Saturday 26 November 2011

   


ነገረ ማርያም [Mariology]

+++ አዳም ዕፀ በለስን ከበላ በሗላ ዕፀ ሕይወት [the tree of life] ነበረለት; ከዕፀ ሕይወት ቢባላ ኖሮ የበደለው ታድሶ በንስሃ ኢየሩሳሌምን ባገኛት ነበር፤ ነገር ግን ከዕፀ ሕይወት አልበላም ለምን ቢሉ እሳታዊያን መላእክት የሆኑት ኪሩቤል በነበልባላዊ ሰይፋቸው ዕፀ ሕይወትን ይጠብቋት ነበርና ይለናል ዘፍጥረት 3:22። ታሪኩን ብናነበው በጣም ደስ ይላል፦ አዳም እጁን ዘርግቶ ከዕፀ ሕይወት ሊበላ ስላልቻለ በላብህ ደክመህ ኑር ተብሎ ከገነት ተባሮ ለእንስሳት ወደተፈጠረችው ወደዚህ አለም ተጣለ። *በመጨረሻው ዘመን ተስፋሁ ለአዳም የተባለችው እመቤታችን ዕፀ ሕይወትን ለአዳም ወለደችለት; ዕፀ ሕይወት ማን ነው ቢሉ ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው ያለን ጌታችን ነው። (ዩሐ. 6: 54) አንድም ዕፀ ሕይወት ማን ነው ቢሉ እኔ የወይን ግንድ ነኝ ያለው የሕይወት እንጀራ ጌታችን ነው። (ዩሐ. 15:5)

*ዕፀ ሕይወት የምትባለዋ የሕይወት ዛፍ መዓዛዋ ከአፍንጫ ጣእሟ ከምላስ ሳይጠፋ ለ7 ቀን የምትቆይ ግሩም ዛፍ ስትሆን ቅጠሏም እንደሌሎቹ አትክልት አይጠወልግም; ይህች ዕፀ ሕይወት አማናዊውን
ዕፀ ሕይወት ክርስቶስን በወለደችልን በእመቤታችን ትመሰላለች; ቅጠሏ እንደሌሎቹ አትክልት አለመጠውለጉም የድንግልናዋ ምሳሌ ነው። በዚህም ምክንያት የሶርያ ፀሐይ የተባለው ቅ/ኤፍሬም እመቤታችንን እንዲህ ብሎ አወደሳት፦
አንቲ ውእቱ እሙ ለዕፀ ሕይወት ወእሙ ለብርሃን”
[O St Mary you are the mother of the tree of life & the mother of luminous light]
 አንድም እግዚአብሔር ለሙሴ ከወርቅ በተሰራ መሶበ ወርቅ ውስጥ መና እንዲያስቀምጥ አዘዘው፤ ይህ መና ለብዙ ዘመን ከዘመነ ሙሴ እስከ ዘመነ ሥጋዌ ሳትበላሽና ሳትሸት ኖረች; ጌታችን በማህጸነ ድንግል ማርያም ባደረ ግዜ ግን ይህች መና እንደሰም ቀልጣ ጠፋች፤ አማናዊው ሕብስተ መና ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ከእመቤታችን ተወልዷላና። እኛም በውዳሴ ማርያም ላይ የተሰወረ መና ያለብሽ ደብተራ ድንኳን አንቺ ነሽ የምስራቅ ደጃፍ የብርሃን እናቱ ላንቺ ምስጋና ይገባሻል እያልን
እንዳመሰገናት።
  እምነ ፅዮን ይብል ሰብ [ሰው ሁሉ እናታችን ፅዮን ይላታል]  መዝ86:5
  የእመቤታችን ፀጋ የፀጋ ልብስ ይሁንልን ፤አሜን [ተክለ መድህን]

vዕፀ ሕይወት [ዘፍ. 3:22]







ሁሉን አሳልፎ ለዚች ቀን ላበቃን
ቸሩ አምላካችን እግዚአብሔር ይመስገን።

እስኪ እንናገረው የአየነውን ነገር
እግዚአብሔር ፈቅዶልን ለዚህ ቀን ካበቃን
እስኪ እንናገረው የድንግልን ተዓምር
ከልብ ለማይጠፋው እጅግ ታላቅ ነገር
ስሟን ስንጠራ ተስፋ ለሆነችን
ተስፋሁ ለአዳም ለሆነችው ድንግል።

አዳም እየኖረ በብዙ እጽዋት በተዋበች ገነት
ይህችን ዕፀ በለስ አትብላ ተባለ ትእዛዝ ሊያከብርባት
አዳም የሞት ሞትን ሞተ ያቺን ዕፀ በለስ ቀጥፎ ስለበላት

አዳም ሆይ! እስኪ እንጠይቅህ
ከዕፀ በለስ በልተህ እንዴት አልበላህም ከዛች ዕፀ ሕይወት?
ብትበላማ ኖሮ ያቺን ዕፀ ሕይወት
ንስሃ ሆኖልህ ትገባ ነበረ ዳግም ከገነት
ንስሃ ሆኖልህ በገባህባት ነበር የአጣሃትን ገነት።

በዘፍጥረት ምዕራፍ 3 ላይ እንደምናነበው       ዘፍ3:22
አዳም እንዳይበላት ያቺን ዕፀ ሕይወት
ትጠበቅ ነበረ በነበልባላዊ ሰይፍ በኪሩቤል መላዕክት
አዳም ሃዘን ገባው ያቺን ዕፀ ሕይወት አይቶ እየናፈቃት
ከገነት ሲወጣም ፅኑ ሃዘኑ በዛበት
ተስፋሁ ለአዳም እሙ ለዕፀ ሕይወት
ጌታን ወለደችው ፤ አዳም የናፈቀውን ያንን ዕፀ ሕይወት
አዳምም ደስ አለው ይህን ዕፀ ሕይወት በልቶ፤ ገነትን ሲያገኛት።

እስኪ እንናገረው የድንግል ተዓምር
በአይን የታየውን ያንን ታላቅ ነገር
አሥሩን አውታር ቃኘውና ዳዊት አባትሽ ለምሥጋና
በገናውን አነሳና ልጄ ሆይ ስሚኝ አለና
እምነ ፅዮን ይብል ሰብ አለና ዘመረ             መዝ86:5

የአባቱን በገና እየሰማ አድጎ
ጠቢቡ ሰለሞን እህቴ ርግብየ እያለ
ወትረ ግዜ ድንግል የታጠረች ገነት
የታተመች የውሃ ጉድጓድ ናት አለና ዘመረ።    መሓልየ4:12

እስኪ እንዘምር ስለድንግል ክብር
ፅዮን ለተባለች ለዳዊት በገና ለሰለሞን ጥበብ

ጎሳ ልብየ ቃለሰናየ  እሙ ለዕፀ ሕይወት እያሉ
እንዳመሰገኗት እነ አባ ሕርያቆስ፤ የሶርያው ፀሐይ እነ አባ ኤፍሬም

እስኪ እንዘምር ጌታን ለወለደች ለእመቤታችን
እሙ ለዕፀ ሕይወት” የያሬድ ውብ ዜማ እያልን።

                              ሔ ር
/ተክለ መድህን/








No comments: