Friday 9 March 2012

“የቀደመውን ፍቅርህን ትተሃልና የምነቅፍብህ ነገር አለኝ!”


 “አምራለሁ ብላ ተኩላ አይኗን አጠፋችው ቸኩላ!" ብሎ ሲተርባት እሷም ቀበል አድርጋ “መከራው ያላለቀለት በሬ ቆዳው ለነጋሪት ይጠፈራል” ብላ አፉን አስያዛቸው። ከእኛ ሰፈር ሁለት ፍቅረኛሞች ከሚጎሻሸሙበት የቅኔ አዝመራ በመነሳት ይህ ጽሁፍ ተጀመረ።

“የቀደመውን ፍቅርህን ትተሃልና የምነቅፍብህ ነገር አለኝ!”
ራዕይ 2:4

አንድ ወዳጄ የልብ የልቡን ሊያወጋኝ ነበር እንዲህ ብሎ ያጫወተኝ፤ እኔም የልብ የልቤን ስለነገረኝ የልብ የልቡን ሰማሁት፤

እህህህ ……. አያያያያያ…..
እያለ መጣና ንግግሩን ቀጠለ፤ አገልግሎት ቀላል አይደለችም ለካ ጃል! ታንገዳግዳለች ለካ! አለ እራሱን እያንገዳገደ። ኧረ እንዲያውም ታጎብጣለች አለና እራሱ እንደ መጉበጥ አለ፤ ሆዴ በጀርባዬ ቢሆን ገፍቶ ገደል በጣለኝ ነበር ሲል አነጋገሩ አሳቀኝ። ይህ ወዳጄ ወትረ ነገረ ስራው ሁሉ ያስቃል፤ ቀልድ አሳምሮ ስለሚችልበት በንግግሩ ሁሌ እንደሳቅን ነው፤ ካሳቀን በኋላ ወዲያው ቁም ነገር ጣል ያደርጋል፤ ዛሬም እንደለመደው ትንሽ  ቀልዶቹን ከለቀቀ በኋላ ወዳጄ የልቡን ቀጠለ፤

እኔ የምልህ እኔ ብቻ ነኝ እንዲህ የሚሰማኝ ወይስ ሁላችሁም ይሰማችኋል? ለምን? እንዴት? እያለ ጥያቄውን አንጎደጎደው። የልቡን ለሚነግርህ ልብህን ስጠው! የሚለውን አባባል ለመጠቀም ልቤን ሰጥቼው ሰማሁት። ወዳጄ ይህ በአንተ የተጀመረ አይደለም፤ ሁሉም የሚሰማው ነውና ብዙ ራስህን አትረብሽ ብዬ ለማረጋጋትም ሞከርኩ።

   መኑ ይኅድገነ ፍቅሮ ለክርስቶስ?
በእርግጥ አገልግሎት ታንገዳግዳለች፤ እንደ ወዳጄ እኔም እየተንገዳገድኩ እንዳላሳያችሁ ለጊዜው መተያየት አንችልም! የሆነው ይሁንና የፈለገ ብንንገዳገድ የት እንሄዳለን? መኑ ይኅድገነ ፍቅሮ ለክርስቶስ? ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን ማን ነው? ርሃብ ነውን? ስደት ነውን? ግርፋት ነውን? እያለ ታላቁ ሐዋርያ የደረሰበትን ሁሉ እያነሳ ያስብና ይህ ሁሉ ግን ከክርስቶስ ፍቅር፣ ከአገልግሎት ፍቅር እንደማይለየው ይነግረናል። “እናቱ የሞተችበትና ውሀ ልትቀዳ የወረደችበት እኩል ያለቅሳሉ” እንዲል እኛ ይህን ያህል ባንፈተንም እንደ ሐዋርያው የተፈተነ ያህል እንሆናለን። “እንስራዋን ጥላ ወንዝ ወረደች” አሉ፤ አንዘንጋ ይህ እኮ መንፈሳዊ አገልግሎት ነው! ታዲያ እንዴት ያለ ፈተና አገልግሎትን እንጠብቃለን? “የሰይጣንን አመጣት የማያውቅ አይመንኩስ” እንዲል አገልግሎትን ያልተረዳም እንዲሁ ነው።


ብልጥ የሆነ ሰው ግን በዚህ መረበሽ የለበትም። “ለላም ቀንዷ አይከብዳትም” ይባላል እኮ ሰዎች! ኧረ አይክበደን። እስ እራሳችንን እንጠይቅ፤ 

ከአገልግሎት ፍቅር የሚለየን ማን ነው?

ይህ መልስ የሌለው ጥያቄ ነው። በቃ መልስ የለውማ። ለምን ታስባላችሁ? አልኳችሁ እኮ መልስ የለውም። ከአገልግሎት ፍቅር የሚለየን ማንም የለማ። 



ማን ነው ደስ ደስ እያለው አንዳች ሳይፈተን ያገለገለው?
ሐዋርያት ናቸውን? ካህናት ናቸውን? ሐዋርያው “መልካም ገድል ተጋድያለሁ ሩጫዬን ፈጽሜያለሁ ሐይማኖቴን ጠብቄያለሁ የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል” ብሎናል፤ በመንፈሳዊ ህይወት ለጽድቅ አክሊል መጋደል ያስፈልጋል፣ በአለማዊ ህይወት የጀግንነት ጎፈሬ ለማግኘት መጋደል ያስፈልጋል! አንድ አገልጋይ ያለፈተና የአገልግሎት የጽድቅ አክሊልን ማግኘት ፈለገ ማለት “ሳይዋጉ ጎፈሬ” እንደ ማለት ይሆንበታል!

“እርሻው ሲያምር ዳቦው ያምር” አለች ሴትዮዋ እውነቷን እኮ ነው፤ ይህን አባባሏን ስታስረዳም “እርሻ የተባልነው እኛ ነን፤ ይህ እርሻ ሲያምር ለአገልግሎት የሚጋገረው ዳቦም ያምራል” ብላ አስረድታለች። “አንድነት ያገባል ገነት” ይባላል እኮ ሰዎች! “አንድ ጣት ቁንጫ አይገድልም” ይላል የሀገራችን ገበሬ! ኧረ ምን የመሳሰሉ ምርጥ ምርጥ የአንድነት ተረቶች አሉን መሰላችሁ፤ “እርስ በእርሱ ያልተደጋገፈ ግድግዳ አይቆምም” ይልሃል የሀገርህ አባባል። በአንድ ወቅት ጀግናው ቀነኒሳ “ብቻውን የሚሮጥ አይቀድምም” ብሏል። እውነት ነው ብቻውን የሚሮጥ አይቀድምምና እስኪ ከሰው ጋር አብረን እንሩጥ፤ እናንተዬዋ ነገር ነገርን ይወልዳል፤ ሩጫ ሲባል በቅርቡ በከተማችን ለንደን የሚጀመረው ኦሎንፒክ ትዝ አለኝ። ሁሉም ይለማመድና እስኪ ሁሉም ይሩጥ፤ ሁሉም መንፈሳዊ ሩጫን ይሩጥ። ሩጫዬን ፈጽሜያለሁ አለ ሐዋርያው! ይህች ሩጫ በእርግጥ ታደክማለች! ሩጠህ ሩጠህ ሩጠህ መጨረሻ ላይ የምታገኛት የድካም ውጤት ግን እንዴት ትጥማለች መሰለህ! እንዴት የመንፈስ ደስታ ትሰጣለች መሰለህ! “ከባለቤቱ እጅ የዋለ እንቁላል አይሰበርም” እንዲል በጥንቃቄ የያዙት አገልግሎት ብዙዎች አጣጥመውታል፤ “በጅብ ችኩልነት ከምግብ ጣፋጭነት ሳይተዋወቁ ይኖራሉ” እንዲል የምንመገበውን እያጣጣምን ከሆነ በእርግጥ መጣፈጡ አይቀርም። ችግሩ በችኩልነታችን ሳንቀምሰው መቅረታችን ነው፤ እስኪ እንቅመሰው፣ እስኪ በአገልግሎትም እንበርታ።
ጌታን ለማገልገል በመንፈስ የጋላችሁ ሁኑ እንጂ ከዚህ ትጋታችሁ ወደ ኋላ አትበሉ [ሮሜ 12:11]

አገልግሎታችን ለብ ያለ መሆኑን ቅ/ጳውሎስ አይቷል መሰል
“ጌታን ለማገልገል በመንፈስ የጋላችሁ ሁኑ እንጂ ከዚህ ትጋታችሁ ወደ ኋላ አትበሉ” ይለናል። ጌታችንም ለብ ያለውን አገልግሎታችንን አይቷል እኮ፤ ለብ ስላልን እንዲህ ብሎናል በራድ ወይም ትኩስ እንዳልሆንክ አውቃለሁ፤ በራድ ወይም ትኩስ ብትሆንስ መልካም ነበር። እንዲሁ ለብ ስላልህ ከአፌ ልተፋህ ነው” ራዕ [3:13] ይህ ራዕይ ከጅምሩ እንዲህ ነበር፦ ሎዶቂያ የምትባል አንዲት ከተማ ከነበረባት የውሀ አቅርቦት ችግር የተነሳ ከአካባቢዋ ከሚገኙ ፍል ውሀዎች በቦይ ተስበው  ለከተማዋ አገልግሎት ይሰጡ ነበር። ውሀው ወደ ከተማው ሲደርስ ለብ ይላል፤ ይህ ውሀ በብዙ ሚኒራሎች የተሞላ contaminated ስለሆነ ለመጠጣት በጣም አስቸጋሪ ነበር። ለቤተክርስቲያኑ መሪ እንደ ከተማው የውሀ ባህርይ እንዲህ የሚል መልዕክት ተጻፈለት፦ በራድ ወይም ትኩስ እንዳልሆንክ አውቃለሁ፤ በራድ ወይም ትኩስ ብትሆንስ መልካም ነበር። እንዲሁ ለብ ስላልህ ከአፌ ልተፋህ ነው” በአገልግሎታችን ለብ ያልን ሳይሆን ጌታን ለማገልገል በመንፈስ የጋላችሁ ሁኑ! ተብለናል።

“እሳት መጣብህ ቢሉት እሳር ውስጥ ገብቻለሁ አለ ሞኙ!” ፈተና ሲመጣ  ወደ ኋላ ማለት የለብንም፤ ይህ እራስን ለፈተናው ማመቻቸት ነውና።

“ወጣት የነብር ጣት” ነውና ነገሩ ወደ ኋላ ያላችሁ ሁሉ እንደ ቀደመው ኑ እንደ መጀመሪያው በርቱ ፣ እንደ በፊቱ በፍቅር አገልግሉ ይለናል ታላቁ ሐዋርያ! “የቀደመውን ፍቅርህን ትተሃልና የምነቅፍብህ ነገር አለኝ!” ራዕይ 2:4 ይህ መልዕክትም ታላቅ ነው፤

“ሲበላ ለሚከሳ ሲነግሩት ለሚረሳ ለዚያም ምግብ ለዚህም ነገር ንሳ” እንዲል እስኪ ልብ ብለን እንስማ፤ “መናገር መልካም ነው ማዳመጥ ይበልጣል” እንዲል እስኪ እኛም ሐዋርያቱ የሚሉትን እናዳምጥ። አበው የዝሆን ጆሮ ይስጥ ይላሉ።
የአገልግሎት መሰረት የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች ምንድን ናቸው?

አንድ አገልጋይ ይህን ካላወቀ በእውኑ በአገልግሎቱ ሲናወጥ ይኖራል! ይህ የአንድ አገልጋይ የባንኩ የምስጢር ኮድ እንደ ማለት ነው፤ እነዚህም ፍቅር፣ ትዕግስት፣ ትህትና ናቸው።

v                       አገልግሎት ያለ ፍቅር ከንቱ ነው! 

v                       አገልግሎት ያለ ትዕግስት ከቶ አይቻልም!

v                       አገልግሎት ያለ ትህትና ፍሬ ቢስ ነው!

አገልግሎቱን የሚወድ ጆሮ ያለው ይስማ!
የቀደሙት አባቶች በአገልግሎት ያለፉበትን የአገልግሎት ሚስጢር በነጻ ይግዛ! ቅ/ጳውሎስ ለዚህ ነው የአገልግሎት መሰረት የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎችን ፍቅርን፣ ትዕግስትን፣ ትህትናን እንድንገዛ የሚነግረን። ገላትያ 5:21    

አገልግሎት ጨለም ሲል ማማረር የለብንም፤ “ጨለማውን ከምታማርር ሻማውን አብራ” ይባላልና ሻማውን ግዛና አብራ! የፍቅር ሻማ! የትዕግስትን ሻማ! የትህትናን ሻማ ግዛና አብራ፤ ይህን ግዜ ጨለማው ብርኃን ይሆናል።

የፍቅር ሻማ! ፍቅር ማለት የሚወዱንን ብቻ መውደድ ማለት ሳይሆን የሚጠሉንንም መውደድ ማለት ነው!

የትዕግስት ሻማ! የካህናቱ ልብሰ ተክህኖ ሰፊና የተንዠረገገ የሚሆነው ትዕግስታቸው እንደ ልብሳቸው ሰፊ መሆኑን ለማመልከት ነው፤ የመዘምራን ልብስ ግን እንደምናውቀው ጠባብ ነው፤ ትዕግስታችን ሰፊ ሲሆን ምን አልባት ልብሱም ሰፊ ይሆን ይሆናል!

የትህትና ሻማ! ያለ ትህትናማ ማንን ልናገለግል ነው? ታላላቅ አገልጋይ የሚባሉትን እስቲ እንያቸው፤ ከሁሉ ዝቅ ዝቅ ይላሉ። እውቀት ጥበብ ችሎታ ወዘተዎች ለእነሱ አይታሰባቸውም። ሰዎች ከፍ ሲያደርጓቸው ከልባቸው ይጠሉታል ዝቅ ሲሉ ደስ ይላቸዋል።
አገልግሎት በዲያቢሎስ ጥቁር መነጽር

የበጎ ነገር ሁሉ ጠላት የሆነው ዲያቢሎስ እነሆ በየዕለቱ ሐሜትንና ወሬዎችን ሊያቀርብላችሁ ዝግጁ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ጥሎችንና ችግሮችን መከራዎችን ያቀርብላችኋል፤ ኧረ ጆሮ ከሰጣችሁትማ ምርጥ ምርጥ ወሬ ሊያዋራችሁ ሁሌ ዝግጁ ነው! የሰዎችን ሚስጢርና አስተሳሰብ ሳይበርድ በትኩሱ ያቀርብላችኋል። በልባችሁ ቦታ ስትሰጡትም ትበሳጫላችሁ ትጨናነቃላችሁ። ብልጥ የሆነ ግን የጆሮውን በር ከእነዚህ ከንቱ ነገሮች ሁሉ ይዘጋል! ይገርማል! የማይጠቅም ነገር ሰምቶ የውስጥ ሠላምን ማጣት ምንኛ ያላስተዋልነው ነገር ነው!

ቢቻላችሁ ከሰው ሁሉ ጋር በሠላም ኑሩ! የምትለዋን የሐዋርያውን መልዕክት እወዳታለሁ፤ ሮሜ 12:18
ዮሐንስ አፈወር ምን አለ መሰላችሁ፤ “አስተዋይ በየቀኑ ጠላቱን ወዳጁ ሲያደርግ ሌላው ግን በየቀኑ የልብ ወዳጁን ያጣል!” ብሏል። እነዚህ ሁሉ ቢደመሩ ግን ፍቅር ትዕግስት ትህትና ናቸው! 

አንድ አገልጋይ በአገልግሎት እያደገ ሲሄድ ተካፋይ የሚሆንባቸው ነገሮች እያደጉ ስለሚሄዱ ስህተቶችም እያደጉ ይሄዳሉ። ኃላፊነቱ እየጨመሩ ሲመጡ ሙሉ ግዜው ይዋጣል፤ ራሱንም ይረሳል። ለነፍሱ የሚያስፈልጋትን ምግብ ስለማያቀርብላት ቁልቁል ይወድቃል። እንደዚህ አይነቱ ሰው እሱ ራሱ ሳይሻገር ሌሎች ሰዎችን ከአንዱ ወደብ ወደ ሌላኛው ወደብ የሚያሻግር ድልድይን ይመስላል፤ ወይም ደግሞ እሱ ወደ ቤተ መቅደስ ሳይገባ ሰዎች እንዲገቡ የሚጣራ ደወልን ይመስላል! ለዚህ እኮ ነው ሐዋርያው “ለሌሎች ከሰበኩ በኋላ ራሴ የተጣልኩ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጎሰምኩ አስገዛዋለሁ” ያለው። [1ኛ ቆሮ 9:27]
“አገልጋይ” የሚለው ስም ለመላዕክት የተሰጠ ድንቅ ስም እንደሆነ ታውቃላችሁ! መላዕክት ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ የሚያገለግሉ መናፍስት አይደሉምን? ፤ መላዕክቱን መንፈስ የሚያደርግ አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል፤
ዕብ 1:14 መዝ 103:4 ይህን ድንቅ ስም በድንቅ አያያዝ ያዘው።

በአገልግሎት ማንኛውም አይነት ፈተና ሲገጥመን እግዚአብሔር ከፍ ላለ ተልዕኮ እያዘጋጀን እንደሆነ ታውቃላችሁ!? ቅ/ጴጥሮስን ያዘጋጀው ሥጋዊ ድካሙን እንዲያውቅና ከሌሎች ሐዋርያት በላይ ራሱን ከፍ አድርጎ እንዳያይ ነበር። ዮሴፍን በታላቅ ፈተና ውስጥ ለታላቅ ተልዕኮ አዘጋጀው፤ ነነዌን የሰበካት ነቢይን በማዕበል በወጀቡ ቢያልፍም ለካ ይህ ሁሉ ለተልዕኮ የሚያዘጋጁ ነበሩ!

አንተ ዓሣ አጥማጅ አገልጋይ ሆይ!
ይህች ጽሁፍ ለአገልግሎትህ እንደምትጠቅምህ ይታመናል።

“የቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ!”
ይህች ጽሁፍ በአገልግሎታችን የቆምን የመሰለን እንዳንወድቅ፣ የወደቅን እንድንቆም ታስባ የተጻፈች ናት።
1ኛ ቆሮ [10:12]

በዐቢይ ጾም ገብር ኄር /ታማኝ አገልጋይ/ የሚላከው ኢሜልም እጅግ ይጠቅማልና ከወዲሁ አያምልጦ!

አንተ ዓሣ አጥማጅ አገልጋይ ሆይ!
መረቡን ወርውሮ በተገኘው ዘዴ ሁሉ የበዙ ዓሦችን የሚያወጣ ዓሣ አጥማጅ ምንኛ ብልኅ ነው!