉ ክብሬ
ታላቁ ቴዎድሮስ ይለኝ ነበር ታላቅዋ ሀገሬ!

በዚህ ሁሉ ጥበብ በዚህ ሁሉ ስሜ
እምዬ ምንይልክ ይሉኝ ነበር ኢትዮጲያ እምዬ!”

ሕልም ነው ካላችሁ ከእንቅልፌ ቀስቅሱኝ
ሕልም ፈቺው ይምጣ እንዲፈታው ሕልሙን!