Saturday 2 June 2012

“ርግብ”


ቅ/አውግስጢን “እንደ ርግቦች እንጣላለን እንጂ እንደ ተኩላዎች ፈጽሞ አንፋቀርም!!” ብሏል ርግቦች እርስ በእርስ ይጠባበቃሉ፣ ለመመገብ አንድ ይሆናሉ፤ አንድ ላይም ይበራሉ! አንድም መንፈስ ቅዱስ በርግብ ይመሰላል። ርግብ ኃዳጊተ በቀል በቀልን የማትይዝ ናት። መንፈስ ቅዱስም ኃዳጌ በቀል ነውና። አንድም ርግብ ክንፏን ቢመቱባት ዕንቍላልዋን ቢሰብሩባት ቤቷን ካላፈረሱባት አትሄድም። መንፈስ ቅዱስም ኃጢአት ቢሰሩ ፈጽሞ ካልካዱ በስተቀር አይለይምና በርግብ ተመሰለ።

አንድ የተከበሩ አባት “እንደ ርግብ እንጂ እንደ ግመል አትኹኑ” ማለትን ያዘወትሩ ነበር። ብዙም አልገባኝምና ቀረብ ብዬ አባቴ ሆይ ምን ማለት ይሆን አልኳቸው። ፍግግ ብለው እያዩኝ እንዲህ አሉኝ።

 “ልጄ ሆይ ዓለም አቀፍ የሰላም ምልክት ርግብ ናት። ርግብ የዋህና ሰላማዊ ናት። ግመል ግን በቀለኛ ናት። አጥብቆ የመታትን እስከ ስድስትና ሰባት አመት አትረሳም! ቀን ሲመቻት ትረግጠዋለች ስፍራ ሲመቻት ገፍታ ገደል ትጥለዋለች። እኛ ግን ግመልን እንጠቀምባታለን እንጂ ባሕርይዋን አንጠቀምም አንወደውምም” አሉኝ የተከበሩት አባት አሁንም ፍግግ እያሉ። አባባላቸው ማረከኝ። ጠጉሬን እየዳሰሱ ወርቅ አባባላቸውን እንዲህ እያሉ ይመርቁልኝ ዠመር። ልጄ ሆይ “እንደ ርግቦች እንጣላለን እንጂ እንደ ተኩላዎች ፈጽሞ አንፋቀርም!!” ሐሳብ ተለዋውጠው እንደ ጉድ ተወያይተው እንደ ጉድ ተከራክረው በመጨረሻ የሚግባቡ ርግቦች ደስ ይላሉ። ልጄ ሆይ እንደ ተኩላ ከምትፋቀር እንደ ርግብ ያጣላህ አሉኝ። እኔም ጉልበት ስሜ ተሰናበትኳቸውና ይህችን ጽሑፍ መጻፍ ዠመርኩ።




“በኢየሩሳሌም ቆዩ”!

ኢየሩሳሌም ማለት የሰላም ከተማ ማለት ነው። ደቀመዛሙርቱም ኃይለ መንፈስ ቅዱስን ከሰማይ እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ቆዩ” ተብለው ነበር። ሁለት ደቀ መዛሙርት ግን ይህን ቃል ረሱና ከኢየሩሳሌም ከተማ ወጡ! እነማን ይሆኑ?

እነሆ ሁለት መንገደኞች የጌታችንን ነገረ ሕማሙን የእለተ አርብ የቀራንዮ ውሎውን እየተነጋገሩ ከኢየሩሳሌም 11 ምዕራፍ ወደምትገኘው ወደ ኤማሁስ ይጓዙ ነበር። ጌታችን ያዘዛቸው ግን ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡ ነበር። የኤማሁስ መንገደኞቹ ሉቃስና ቀልዮጳ ይህን ቃል ረሱና ከኢየሩሳሌም ለመውጣት ጉዟቸውን ጀመሩ።

የኤማሁስ መንገደኞቹ በጉዟቸው ላይ ይነጋገሩ የነበረው ስለ ቃለ እግዚአብሔር ነበርና ቃል” በመካከላቸው ተገኘ። ሁለት ወይም ሦስት ሆናችሁ በስሜ ብትሰበሰቡ በመካከላችሁ እገኛለሁ ያለ ጌታ በመካከላቸው ተገኘ። ልባቸውን ከፈተ። ያን ጊዜም በኢየሩሳሌም ቆዩ” የሚለው ቃል ትዝ አላቸውና በዛች ሰአት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። ሉቃስ [24: 13-33]

ይህ ወንጌል እኛም እንደ ኤማሁስ መንገደኞች ስለ ነገረ ቤተክርስቲያን እየተነጋገርን ከቤተክርስቲያን እርቃ ወደምትገኘው ወደ ዓለም እንዳንጓዝ ያስተምረናል። በተለያዩ ምክንያት ከቤተክርስቲያን ስንርቅ በሥጋም በነፍስም መጠውለግ ቀጥሎም መድረቅ ይመጣል! ለዚህ እኮ ነው ጌታችን “እየጠወለጋችሁ ስትሄዱ እርስ በእርሳችሁ የምትነጋገሩት ስለምንድን ነው?” ያለው። ሉቃስ [24:16]

ኢየሩሳሌም”
ጌታችን መከራ መስቀልን የተቀበለው፣ የሞተው፣ የተቀበረው፣ የተነሣውና ያረገው በኢየሩሳሌም ነው። በመሆኑም ለክርስቲያኖች የተቀደሰች ከተማ ናት። ሐዋርያት ጸጋ መንፈስ ቅዱስን እስከሚቀበሉ ድረስ በጸሎትና በጾም የተጉት በኢየሩሳሌም ነው። መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያቱ የወረደው፣ የመጀመሪያዎቹ 3000 ምዕመናን ቤተ ክርስቲያንን የመሰረቱት በኢየሩሳሌም ነው። ቀዳሜ ሰማዕት ቅ/እስጢፋኖስ በድንጋይ ተወግሮ የሞተው፣ ከሐዋርያት የመጀመሪያ ሰማዕት ቅ/ያዕቆብ በሰይፍ የተከለለው በኢየሩሳሌም ነው። የመጀመሪያው ሲኖዶስ የተካሄደውም በዚህች ታሪካዊት ከተማ በኢየሩሳሌም ነው።

ኢየሩሳሌም በዕብራይስ ቋንቋ “ይሩሻሌም” ስትባል የሰላም ከተማ ማለት ነው። በአሁኑ ዘመን ዓረቦች አል-ቁዱስ ብለው ይጠሯታል። የኢየሩሳሌም የመጀመሪያ ስም “ሳሌም” ይባላል። ይህም “ሰላም” ለማለት ነው። ኢየሩሳሌም ተብላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠራችው በመፅሐፈ ኢያሱ 10: 1 ላይ ነው።  በሌላ በኩል ኢየሩሳሌም ጽዮን  ተብላ ተጠርታለች። ይህም በተመሰረተችበት ተራራ ለመጥራት ሲሆን፣ ሞርያ ደግሞ በሌላኛው በኩል የሚገኘው የተራራዋ ስም በመሆኑ ነው። ይህ ተራራ አብርሐም ይስሐቅን ለመሥዋዕትነት ያቀረበበት፣ በኋላም ንጉሥ ሰለሞን ቤተ መቅደሱን የሰራበት ተራራ ነው።

“በኢየሩሳሌም ቆዩ”!
አማናዊት የሠላም ከተማ ኢየሩሳሌም የተባለችው እመቤታችን ናት፤ ዳዊት በበገናው ዕግትዋ ለጽዮን /ጽዮንን ክበብዋት/ መዝ [47: 12] እንዳለ 72ቱ አርድእት 36ቱ ቅዱሳን አንዕስ 12 ሐዋርያቱ በአጠቃላይ 120ው ቤተሰብ  እመቤታችን በመካከላቸው አድርገው ዙሪያዋን ከበው ለጸሎት ይተጉ ነበር፤ ያን ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያቱ ወረደ! ይለናል የሐዋ [1: 14]

የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ!”

በማርቆስ እናት በማርያም ባውፍልያ ቤት በላይኛው ፎቅ መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያቱ ወረደ፤ የሐዋ [2: 1] መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያቱ ላይ ወረደ ማለት መንፈስ ቅዱስ በአካል በሐዋርያቱ ላይ ወረደ ማለት አይደለም። ብዙዎቻችን ይህ ይመስለናል። ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያቱ ላይ ወረደ ሲባል በአካል ወረደ ማለት ሳይኾን በጸጋ በሐዋርያቱ ላይ ወረደ ማለት ነው። ይበልጥ እንዲገባን ምሳሌ እንይ።

አንዱ የተመረጠው ዲቁና ሊቀበል ቀረበ እንበል። ሕዝቡ በተሰበሰበበት በቤተክርስቲያን ጳጳሱም ተገኝተው ጸልየው እፍ እያሉ ንሳ መንፈሰ ቅዱሰ /መንፈስ ቅዱስን ተቀበል/ ይሉታል። ያ ሰው መንፈስ ቅዱስን ተቀበለ ማለት የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ አደረበት ማለት ነው እንጂ መንፈስ ቅዱስ በአካል መጥቶ አደረበት ማለት አይደለም። ይህማ ከሆነ መንፈስ ቅዱስ በአንድ ሰው ተወሰነ ማለት ይሆናል። ይህ ደግሞ ስህተት መኾኑ ግልጽ ነው። አንድም መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያቱ ላይ በአካል ወረደ ካልን ሐዋርያቱ የጸጋ ሳይኮን የባሕርይ አምላክ ሆኑ ማለት ነውና ይህን ልብ ብለን ልንረዳ ያስፈልጋል። መንፈስ ቅዱስ በሰዎች ላይ የሚወርደው በጸጋው ነው እንጂ በአካሉ አይደለም።

“የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በሐዋርያቱ ላይ የወረደበት ደገኛይቱ ቀን!”

እስራኤላዊያን በአመት አንዴ ለመስገድ ወደ ኢየሩሳሌም ይሄዱ ነበር፤ ኢትዮጲያዊው ጃንደረባ /ባኮስ/ ወደ ኢየሩሳሌም የሄደውም በዚህ በዓል ምክንያት ነው፤ ይህም በዓለ ሰዊት /የእሸት በዓል/ በመባል ይታወቃል። ከየሃገሩ የመጡ እስራኤላዊያን እንዴት ይግባባሉ? ቢባል እነሆ እስራኤላዊያን የሚታወቁበት ጥሩ ባህል አላቸው፤ አራቱ የአይሁድ ወገኖች /ፈሪሳዊያን፣ ሰዱቃዊያን፣ኤሴናዊያንና ቀናዕያን/ የትም ሀገር ቢኖሩ ባህላቸውንና ሃይማኖታቸውን ቢሞቱ አይደባልቁም! አይረሱምም! በፍልስጤም ምድር ቋንቋችንን አንናገርም ያሉ ቀናዕያን የተባሉ አይሁድም ነበሩ። አፍቃሬ ወግ የሆኑ ፈሪሳዊያንም ባህላቸው እንዲነካባቸው አይፈቅዱም፤ ምንም እንኳን እንደ ፈሪሳዊያንና ቀናዕያን እንሁን ባይባልም  ባህላችንን በአውሮባ እርሾ እንዳንደባልቅ ግን በአንድም በሌላም ያስተምረናል። ዛሬ በውጭው አለም የሀገሩን ባህል የማያውቅና የሀገሩን ቋንቋ የማይናገር ብሎም ቋንቋውን ጭራሽ የማይሰማ ትውልድ ብቅ እያለ ነው፤ ልጆቻችንን የሀገራቸውን ባህል በሚገባ በማስተማር ከትውልድ ወቀሳ መዳን አለብን።
ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስ፤ እስራኤላዊያኑ ምንም እንኳን በስደት ሀገር ቢኖሩም የራሳቸውን ቋንቋ ልጆቻቸው ጭምር በሚገባ ስለሚያውቁ በትውልድ ቋንቋቸው ማለትም በአረማይክ በዕብራይስጥ እና በዘመኑ ኢንተርናሽናል ቋንቋ በነበረው በግሪክ እርስ በእርሳቸው ይግባቡ ነበር። በአንድ ወቅት ግን ያልተለመደ እንግዳ ነገር ተፈጠረ! ከተለያዩ ሀገራት የመጡት አይሁድ በኢየሩሳሌም በተገኙበት በዛች ደገኛዋ ቀን መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያቱ ወረደ! ሐዋርያቱም አይሁድን በመጡበትን ሀገር ቋንቋ አናገሯቸው! ይህን ጊዜ አይሁድ ጉድ እንግዳ ነገር ብለው እጃቸውን በአፋቸው ላይ ጫኑ! ይህ ነው የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ!

አዳምና እንስሳቱ የሚግባቡባት አንድ ቋንቋ ነበረች፤ አዳም ለእንስሳቱ ስም ያወጣላቸውም ነበር፤ አዳም ሲበድል የሰውና የእንስሳት ቋንቋ ተከፈለ። ባቢሎን ማለት የተደበላለቀ ማለት ነውና ባቢሎናዊያን ሲበድሉም ቋንቋቸው ተደበላለቀ። 

ቋንቋ ለሐዋርያቱ የተሰጠበት ምክንያትም በአለም እየዞሩ ወንጌልን እንዲያስተምሩበትና በቋንቋ ምክንያት አገልግሎታቸው እንቅፋት እንዳያገኘው ነው። የሐዋርያው ቶማስ ስብከት እስከ ሩቅ ምሥራቅ ቻይና ድረስ ደረሰ! የቋንቋ ስጦታ ይህን ለመሰለ አገልግሎት ነው እንጂ መግባባት የሚቻልበት ቋንቋ እያለን የማይገባ ቋንቋ እንድንናገር አይደለም።

ጅብ ከጅብ ይግባባል
ወፍ ከወፍ ይግባባል
እንስሳቱ ኹሉ ይግባባሉ
ቋንቋ የሌለው ሕዝብ ፤ ሕዝብ የሌለው ቋንቋ ከቶ አልተፈጠረም።


ትዝ የሚላችኹ ከሆነ ባለፈው ሳምንት ስለበዓለ ዕርገቱ ስናነሳ ጌታችን ሞትን ድል አድርጎ ከተነሳ በኋላ ለ40 ቀናት ለሐዋርያቱ እየተገለጸ ያስተምራቸው ነበር ብለናል   
[ሐዋ. 1:3] አርባው ቀናት ሲፈጸም ዓረገ። ባረገ በ10ኛው ቀን መንፈስ ቅዱስን ላከላቸው። እስከዚያው የት ነበር?


እነኾ በ9ኙ ከተማ የነበሩት መላእክት ሚሥጢረ ሥጋዌን ያላወቁ ነበርና ለመላእክቱ ሲያሳውቃቸው ነበር።




“መንፈስ ቅዱስ ከጥምቀት እስከ ትንሣኤ ዘጉባኤ”

አንድ ሰው በጥምቀት መንፈስ ቅዱስን ከተቀበለ በኋላ ክህደት ካልፈጸመ በቀር መንፈስ ቅዱስ ከእርሱ ፈጽሞ አይለይም፡፡ ስንሞትም መንፈስ ቅዱስ አይለየንም! ለዚህ ነው መንፈስ ቅዱስ ያልተለየው የነብዩ ኤልሳዕ ዐፅም የሞተውን ያስነሳው 2ኛ ነገሥት [13:21] በነገራችን ላይ የሞተውን ያስነሳው የኤልሳዕ ዐፅም በግብፅ ገዳመ አስቄጥስ ይገኛል። ቅዱሳን ጻድቃን እና ሰማዕታት ምንም ተፈጥሮአዊቱ ነፍስ ከሥጋቸው ብትለይም ከእነርሱ ሰውነት መንፈስ ቅዱስ አድሮ ስለሚገኝ አጋንንት በእነርሱ አስከሬን ፊት ጸንተው መቆም አይቻላቸውም፡፡ ወይም በእነርሱ አካል አድሮ በሚኖረው መንፈስ ቅዱስ ምክንያት ሲጮኽ ይስተዋላሉ፡፡ እንዲሁም በእነርሱ ዐፅም ተዓምራት ሲፈጸም፣ ሕመምተኞችም ከሕመማቸው ሲፈወሱ እንመለከታለን።

መንፈስ ቅዱስ ከትንሣኤ በኋላም አይለየንም! ከትንሣኤ በኋላ ነፍስ ወደ ማደሪያዋ ሥጋ ስትመለስ በእነርሱ ውስጥ መንፈስ ቅዱስ አድሮ ይኖራል፡፡ ከእነርሱ ፈጽሞ አይለይም። ስለዚህም ነው ጻድቃን ነፍሳቸው ከሥጋቸን ስትለይ አረፉ እንጂ ሞቱ የማንለው፡፡

መንፈስ ቅዱስ (ፓራክሊቶስ)

መንፈስ ቅዱስ በጽርኡ ፓራክሊቶስ ፣ ፔንዲኮንዳ ሲባል አረጋጊ አጽናኝ አስደሳች ማለት ነው።

* በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቁ። ማቴዎስ [28:19] በመንፈስ ቅዱስ ስም እንጠመቃለን። ፍጡር ነው ለሚሉት ግን በፍጡር ስም እንጠመቃለን ማለታቸው እንደኾነ ሊረዱት ይገባል።

የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ
የእግዚአብሔር ፍቅር
የመንፈስ ቅዱስም ሕብረት
ከሁላችን ጋር ይኩን። አሜን።
2ኛ ቆሮንቶስ [13: 14] ቅ/ጳውሎስ መንፈስ ቅዱስ የባሕርይ አምላክ መሆኑን ለማስረዳ ይህን የመሳሰሉ ብዙ ጥቅሶችን ጽፋል።

የእግዚአብሔር ቀኝ ኃይልን አደረገች
የእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ አደረገች
የእግዚአብሔር ቀኝ ኃይልን አደረገች
መዝ [117 (118):16] ቃላቱ የተደጋገመበት ምክንያት አለው።
አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስን ሲነግረን ነው።



* መንፈስ ቅዱስ “መንፈስ” ስለተባለ አካል የለውም የሚሉ አሉ። እግዚአብሔር መንፈስ ነው” ሲል እግዚአብሔር አካል የለውም ማለት አይደለም። ዮሐንስ [4: 24] አንድም ጌታችን ሲጠመቅ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል በራሱ ላይ አርፏል። አካል ባይኖረው በርግብ አምሳል አይገለጽም ነበር። አንድም ጌታችንን አብና መንፈስ ቅዱስ ልከውታልና “እግዚአብሔርና መንፈሱ ልከውኛል” የሚል ቃል አለ። ኢሳይያስ [48:16] “ልከውኛል” የሚለው ቃል ኹለት መኾናቸውን ያሳያል። እነሱም አብና መንፈስ ቅዱስ ናቸው።

ወንጌሉ እንዳለው አንድ ገበሬ ዘር ሊዘራ ወጣ። መልካሙንም ዘር ዘራ። ጠላት መጥቶ እንክርዳዱን ዘራ። ይህም ምሳሌ ነው። መልካሙን ዘር ሐዋርያት ከዘሩ በኋላ  ዲያቢሎስ በአርዮስ አድሮ እንክርዳዱን ዘራ። አንድም አርዮስን ካወገዙት አበው በኋላ እነ መቅደንዮስና ንስጥሮስ እነ ሰባልዮስና አርጌንስ እንክርዳዱን ዘሩ። መቅደንዮስ መንፈስ ቅዱስ ፍጡር ነው ብሎ ተነሳ። መንፈስ ቅዱስን የካደ በዚህም ሆነ በወዲያኛው ዓለም ይቅር አይባልም። ማቴዎስ [12:32] ለምን በወዲያኛውም ዓለም ተባለ ልንል እንችላለን። አልቦቱ ለሰብእ ንስሐ እምድኅረ ሞት እንዲል በወዲያኛው ዓለምማ ንስሐ የለም ለምን መጥቀስ አስፈለገ ቢሉ እነሆ ኃጢአትን ለካህን ነግሮ ቀኖና ጀምሮ ቢሞት ሳይጀምረውም ቢሞት መካነ ንስሐ አለ ከዚያ አድርሶ ይወጣልና ይህን ለማሳየት ነው ። መንፈስ ቅዱስን የካደ ግን መካነ ንስሐ አይገባውም። በዚህም ሆነ በወዲያኛው ዓለም ይቅር አይባልምና።

*****************
ይወርድ መንፈስ ቅዱስ በላለ ህብስቱ ወወይኑ ሶበ ይብል ካህን “ፀጋ መንፈስ ቅዱስ ፈኑ”

As the priest says let the holy sprite descend,
On this revered Holy of the holies

ፈኑ ፀጋ መንፈስ ቅዱስ ላዕሌነ
Send the grace of the holy sprite upon us

የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ላክልን”







በሕይወታችን ከክፉ ነገር ሁሉ በመውጣት መግባታችን የሚጠብቀን ፣በአገልግሎታችን የሚረዳንም እነሆ መንፈስ ቅዱስ ነው።

የመንፈስ ቅዱስ” ፍሬዎችም

ፍቅር
.
.
.
.
.

ትህትና
.
.
.
.
.
ትዕግስት
.
.
.
.
.

ሰላም ፣ ደስታ ፣ ቸርነት ፣ በጎነት ፣ ቅንነት ፣ የዋህነት፣ ራስን መግዛት፣ ታማኝነት ናቸው። ገላትያ 5:22











“ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ”




      እስራኤላዊያን ኀዘናቸውን የሚገልፁበት ለየት ያለ ባህላዊ አገላለጽ አላቸው፤ “ሲያዝኑ ልብሳቸውን ይቀዳሉ!ለምሳሌ የዳዊት ልጅ አምኖን በገዛ እህቱ በትዕማር ላይ የማይገባ ድርጊት ፈፀመ፤ አምኖን ትዕማርን በፈቃደ ሥጋ አስነወራት። ትዕማርም ልብሷን ቀደደች፤ ታላቅ ኅዘኗንም ገለፀች [2ኛ ሳሙ. 13:1]

       እስራኤላዊያን ደናግል ሴቶች የሚለብሱት እጅግ ያማረ ቀሚስ አላቸው፤ ድንግል አይደለንም ሲሉ ይህን ልብሳቸውን ይቀዳሉ፤ የዛሬ እህቶቻችን በሀገር ቤትም ኾነ በውጭው ዓለም ልብሳቸውን ሲቀዱ ምን ማለታቸው እንደሆነ ሊረዱ ይገባቸዋል ማለት ነው!

       ትዕማር ልብሷን ቀዳ ኅዘኗን እንደገለፀችው ኹሉ ሴኬም የተባለው ሰው የያዕቆብ ልጅ የነበረችውን ዲናን ባስነወራት ግዜ ልብሷን ቀዳ ታላቅ ኅዘኗን ገልፃለች [ዘፍ. 34:1]

        እነኾ እስራኤላዊያን ኅዘናቸውን የሚገልፁት ልብሳቸውን በመቅደድ እንዲህ ባለ መልኩ ነው፤ በዚህ ምክንያት ነበር እግዚአብሔር በነቢዩ ኢዩኤል አድሮ እንዲህ ያለው፦

“ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ” በፆምና በፀሎት በፍፁም ልባችሁ ወደ እኔ ተመለሱ [ኢዩኤል2:12]    
    

ነቢያት በቀየሱ ሐዋርያት ገሠገሡ! እንኳን ለጾመ ሐዋርያት በሰላም አደረሳችኹ።
ሰውን እንደ ዓሣ ወንጌልን እንደ መረብ ይህችን ዓለም እንደ ባሕር አድርጋችኹ አስተምሩ አላቸው።

ጾመ ሐዋርያት   እስራኤላዊያን በአንድ ወቅት ለምን ጾማችን በእግዚአብሔር አይሰማም? ብለው ይጠይቁ ነበር፤ በውኑ ብዙ ግዜ ጾማችን የማይሰማው ለምን ይሆን? ለዚህ የእስራኤላዊያን ጥያቄ ነቢዩ ኢሳይያስ ድምፁን ከፍ አድርጎ  ለእስራኤላዊያን  መለሰላቸው፤ እነኾ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦

በውኑ እኔ የመረጥኩት ፆም ይህ ነውን? ፆማችሁ በጥልና በክርክር የተከበበች ናት፤ የልባችሁን ሁሉ ትፈጽማላችሁ፤ በውኑ እኔ የመረጥኩት ፆም ይህ ነውን? ኢሳ 58:5


ዛሬም እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ እኛን ይጠይቀናል “በውኑ እኔ የመረጥኩት ጾም ይህ ነውን”? እግዚአብሔር የመረጠው ጾም ምን አይነት ጾም ይሆን? መልሱን በወንጌል ላይ እንዲህ እናገኘዋለን፦ ስትጾሙ እንደግብዞች አትጠውልጉ ፊታችሁን በፍቅር ቅባት ተቀብታችሁ የምትጾሟት ጾም ታላቅ ዋጋ አላት [ማቴ. 6: 16]

ልበ አምክ ዳዊት ከመጾሙና ለመዘመር በገናውን ከመደርደሩ በፊት እንዲህ አለ፦
አቤቱ ንፁህ ልብን ፍጠርልኝ// ልበ ንጹኃ ፍጥር ሊተ እግዚኦ [መዝ. 50: 10] ዳዊት ንጹህ ልብን ፍጠርልኝ ብሎ ከለመነ በኋላ በገናውን እየደረደረ ዘመረ ጾመ ጸለየ ፤ ጾምና ዝማሬውም በእግዚአብሔር ተሰማች! እኛም ለመዝሙር በገና ከመደርደራችን፤  ከመጸለያችንና ከመጾማችን በፊት አቤቱ ንፁህ ልብን ፍጠርልኝ ማለት እንዳለብን ልበ አምላክ ዳዊት አስተማረን።

ጌታችን ሦስቱን አእማደ ሐዋርያት ቅ/ጴጥሮስ ፣ቅ/ዮሐንስና ቅ/ያዕቆብን አስከትሎ ወደ ደብረ ታቦር ተራራ ወጣ። ቀሪዎቹ 8 ሐዋርያት ይሁዳን ጨምሮ ከታቦር ተራራ ስር ነበሩ። አንዱ ወደ ሐዋርያቱ መጣና ልጄን ጋኔን ይዞታልና ፈውሱልኝ አላቸው። ሐዋርያቱ ግን ጋኔኑን ሊያወጡ አልቻሉም። ለምን? መልሱ ለጊዜው ይቆየን።

ጌታችን ብርኅነ መለኮቱን ለሐዋርያቱ ካሳያቸው በኋላ ከታቦር ተራራ ወረደ። ያ ሰው ወደ ጌታችን ሰግዶ ጌታ ሆይ ልጄን ጋኔን እጅግ ያሰቃየዋል። በእሳትና በውኃ ላይ ይጥለዋል። ብርድ ብርድ ያሰኘዋልና እባክህ ፈውስልኝ ሐዋርያቱ ጋኔኑን እንዲያወጡልኝ ብለምን አልቻሉም አለው።

ጌታችንም ዝንቱ ዘመን እይወጽእ ዘእንበለ በጾም ወበ ጸሎት

ይህ ክፉ ጋኔን ያለጾምና ያለ ጸሎት አይወጣም አላቸው።

ሐዋርያቱም ጋኔኑን ሊያወጡ ያልቻሉት ገና ጾም ስላልጀመሩ ነበር። [ማቴ. 17: 21]

ጾም አጋንንትን እንዃን የማስወጣት ታላቅ ኃይል አለው!!!  ነገር ግን የመናፍቃኑን መፅሐፋ ቅዱስ ስንመለከት ይህን ቁጥር ዘለውታል! ጾም አጋንንትን ለማውጣት ኃይል እንዳለው ስለሚናገር የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 17 ቁጥር 21 የሚለው እንዳለ ተዘሏል!

አንድም አማን አማን እብልክሙ እመብክሙ ሃይማኖት መጠነ ሰናፔ (እውነት እላችኋላሁ የሰናፍጭ ቅንጣት ፍጽምት እምነት ቢኖራችሁ ይህን ተራራ ከዚህ ተነስተህ ወዲያ ሒድ ብትሉት ይኾናል። ተራራ የተባለው ዲያቢሎስ ነው። እምነት ቢኖራችሁ ከዚህ ወጥተህ እዚያ ግባ ብትሉት ከዚህ ወጥቶ ወዲያ ይገባልና አጋንንት ይወጣላችኋል ሲል ነው። አንድም ፍጹምት እምነት ቢኖራችሁ ይህን ተራራ ከዚህ ተነስተህ ወዲያ ሒድ ብትሉት ይኾናል አለ። ይህም በስምኦን ጫማ ሰፊው የተደረገ እውነታ ነው።


 ጌታ ተዓምራት ከማድረጉ በፊት እኛን ሊስተምረን ጾመ ፣ እነ ዳዊት ንጉሥ ኾነው ሳለ ጾሙ ፣ ነብያቱ ሁሉ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሰው መሆን በተስፋ እየተጠባበቁ  ጾሙ ፣ ሐዋርያቱም ከአገልግሎታቸው በፊት   ጾሙ!

ጾምሰ እማ ለፀሎት ወእህታ ለአርምሞ ወነቃየ ለአንብዕ // ጾም የጸሎት እናት የትዕግሥት እህት የንስሐ ዕንባ ምንጭ ናት!!


በየአመቱ በዕለተ ሰኑይ ብቻ (ሰኞ ቀን ብቻ) የሚጀምሩ ሦስት አጽዋማት አሉ፡፡ እነርሱም ዓቢይ ጾም፣ ጾመ ነነዌ እና ጾመ ሐዋርያት ናቸው፡፡ እነዚህ አጽዋማት ምን ጊዜም ቅበላቸው እሑድ ሲሆን የሚገቡት ደግሞ ሰኞ ቀን ነው፡፡ በየትኛውም አመት ይህን ዕለት አይለቁም፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ በየግላችንም ያጋጠሙንን መንፈሳዊና ሥጋዊ ውጊያዎች በማሰብ ድል የምናደርግበትን ኃይል ፈጣሪያችን ይሰጠን ጾሙን ከወትሮው በበለጠ ጥንቃቄ ልንጾመው ይገባናል፡፡

ጾመ ሐዋርያት በራሳቸው በሐዋርያት የተጀመረ ጾም እንደመሆኑ መጠን በአንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማለትም ከዛሬ አንድ ሺህ ዘጠኝ መቶ ዓመታት በፊት ጀመሮ ሲጾም የኖረ ጾም ነው፡፡ ለዚህም የመጽሐፍ ቅዱስ፣ የአዋልድ መጻሕፍትና የታሪክ በርካታ ምስክሮች አሉ፡፡ ስለዚህ ጾሙን እንደ እንግዳ ነገር መቁጠርና ዘመን አመጣሽ አድርጎ ማየት የራስን አላዋቂነት ያሳያል፡፡ ይህን ማለት ያስፈለገው ጥቂቶች ጾሙን ድሮ ያልነበረና ዘመን አመጣሽ አድርገው ስለሚናገሩ ነው፡፡ 

     ጾመ ሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን ዕድሜያቸው ለጾም የደረሱ ምእመናን በሙሉ እንዲጾሙአቸው ካወጀቻቸው ሰባት የአዋጅ አጽዋማት መካከል አንዱ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በጌታችንና በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ አንደበት ቀን የተቀጠረለት፣ ትንቢት የተነገረለትና ምሳሌ የተመሰለለት ጾም መሆኑ ከአጽዋማት ሁሉ ለየት ያደርገዋል።

ጌታችን ስለዚህ ጾም ትንቢተ በመናገር፣ ምሳሌ በመመሰል ሰፊ ትምህርት የሰጠው ፈሪሳውያን ወደ እርሱ ቀርበው ‹‹ደቀ መዛሙርትህ የማይጦሙት ስለ ምንድር ነው›› ብለው በጠየቁት ጊዜ ነው፡፡ እርሱም ሲመልስ እንዲህ አላቸው፡- ‹‹ሚዜዎች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ ይችላሉን? ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል$ በዚያ ጊዜም ይጦማሉ፡፡ በአረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚያኖር የለም፤ መጣፊያው ልብሱን ይቦጭቀዋልና$ መቀደዱም የባሰ ይሆናል፡፡ በአረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን አቁማዳው ይፈነዳል የወይን ጠጁም ይፈሳል፡፡ አቁማዳውም ይጠፋል፡፡ ነገር ግን አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ያኖረዋል ሁለቱም ይጠባበቃሉ፡፡›› (ማቴ9.14-17) በመቀጠል እስከ መጨረሻ የምንመለከተው ከላይ የሰፈረውን የሉቃስ ወንጌል አጭር ገጸ ንባብ ሐሳብ በመሆኑ መለስ እያሉ ታሪኩን ማንበብ ወይም በልብ ከመዘገቡ በኋላ ቀጣዩን ክፍል ማንበብ ምሥጢሩን ለመረዳት ያግዛል፡፡


      በዚህ የጌታችን መልስ ውስጥ ‹‹ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል በዚያ ጊዜም ይጦማሉ፡፡›› የሚል ስለ ጾመ ሐዋርያት የተነገረ የትንቢት ቃል እናገኛለን፡፡ ይህ አምላካዊ ቃል ጾሙ ስለሚጀመርበት ወራት ቀጠሮ ይሰጣል፡፡ ያም ጊዜ ሙሽራው ከእነርሱ ከተወሰደ በኋላ ያለው ጊዜ ነው፡፡ ‹‹ሙሽራው ከተወሰደ›› በኋላ ማለት ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ ማለት ሲሆን በቤተ ክርስቲያን ጾመ ሐዋርያት ከዕርገት በኋላ የሚጀምረው በዚህ ቃል ምክንያት ነው፡፡ ይህም ቤተ ክርስቲያን ምን ያህል መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያላት መሆኗን ያሳያል፡፡

      ጾመ ሐዋርያት ከዕርገት በኋላ ለዐሥር ቀናት ያህል ዘግይቶ እንጂ ወዲያው አይጀምርም፡፡ ምክንያቱም የሐዋርያት ሰውነት በአዲስ ሁኔታ ጌታችን ላዘጋጀው የአዲስ ኪዳን ጾም ተመቻችቶ ያልተገኘ በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ በመጀመሪያ የሐዋርያት ሰውነት ለጾሙ መዘጋጀት ነበረበት፡፡ ከዚያ በኋላ ሐዋርያት መጾም ጀምረዋል፡፡ ይህም በጌታችንን የመልስ ቃል ውስጥ የተካተተ እንጂ የፈጠራ ድርሰት አይደለም፡፡ ‹‹በአረጀ ልብስ ላይ›› እና ‹‹በአረጀ አቁማዳ›› የሚሉት ሁለት ተከታታይ ምሳሌያዊ ማብራሪያዎች ሐዋርያት ሰውነታቸው በመንፈስ ቅዱስ ከመታደሱ በፊት ጾም መጾም እንደማይጀምሩ ወይም እንደሌለባቸው የሚያስረዱ ምሳሌዎች ነበሩ፡፡ ስለዚህ ሐዋርያት የተዘጋጀላቸውን ጾም መጾም የጀመሩት ከኢየሱስ ክርስቶስ ዕርገት በኋላ በዐሥረኛው ቀን በወረደ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ የሕይወት ሕድሳት አግኝተው ነው፡፡

      ከላይ በተጠቀሰው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት ውስጥ ስለ ጾመ ሐዋርያት የቀረቡ ሦስት ዓይነት ምሳሌዎችን እናገኛለን፡፡ ምሳሌዎቹ በምሥጢር የተሞሉ በርካታ መንፈሳዊ መልእክቶችን ያዘሉ ናቸውና ተራ በተራ እንመለከታቸዋለን፡፡

      1. ‹‹ሚዜዎች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ ይችላሉን?›› የሚለው ዐረፍተ ነገር በገጸ ንባቡ ውስጥ ስለ ሐዋርያት ጾም የተመሰለው የመጀመሪያው ምሳሌ ነው፡፡ ሚዜዎች የተባሉት እንደ መጥምቁ ዮሐንስ መንገድ የሚጠርጉ፣ የሚያስተምሩና ምእመናንን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚያቀረቡ ሁሉ ናቸው፡፡ ሙሽሪትን ወደ ሙሽራው መውሰድ የሚዜዎች ሥራ መሆኑ በአይሁድና በኢትዮጵያውያን ባህል ሲሠራበት የኖረ ነው፡፡ ስለዚህ ዋነኞቹ ሚዜዎች ሐዋርያት ናቸው ማለት ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ሙሽራ ሲሆን ቤተ ክርስቲያን (ምእመናን) ደግሞ መርዓት (ሴት ሙሽራ) ትባላለች፡፡ (2ቆሮ11.2 ዮሐ3.29)
‹‹ሚዜዎች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ ይችላሉን?›› ሲል ሚዜዎች ሙሽራውን ለማስደሰት ሲሉ ምንም የሚያሳዝን ነገር ቢያጋጥማቸውም እንኳን ጨክነው በመቻል ያሳልፉታል እንጂ በሙሽራው ፊት እንደማያዝኑ፤ እንደዚሁም መጾም ተገቢ ነገር ቢሆንም ሐዋርያት ኢየሱስ ክርስቶስ ከእነርሱ ጋር ሳለ መጾም እንደማይገባቸው ነገር ግን ከእነርሱ ተለይቶ ሲያርግ መጾም እንደሚጀምሩ ያስረዳል፡፡

በዚህ ምሳሌያዊ ንባብ ውስጥ ጾም በኀዘን ተመስሏል፡፡ መጾም ተድላነቱ ለነፍስ እንጂ ለሥጋ አይደለምና፡፡ ሥጋ ጾምን እስኪለምድ ድረስ ቅጣት ይሆንበታል፡፡ ስለዚህ በጾም ነፍስ ስትደሰት ሥጋ ግን ያዝናል፡፡ በዚህ ምክንያት ጾም በኀዘን ተመስሏል፡፡ በዚህም ምክንያት ጾም በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከኀዘን፣ ከዕንባ፣ ከጸጸትና ከንስሐ ጋር ተያይዞ ቀርቧል፡፡ (ኢዩ2.12)

2. ‹‹በአረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚያኖር የለም፤ መጣፊያው ልብሱን ይቦጭቀዋልና መቀደዱም የባሰ ይሆናል፡፡›› ይህ ዐረፍተ ነገር ደግሞ ሁለተኛው ምሳሌ ነው፡፡ እራፊ ማለት ቅዳጅ ወይም መጣፊያ ጨርቅ ማለት ነው፡፡ የስፌት ባለሙያ ባረጀ ልብስ ላይ አዲስ ጨርቅ አይጥፍም (አይሰፋም) ወይም አይለጥፍም፡፡ ይህም አንደኛ ግንጥል ጌጥ እንዳይሆን፤ ሁለተኛ ላሮጌ ልብስ ሲባል አዲሱን ማበላሸት እንዳይመጣና አዲሱ ካሮጌው ስለሚበረታ የባሰ እንዳይቦጭቀው በማሰብ ነው፡፡

በምሳሌው መሠረት በጣፊ ወይም በልብስ ሰፊ የተመሰለው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ በአዲስ እራፊ ጨርቅ ምሳሌነት የተወከለው ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ በአዲስ ኪዳን እንድንጾመው የሠራልን ጾም ነው፡፡ የተቀደደውና መጣፊያ የሚያስፈልገው ልብስ ደግሞ የሐዋርያት ሕይወት ምሳሌ ነው፡፡

እንደ ምሳሌው ሁሉ ሰዎች የክርስቶስ ልብሶች ይባላሉ፡፡ ‹‹አልባሲሁሰ ለክርስቶስ መሃይምናን እሙንቱ›› እንዲል፡፡ ይህም ‹‹የክርስቶስ ልብሶቹ ምእመናን ናቸው፡፡›› ማለት ነው፡፡ ክርስቶስም ለሰዎች ልብሳቸው ነው፡፡ ሐዋርያው ‹‹እናንተ የተጠመቃችሁ ክርስቶስን ለብሳችኋል›› ብሏልና፡፡ (ገላ3.27) ምእመናን የክርስቶስ ልብሶች ናቸው ማለት የክብሩ መገለጫዎች ናቸው ማለት ነው፡፡ ልብስ የክብር መገለጫ ይሆናልና፡፡ እርሱ ደግሞ ለምእመናን ልብስ ነው ማለት ጌጣቸው፣ ነውራቸውን የሚሸፍንላቸውና ክብራቸውም እርሱ ነው ማለት ነው፡፡

ጾም ‹‹እራፊ›› መባሏ ምሥጢር አለው፡፡ ይኸውም እራፊ የተለያየውን እንደሚያቀራርብና አንድ እንደሚያደርግ ጾምም የተለያዩ ፈቃዳት ያሏቸውን ነፍስና ሥጋ አንድ ታደርጋለች፡፡ ከዚህም በላይ ከእግዚአብሔር የተለየውን ሰውም አስታርቃ አንድ ታደርገዋለች፤ ከመንጋውም እንዲቀላቀል ትረዳዋለች፡፡

‹‹በአረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚያኖር የለም፤ መጣፊያው ልብሱን ይቦጭቀዋልና መቀደዱም የባሰ ይሆናል፡፡›› ማለት አንድ የስፌት ባለሙያ ባረጀ ልብስ ላይ አዲስ እራፊ እንደማይጥፍ ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስም የሐዋርያት ሰውነት በኃጢአት ያረጀ ሆኖ ሳለ በመንፈስ ቅዱስ ሳያድስላቸው አዲስ የሠራውን የአዲስ ኪዳን ጾም ጹሙ ብሎ ሐዋርያትን አያዛቸውም ማለት ነው፡፡ ሰውነታቸው ሲታደስ ያን ጊዜ ግን ይጾማሉ፡፡     

ይህ አገላለጥ እግዚአብሔር መንጋዎቹን ያለ አቅማቸው እንዲሸከሙ የማያደርግ አዛኝ ጌታ መሆኑን ያሳያል፡፡ እንዴት ቢባል ሐዋርያትን ሊፈጽሙት በማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ እያሉ እንዲጾሙ አላዘዛቸውምና፡፡ ፈጣሪ ለሕዝቡ መቼ ሕግ መስጠት እንዳለበት በሚገባ ያውቃል፡፡ ለእስራኤላውያን በባርነት ሳሉ ዐሥርቱ ትእዛዛትን ያልሰጣቸው ስለዚህ ነው፡፡ ቢሰጣቸውም ሊጠብቁት አይችሉም ነበርና፡፡ በባርነት ያለ ሰው የራሱ ነጻነት እስከሌለው ድረስ የፈቀደውን ማድረግ አይችልም፡፡ በታላላቅ ተአምራት ከባርነት ካወጣቸው በኋላ ግን ሕጉን ሰጣቸው፡፡ ስለዚህ ከክርስቲያን ወገን ማንም ቢሆን ከአቅሙ በላይ የሆነ ነገር ፈጣሪ እንዳዘዘው አያስብ፡፡ የታዘዝነው ሁሉ በዐቅማችን ልክ እንደሆነ እንመን፡፡

3. ‹‹በአረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን አቁማዳው ይፈነዳል: የወይን ጠጁም ይፈሳል፡፡ አቁማዳውም ይጠፋል፡፡›› ይህ ስለ ጾመ ሐዋርያት የተመሰለው ሦስተኛውና የመጨረሻው ምሳሌ ነው፡፡
በአረጀ አቁማዳ የተመሰለው ሐዋርያት በጸጋ መንፈስ ቅዱስ ሳይታደሱ በፊት የነበራቸው ሕይወት ሲሆን፤ በአዲስ ወይን የተመሰለው ደግሞ ጌታችን በወንጌል የመሠረተልን ጾም ነው፡፡ የጾም ሕግን የሰጠን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ደግሞ በጠጅ ጣዩ (በጠማቂው) ተመስሎ ቀርቧል፡፡ አዲስ ጠጅ ባረጀ አቁማዳ እንደማይጣል አምላካችንም ባልታደሰ ሕይወታቸው ሐዋርያትን እንዲጾሙ አላዘዛቸውም፡፡

ቀደም ሲል ጾም ሥጋን ለጊዜው ደስ ባለማሰኘቱ በኀዘን እንደሚመሰል ተመልክተን ነበር፡፡ አሁን ደግሞ በዚህ ምሳሌ ጾም ነፍስን ደስ የሚያሰኝ በመሆኑ በወይን ተመስሎ አገኘነው፡፡ ‹‹ወይን የሰውን ልብ ደስ ያሰኛል›› እንዲል፡፡ (መዝ103.15) ጠጅ ጣዮች ሲጥሉ (ሲጠምቁ) ተመልክታችሁ ታውቃላችሁ? አስቀድመው ቦታ ያዘጋጁለታል፡፡ እግር እንዳይበዛበትም ጥላ እንዳይወድቅበትም ይጠነቀቃሉ፡፡ እንዳይነፍስበትም ቀን ከሌሊት ይተጉለታል፡፡ በመጨረሻ ሥራው አልቆ ሳለ ጠጁ ከደረቀ (ከጠነከረ) ይላላ ብለው ማር ያልሱታል (ይበርዙታል)፡፡ ከላላ ደግሞ ይድረቅ ብለው ጊዜ ይሰጡታል፡፡

በጠጅ ለተመሰለ ለጾምም በዓይነቱ ተመሳሳይ ከጥቅሙ አኳያ ደግሞ የበለጠ ጥንቃቄ ሊደረግለት ያስፈልጋል፡፡ ለጠጅ ቦታ እንደሚዘጋጅለት ለጾምም ሰውነትን ማዘጋጀትና ጊዜና ዕለት ወስኖ መመደብ በአጠቃላይ ጾምን ማወጅ ይገባል፡፡ ስንዱ እመቤት ቤተ ክርስቲያናችን የአጽዋማት ዐዋጅ ስላላት እኛ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች የዚህ ችግር የለብንም፡፡ ለጠጅ እግር እንዳይበዛበትና ጥላ እንዳይድቅበት እንደሚጠነቀቁለት ጾማችንም በከንቱ ውዳሴ አጋንንት እንዳይገቡበትና ያለ መልካም ሥራ በጾም ብቻ ቀርተን ዋጋው እንዳያንስብን እየተጠነቀቅን መጾም ይገባናል፡፡ ጠጅ ደረቀ ይላላ፤ ላላ ይድረቅ እንደሚባል ጾማችን በሕግ ከተሠራልን በላይ ሰዓቱ እንዳይበዛና ከዓቅማችን በላይ አልፎ ሰውነታችን እንዳይጎዳ፤ እንደዚሁም የአጽዋማትን ሰዓት ሳንጠብቅ ቀርተንም መንፈሳዊ ሕይወታችን እንዳይላላ ማዕከላዊውን ስፍራ ይዘን በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት በጥንቃቄ መጾም እንደሚገባን ይህ ሦስተኛው ምሳሌ ያስረዳናል፡፡

ይህን ትምህርት ጌታችን መድኃኒታች ኢየሱስ ክርስቶስ የሚቋጨው ‹‹አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ያኖረዋል ሁለቱም ይጠባበቃሉ፡፡›› በሚለው ኃይለ ቃል ነው፡፡ ዐረፈተ ነገሩ አዲስ የወይን ጠጅ መጣል ያለበት በአዲስ አቁማዳ መሆኑን ይናገራል፡፡ ስለዚህ ሐዋርያት ሕይወታቸው በጸጋ መንፈስ ቅዱስ ከታደሰ በኋላ በአዲሱ አቁማዳቸው አዲሱን ወይን ጣሉ፡፡ ማለትም በአዲስ ሕይወት የአዲስ ኪዳንን ጾም (ጾመ ሐዋርያትን) መጾም ጀመሩ፡፡

አዲስ የወይን ጠጅ በአሮጌ አቁማዳ ሲጣል ያፈነዳዋል፡፡ በአዲስ አቁማዳ ሲጣል ግን ያለፋዋል እንጂ ሊያፈነዳው አይችልም፡፡ ስለዚህ ወይኑም አቁማዳውም አዲስ የሆኑ እንደሆነ አቁማዳው ወይኑን ያፈላዋል፡፡ ወይኑ ደግሞ አቁማዳውን ያለፋዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ‹‹ሁለቱም ይጠባበቃሉ›› የሚለው ቃል ይፈጸማል፡፡
ጾምና ሰውነት እንደ ወይንና አቁማዳ ናቸው፡፡ ወይንና አቁማዳ እንደሚጠባበቁ (እንደሚጠቃቀሙ) ጾምና ሰውነትም እንዲሁ ናቸው፡፡ ሰው የጾም ሕግን ቢጠብቅ ሕግም እርሱን ትጠብቀዋለች፡፡ ‹‹ይጠባበቃሉ›› የተባለው ለዚህ ነው፡፡ ይህን የሚያስረዳ ‹‹አኮ ንሕነ ዘነዓቅቦሙ ለሕገጋት አላ እማንቱ ሕገጋት የዓቅቡነ ለዓቂብ ወለተፀውኖ›› የሚል ቃል ይገኛል፡፡ ይህም ‹‹ሕጎችን እኛ አንጠብቃቸውም፡፡ እነርሱ መጠበቅን ይጠብቁናል፤ መጠጊያም ይሆኑናል እንጂ፡፡›› እንደ ማለት ነው፡፡

ወይኑ ቆዳውን ማልፋቱ መልካም ነገር ነው፡፡ የለፋ ቆዳ ብዙ አገልግሎት ስላለው ይፈለጋልና፡፡ ለቀበቶ፣ ለቦርሳ፣ ለጫማና ለልብስ የሚሆነው የለፋ ቆዳ ነው፡፡ የጾምም ጥቅም እዚህ ላይ ነው፡፡ ለልዩ ልዩ አገልግሎትና ጥቅም የሚውል መንፈሳዊ ሕይወት እንዲኖረን ከፈለግን በጾም የለፋ (የደከመ) ሰውነት ያስፈልገናል፡፡ ቆዳን ማልፋት ማዘጋጀት እንጂ ከጥቅም ውጭ ማድረግ አይደለም፡፡ ሰውነትን በጾም ማድከምም ለመንፈሳዊ ሥራ ማዘጋጀት እንጂ እንዳይሠራ ማድረግ እንዳልሆነ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ የታረሰ መሬት ለዘር እንደሚመች በጾም የደከመ ሰውነትም ለመንፈሳዊ ጉዞ ይመቻል፡፡ ቅዱስ ዳዊት ‹‹ጉልበቶቼ በጾም ደከሙ›› ያለው ለዚህ ነው፡፡ (መዝ108.24)

ይህን የመሰለ ምሥጢር ያለውን ጾም ‹‹የሽማግሌዎች ጾም፣ ከጥንት ያልነበረ›› እያሉ በመጽሐፍ እና በቀኖና የሌላ ስም በመስጠት ምእመናን እንዳይጾሙት ማድረግ የዲያብሎስ ትጥቅ የማስፈታት ዘዴ እንጂ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?
ላለመጾም ምክንያት ከመፍጠር ምክንያት ፈጥሮ መጾም በእጅጉ ይጠቅማል፡፡ ደሀው ድኅነት ራሱ ጾም ነው ካለ፤ ሌላው ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር ራሱ ጾም ነው ካለ ለመጾም ክርስቲያን መሆን ሳይሆን ሀገር ወይም ዜግነት መቀየር ሊያስፈልግ ነው ማለት ነው? ምእመናን ‹‹ይህ የሽማግሌዎች ጾም ነው›› ካሉ ስለ ጾም ማስተማርና ጾመው ማሳየት የሚጠበቅባቸው ‹‹ሰባክያን›› ደግሞ ‹‹ቃለ እግዚአብሔር ይመትር ነደ እሳት›› እያሉ ጾም  ሽሮ ለመብላት ጥቅስ ከጠቀሱ ጾምን በጽሑፍ እንጂ በሥራ ላናውቃት ነው ማለት ነው፡፡

ሐዋርያት እንደታዘዙት ዓለምን ሁሉ ለማስተማር ከመሰማራታቸው በፊት መጀመሪያ ያደረጉት ጾምን ነው፡፡ ሐዋርያት አልጾሙም ማለት ከላይ የተብራራው የኢየሱስ ክርስቶስ ትንቢትና ምሳሌ ሐሰት ሆነ ማለት ነው፡፡ ሎቱ ስብሐት! ቃሉም ተፈጽሟል ሐዋርያትም ጾመዋል፡፡ እኛም ጾሙን ጾመን የምናስበውና የምንሠራው በጎ ሥራ ሁሉ ይከናወንልን ዘንድ ፈጣሪ በረድኤት አይለየን! እንደነ ዳዊት በንጹህ ልብ የምትጾም ጾም ዋጋዋ ታላቅ ናት፤ ለዚህ ነው ዲያቆኑ በቅዳሴ እንዲህ የሚለው፦ ሰው በልቦናው ቂምን እና በቀልን ማንም በማንም ላይ ቢሆን አይያዝ // ትዕዛዝ አበዊነ  ሐዋርያት እያንብር ብዕሲ ውስጠ ልቡ ቂመ ወበቀለ በቅንአተ ላዕለ ቢፁ ወኢላዕለ መኑሂ።

የተጣላን ታርቀን የበደልን ይቅርታ ጠይቀን ከኃጢአት ሁሉ ርቀን ዋጋ ያላት ደስ የምታሰኝ፤ የእግዚአብሔርን ፀጋ ፤ ምህረቱን፤ ቸርነት ደግነቱን የምንቀምስበት ጾም ትሁንልን ፤አሜን።

“ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ” በፆምና በፀሎት በፍፁም ልባችሁ ወደ እኔ ተመለሱ [ኢዩኤል2:12]