Monday 15 July 2013

//የፕሮቴስታንት መዝሙሮችን እንፈትሽ//



ሁለት አይወዱ ከመነኮሱ አይወልዱ አሉ!

መንፈሳዊነትን ከዓለማዊነት ማን አንድ አደረገው? ዓለማዊያን በሄዱበት ጎዳና መንፈሳዊያን እንዴት ይሄዳሉ? 

መዝሙረ ዳዊት 137
1 በባቢሎን ወንዞች አጠገብ በዚያ ተቀመጥን ጽዮንንም ባሰብናት ጊዜ አለቀስን።
2 በአኻያ ዛፎችዋ ላይ መሰንቆቻችንን ሰቀልን።
3 የማረኩን በዚያ የዝማሬን ቃል ፈለጉብን፥ የወሰዱንም። የጽዮንን ዝማሬ ዘምሩልን አሉን።
4 ((የእግዚአብሔርን ዝማሬ በባዕድ ምድር እንዴት እንዘምራለን?))
5 ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ብረሳሽ፥ ቀኜ ትርሳኝ።
6 ባላስብሽ፥ ምላሴ በጕሮሮዬ ይጣበቅ

በዳዊት መዝሙር እንዳየነው የእግዚአብሔርን ዝማሬ እንኳን እንደፈለግነው ልንዘምር ቀርቶ በባዕድ ሀገር እንኳን አንዘምርም የተባለበት ዘመን ነበር። አሁን አሁን ግን መዝሙርና ዘፈን መንታ እህትማማች ሆነዋል። ዘፈን ላይ ያየነውን ዝላይ አንዳች ሳይለወጥ በመዝሙር እናየዋለን። ሁሉ በሥርዓት ይሁን የሚለው ቃል መዝሙሩ ላይ የሚሰራ አይመስለኝም። የተረጋጋ መዝሙር ሰምቼም አላውቅም። ዓለማዊው ዘፈን እንኳን አንዳንዴ ረጋ ይላል። መንፈሳዊያን እንዴት መርጋት አቃታቸው? መንፈሳዊነትን ከዓለማዊነት ማን አንድ አደረገው? ዓለማዊያን በሄዱበት ጎዳና መንፈሳዊያን እንዴት ይሄዳሉ? ((የእግዚአብሔርን ዝማሬ በባዕድ ምድር እንዴት እንዘምራለን?)) የእግዚአብሔር ምስጋና በተቀደሰች ቦታ ትዘመራለች እንጂ እንዴት በየአዳራሹ ይዘመራል? አዳራሽ ለስብሰባ ለዕድር ለዘፈንም ይኬዳል። አለማዊያን በዘፈኑበት አዳራሽ የእግዚአብሔርን ዝማሬ መዘመር ከቶ አይገባም።

ፕሮቴስታንት ዘመዶቻችን ሆይ ዳዊት እንዴት እያነባ እንደዘመረ የንስኃ መዝሙሩን ስሙ፦
መዝሙረ ዳዊት 6
1 አቤቱ፥ በቍጣህ አትቅሠፈኝ፥ በመዓትህም አትገሥጸኝ።
2 ((ድውይ ነኝና አቤቱ፥ ማረኝ)) አጥንቶቼ ታውከዋልና ፈውሰኝ።
3 ነፍሴም እጅግ ታወከች አንተም አቤቱ፥ እስከ መቼ ድረስ ነው?
4 አቤቱ፥ ተመለስ ነፍሴንም አድናት፥ ስለ ቸርነትህም አድነኝ።
5 በሞት የሚያስብህ የለምና፥ በሲኦልም የሚያመሰግንህ ማን ነው?
6 በጭንቀቴ ደክሜያለሁ ((ሌሊቱን ሁሉ አልጋዬን አጥባለሁ፥ በዕንባዬም መኝታዬን አርሳለሁ))
7 ((ዓይኔ ከቍጡ ዕንባ የተነሣ ታወከች ከጠላቶቼ ሁሉ የተነሣ አረጀሁ))

እንግዲህ ምን እንላለን፤ ዘመዶቻችን ሆይ የዳዊት ዕንባ በጉንጫችሁ ላይ ወርዶ ያውቃል? ብዙዎቻችሁ እንደ ዳዊት ልብሳችን እየወለቀ እንዘምራለን ትላላችሁ፤ ታድያ እንደ ዳዊት እያለቀሳችሁ ዘምራችሁ ታውቃላችሁ? መልሳችሁ ለጊዜው ይለፈን። ቅ/ጴጥሮስም እንደ ጅረት ወንዝ ስለንስኃው አነባ። ፕሮቴስታንት ዘመዶቻችን ሆይ ስለ ኃጢአታችሁ መቼ ይሆን የምታነቡት? እንደ ማርያም እንተ ህፍረት እግሩ ላይ ዝቅ ብላችሁ ሽቱ ቀብታችሁ ማረኝ የምትሉት መቼ ነው? እንደ በጥለሚዮስ የዳዊት ልጅ ሆይ ማረኝ የምትሉትስ መቼ ይሆን?
ይህን ማለታችን ቤተክርስቲያን ሙሾ የሚወርድባት ለቅሶ ቤት ናት ማለታችን አይደለም። ሰው ሲሞት እንኳን ጥቁር ልብስ እንዳይለበስና እንደ ተሰሎንቄ ሰዎች ከገደብ ያለፈ ክፉኛ ሐዘን እንዳናዝን ቤተክርስቲያን ታዛለች። ጠቢቡ ሰለሞን ቦ ጊዜ ለኩልክሙ // ለሁሉ ጊዜ አለው እንዳለ በቀራንዮ እያነቡ እየሰገዱ ለመዘመር ጊዜ አለው ፤ ይህም በቤተክርስቲያናችን ሰሞነ ሕማማት ይባላል። በብርኃነ ትንሣኤው እንደ መላዕክቱ ብርኃንን ለብሶ ጧፍ ይዞ እልል ብሎ ለመዘመርም ጊዜ አለው።

ስንከፋ ቤተክርስቲያን እንሮጣለን፤ ስንደሰትም ወደ መቅደሱ እንገሠግሣለን። ዳዊት ሲደሰት ብቻ አልነበረም የሚዘምረው። አልጋዬን በእንባዬ አጥባለሁ እያለ እያነባ ይዘምራል። ጸሎቱ ሲሰማ ደግሞ ጩኸቴን ሰማኝ እያለ እልል እያለም ይዘምራል።

ፕሮቴስታንት ዘመዶቻችን ሆይ ዳዊት ጸሎቱ ሲሰማ ልቡ ደስ ደስ ብሎት የዘመረውን ዝማሬ ስሙ፦
መዝሙረ ዳዊት 30
11 ክብሬ ትዘምርልህ ዘንድ ዝምም እንዳትል ((ልቅሶዬን ለደስታ ለወጥህልኝ፥ ማቄን ቀድደህ ደስታንም አስታጠቅኸኝ))

መዝሙረ ዳዊት 81
1 በረድኤታችን በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ፥ ለያዕቆብም አምላክ እልል በሉ።
2 ዝማሬውን አንሡ ከበሮንም ስጡ፥ ደስ የሚያሰኘውን በገና ከመሰንቆ ጋር

እመቦ ዘይተክዝ ለይጸልይ ወእመቦ ዘተፈስሃ ለይዘምር // ያዘነ ቢኖር ይጸልይ ደስም ያለው ይዘምር የታመመ ቢኖር የቤተክ ቀሳውስትን ይጥራና ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት። /ምስጢረ ቀንዲል/ ኃጢአት ሰርቶም ከሆነ ይሰረይለታል //ምስጢረ ንስኃ/ ያዕቆብ 5፦13 ይህን ሁሉ አስተባብራ የያዘች አንድ እናት ቤተክርስቲያን አለች!

No comments: