Wednesday 17 July 2013

ልፋ ያለው በሕልሙ ክብደት ይሸከማል!



ካህን ኃጢአት ያስተሰርያል?

እንደኛው ኃጢአት የሚሰራ ሰው እንዴት ኃጢአትን የመሰረዝ ሥልጣን አለው? ካህኑ ማን ነውና ከእኔ ይበልጣል? እውነት ግን እንደኛው ኃጢአተኛ ሰው እንዴት ኃጢአትን ያስተሰርያል???

ይህን የሚጠይቁ ብዙ ናቸው። "ልፋ ያለው በሕልሙ ክብደት ይሸከማል" ያልኳችሁም ለዚሁ ነው። ጴጥሮስ ጌታን አላቅም ብሏልና እንዴት የሐዋርያቱ አለቃ ሆነ? እያለ የሚጠይቅ ልፋ ያለው ሰው ነው። እናንተዬዋ ሐዋርያቱ ግን ጴጥሮስን እንዴት ዝም አሉት? አንተ ኃጢአትን ሰርተሃልና አለቃችን አትሆንም ብለው መፈንቅለ ሐዋርያዊ ሥልጣን ለምን አላደረጉም?

ሰዎች ሆይ ካህኑ ራሱ ንስኃ እንደሚገባ አታውቁምን? ካህኑም ጳጳሱም ፓትርያርኩም ኃጢአታቸውን ልክ እንደኛው እንደሚናዘዙ አታውቁምን?

እስኪ ደግመን እንጠይቅ ፦ ካህን ኃጢአት ያስተሰርያል? ለጥያቄው መፅሐፍትን አብረን እንመርምርና መልሱን ለሕሊናችሁ አሳልፌ እሰጣለሁ።

ምስጢረ ቀንዲል፦ ምስጢረ ቀንዲል በካህኑ ጸሎት እና ቡራኬ በሽተኛው ሰውዪ በተባረከው ዘይት በመቀባቱ ከበሽታው መዳንን ከኃጥያት መንፃትን የሚያስገኝ ምሥጢር ነው። ይኸውም ምሥጢር ለአካለ ስጋም ለአካለ ነፍስም ጤንነትን ለመስጠት የእግዚአብሔር ጸጋንም ለማስተላለፍ የሚችል ነው። ቀንዲል ማለት መብራት ማለት ነው። ምስጢረ ቀንዲል በሚደረግበት ጊዜ መብራት ይበራል ስለዚህም ስያሜው ከስርዓቱ አፈጻጸም ተዋስዷል (ዘፍ 40፡4 ዘኁሉ 4፡9)።

ይህንን ምሥጢር የመሰረተው ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። አስራሁለቱን ሐዋርያት ጠርቶ ስልጣንን በሰጣቸው ጊዜ የመፈወስ ስልጣን ሰጥቷቸዋል (ማቴ 10፡1 ማር 6፡7 ሉቃ 9፡1)። “በወጡ ጊዜም አስተምሮ ንስሀ ይገቡ ዘንድ እጅግም ሰይጣናትን አውጡ በዘይትም ብዙ ድውያንን ቀቡ አድኗቸውም” (ማር 6፡12-13)። ከትንሳኤ በኋላ ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድውይ የመፈውስ ሃይል ሰጥቷቸዋል። (ማቴ 6፡17-18) ሐዋርያትም ምስጢር መጋቢዎች እንደመሆናቸው በትዕዛዙ መሰረት ሲሰሩበት ኖረዋል (1ኛ ቆሮ 4፡1)። ቀጥሎ ቀሳውስቱን በዘይት እየቀቡና እየፀለዩ ህሙማንን እንዲፈውሱ ሐዋርያት አዘዋል። “ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር የቤተክርስቲያን ቀሳውስትን ወደ እርሱ ይጥራ በጌታም ስም እርሱን ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት /ምስጢረ ቀንዲል/ የእምነት ጸሎት ድውይን ያድናል፣ ጌታም ያስነሳዋል ((ኃጥያትም ሰርቶ እንደሆን ይሰረይለታል)) /ምስጢረ ንስኃ/ ያዕ 5፡14-15 ቤተክርስቲያን ይህን ቅዱስ ምስጢር ሲወርድ ሲዋረድ በመጣው ትውፊት መሰረት ስትፈጽመው ትኖራለች በመፈጸምም ላይ ትገኛለች።

ምስጢረ ቀንዲል የሚፈጸመው ከንጹህ የወይራ ዘይት ነው። ቅብዐ ቅዱስ እየተባለ ይጠራል። ማንም ሰው በማንኛውም ጊዜ ሲታመም ካህኑን ጠርቶ ምስጢረ ቀንዲል ሊጠይቅና ሊፈጸምለት ይችላል። ቅባ ቅዱሱን ጳጳስ ይባርካል። ምስጢረ ቀንዲል በቤተክርስቲያን፣ በመኖሪያ ቤት እና በሆስፒታል ሊፈጸም ይችላል። በሽተኛው ከመቀባቱ በፊት ኃጢያቱን ይናዘዛል ከዚያም ዘይቱ ቀርቦ ሥርአተ ጸሎቱ ይፈጸማል። በመቀጠል ካህኑ በሽተኛውን በጭንቅላቱ ላይ እጁን ጭኖ ይጸልያል በመጨረሻም አምስቱን ህዋሳት ማለት አይኑን፣ አፉን፣ ጆሮውን፣ አፍንጫውን እና እጁን ይቀባል። በዐይኑ አይቶ፣ በአንፍጫው አሽትቶ፣ በጆሮው ሰምቶ፣ በአፉ ተጋግሮ፣ በእጁ ዳሶ ለሰራው ኃጢያት ስርየት እንዲሆንለት ሲል ነው። በዚህ ጊዜ በሽተኛው በሥጋ ደዌ ደክሞ የነበረው መንፈሳዊ በሽተኛው ሥርየት ያገኛል። በዚህ በሚታየው ምሥጢር የማይታይ ፀጋ ይገኝበታል።

የዮሐንስ ወንጌል 20
23 ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል አላቸው።

ይህ የተነገረው ለማን ይሆን? ይህች ሥልጣን የማን ትሆን? አንዱ ተነስቶ ኃጢአትህን ያዝኩብህ ቢል ማን ይሰማዋል? ይህን የማድረግ ሥልጣን አለው? እንግዲያውስ ይህች ታላቅ ሰማያዊ ሥልጣን ከቶ የማን ናት???

የማርቆስ ወንጌል 1
4 ዮሐንስ በምድረ በዳ እያጠመቀ የንስሐንም ጥምቀት ለኃጢአት ስርየት እየሰበከ መጣ።
5 የይሁዳም አገር ሁሉ የኢየሩሳሌምም ሰዎች ሁሉ ወደ እርሱ ይወጡ ነበር፥ ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ ከእርሱ ይጠመቁ ነበር።
(ኃጥያትም ሰርቶ እንደሆን ይሰረይለታል)) (ያዕ 5፡14-15)

ፕሮቴስታንት ዘመዶቻችን ሆይ ካህን ኃጢአት ያስተሰርያል?

No comments: