Friday 26 July 2013

ሕሊና እና ምክንያት





በጎ ሕሊና ያለው ሰው እንዴት የታደለ ነው? ብዙዎች ግን ሕሊናቸውን በምክንያት ያታልሉታል። ድሮ ድሮ ኢየሱስ ጾሞልኛል ብለው ለሕሊናቸው ምክንያት ነግረውት ነበር። ነበር ካልኩ ነገር አለ ማለት ነው፤ ዛሬ ግን መጾም ተጀምሯልና ተመስገን ነው። ግን ግን ምስጢር መደበቁ ነው? መጾማችሁን ሳትነግሩን ድንገት መጾም ጀመራችሁሳ፤ ሆኖም ሁል ጊዜ ወቀሳ ብቻ ሳይሆን ማበረታታትም ይገባልና በርቱ።

በጅብ ሆዳምነት በእህል ጣፋጭነት ሳይተዋወቁ ይኖራሉ አሉ! የሀገራችን ጅብ ቀን ሙሉ ጾሞ ማታ ያገኘውን ሁሉ ግጥም አድርጎ ይጠልፋል አሉ። ጅብ በእኛ ጊዜ ቀረ!! መቼስ የዘንድሮ ጅብ አይረባም ፤ ሲዖል ይዘጋላችሁና ጅቦቹ እንደ ድሮ ከመጥለፍ አፕታይታችን ተዘግቷል አሉ። መቼስ የመርካቶ አራዳ ምግብ ሲበላ እንደ ጉድ ጠለፍን ነው የሚለው አሉ። የዛሬ ዘመዶቻችን ጾማችን ከጅብ ጾም መለየት አለበት አትሉም? ዳንኤልና ሰልስቱ ደቂቅ ጮማ ቁረጡ ጠጁንም ገልብጡ ሲባሉ አትክልትና ውኃ ይበቃናል አሉ።

መዝሙረ ዳዊት

109፥24 ጕልበቶቼ በጾም ደከሙ ሥጋዬም ቅቤ በማጣት ከሳ።

አሁን ማን ይሙት ዳዊት በቤተ መንግሥቱ ቅቤ ጠፋ? ታድያ ሥጋዬም ቅቤ በማጣት ከሳ ለምን አለ?

እንግዲያውስ ምን እንላለን? ኢየሱስ አድኖኛልና ሁሉ ተፈጸመ ካላችሁ ጾም ለምን አስፈለጋችሁ? ይህን በእጅጉ አስቡበት። ሐዋርያው በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ አለን። ያለመከራ አይገኝም እንጀራ እንዲሉ በመከራችን ብዛት የዘላለም ሕይወትን ባንወርስም ዘላለማዊ ሕይወት በቀላሉ አትገኝም። በጠባብዋ በር ተመላለሱም የተባለው ለዚህ ነው። ጮማ መቁረጥ ቢራ መገልበት ሲቻል አባቶች በበረሃ አትክልት መብላታቸው ዳዊትና ዳንኤል የጾሙትን አይተው ነው። እናንተም ትጾማላችሁ ፤ ገዳማዊያኑም ከእናንተ አስበልጠው ይጾማሉ። ታድያ ከእናንተና ከአባቶች የተሻለውን ማን አደረገ?? በስራና ያለ ስራ መንግስተ ሰማይ አንገባም! በሌላ አነጋገር ስራ የግድ ያስፈልጋል።

አንዳንዶቹም ምክንያት ፍለጋ ይደክማሉ። በየአይነቱ እየበላችሁ ቢራ እየገጠማችሁ ለምን ትጾማላችሁ እያሉ ለሕሊናቸው ምቹ ምክንያት ይነግሩታል። ይህ ግን ምክንያት እንጂ ትክክለኛነትን አያስረዳም። ቢራ ለሚደረግመው ስጋን የሚተኩ ምርጣምርጥ ምግቦች ለሚበላው ጾም ይህ አይደለም ብለን እንነግረዋለን እንጂ ሕሊናዬ ሆይ ደስ ይበልህ ምክንያት አለልህና አትረበሽ አንለውም!

ሕሊና እና ምክንያት

አንድ ኦርቶዶክስ ወንድሜ እንዲህ ብሎ ጠየቀ፦ ሴቶች ራሳቸውን ሳይከናነቡ ለምን ይጸልያሉ? አንዱ ፕሮቴስታንት ደግሞ ተከናንቦ የሚጸልይ ወንድ ራሱን ያዋርዳል ይላልና ካህናቱ ለምን ይጠመጥማሉ ብሎ ጠየቀ። ወዲያው አንዷ እህቴ አሁንማ የነብርን ጭራ ያዝን ብላ እጅግ ስትደሰት አየሁና ተገረምኩ። ለዘመናት የሕሊናዋ ጥያቄ ነበር ማለት ነው። እንግዲያውስ ስለምን ከህሊናዋ ጋ ስትጣላ ኖረች? በመሰረቱ ካህናቱ ከተሳሳቱ እኛን አትናገሩን እንደፈለግን እንሁን እንዴት ይባላል? ሁለታችንም ወደ እውነት እንምጣ ይባላል እንጂ ለሕሊና ምክንያት መደርደር ሕሊና ራሱ ይታዘባል! የዳዊት በገና ይደረደራል እንጂ የሕሊና ምክንያት አይደረደርም!

ተከናንቦ የሚጸልይ ወንድ ራሱን ያዋርዳል ካህናቱ ለምን ይጠመጥማሉ? ካህኑ ኢያሱ በራሱ ላይ ይጠመጥም ነበር። እነሆ መልአኩም አዲስ ጥምጣም ጠመጠመለት እንዲል ካህናት የሚጠመጥሙት ለዚህ ነው።

ዘፀ28:40 ቆቦችንም ለክብር ታደርግላቸዋለሀ...41 በክሀነት እንዲያገለግሉ
ዘሌ8:9 እግዚአብሄርም ሙሴን እንዳዘዘው በራሱ ላይ መጠምጠሚያዉን አደረገ...የተቀደሰዉንም አክሊል
ዘካ6:11 አክሊሎችንም ስራ በታላቁም ካሀን ...ራስ ላይ ደፋ 1ነገ21...

እንግዲያውስ ምን እንላለን? ካህናቱ የሚጠመጥሙት በዚህ ምክንያት ከሆነ እህቶቻችን ፍሪዝ አድርገው የሚጸልዩት ለምን ይሆን? ዘመዶቼ ሆይ ለሥጋችሁ ምኞት ስለምን ምክንያት ፈለጋችሁ? እህቶች ሆይ ኢስላም እህቶች ሲከናነቡ ጌታን ተከታይ መንፈሳዊያኑ ምክንያት ከምትፈልጉ ሥጋዊ ምኞታችሁን መቆጣጠር እንዴት አቃታችሁ? ቅ/ጳውሎስ ሰውን ከማሰናከል ከቶ ሥጋ አልበላም አለ። አስቡት ስጋ መብላት ኃጢአት ባይሆንም ሰውን ላለማሰናከል ብቻ ስጋ አልበላም አለ። ዘመዶቼ ሰውን ላለማሰናከል ይህን ያህል ባታስቡ ትንሿን ነገር መፈጸም እንዴት ተሳናችሁ? በመላዕክት ምክንያት ሴት ራስዋን ትከናነብ ይላል። መላዕክት ሥርዓትን ነቅተው ስለሚጠብቁ በቅድስት ቤተክርስቲያን ሴቶች ራሳቸውን ተከናንበው እንዳማረባቸው ውብ ሆነው ያመሰግናሉ።

አንዳንዶቹም ቅ/ጳውሎስ የጻፈበት ባህል እንጂ ግዴታ አይደለም እያሉ በባህል እያማካኙ እንደተለመደው ለሕሊናቸው ምክንያት ይሰጣሉ። ሕሊና ምክንያት ካላገኘ ደጋግሞ ይጠይቃልና ምክንያት ማቅረባቸው የግድ ነው። ከዚህ ውጪ የሆኑ ብዙ ምክንያቶችም እንደሚደረደሩ እናውቃለንና ሰው በገና ይደረድራል እንጂ ምክንያት አይደረድርም እንላቸዋለን።

ሴቶች ፓስተር ለምን አይሆኑም የሚሉም አሉ። ክርስቶስ 12 ሐዋርያትን ሲመርጥ 6 ወንድ 6 ሴት አድርጎ መምረጥ ይችል ነበር። ከየት እንደመጣ አይታወቅም በድፍረት ይፈጽሙታል። ፕሮቴስታንት ዘመዶቻችንን የሚመሩ አውሮፓዊያን በድፍረት ሁሉን ያከናውናሉ። የሰውን ልጅ ፍቅር እግዚአብሔር ይወዳልና ወንድ ከወንድ ሴት ከሴት ቢጋቡ የፍቅር አምላክ ቅር አይለውም የሚል መፅሐፍ ቅዱስ በቅርቡ ይወጣልና ጠብቁ።

እንግዲህ ለዚህም ክፉ ነገር የሕሊና ምክንያት ይደረደር ይሆን? እንግዲያውስ ምን እንላለን? ለሁሉ ምክንያት ቀረበ፤ ለጾም ምክንያት ....ጅብ በጎቹን ጠብቅ ቢባል ይጠፉብኛል አለ አሉ! ምን አለ ምክንያት ከሚሰጥ እውነቱን ነግሮን ልበላቸው ፈልጌ ነው ቢል? ምክንያት ለሰው ብቻ ሳይሆን ለጅብም ይሰራል ለካ።

No comments: