Sunday 7 April 2013

ደብረ ዘይት




ማራናታ ማለት ጌታ ይመጣል ወይም ጌታ መጣ ማለት ነው (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ገጽ 609)፡፡ ይህ ቃል ዮሐንስ ራእዩን ሲዘጋ ተጠቅሞታል፡- “ አሜን ጌታ ኢየሱስ ሆይ ” (ራእ. 22÷20) ዮሐንስ በራእዩ ስለሚመጣው የዘመናት ጣር ካየ በኋላ የዚህ ሁሉ ማብቂያው ምንድነው? ብሎ ሲያስብ የጌ መምጣት ነው፡፡ ስለዚህ ማራናታ አለ፡፡ የጌታችን መምጣት የመከራው ድንበር ነው፡፡ በመጀመሪያ ምጽአቱ ሞት ተገደበ፣ በዳግመኛ ምጽአቱ መከራ ገደብ ያገኛል፡፡ 
የዐቢይ ጾም አምስተኛ እሑድ ደብረ ዘይት ተብሎ ይጠራል፡፡ የጌታችን ዳግም መምጣትና የዘመኑ ምልክት የሚነገርበት ቀን በመሆኑ ዕለቱ ደብረ ዘይት ተብሎ ተጠርቷል፡፡ ጌታችን ስለ ዓለም መጨረሻና ስለ መምጣቱ ምልክት የተናገረው በደብረ ዘይት ተራራ ላይ በመሆኑ ዕለቱ ደብረ ዘይት ተባለ (ማቴ.24÷ 3)፡፡ ቅዱስ ያሬድ ዕለቱን ደብረ ዘይት ብሎ መሰየሙ ብቻ ሳይሆን በዕለቱም ያቀረበው ዝማሬ እንዲህ የሚል ነው፡- 

ወአመ ምጽአቱሰ ለወልደ እጓለ እመሕያው ይትከወሰ ኲሉ ኃይለ ሰማያት ወምድር አሜሃ ይበክዩ ኲሎሙ ኃጥአን ምድር ወይወርድ እግዚእነ እምሰማይ ዲበ ምድር በትእዛዙ ወበቃሉ ወበአእላፍ መላእክቲሁ በንፍሐተ ቀርን ዘእም ኀበ እግዚአብሔር ይምሐረነ አብ በይእቲ ሰዓት እሞተ ኃጢአት እስመ ገባሬ ሕይወት 
ትርጉም፡-
የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜ የሰማይና የምድር ሠራዊት ሁሉ ይነቃነቃል። ያን ጊዜ በምድር የሚኖሩ ኃጢአተኞች ሁሉ ያለቅሳሉ፡፡ ጌታችንም ከአእላፍ መላእክት ጋር በተእዛዙና በቃሉ መሠረት ከሰማይ ወደ ምድር ይወርዳል፡፡ የእግዚአብሔር መለከትም ይሰማል፡፡ በዚያች ሰዓት እርሱ ያድነን። እርሱ የሕይወት ባለቤት ነውና። 

ቅዱስ ያሬድ የዘመረው የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 24 ነው፡፡ ጌታችን ሲመጣ ፍጥረት እንደማይፀና ኃጢአተኞች ደስታ እንደማይሰማቸው ይገልጣል፡፡ በኃይሉ ፊት ፍጥረት፣ በፍርዱ ፊት ኃጥአን መቆም አይችሉምና፡፡ 

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይመጣል። በብሉይ ኪዳን እመጣለሁ ብሎ መጥቷል፡፡ በአዲስ ኪዳንም እመጣለሁ ብሎ ቤተ ክርስቲያንን በተስፋ አስገዝቷታል፡፡ ፍጥረት ሁሉ የሚጠብቀው አንድ ታላቅ እንግዳ ከፊታችን ባለው ባልራቀው ዘመን ይመጣል፡፡ የሚመጣው በትሕትና ሳይሆን በልዕልና ነው፡፡ በከብቶች በረት ሊጣል ሳይሆን በደመና በዙፋን ተገልጦ ይመጣል፡፡ ስምዖን አረጋዊ እንደ ታቀፈው ሆኖ አይመጣም፣ ሰማይና ምድር የማይችሉት ሆኖ ይመጣል፡፡ ከእናቱ ጡትን እየለመነ አይመጣም፣ ለፍጥረት ሁሉ የሩጫውን ዋጋ ለመስጠት ይመጣል፡፡ ከሄሮድስ ፊት የሚሸሽ ሆኖ አይመጣም፡፡ ሰማይና ምድር ሲያዩት ከፊቱ ይሰደዳሉ፡፡ ለእኛ ለክርስቲያኖች መጣልን የምንለው እንግዳችን፣ ፈራጃችን እንጂ መጣብኝ የምንለው አይደለም፡፡ 

