Friday 21 December 2012

“የቤት ሰራተኛዋ”



እናትዋ የሞተችባት አንድ የቤት ሰራተኛ ነበረች። የምታሳድገው ልጅ እናቱ ለስራ ወጥታ ሲያለቅስ አየችና “እናቱ የሞተችበትና ውኃ ልትቀዳ የወረደችበት እኩል ያለቅሳሉ!” ብላ ዕንባ እየተናነቃት ታሪኳን እንዲህ ስትል አወጋችኝ። ከቀናት አንድ ቀን የቤት እመቤትዋ በቤት ሰራተኛዋ ላይ መፈጠርን የሚያስጠሉ ስድቦች እንደ ዝናብ ያዘንቡት ጀመር። ገልቱ፤ ደንቆሮ ፣አህያ ፣ደደብ ወዘተ ተረፈዎች ተባሉና የቤት እመቤትዋ በስህተትም ቢሆን አንዳች ስድብ እንዳልቀረ አሰብ አደረጉና ትዝ ሲላቸው ዲ-ቃ-ላ! ብለው እንደ መብረቅ ጮሁ። ዝናብ በመብረቅ እንዲታጀብ ስድቡም ዲ-ቃ-ላ! በምትል መብረቅ መታጀብዋ ነው! እንዲህ እየተባለ የስንቱ ሞራል ነው የደቀቀው? ከዚህ ከፍ ሲል ደግሞ የሰውን ልጅ የመሰለ ክቡር ፍጡር በምግብ አለንጋ ክፉኛ እንገርፋለን። የአንዳንድ የቤት እመቤቶች ሕሊና ያናድደኛል። በሰለጠነው ሀገር ውሻ እንኳን ጠግቦ ፈልሰስ ብሎ ሲያድር እኛ ቤት ደግሞ የሰውን ልጅ በረሀብ አኮራምተን እናሳድራለን። እንጀራውን በመቁጠር፣ ፍሪጁን በመቆለፍ፤ ስኳሩን ዘይቱን በመደበቅ ስስት የተዋሃዳቸው የቤት እመቤቶች ሞልተዋል። እባብ አፈር ያልቅብኛል ብሎ ሲሰስት ይኖራል አሉ! አባ ወራ እና እማ ወራዎቻችን ሲገርፉን እንኳን አስቀድመው ምግብ አብልተውን ነበር። ከበላን በኋላ ነበርኮ የሚገርፉን። የዘመኑ ሰው ደግሞ በረሀብ አለንጋ ሰውን ይጋረፋል!


ከእናቱ ተለይቶ ያደገ ልጅ
በዶሮ መሃል ያደገ የርግብ ልጅ

ይህች የቤት ሰራተኛ እናትዋ ስለሞተችባት የደረሳጥ ሎተሪ ነው። ልጅ ከእናቱ ተለይቶ ካደገ ደግሞ ልጅነቱ በፍጹም ሙሉ አይሆንም። እኔ ነኝ ያለ የናጠጠ ቤት ይሁን በማንም እጅ ይደግ ልጅ ከእናቱ ከተለየ በአጭሩ ልጅነቱ በፍጹም ሙሉና ደስተኛ አይሆንም። ከእናት ሌላ ፍቅርን ሰብአዊነትን ሰዋዊነትን ማህበራዊ ኑሮን መግቦ አስተምሮ ኮክኩቶ የሚያሳድግ ከየት ይገኛል? ከእናት ቤት ሌላ ሆድ ሳይራብ ፣ ሞራል ተጠብቆ፣ ልብስ ጫማ ተገዝቶ፣ የት/ቤት ደብተርና እስኪቢርቶ ተሟልቶ የሚኖሩበት አለ ካላችሁ ሞኝ ናችሁ። እናቶች ሆይ ጥርሳችሁን ነክሳችሁ ልጆቻችሁን አሳድጉ እንጂ ለማንም አሳልፋችሁ አትስጡ። ከቶ ለማንም!


 አንዱ ነው አሉ ት/ቤት ገባና አስተማሪው የአያትህ ስም ማነው? አሉት። ልጁም “አያት የለኝም” ብሎ አረፈው። ሁላችንም ሆዳችንን ይዘን ክትክት ብለን ሳቅንበት! “አያት የለኝም” ሲል ምን እናድርግ ታዲያ። ሆሆ! አስተማሪውም ግራ ገባቸው። የሚቀልድባቸውም መሰላቸው። እየተንደረደሩ መጡና አህያ በሚጥል እጃቸው አንዴ በጥፊ አላሱት። “እንዴት አያት የለኝም ትላለህ?” አስተማሪው ልጁ ላይ ጮሁ። ልጁም እናቴ መሰረት ትባላለች አለ ጥፊው እንዳይደገም ፈርቶ። “በቅሎ አባትህ ማነው ቢሉት እናቴ ፈረስ ነች አለ አሉ” የተጠየከውን መልስ አሉና አሁንም በጥፊ አንዴ አሞቁት! ጥፊ እንኳን ይደገማል ይባል የለ። ልጁም “በቃ አያቴን ስማቸውን ስለማላውቀው ነው አይቻቸውም አላውቅም” ብሎ ቁጭ አለ። የልጁ ሁናቴ አንጀታችንን በላው። ይህ ልጅ የቤተሰብ ፍቅር ሳያይ ነው ያደገው ማለት ነው።

ይህን ከሚያነብ ሰው ልጅ ከእናቱ ተለይቶ እንዴት እንደሚያድግ ቢያንስ ቢያንስ 90% የሚሆነው በዐይኑ አይቷል ወይም ሰምቷል አልያም ደርሶበታል። 10% ደግሞ ምን አልባት የቤት እመቤቶች ይሆኑ ይሆናል። ይድረስ ለቤት እመቤቴ። የሰው ልጅ ክቡር ነውና “የቤት ሰራተኛዋ” የቱንም ያህል አትማር ከየትም ገጠር ትምጣ እባካችሁ ርህራሄ አሳዩ። ቢያንስ ቢያንስ ሞራላቸውን አታድቁ። ምግብስ ለሥጋ ነው። ሞራል እና ሕሊና ግን የሰው ልጅ የመኖር ምሥጢር ነው። ከእናታቸው ተለይተው የሚያድጉ ልጆች እንዲህ በሞራል እየቆሰሉ እናታቸውን እየናፈቁ በደስታና በፍቅር በሰላም ይኖራሉ!


እስኪ ወደቀደመው ነገራችን እንመለስ። “የቤት ሰራተኛዋ” ልብስ አጥባ፣ ቤቱን አጽድታ፣ እንጀራ ጋግራ ፣ ወጥ ሰርታ፤ የሰራችውን ምግብ አቅርባ፣ ቡና አፍልታ ያፈላችውን አቅርባ መጨረሻ ላይ ምግብ ቀመስ ታደርጋለች። ይህችው የኛ ሮቦት ልበላት? አዎ ሮቦት የቤት ሰራተኛዋ” ብያታለሁ። የጋገረችው እንጀራ ዐይን ከሌለው “እውር ትባላለች። ያፈላችው ቡና ድንገት ቢገነፍል “ደንቆሮ አትሰማም እኮ” ትባላለች። የቤት እመቤቶች የሞራል ድቀት ት/ቤት” የተመረቁ ይመስል እንዲህ የብዙዎችን ሞራል ያደቃሉ ይጎሽማሉም! እናላችሁ ይህች የቤት ሰራተኛ ችግር ሲበዛባት እጅግ ተማረረች። ልክ እንደ ኢዮብ የተወለደችባትን ለሊት ረገመች። እንዲህ የሚል አባባል አለ ችግር አንዳንድ ሰውን ይሰብረዋል ፤ አንዳንድ ሰውን ደግሞ ሪከርድ እንዲሰብር ያደርገዋል!” አልኳት። ልጅቱ ፈገግ አለች። በችግር ልትሰበር ሳይሆን በችግር ሪከርድ ለመስበር ቆርጣ ተነሳች።

በእንዲህ ሁናቴ ያሳደጉን እናቶቻችንን እስኪ ለሰከንድ አስቡ። ውጣ ውረዱን እንግልቱን ስቃዩን ሁሉ ለሰከንድ አስቡት። የየትኛውም ዓለም እናት ድንቅ ብትሆንም ኢትዮጵያዊያን እናቶች ግን በገድል ይበልጣሉ።

የበግ ልጅ በፍየል መሃል ቢያድግ መልካም አይደለም።
የርግብ ልጅ በዶሮ መሃል ሊያድግ አይችልምና!!

ከእናቱ ተለይቶ ያደገ ልጅ
በዶሮ መሃል ያደገ የርግብ ልጅ!!

የቤት ሰራተኛዋ እግሯን ለምታጥባት ለገዛ ልጅዋ ነበር ይህን ሁሉ ታሪክ የምታወጋት። ታሪኩን የምታዳምጠው ልጅም ድምጽ ሳታሰማ እንደ ጅረት ወንዝ ዕንባዋ ይጎርፍ ነበር።



244Like ·  ·