Thursday 5 January 2012


የዓለም እረኛ በግ ሆኖ ተወለደ፤
እንዃን በሠላም አደረሳችሁ፤ ልደተ ክርስቶስ በትርጓሜ፦

መቶ ነገደ መላእክት ካለመኖር ወደ መኖር መጡና ከእነርሱ ቀደም ብለዉ በተፈጠሩ ሰማያት ላይ አንድ ጊዜ ፈሰሱባቸዉ፡፡ አወቂ አድርጎ ፈጥሮአቸዋልና ‹‹ማን ፈጠረን ከየት መጣን›› እያሉ መጠያየቅ ጀመሩ፡፡አንድ ሣጥናኤል ይባል የነበረ፣በፍጥረቱም የከበረ የነበረ መልአክም በልቡናዉ ታበየና በድፍርት እኔ ፈጠርኳችሁ ብሎ ተናገረ፡፡ በዚያች ቅጽበትም ራሱን ሰይጣን አደረገ፡፡ ኀጢኣትንም ወደ ዓለም አስገባት ይህም ብልጠት መስሎት ሳይሆን አይቀርም የኀጢአትን እድሜዋን ከሰዉ እድሜ አስረዘመዉ፡፡ ንግግሩን ከሰሙትም አዳንዶቹ ቢቀበሉትም ብዙዎቹ ግን ተቃወሙት፡፡ ስሙ ገብርኤል የሚባል አንድ የከበረ አርያማዊ መልአክም ‹‹ ንቁም በበህላዌነ እስከ ንረክቦ ለአምላክነ-አምላካችን እስከሚገለጽልን በያለንበት ጸንተን እንቁም›› ብሎ ማረጋጋት ጀመረ፡፡ ብጥብጡ ግን ቀጠለ እንጂ አልተገታም፡፡ሁከትም ከጥብቅ ወዳጃችን ከኃጢአት ባይቀድምም ሰዉን ቀድሞ በመላእክት በኩል ወደ ዓለማችን በመግባቱ ቁም ነገር መስሎት ተኩራራ፡፡ በዚህ ምክንያት ነዉ መሰለኝ እስከ ዛሬ ድረስ በዙ ሰዎችን እንደ ታላቅ ወንድም ሆኖ ሲያሠለጥን ይኖራል፡፡ በዚህ ጊዜ ድንገት ‹‹ብርሃን ይሁን›› የሚል የፈጣሪ ድምፅ ተሰማ፡፡ ድምፁ ድምፀ ሰብእ (የሰዉ ድምጽ) አልነበረም፡፡ ይሁን እንጂ ለመላእክት ሊሰሙት በሚቻላቸዉ አድርጎታልና ድምፁን ያሰማዉ ፈጣሪ መሆኑን አወቁ፡፡ በዚህም እርሱን በርግጥ አዉቀዉ ማመስገን ቢጀምሩም ከሣጥናኤል ጋር ጦርነቱ ዕለቱን ተጀመረ፡፡ይገርማል! ጦርነትም ሰዉን ቀድሞ ተጀመረ፡፡ ነገሩስ ሁላችሁም እንኳንም ቀደማችሁን፤ ባትቀድሙን ኖሮ ዛሬ ስንበላላ ‹‹ክፋት፣ሁከትና ጦርነት ከሰዉ በፊት ነበሩ›› እያልን እየተጽናናን በክፋታችን ለመቀጠል አንችልም ነበር፡፡ ኧረ እንኳንም ቀደማችሁን፡፡እግዚአብሔር ይስጣችሁ የሚል ባታጡም እኔ ግን ይህችን አልልም፡፡ ባይሆን የአባታችሁን የሰይጣንን አትጡት ለማለት አልነፍጋችሁም፡፡ ይገርማል ክፋትና ተንኮልም በመጀመሪያዉ ዕለት አብረዉ ወደ ዓለም ገቡ ማለት ነዉ፡፡ምን ይደረግ እንግዲህ እንኳንስ ቀድመዉን ብንቀድማቸዉም እኛን ሳይጨርሱን የሚጠፉ አይመስለኝም፡፤መላእክት ግን የፈጣሪያቸዉን ድምፅ በየዕለቱ እየሰሙ ፍጥረቱንም እያዩ መደነቃቸዉን አበዙ፡፡ ፍጡራኑን እንዲህ የሚያስዉባቸዉ እርሱ ምን ይመስል ይሆን እያሉ በፍጥረቱ ዉበት እየተደነቁ፤ ፈጣሪያችን ብናየዉ እያሉ ሲጓጉ ድንገት አንድ ነገር ሰሙ፡፡‹‹ሰዉን በመልካችን እንደ ምሳሌያችን እንፍጠር››ሲል አደመጡና መደመም ያዛቸዉ፡፡ ፈጣሪያቸዉን ዐሥራ አራት ፍጥረታትን በመናገር አስዉቦ ሲፈጥር እየሰሙና እያዩ ሲደነቁ ሰንብተዉ አሁን ደግሞ ራሱን የሚመስል ፍጡር ለመፍጠር መናገሩን ሰምተዉ አዳምን ተፈጥሮ ያዩት ዘንድ ተቻኮሉ፡፡ ምን ያህልስ ቢወደዉ ነዉ እያሉም ተደነቁ፡፡ ይልቁንም ከአራቱ ባሕርያት ተፈጥሮ እነደነርሱ አመስጋኝ፣ ስሙን ቀዳሽ ክብሩን ወራሽ መሆኑን ሲያዉቁ አብዝተዉ ተደነቁ፡፡ ምን አልባት ግን ሰዉን ለማየት የተቻኮሉት መላእክት ብቻ ላይሆኑ ይችላሉ፤ እነ ክፋትስ ተቻኩለዉልን እንደሆነ ማን ያዉቃል? ለማንኛዉም ሰዉ ገና ከመፈጠሩ በፊት መላእክትን እንኳ የሚያጓጓ ሆነ፡፡
መላእክት የተደነቁትም ከአዳም አፈጣጠር ጋር በተገናኙ በሦስቱ አስደናቂ ነገሮች መኖራቸዉን ትንቢት የሚባል አጉሊ መነጽር ከፈጣሪ ተቀብልዉ ዘወር ብለዉ ያዩ አንዳንድ ደጋግ ሰዎች ምስጢር መቻል አቅቷቸዉ ለሚያምኑአቸዉ ሹክ እንዳሉ እኛም ሰምተናል፡፡እንዲዉም በሊቃዉንቱ አነጋገር እግዚአብሔር ለሰዉ ያለዉ ፍቅር በሦስት ደረጃ ይገለጻል፡፡ ከመፍጠሩ በፊት፣አዳም ከተሳሰተ በኋላ፣ እና ከእርሱ ሰዉ መሆን በኋላ ያለዉ፡፡ እንዲህ ነዉ አሉ ነገሩ፡
እግዚአብሔር አዳምን የፈጠረዉ እጅግ ቢወደዉ ነዉ አሉ፡፡መላእክት ከመጠን በላይ የተደነቁትም እግዚአብሔር አዳምን እንደሚበድለዉ እያወቀ በመፍጠሩ ነዉ፡፡ የአዳምን መበደል አስቀድሞ ማወቁ እንዳይፈጥረዉ ለምን አልከለከለዉም እያሉ ዘወትር መደነቂያ አገኙ፡፡ ከሰዉ ወገን አንዱ ሰዉ ሌላዉን ከርሞ እንደሚያስቀይመዉ ቢያዉቅ ባወቀበት ጊዜ ሊኖረዉ የሚችለዉንም ሲያስቡት ነዉ መሰል እግዚአብሔር ምን ያህል ቢወደዉ ነዉ እያሉ ፍርዱንና ፍቅሩን እያጣጣሙ ዘወትር ያመሰግናሉ፡፡በርግጥም መበደሉን እያወቀ የፈጠረዉ እጅግ አድርጎ ቢወደዉ ነዋ፡፡እንዲህ ያለ ፍቅርስ በእዉነት ከወዴት ይገኛል?
ዳግመኛም በአፈጣጠሩ ተደነቁ፡፡ሰባቱን ፍጥረታት(መሬት፣ዉሃ፣ነፋስ፣ እሳት፣ጨለማ፣ሰማያት እና መላእክት)በሃልዮ(በአሳብ) ብቻ፣ቀሪዎቹን አሥራ አራቱን ደግሞ በነቢብ(በመናገር) ከፈጠረ በኋላ በእጁ የሠራዉ ብቸኛዉ ፍጥረት ሰዉ ነዉና፡፡ በዚህም ከሌሎቹ ፍጥረታት ይልቅ ሰዉን በብዙ አብልጦ እንደሚወደዉ ታወቀ ተረዳ፡፡ዳግመኛም ከርሱ በፊት ከተፈጠሩት ሁሉ ልዩ ሆኖ የተፈጠረዉ ሰዉ ብቻ ሆነ፡፡ ምክንያቱም ሌሎቹ ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋ የሆኑት ፍጥረታት ሁሉ ኃላፍያት ናቸዉ፡፡ከዕለተ ምጽኣት በኋላም እንኳን አካል ከህልዉና ሊተባበርላቸዉ ቀርቶ መታሰቢያም የላቸዉም፤ ሰዉ ግን ዓለም ስታልፍ እንኳ የሚኖር ፍጡር ነዉ፡፡ በርግጥ ራሳቸዉ መላእክትም ሕያዋን ናቸዉ፤ነገር ግን ሕይወታቸዉ ካለመሞት ባሕርያቸዉ የሚመነጭ ስለሆነ አዳምን ሟች ባሕርዩ ልዩ ታደርገዋለችና አሁንም በእርሱ አፈጣጠር መደመማቸዉን አበዙ፡፡ መዋቲነትን ከሕያዉነት አስተባብሮ(ሁለት የማይስማሙ ጠባይዓትን አስማምቶ) ሊኖር የተፈጠረ ከርሱ በቀር ማንም የለምና፡፡ ሕያዉነት የኖረዉም በሕያዊት ነፍስ ምክንያት ነዉ፡፡ ‹‹ ወዓዲ አክበሮ በንፍሐት ዘይእቲ ማኅተመ ሕይወት መንፈሳዊት እንተ ባቲ አክበሮ እም ኵሉ ፍጥረት ዘታሕተ ሰማይ፡ዳግመኛ በአራቱ መዓዝን ካለ ፍጥረት ለይቶ ባከበረበት የሥጋ ሕይወት የደመ ነፍስ ሕየወት በምትሆን በነባቢት ነፍስ አከበረዉ›› ተብሎ እንደተጻፈ ነፍስ ለሰዉ ከፍጥረት ሁሉ የከበረበት እግዚአብሔርም ለሰዉ ያለዉን ፍቅር የገለጸበት ነዉና በርግጥም አስደናቂ ፍጥረት ሆነ፡፡
ሌላም ተጨማሪ አዳምን ልዩ የሚያደርገዉ ነገር አስተዋሉና መላእክት መደነቅ በዛባቸዉ፡፡ ሰዉ እንደ እንስሳት በኀይለ ዘርዕ(በዘር በሩካቤ) ይራባል፤ እንደ መላእክትም ደግሞ አዋቂ ነዉ፡፡እንስሳት ቢራቡ አያዉቁም፤ መላእክትም ቢያዉቁ አይራቡም፡፡ስለዚህ አሁንም ኀይለ ዘርዕን ከእዉቀት አስተባብሮ የያዘ ከሰዉ በቀር ሌላ ፍጥረት አላዩምና በእዉነት እግዚአብሔር ለሰዉ ያለዉ ፍቅር ምንኛ የበዛ ነዉ እያሉ ስለኛ እነርሱ ምስጋና አብዝተዉ አቀረቡ፡፡ እግዚአብሔር ይስጣቸዉ እንጂ ሌላ ምን እንላለን፡፡ገና ሳንፈጠር ጀምረዉ ባለዉለታዎቻችን ናቸዉና ምን ልናደርግላቸዉ እንችላለን፡፡
እነርሱ ግን በዚህ ሊያበቁ አልቻሉም፡፡ይልቁንም በአርያዉና በአምሳሉ መፍጠሩን ሲያሰቡት ለሰዉ ላለዉ ፍቅር የሚመጥን ምስጋና ለማግኘት አብዝተዉ ደከሙ እንጂ፡፡በእዉነትም ይህ እጅግ ታላቁና አስደናቂዉ የፍቅሩ መግለጫ ነዉ፡፡መላእክቱ ቢቸግራቸዉ በዝምታ ዉስጥ ባለ ታላቅ ምስጋናቸዉ እጅግ አድርገዉ አመሰገኑት፡፡ እንዲህ ሆነን መፈጠራችን መላእክትን ወሰንና ምሳሌ በሌላት መደነቅ ዉስጥ ቢከትም ሰይጣንንም ደግሞ አእጅግ አድርጎ አበሳጭቶታል፡፡ እርሱ ሆኑ መላእክቱ የእግዚአብሔርን ድምፁን ሲሰሙት ሰነበቱ እንጂ ሊያዩት አልተቻላቸዉም ነበርና፡፡ወንጌላዊ ዮሐንስ ‹‹መቼም ቢሆን እግዚዘብሔርን ያየዉ አንድ ስንኳ የለም››/ዮሐ118/ እንዳለ በርግጥም ከእነርሱ ወገን ያየዉ የለም፡፡ሐዋርያዉ ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹ማንም ሊቀርበዉ በማይችል ብርሃን ይኖራል፤ አንድ ሰዉ እንኳ አላየዉም፤ ሊያየዉም አይቻለዉም››/1 ጢሞ 616/ እንዳለ እግዚአብሔርን ሊያዩት አልተቻላቸዉም፡፡መርምረዉም ሊደርሱበት አይቻላቸዉም፡፡ ‹‹አንተ ሁሉን ታያለህ እንጂ አንተን ማየት የሚችል የለም››(3 መቃ 9÷26) ተብሎም ተጽፏል፡፡የኛዉ አባት ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ‹‹ወቆባር ታሕተ እገሪሁ፣ተጽዕነ ላዕለ ኪሩቤል ወሰረረ፣ወሰረረ በክንፈ ነፋስ፣ወረሰየ ጽልመተ ምስዋሮ ወዐዉዶሂ ጽላሎቱ-ጨለማ ከእግሩ በታች ነበረ፣በኪሩቤልም ላይ ተቀምጦ በረረ፣በነፋስም ክንፍ በረረ፣መሰወሪያዉን ጨለማን አደረገ፣በዙሮያዉም ጨለማ ነበረ››(መዝ 17÷9-11 ) በማለት እንደመሰከረለት ሊመረመር የማይቻል መሆኑን በአኗኗሩ ተረዱ፡፡ በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር ራሱን እስኪገልጥ ድረስ መላእክቱ ድምጹን እየሰሙ ፍጥረቱን እያዩ ከማድነቅ ዉጭ ሌላ አማራጭ አልነበራቸዉም ነበር፡፡ ስለዚህም ሰዉን ተፈጥሮ ማየት ፈጣሪን ማየት ሆኖላቸዋልና ሰዉን ለማየት መላእክት ተፋጠኑ፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ወደ ቀደመ ክብሬ ሊመልሰኝ ይችላል እያለ በማሰብ ከትዕቢቱ ያልተመለሰዉን ዲያብሎስንም በምትኩ አመስጋኝ ፍጡር ከመሬት በመፍጠር እንዳይመልሰዉ አስረግጦ ነገረዉ፡፡‹‹ዘለፎ እግዚአብሔር በፈጠረ ብእሲ ዝልፈተ ክሱተ፤ በአሠንዮ ፍጥረቱ ለአዳም፡ አዳምን አሳምሮ በመፍጠሩ እግዚአብሔር ሰይጣንን መዝለፍን ዘለፈዉ፣ማሳፈርን ሳፈረዉ›› ተብሎ ተጽፎአልና፡፡/መቅድመ ወንጌል/ በዚህም ሰይጣን ቀንቶበታል፡፡ ‹‹ወሶበ ርእየ ሰይጣን ዕበየ ስብሐቲሁ ወክብራቲሁ፣ወብርሃነ ዘይትዓጸፍ ቦቱ ወርእየ ርእሶ በርእሱ እምድኅረ ክብር ወሲመት ዐባይ ወድቀ በድቀተ ቅንዓት፣ደንገጸ በድንጋጼ ቅንዓት፣ኀዘነ በኀዘነ ቅንዓት፣ተከዘ በትካዘ ቅንዓት፣ ወድቀ መዉዱቀ ዉዱቅ፣ ወቀብጸ ተስፋሁ፡ሰይጣን ከሹመቱ ከተሻረ በኋላ የራሱን ደግ ክብሩን፣ ጌትነቱንም [በአዳም ላይ ሆኖ] ባየ ጊዜ ቅንዓት ባመጣዉ ዉድቀት ወደቀ፣ ቅንዓት በሚያመጣዉ ድንጋጤ ደነገጠ፤….ተስፋም ቆረጠ›› ተብሎአልና፡፡ እርሱም ግን የዋዛ አይደለምና ‹‹ወነሥአ ሎቱ ተሃይሎተ ዘበእኪት፣ወመንሱተ ወልታ፣ወመጽአ መንገለ ብእሲ፡የክፉ መበረታትን ተበረታታበት፤ድል የሚነሳበትን ጋሻም አንግቦ በክፉ መበረታት ወደ አዳም መጣ ››ተብሎ እንደተጻፈ ሰዉን ይዋጋዉ ዘንድ ከዚያ ጀምሮ አሸመቀ፡፡ቢሆንም ሰዉ ገና ሲፈጠር ጀምሮ ሰይጣንን ያስደነገጠ፣ያሳፈረ፣ ያስወተወተ፤ መላእክትን ደግሞ ያስደሰተ ያዩትም ዘንድ ያስቸኮለ መሆኑ አልቀረም፡፡የሰዉ ልጅ ግን ይህን በአግባቡ የተረዳዉ አይመስልም፡፡አባታችን ዳዊትንም የሚያሳዝነዉ የሰዉ ይህን አለማወቁ ይመስላል፡፡ ‹‹ሰብእሰ እንዘ ክቡር ዉእቱ ኢያእመረ፤ወኮነ ከመ እንስሳ ወተመሰሎሙ፡ሰዉ ክቡር ፍጡር ነበረ፤ ነገር ግን አላወቀም፤ይልቁንም እንደ እንስሳ ሆነ፤ እነርሱንም መሰለ ›› እያለ የዘመረዉም ለዚሁ ይመስላል፡፡አዳም አባታችን ይቆጠሩ ዘንድ የማይቻላቸዉንና ይበላቸዉ ዘንድ የተፈቀደለትን ትቶ ወደ ተከለከላት አንዲት ዛፍ ይበላ ዘንድ ተቻኩሏልና፡፡እግዚአብሔርም ሰዉን እንዲህ አድርጎ የፈጠረዉ ቢወደዉ ስለሆነ ሰዉ ይህን ይረሳበት ዘንድ አይፈልግም ነበረ፡፡በርግጥም ተናግረን ልንጨርሰዉ የማንችለዉን ፍቅሩን ገለጸልን፡፡ቅዱስ ዳዊትም ‹‹ታስበዉ ዘንድ ሰዉ ምንድን ነዉ?›› (መዝ 8÷10) ያለዉ የሰዉን ልጅ እንዲህ አድርገህ አክብረህ ትፈጥረዉ ዘንድ ሰዉ ምንድን ነዉ? ለማለት ነዉ፡፡ በርገጥም እግዚአብሔር በነዳዊት ምስጋና የተጽናና ይመስላል፡፡ ያን ባያስብ ኖሮ ዛሬ በማን ተደስቶ ሊታገሰን ይችል ነበር፡፡
አባታችን ዳዊት ግን አሁንም እየተገረመ ይጮሃል፤ እያለቀሰም ይዘምራል፡፡ ከዐራቱ ባሕርያት ፈጥረህ እንደ መላእክት አመስጋኝ፣ ስምህን ቀዳሽ፣ ክብርህን ወራሽ ሕያዉ እና አዋቂ ታደርገዉ ዘንድ ሰዉ ምንድን ነዉ?ሲል በአድናቆት እንደጠየቀ አሁንም ደግሞ በምስጢር እንደገና ይጠይቃል፡፡ አዳም አትብላ የተባለዉን ዕፀ በለስ በልቶ ከፈጣሪዉ ተጣላ፡፡ የበላዉም ርቦት ወይም ቸግሮት ሳይሆን አምላክነትን ፈልጎ ነበር፡፡ በዚህ ሥራዉም ሰይጣን በተያዘበት ወጥመድ ተያዘ፤እርሱ በወደቀበት መዉደቅም ወደቀ፡፡ በርግጥም ሰይጣን እንደ ሸመቀበት አልቀርም ተዋግቶ ድል ነሣዉ፡፡ ከዚህም የተነሣ ባሕርዩ ጎሰቆለ፣ጸጋዉም ተገፈፈ፡፡ የተራቆተ ሰዉነቱንም ለመሸሸግ ከእንስሳት እንደ አንዱ ወደ ዛፍ ሥር ተሸጎጠ፤ ከጸጋ የተገፈፈዉን ሰዉነቱንም በቅጠል ለመሸፈን ደከመ፡፡ እግዚአብሔር ግን ‹‹ አዳም ወዴት ነህ›› ሲል በሰዉ መጠን ተጣራ፤እንደ ሰዉም በገነት ዉስጥ ዱካ(ኮቲ) እያሰማ አዳምን ለመፈለግ ተመላለሰ፡፡ ወደ አዳም አሁንም በፍቅር እና በምሕረት ቀረበ፡፡አዳምም በፍርሃት እና በመንቀጥቀጥ ለእግዚአብሔር መልስ ሰጠ፡፡ እርሱም ከፍቅሩ የተነሳ ያልሰማ እና ያላወቀ መስሎ ከአዳም ጋር ተጠያየቀ፤ ተነጋገረም፡፡ አዳምን ከፈጠረበት የሚበልጠዉንና አስደናቂዉ ፍቅሩም በዚህ ተገለጠ፡፡ እግዚአብሔር እንደ አምላክነቱ ቀርቶ ትንሽ ኀይሉን እንኳን ገልጦ ቢሆን ኖሮ ስንኳን አዳም ገነትም በቀለጠች ነበር፡፡ እርሱ ግን አዳምን ስለወደደዉ እና ስለሚወደዉም እርሱን ለመርዳት ሲል ያላወቀና ያልሰማ መስሎ ‹‹ አዳም አዳም ወዴት ነህ›› እያለ ይፈልገዉ ዘንድ መጣ፡፡ ስለዚህም ነቢዩ አምላክነትህን ሽቶ በአንተ ላይ ተነሳስቶ፣ ምክርህን ረስቶ ዲያብሎስን ሰምቶ፣አትብላ ያልከዉን በልቶ በበደለህ ጊዜአዳም አዳም ወዴት ነህእያልክ በፍቅር ትፈልገዉ ዘንድ በእዉነት ሰዉ ምንድን ነዉ? ከዐራቱ ባሕርያተ ሥጋ ፈጥረህ አምስተኛ ባሕርየ ነፍስን አዋሕደህ፣ በዕዉቀት አክብረህ፣ ከፍጥረት ለይተህ፣ ከመላእክት እንኳ ስታከብረዉ በአንተ ላይ ያመጸዉን ትፈልግ ዘንድ ፍቅርህ ምን ያህል ጽኑ ነዉ? ሰይጣንን የዘለፍህበት መላእክትን ያስደነቅህበት የምትወደዉ ፍጥረትህ ከዚያ ሁሉ ጸጋህ በራሱ ተራቁቶ፣ ከልጅነት ወጥቶ ሲበድልህ፣ የእርሱን ወደ ላይ የመዉጣት መሻት ትተህ አንተ ወደ ታች ወርደህ ትፈልገዉ ዘንድ ሰዉ ምንድን ነዉ? በፍጥረት ሁሉ ላይ ካሰለጠንከዉ በኋላ ከአንተ ጋር በመጣላቱ ፍጥረታቱ ሁሉ ሲነሱበት ጦርነትም ሲከፍቱበት እንደገና ትጠብቀዉ ዘንድ የወደድከዉ ሰዉ ምንድን ነዉ? እያለ የእግዚአብሔርን ፍቅር እያሰበ አባታችን ዳዊት አለቀሰ፡፡ ልጁ ሰሎሞንም አባቱን ተከትሎ አለቀሰ፤ ከመዝሙራት በሚበልጥ መዝሙሩ፣ ከምስጋና በሚበልጥ ምስጋናዉም ራሱን ለእግዚአብሔር የታጨ፤ ነፍሱንም የእግዚአብሔር ሙሽራ አድርጎ ቆጥሮ አሻግሮ እየተመለከተ ‹‹ነፍሴ የወደደችህ አንተ ንገረኝ›› (መኃ1÷7) እያለ ጠየቀ፡፡ መልሶ መላልሶም አለቀሰ፤ እየዘመረ አነባ፣ እያነባም ዘመረ፤ እንዲህም አለ፦‹‹ በእኔ ላይ ያለዉ ዓላማዉ ፍቅር ነዉበዘቢብም አጽናኑኝ፣ በእንኮይ አበረታቱኝ፣ በፍቅሩ ተነድፌ ታምሜያለሁና›› (መኃ2÷4-5) እያለ የፍቅር ሙሾዉን ይደረድር ጀመረ፤ቤተ ክርስቲያንንም ‹‹ወዳጄ ሆይ ተነሺ፣ ዉበቴ ሆይ ነዪ፡፡ እነሆ ክረምት አለፈ፣ዝናቡም አልፎ ሔደ፣ አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፣ የዜማም ጊዜ ደረሰ፣…››ሲል ማኀሌት አብራዉ ትቆም ዘንድ ጠራት፡፡ ነቢያትን ሁሉ እንዲህ ያደረገ በሱባኤ አድክሞ በመንፈስ አበርትቶ፣ በምስጢር አስክሮ ያዝዘመራቸዉ ይኸኛዉ ደግሞ ከወደቅን በኋላ ያለዉ ልዩ ፍቅሩ ነበር፡፡በርግጥም የሚያስደንቅ ፍቅር፡፡መላእክት ግን ለሰዉ ያለዉንና ሲበድለዉ እንኳ ሊቀንስበት ቀርቶ የሚጨምረዉን ፍቅሩን አይተዉ ከዚያ በፊት ባልነበራቸዉ መደነቅ አመሰገኑት፤ እርሱን ካዩ በኋላ እነረሱም ያዝኑለት ጀመሩ፡፡ ነገር ግን እንደታዘዙ የገነትን በር ጥርቅም አድርገዉ ዘጉብን፡፡ እናንተማ ምን ታደርጉ፤ ለዚያዉም የሱን ፍቅር አይታችሁ ራርታችሁልን ነዉ እንጂ በጌታዉ ላይ ለሚነሳ የትኛዉ አገልጋይ ራርቶ ያዉቃል?
የሆነዉ ሆኖ እየቆዩ ሲሔዱ መላእክትም እግዚአብሔርን ሳይታዘቡት አልቀሩም፡፡ አዳምን ተጣላሁት ብሎ ከገነት ካስወጣዉና የገነትን በር በእነርሱ ጥርቅም አስደርጎ አዘግቶ ምድረ ፋይድ ከላከዉ በኋላ እንደገና ሂዱ፤ ጸሎቱን አሳርጉ፣ ከጠላት ጠብቁት፣ ምሕረቴንም አዉርዱለት እያለ ትእዛዝ ሲያበዛባቸዉ ጊዜ አሁንም መገረማቸዉ ጨመረ፡፡ እርሱም አንድንድ ጊዜ ልጅነት አለበት መሰል ጭራሽ እነርሱንም ትቷቸዉ ከአዳም ልጆች ጋር ሲጫወት ዉሎ ሲመለስ ያዩታል፡፡ በዚህም መገረማቸዉን አየና ይባስ ብሎ ወደ አብርሃም ቤት ወርዶ በሬ አሳርዶ ቂጣ አሰጋግሮ ሲበላ ተመልክተዉ ደነገጡ፡፡ በኋላ ግን እነርሱም ቀኑ መሰለኝ እየተንደረደሩ ወርደዉ ከሎጥ ቤት ገብተዉ ይቀላዉጡ ጀመር፡፡እነርሱ ግን እንደርሱ አልቀናቸዉም፤ በመንደሩ ሰዎች ስለተከበቡ መብላታቸዉን ትተዉ ወዳጃቸዉን ሎጥን ከነልጆቹ ብቻ አትርፈዉ ከተማዉን እሳት ለቀዉበት ተመለሱ፡፡ እንኳን ለሌላ ሰዉ ሊራሩ ጨዉ ላምጣ ብላ ሔዳ ሰዎቹን ጠርታ ያስከበበቻቸዉን ሚስቱንም ዘወር ብላ አየች ብለዉ የኋላ ኋላ የጨዉ ሐዉልት አድርገዉ ተጫወቱባት እንጂ አልማሯትም፡፡እርሷም ቅልብልብ ቢጤ የከተማዉን መቃጠል እንኳን አይታ የመላእክትን ንግግር የማታከብር ድንጋይ ሆና ቀረች፡፡ ጌታ ግን ሐሜታቸዉን ሰምቶ ሊሳቀቅ ቀርቶ ጭራሽኑ ከነ ሙሴ ጋር በየተራራዉ እየወረደ በእሳት ይጫወት ጀመር፡፡ በዚህ ሲገረሙ ዉጭ ሀገር እንደሚሔድ አንድ የእኛ ሀገር ሰዉ እዚህ ሔድኩ ሳይላቸዉ ከሙሴ ጋር ተቀጣጥሮ ደብረ ሲና ወርዶ አርባ ቀን ሰንብቶ ሲመጣ እጅግ ተደነቁ፡፡ እርሱም የዋዛ አይደለም ከሙሴ ጋር ተዋዉሎ ዲዛይኑንም አሳይቶ የእኛኑ ሀገርንም ወደደዉ መሰል ቤት ሥሩልኝ ብሎ አሠርቶ ከእኛዉ ጋር መኖር ጀመረ፡፡ሙሴም ተቀናጣና ከጌታ ብርሃን በፊቱ ላይ አድረጎ ሰዉን እያስፈራራ የሰማዉን ሁሉ ይናገር ጀመረ፡፡ ከእግዚአብሔርም አንዲት ዱላ ተቀብሎ ግብጾችን ገረፈባት፡፡ሃይሏን ካየ በኋላማ ያለደረገባት ነገር የለም፡፡ እግዚአብሔርም ከአብርሃም ቤት የቀመሰዉ ምግብ ጣፈጠዉ መሰል ከሙሴ ጀምሮ አንዳንድ ወዳጅ እያበጀ ሁሉንም ሊመጣና ሊበላና ሊጠጣ ቀጠሮ ሲሰጥ ቆየ፡፡
መላእክቱንም ቁርጥ ይወቊ ብሎ ነዉ መሰል ወርዶ ተወልዶ በልቶ ጠጥቶ ሊመለስ መሆኑን ነገራቸዉ፡፡እነርሱም ቀኑን ሲጠባበቁ ከቆዩ በኋላ ቀጠሮዉ በደረሰ ጊዜም ከእነርሱ ወገን የሚሆን የከበረ መልአክ ቅዱስ ገብርኤልን ጠርቶ ለድንግሊቱ እንዲያበስር ሲልከዉ ሰሙ፡፡አቤት ፍቅር፤ የሚደነቅ ፍቅር፤ በእዉነት አዳም ከመበደሉ በፊት ይህን አድርጎት ቢሆን ባልተደነቀም ነበር፡፡ አሁን ግን ያስደንቃል፤ ከፈረደበት፤ ‹‹አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ ››ካለዉ በኋላ ነዉና ሰዉ ይሆን ዘንድ የወደደዉ እጀጉን ያስደንቃል፡፡ መላእክት እንደሆኑ ቀድሞ ምሳሌዉን አይተዉም ተደንቀዉ ነበር፤ አሁን ግን እርሱን ራሱን ሊያዩት ነዉና ሲኦል ሆነዉ መምጣቱን ይጠባበቁ ከነበሩት ከነአዳም፣ከነአብርሃም፣ ከነዳዊት፣ ከነቢያትም ሁሉ ይልቅ መላእክት ያዩት ዘንድ በእዉነት ተቻኮሉ፡፡ምሳሌዉን ለማየት ያን ያህል ከቸኮሉ አሁንማ ራሱን ለማየት እንዴታ፡፡ ወደ ድንግሊቱ የተላከዉ መልአክ ቅዱስ ገብርኤልም ከደስታዉ ብዛት የተነሣ ክንፉን እያማታ በወረደ ጊዜ በአድባረ ሊባኖስ ተሰማ፡፡ አንድ አርያማዊ ኀይል እየተንደረደረ ወረደ፡፡ ወደ ድንግሊቱም ቀርቦ ደስ ይበልሺ እያለ ሰገደ፡፡ ከደስታዉም የተነሣ አመሰገነ፤ እጅ እየነሣም ብሥራቱን አደረሰ፡፡ ድንግሊቱም ‹‹ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ-እንደቃልህ ይሁንልኝ›› ባለች ጊዜም አካላዊ ቃል የዕለት ጽንስ ሆኖ በማኅፀኗ አደረ፡፡ ረቂቁ ገዘፈ፣ምሉዑም ተወሰነ፤ በተዋሕዶ በተአቅቦ አምላክ ሰዉ ሆነ፡፡ ማኅፀነ ማርያምም የማይቛረጥ ምስጋና መቅረቢያ ሕያዉ ቅኔ ማኅሌት ሆነ፡፡ ሐዋርያዉ ቅዱስ ጳውሎስ እንደጻፈዉ አምላክ በሰዉ እጅ ወዳልተተከለች መቅደስ ሲገባ ታየ፡፡ ‹‹ምን ዓይነት ቤት ትሠሩልኛላችሁ፤ እኔ የሰዉ እጅ በሠራዉ አልኖርም ይላል እግዚአብሔር›› ሲል ኢሳይያስ የተናገረዉም በድንግል ማርያም ተፈጸመ፡፡ በርግጥም በሰዉ እጅ ያልተሠራችዉ መቅደሱ እርሷ ናትና፡፡ እግዚአብሔር ራሱ በሠራዉ ንጹሕ መቅደሱ ሲገባ ያዩ መላእክትም ተዥጎድጉደዉ ወረዱ፤ ማኅፀነ ድንግልንም ማኅሌት አድርገዉ ምስጋናቸዉን አቀረቡ፡፡ ግሩምና ድንቅ ምስጢር፤ ሊነገርም የማይችል ፍቅር፡፡
አባቷ ዳዊትም ይህን እያሰበ ብደስታ ያለቅስ ጀመረ፡፡ ‹‹ ልጄ ሆይ ስሚ፣ እዪ ጆሮሺንም አዘንብዪ፤ ወገንሺን የአባትሺንም ቤት እርሺ፣ ንጉሥ ዉበትሺን ወድዶአልና፤ እርሱ ጌታሺ ነዉና›› (መዝ 44÷12) እያለ ደጋግሞ አመሰገነ፡፡ሰሎሞንም አባቱን ተከትሎ ጮኸ፡፡ ‹‹ወዳጄ ሆይ ሁለንተናሺ ዉብ ነዉ ነዉርም የለብሺም፤ ልቤን በፍቅር አሳበድሺዉ….›› እያለ ዐነባ፡፡ ኢሳይያስም የተናገረዉ ትንቢት ሲፈጸም አይቶ ከአባቶቹ የደስታ ዕንባ ተቀላቀለ፡፡የታተመችዉን መጽሐፍ የታሸገችዉን ደብዳቤ ሲያያት ጊዜ ተገረመ፡፡ (ኢሳ 28÷ 12) አብ በድንግልና አትሞ ሲያበቃ በዉስጧ አካላዊ ቃልን የጻፈባት ማንበብ የሚችሉም(እሥራኤል) ማንበብ የማይችሉም(አሕዛብ) እናነበዉ ዘንድ አንችልም ታትሟልና (በድንግልና በንጽሕና በክብር በምስጢር) አሉ ብሎ የተናገረላት ደብዳቤ አካላዊ ቃልን ይዛ ባያት ጊዜ በደስታ ዘለለ፡፡ በእርሷም እየተመካ ‹‹የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን(አንቺን) ባያስቀርልን ኖሮ እንደ ሰዶም በሆንነ እንደ ገሞራም በመሰልነ ነበር›› (ኢሳ 1÷9)እያለ እንደ ልማዱ አለቀሰ፡፡ዳዊት አባቱ ግን ምስጋናዉን እንደቀጠለ ነዉ፡፡ ዝማሬወቹን እያስታወሰ ይዘምራል፤ ‹‹ ለጥርሻቸዉ ንክሻ(ለሠራዊተ ዲያብሎስ) ያላደረገን እግዚአብሔር ይባረክ፤ ነፍሳችን እንደወፍ ከአዳኞች(ከአጋንንት) ወጥመድ አመለጠች፤ ወጥመድ ተሰበረ እኛም አመለጥን›› (መዝ 123÷6)ሲል በሣጥናኤል ላይ ተጓደደ፡፡ እዉነት ነዉ ‹‹ዕፀ በለስን ብትበላ አምላክ ትሆናለህ›› ሲል ወጥመዱን አጥምዶ አዳምን የያዘ ዲያብሎስም ደነገጠ፤ ሰዉ አምላክ ይሆናል ብሎ አስቦ አያዉቅም ነበርና፡፡ አሁን ግን አምላክ ሰዉ በሆነ ጊዜ ሰዉም በተዋሕዶ አምላክ ሆነ፡፡ ስለዚህም ዲያብሎስ በተሳልቆ የተናገረዉ ‹‹የአምላክ ትሆናለህ›› ወጥመድ ተሰበረ፤ አዳምም አመለጠ፤ እኛ ሁላችንም ከዘር ቁርኝት ተላቀቅን፡፡ ዲያብሎስም በርግጥ ደነገጠ፡፡ እንግዲያስ እኛም ከአባታችን ከዳዊት ጋር ‹‹ ሰይጣን ሆይ ወጥመድህ ተሰበረ፣ እኛም ሁላችን ከአንተ ፈቃድ፣ ከመኖሪያወችህ ከሲኦልና ከገሃነምም አመለጥን›› እያልን እንዘምር፡፡ ዳዊት አባታችን ግን አሁንም ይዘምራል፤ ወደ ሰገነቱ ወጥቶ ወደ እኛ ተጣራ፡፡ ልደቱን በከተማዉ በቤተ ልሔም አይቶ ‹‹እነሆ በኤፍራታ ሰማነዉ በዱር ዉስጥም አገኘነዉ፤ እንግዲህስ ወደ ማደሪያወቹ እንገባለን፤ እግሮቹም በሚቆሙበት ስፍራም እንሰግዳለን›› እያለ ሊሰበስበን ተጣራ፡፡ መላእክትም እዉነት ነዉ አሉ፡፤ ‹‹ሰዉን እንፍጠር ሲል እንደሰማነዉ ሰዉ ልሁን ሲል ሰማነዉ፤ የአዳምን ዕንባ ሊጠርግ አዳም ወዴት ነህ ሲል እንደሰማነዉ የአዳምን ሥጋ ተዋሕዶ እንደ አዳም ሲያለቅስ ሰማነዉ አሉ፡፡ ምንኛ ግሩምና አስደናቂ ምስጢር ነዉ፡፡ ‹‹ብርሃን ይሁን›› ሲል የሰሙትን አዳም በገነት ከጸጋዉ ሲራቆት የለበሰዉን ቅጠል ለብሶ አዩት፡፡ ‹‹ዉኆች ከሦስት ወገን ይለዩ››ሲል የሰሙትን ዉኃ ጠማኝ ሲል ሰሙት፡፡ ‹‹ባሕር በየወገኑ ፍጥረትን ታዉጣ›› ሲል የሰሙትን አሁንም ዉኃዉን ወይን እያደረገ እንደ ቀድሞዉ ዉኆችን እያዘዘ ተመለከቱት፡፡ መላእክቱ ቢጨንቃቸዉ ወደ ዱር ወርደዉ ላልተኙ እረኞች ተናገሩ፤ እነርሱን ቢደንቃቸዉ እረኞቹን መጥታችሁ እዩ እያሉ ጨቀጨቁ፡፡ ወንጌልንም ቀድመዉ ለመስበክ ተሽቀዳደሙ፡፡ በእዉነት መላእክቱን ምን አስቸኮላቸዉ፤ ገና በልደቱ ለስብከት ተቀዳደሙ፡፡ ሐዋርያ ጴጥሮስ ቢያዝንላቸዉ ‹‹ይህንንም ነገር መላእክቱ ሊመለከቱ ይመኛሉ››(1ኛጴጥ 1÷2) በማለት ሲጠብቁት የኖረ ነዉና ይገባቸዋል ብሎ ተከራከረላቸዉ፡፡ እነርሱ ግን እንደተፈጠሩ በጨለማ ዉስጥ ሆነዉ ማን ፈጠረን ሲሉ ብርሃንን ፈጥሮ ለእነርሱ መገለጡን አስታዉሰዉ ነዉ መሰል ምድሪቱን በብርሃን አጥለቀለቐት፡፡ ቢቸግራቸዉ ከደስታቸዉ ብዛት የተነሣ ከእረኞች ጋር ተጎዳኝተዉ ከእነርሱ ጋር ተጫወቱ፡፡ ባናያቸዉ ነዉ እንጂ ገናዉንም ሳይሞክሩት አይቀሩም፡፡እረኖቹስ ምን ቢታደሉ፤ በአንዲት ሌሊት ጌታን አይተዉ ከመላእክት ጋር ጌታቸዉን አመስግነዉ ያደሩት፡፡ መታደል ብቻ ነዉ፡፡
ዳዊት ግን አሁንም ይናገራል፤‹‹በዱረ ዉስጥም አገኘነዉ›› እያለ፡፡ እዉነት ነዉ፤ በገነት ያጣነዉን ልጅነት ቤተ ልሔም ዋሻ ዉስጥ አገኘነዉ፤ በሰማይ ያጣነዉን በምድር አገኘነዉ፤ በሰይጣን ተንኮል ያጣነዉን በአግዚአብሔር ልጅ በቃል መወለድ አገኘነዉ፡፡አዳም የተመኘዉን አምላክነትም ሳይቀር በአምላክ ሰዉ መሆን አገኘነዉ እያለ በገናዉን ይደረድራል፤ በምድር የተቀኘዉንም በሰማይ እያመሰጠረ ይዘምራል፡፡በምድር በመጽሐፉ አማካኝነት ከእኛ ጋር ይነጋገራል፤በሰማይም ከአባቱ ከአብርሃም ጋር ቀኒቱን አይቶ ይደሰታል፡፡(ዮሐ 8÷56) አምላክ ሰዉ በመሆኑ የተገለጠዉንና ፍጹሙን ፍቅሩንም እያሰበ እንዲህ አለ፡፡ ከአፈር አበጅተህ በፍጥረት ሁሉ ላይ ታሠለጥነዉ ዘንድ፤ ዕፀ በለስን በበላ ጊዜ አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ ብለህ ሥጋዉን ወደ መቃብር ነፍሱንም ወደ ሲኦል ካወረድክ በኋላ እንደገና ከሰማየ ሰማያት ወርደህ ሥጋዉን ነፍሱን ነሥተህ እርሱን ሆነህ ትወለድ ዘንድ ሰዉ ምንድን ነዉ? በአንተ ላይ አምፆ የተነሳብህን ሰዉ ስለትንሽ ንሰሐዉ ብለህ አንተ ሰዉ ሆነህ እርሱን አምላክ ታደርገዉ ዘንድ ስዉ ምንድን ነዉ? መጨረሻ የፈጠርከዉን ሰዉ የፍጥረት ተቀደቀሚ ብቻ ሳይሆን በተዋሕዶተ መለኮት ፈጣሪም ታደርገዉ ዘንድ ሰዉ ምንድን ነዉ? በዲያብሎስ ተታሎ ከወደቀ በኋላ በመከራ ጅራፍ እየተገረፈ በኀጢኣት ስለት እየተወጋ በሲኦል ሲቀጣ የነበረዉን ሰዉ በተዋሕዶ ሰዉ ሆነህ አጋንንትን ይቀጠቅጥ፣ ሠራዊተ ዲያብሎስን ያስር ዘንድ እንዲቻለዉ ታስበዉ ዘንድ ሰዉ ምንድን ነዉ? እያለ ይዘረዝራል፣ ቅኔዉን ይተረጉማል፣አባታችን ዳዊት እያለቀሰ ይዘምራል፤እየዘመረም ያለቅሳል፡፡ እየተደሰተ ይደነቃል፤ እየተደነቀም የተደረገልንን ይመረመራል፤ ለትዉልዱም በመጽሐፉ ይነግራል፡፡ ሐዋርያ ጳዉሎስም የመላእክትን ዝማሬ አይቶ፣ አምላክ በሥጋዌዉ የገለጠዉ ፍቅርም ወሰን የሌለዉ መሆኑን ተረድቶ ለጢሞቴዎስ አሁንም አሁንም ይነግረዋል፡፡‹‹ እግዚአብሔርን የመምሰል ምስጢር ታላቅ ነዉ፤ በሥጋ የተገለጠ፣ በመንፈስ የጸደቀ፣ለመላእክት የታየ፣ በአሕዛብ የተሰበከ፣በዓለም የታመነ፣በክብር ያረገ›› (1 ጢሞ 3÷16) ብሎ አሳጥሮ መደመሙን ቀጠለ፡፡ በርግጥም ያስደምማል፤ እየጨመረ የመጣ ፍቅር፡፡ስለዚህ አምላካችንን እናመስግነዉ፤ ከሰሎሞን ጋር ‹‹ በአንተ ደስ ይለናል፣ሐሴትም እናደርጋለን፤ ከወይን ጠጅ ይልቅ ፍቅርህን እናስባለን›› (መኃ 1÷4) እንበለዉ፡፡ ከዳዊትም ጋር ሆነን ዲያብሎስን ድል የነሣሁብህ ‹‹ አቤቱ ጉልበቴ ሆይ እወድሃለሁ›› ስንል እናመሰግነዉ፡፡ በርግጥ ሕይወታችንንም እንኳን ብንሰጠዉ ለእግዚአብሔር ምን እንጨምርለታለን?ምንስ እንፈጽምለታለን? ምን አልባት አንድ ነገር ብቻ፤ ስሙን ቀድሶ ክብሩን መዉረስ፤ ይህም ቢሆን ለእኛ ጥቅም፡፡ ታዲያይህ ሁሉ ፍቅር ይሰጠዉ ዘንድ፣ ይህንንስ ሁሉ ጸጋና ክብር ያገኝ ዘንድ ሰዉ ምንድን ነዉ?መላእክት ባለመዉደቅ የሚያገኙትን ሰዉ ከዉድቀት ተነሥቶ ያገኘዉ ዘንድ፤ ለእነርሱ ያልተቻለዉን የማይቻለዉንም አምላክነት ያገኝ ዘንድ ሰዉ ምንድን ነዉ? ሐዋርያዉ ቅዱስ ጳዉሎስ እንደተናገረዉ ‹‹በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን›› (ኤፌ 2÷7) ብሎ ይናገር ዘንድ በእዉነት ሰዉ ምንድን ነዉ? አምላክ ሰዉ በመሆኑ መራባችንን፣መጠማታችንን፣ መሰደዳችንንም ተቀበለ፡፡ አንቀላፋ፣ተራበ፣ ተጠማ፣ አለቀሰ፣ ፈራ፣….እስኪባል ድረስ የእኛን ባሕርይ ሁሉ ገንዘብ አደረገ፡፡ ከአንድ ከኀጢኣት በቀር ነዉራችንን ሁሉ ተሸከመ፡፡ይህን ሁሉ ያደርግልን ዘንድ በእዉነት ሰዉ ምንድን ነዉ? በርግጥም ልዩ ፍቅር፡፡ እንግዲህስ ወደ ማደሪያዎችህ እንገባለን፣ እግሮችህ በቆሙበት ስፍራም ሁሉ እንሰግዳለን፡፡ (መዝ 131÷)  
ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰብእ፡፡
እንዃን  ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት አደረሳችሁ፡፡
                                                           -//-
መልካም በዓል ይሁንላችሁ!
http://yonas-zekarias.blogspot.com/