የጌታችን ዳግም ምጽአት፡- 

የጸሎታችን መልስ ነው

ብዙ ሰዎች ክርስቶስ ዳግም ይመጣል ሲባሉ ይፈራሉ፡፡ ፍርሃታቸው ግን ለንስሐ አያዘጋጃቸውም። ልበ ሙሉ ሆነው ኃጢአት እንዳይሠሩ የመምጣቱ ዜና ስለሚረብሻቸው ነው፡፡ የጌታችን ዳግም ምጽአት በሚታሰብበት ቀን እንኳ ብዙ የኃጢአት መታሰቢያ ሲደረግ ይውላል፡፡ ለብዙ ሰዎች እኩለ ጾም ከሥጋና ከስካር ከተላቀቁ አንድ ወር መሆኑን ለመገናኘትም ወር እንደሚቀራቸው የሚያስቡበት ቀን ነው፡፡ በጊዜያዊ ጨዋነት የሰነበቱትም ሲሰክሩ የሚውሉበት የተውኔት ቀናቸው ነው፡፡ ሃይማኖት የማይሞት ኃይል ነው፡፡ ከሰው ልብ ግን ሊሞት የሚችለው ሰዎች እንደ ባሕል ቆጥረውት ሲኖሩ ነው፡፡ 


የጌታችን መምጣት ግን የጸሎታችን መልስ ነው፡፡ የምንፈራውና ያርቅልኝ የምንለው ሳይሆን በየዕለቱመንግሥት ትምጣእያልን የምንጸልይበት ትልቅ ርዕሳችን ነው፡፡ የዚህ ዓለም መንግሥት በግፍ ተጀምሮ በግፍ የሚጠናቀቅ፣ በውሸትና በሐሰተኛ ተስፋ ሰውን የሚያደክም፣ በጭካኔ ሲወዳደር የሚኖር፣ ደም በደም የሆነ መንገድ ነው፡፡ በዚህ ክፉ ሥርዓት የተጨነቁ ሁሉ ጽድቅና ሰላም የነገሠባትን የክርስቶስን መንግሥት ይናፍቃሉ (ሮሜ. 14÷17)፡፡ የክርስቶስ መንግሥቱ የምትገለጠው ጌታችን ምድራውያን ነገሥታትን አሳልፎ ንጉሠ ነገሥት ሆኖ በሚነግሥበት በዳግም ምጽአቱ ነው፡፡ ዳግም ምጽአቱ ምድራዊውን ሥርዓት አሳልፎ አንድ መንግሥትን በሁሉ የሚያፀና ነው፡፡ 


የአዲስ ዓለም ጅማሬ ነው

በዮሐንስ ራእይ ላይ እንደ ተጻፈውአዲስ ሰማይና አዲስ ምድርን አየሁ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና፤ ባሕርም ወደፊት የለምይላል (ራእ. 21÷1)፡፡ አዲስ ነገር የሚያስፈልገው ፊተኛው ሲያረጅ ነው። ያረጀ ነገር መልኩ የወየበ፣ ጉልበቱ ያለቀ፣ ወደፊት ሊጠቅም የማይችል ነው፡፡ አሁን ፍጥረት አርጅቷል፡፡ በረዶ እየቀለጠ፣ የምድር ሙቀት እየጨመረ፣ መሬቱ ማዳበሪያ እየፈለገ፣ ሰውም በብዙ መድኃኒት እየኖረ ነው። ይህ የማርጀት ምልክት ነው፡፡ ይህን አዲስ የሚያደርገው የክርስቶስ መምጣት ነው፡፡ ሰውም ሞት ላይዘው በትንሣኤ፣ የሚመጣው ዓለምም ማርጀት ላያገኘው በአዲስነት ይኖራል፡፡ 

የዘላለም ሕይወት መክፈቻ ነው

ጌታችን ሲመጣ ዘላለማዊት የምትሆን መንግሥተ ሰማያት ትከፈታለች፡፡ ዛሬ በክርስቶስ ያመኑ በበጎ ሥራ የፀኑ አማንያን በጊዜያዊ ማረፊያቸው በገነት ይኖራሉ፡፡ ገነት ጊዜያዊ የነፍሶች ማረፊያ ናት፡፡ ክርስቶስ ሲመጣ ገነትና ሲኦል ያልፋሉ፡፡ መንግሥተ ሰማያትና ገሀነመ እሳት ይከፈታሉ (ማቴ. 25÷34.41)፡፡ 


የጌታችን መምጣት ብዙ ትርፎች ያሉት ወደማይነገርም ክብር የምንገባበት ነው፡፡ ዛሬ በዓለም ላይ የምናየው መከራና ሰቆቃ የምጽአቱ ዋዜማ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ጭንቅ በክርስቶስ መምጣት ይጠናቀቃል፡፡አሜን ጌታ ኢየሱስ ሆይ ቶሎ ” /ራእ.22÷20/