Tuesday 16 July 2013

ፍቅር ማን ነው?



ሆድ ሲሞላ ፍቅሩ ሌላ ፤ ሆድ ሲጎድል ሰው ያጋድል አሉ!

እስኪ አንድ ታሪክ ላውጋችሁ፦ አንድ የዋህ አባት ነበር አሉ። ይህን የዋህነቱን ያዩ አሥራ ሦስት ሽፍቶች ጩቤ ጎራዴ ሳንጃ በልብሳቸው ውስጥ ደብቀው የዚህን ሰው ቤት አንኳኩ። ይህ ሰው የዘመኑ አብርሐም ይባላልና እንግዶቹን በደስታ ተቀበለ። ሲቆጥራቸው 13 ሆኑ። ጌታ ከአስራ ሁለቱ ሐዋርያት ጋ ቤቴ መጣ ብሎ እጅግ ደስ ደስ አለው። ጌታ የቱ ይሆን ? እያለ ጠየቃቸው። ጴጥሮስ የቱ ነው? ዮሐንስና ያዕቆብስ ? እያለ ጠየቃቸው። እግራቸውን አጥቦ ምግብ አቅርቦ በታላቅ ፍቅር ተቀበላቸው። ሽፍቶቹ ይህን ሁሉ ደግነቱን አዩና ልባቸው ራራ። ሊገድሉት መጥተው በፍቅሩ ተሸንፈው ከእግሩ ስር ተንበረከኩ። ኃያላን ጉልበተኛ ቢሆኑም በፍቅር ተሸነፉ። በሽፍታነት የዋኙበት ይህችን ዓለም ንቀው የቅድስና ሕይወት መኖር ጀመሩ!

ፍቅር ማን ነው?

ፍቅር ኃያል ነው ጉልበተኛውን ያንበረክካልና
ፍቅር ጉልበተኛ ነው ትዕቢተኛውን ትሁት ያደርጋልና
ፍቅር ጠቢብ ነው በጥላቻ የታወረውን ዓይኑን ያበራልና
ፍቅር ታጋሽ ነው ዕልኸኛውን ያረጋጋልና
ፍቅር ይቅር ባይ ነው የበደለን ያጸጽታልና
ፍቅር ጥበበኛ ነው ተሳዳቢውን ይመክራልና
ፍቅር መካሪ ነው ስሜታዊውን ይገስጻልና
ፍቅር ሩህሩህ ነው የካደውን ዳግም ይወዳልና
ፍቅር ጤና ነው የሕሊና ሰላም ይሰጣልና
ፍቅር ቸር ነው የነፈገን አይነፍግምና
ፍቅር ርግብ ነው ቂም አይዝምና
ፍቅር ብሩህ ፊት ነው አይመቀኝምና
ፍቅር የተረጋጋ ነው በቶሎ አይቆጣምና
ፍቅር የዋህ ነው በደልን አይቆጥርምና

ፍቅር ማን ነው?

ፍቅርማ እንደ ረጅም ፈትል ከዙፋኑ የወረደው ነው
ዝቅ ዝቅ ብሎ የፈጠረውን እግር ያጠበው ነው
እንደሚታረድ በግ አንገቱን ለሸላቾቹ የሰጠው ነው

ፍቅርማ በመስቀል ላይ እጁን የዘረጋው ነው

የፍቅር አምላክ ሆይ ፍቅርህን አልብሰን፤ አሜን።

http://yonas-zekarias.blogspot.com/

No comments: