Wednesday 14 August 2013

ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው!


ዮሐ 4፦6 ክርስቶስ ደክሞት ተቀመጠ ይለናል። 



እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ወደ እኔ ኑ እኔም አሳርፋችኋለሁ ያለ ጌታ በተዋሃደው ስጋ ደከመ ተባለ።

አንድም በገዳመ ቆሮንቶስ ጾመና ተራበ፤ በ፭ አሳ ብዙ ሺሕ ህዝብ መገበ!

አንድም ተጠማሁ ያለ ጌታ ውኃውን ቀይሮ ወይን ሰጠ፤ ሀኖስንና ውቂያኖስን የፈጠረ ተጠማ! የተጠማ ቢኖር የህይወትን ውኃ ይጠጣና ይርካ ያለ ጌታ ስለ ሰው ፍቅር ተጠማ!

አንድም አልአዛርን ከሞት ያስነሳ ክርስቶስ በስጋው ሞተ ተባለ። ሞትን በሞቱ ገደለ!


እውነትም ይህ ምሥጢር ግሩም ድንቅ ነው። ዳዊት በበገናው ምን አለ? በልዎ ለእግዚአብሔር ግሩም ግብርከ// እግዚአብሔርን ሥራህ ግሩም ድንቅ ነው በሉት። በድንቅ ሥራህ በታላቅ ምህረትህ ቤትህ የጠራኸን አምላክ ሆይ ሥራህ ግሩም ድንቅ ነው!

ቅ/ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በጻፈው መልዕክቱ ስለ ነገረ ሥጋዌ ሲናገር ይህ ምሥጢር ያለጥርጥር ታላቅ ነው ብሏል። እውነትም አምላክ ሰው የሆነበት ምሥጢር ታላቅ ነው። አንበሳ የሜዳ አህያን ቢዘነጣጥል አይደንቅም። አንበሳ ከሜዳ አህያ ሸሽቶ ሲታይ ግን ይደንቃል። አንበሳ በከብቶች በረት ገብቶ እንስሳቱን ቢፈጅ አይደንቅም። በከብቶች በረት ተኝቶ በእንስሳቱ እስትንፋስ ቢታጀብ ግን ይደንቃል።

ረቂቅ መለኮት ከግዙፉ ሥጋ
ህያው መለኮት ከሟቹ ስጋ
ዘለዓለማዊው መለኮት ከጊዜያዊው ስጋ መዋሃዱ ግሩም ድንቅ ነው!

ይህን ያደረገ ጌታ እናትነትን ከድንግልና ጋር አስተባብራ ከተገኘች እመቤት ተወለደ!
እግዚአብሔር በፀጋ ያደረበት ሞልቷል። እግዚአብሔርን የወለደች ግን አንዲት እናት ብቻ ናትና ይህ ምሥጢር ግሩም ድንቅ ነው።

ልባችንን ሞልተን እናምናለን፤ አፋችንን ሞልተን እንናገራለን ።

ከእርሷ በፊት አምላክን የወለደ አልነበረም፣ ወደፊትም ክርስቶስ አይወለድምና ይህች እናት ከሴቶቹ ሁሉ ተለይታ የተባረከች ናት።

http://yonas-zekarias.blogspot.com/




Unlike ·  · 

No comments: