Thursday 25 July 2013

እናት ለልጅዋ ነቢይ ናት!


የነቢዩ ዮናስ እናት ያቺ ሱናማዊት የኤልሳዕን በረከት አግኝታለች። ያልሰማ ካለ ይሂድና እንስራዋን ይይ። በዘይት መሞላቱን ይይ። ዕዳዋ መከፈሉን ይይ። ነቢዩ ኤልሳዕ ምን ላድርግልሽ አላት። ልጅ አልነበራትምና ልጅ እንድትወልድ አበሰራት። ልጇ ሲሞት አስነሳላት። እንግዲያውስ ይህን ህይወት እኛም ብንኖር እንዴት መታደል ነበር? ዕዳ እየከፈሉልን የሞተብንን እያስነሱ መኖር አይ መታደል ነበር!!

ቆይ ግን ሱናማዊቷ እግዚአብሔርን አታውቅም እንዴ?? ደግሞ ኤልሳዕን አገልጋይህ ነኝ ትላለች። የሰው አገልጋይ ነን እንዴ? ይህ ሁሉ አምልኮት ሲደረግ እግዚአብሔርስ እንዴት ዝም አለ?

ሱናማዊቷ ኤልሳዕን ቅዱስ የእግዚአብሔር ሰው ብላ ጠርታዋለች። እግዚአብሔር ማን ኤልሳዕም ማን እንደሆነ በሚገባ ታውቃለች። እነሆ የኤልሳዕን በረከት አፍሳለች፤ አምላክዋ እግዚአብሔርም ማድጋዋን ሞልቶ ልጅ አግኝታ ኖራለች። ደም ከደም ስር ጋ እንደማይጋጭ ሁሉ የእግዚአብሔር ስራ ከቅዱሳኑ ስራ ጋ አይጋጭምና!

የነቢያት ማህበር ለነቢዩ ኤልሳዕ ሰገዱ 2ኛ ነገሥት 2 ፦15 እነዚህ ነቢያት ሁል ጊዜ ይገርሙኛል። እኔ ብሆን ግን እኔም ነቢይ ኤልሳዕም ነቢይ ብዬ የማልሰግድለት ይመስለኛል። ግን ግን እኛም ነቢይ ኤልያስም ነቢይ ምን ያመጣል ብለው እንዴት አልተከራከሩም? ደግሞ እኮ ነቢይ ስለሆኑ ያለፈውንና የሚመጣውን ያውቃሉ። ታድያ ለጌታ ብቻ እንሰግዳለን ለምን አላሉም? የኤልያስ መንፈስ በኤልሳዕ ላይ ሆኗል ብለው ነቢያቱ ሰገዱ። ለሰው ሲሰገድ ይህ ሁሉ ባዕድ አምልኮ መፅሐፍ ቅዱስ ላይ እንዴት ተጻፈ? ይባስ ብለው ነቢያቱ ለኤልሳዕ "እነሆ እኛ አገልጋዮችህ ነን" አሉ። አሁን ማን ይሙት ሁሉም ነቢይ ከሆኑ ለምን አገልጋዩ ሆኑ? ደግሞ የሰው አገልጋይ አለ? ለማየት የሚፈልግ አይኑን ይገልጣል አሉ!

በዮሴፍ ምክንያት ግብጽ ጠገበች። በሙሴ ባህር ተከፈለ ፤ በኢያሱ ፀሐይ ቆመ፣ በኤልያስ ሰማይ ተለጎመ፣ በዳንኤል ምስጢር ተፈታ፤ ስለ ማን እንጨምር ? ለመተረክ ጊዜ የለንም ። እነዚህ ሁሉ እንደ ደመና በዙሪያችን ከበውን አይደለምን? እንግዲያውስ ካላየሁ አላምንም ማለት ዳግማዊ ቶማስ መሆን አይደለምን? ቶማስማ አምኖ አምላኬ ብሏል። ሁሉም ነቢይ አይደለም ሁሉም ጻድቅ አይደለም፤ ሁሉም ካህን ሁሉም ሐዋርያ አይደለም። እንግዲያውስ ሐዋርያቱን ለምን መረጣቸው? አስቀድሞ የወሰናቸውን ጠራቸው። ሁሉን ጥለው ተከተሉት። የጠራቸውን አጸደቃቸው አከበራቸውም። ወደ ቀደመው እንመለስ ፦ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል፥ ማለት ምን ማለት ነው? ጌታችን ይህን ቃል ለምን ተናገረ? ትርጉም የሌለው ቃል ነው?

No comments: