Monday 28 November 2011

ቅዱስ ያሬድ ማነው?

 




ቅዱስ ያሬድ ማነው?
 የቅዳስ ያሬድ አባቱ አብድዩ /ይስሐቅ/ እናቱ ክርስቲና /ታውክልያ/  ይባላሉ /በሌላም በኩል አባቱ እንበረም እናቱ ትውልያ ይባላሉ የሚል ታሪክም አለ፡፡/ የትውልድ ሥፍራው አከሱም ነው፡፡ የተወለደው በ505 ዓ.ም/  ሚያዝያ 5 ቀን የሚል አለ/ ሲሆን በተወለደ በ7 ዓመቱ ወላጅ አባቱ ስለሞተ እናቱ የአክሱም ጽዮን መምህር ለነበረው ለአጎቱ ለጌዴዎን እያስተማረ እንዲያሳድገው ሰጠችው፡፡ ከአባ ጌዴዎንም ዘንድ እየተማረ ለ25 ዓመት ተቀመጠ፡፡

ሆኖም ቃለ እግዚአብሔር የመቀበል ችሎታው ደካማ ስለሆነ በጣም ያዝን ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ከትምህርት ድክመቱ የተነሣ አጎቱ በጨንገር ቢገርፈው በዚህ ተበሳጭቶ ትምህርቱን ትቶ ሄደ፡፡ በመንገድም ሲጓዝ ውሎ በቀትር ደክሞት ከዛፍ ሥር ዐረፈ፡፡ በዚያ ጊዜ አንድ ትል ከዛፉ ላይ ያለውን ፍሬ ለመብላት ስድስት ጊዜ በመውደቅና በመነሣት ዛፉ ላይ ለመውጣት ሞክሮ በሰባተኛው ሰተት ብሎ ወጥቶ ሲበላ ተመለከተ፡፡ እርሱም በፈጸመው የብስጭት ተግባር በመጸጸት ተመልሶና አጎቱን ይቅርታ ጠይቆ ትምህርቱን ቀጠለ፡፡ አጎቱም ተደስቶ ዓይነ ልቡናውን ያበራለት ዘንድ እያለቀሰ ፈጣሪውን ለመነለት፡፡ እግዚአብሔርም ጸሎቱን ሰምቶ ለቅዱስ ያሬድ ዕውቀትን ገልጾለት መጻሕፍተ ብሉያትንና ሐዲሳትን ዐወቀ፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይህን በተመለከተ

ሰላም ለያሬድ ስብሐተ መላእክት ለሕዋጼ
እንተ አዕረገ በልቡ ኅሊና መንፈስ ረዋጼ
ለትምህርተ መጽሐፍ ገብአ እምኀበ ኮነ ነፋጼ
በብዙኀ ፃማ ዘአልቦ ሐጻጼ
መልዕልተ ዕፅ /ኮሞ/ ነጸሮ እንዘ የዐርግ ዕጼ

የሚል ዐርኬ ደርሰውለታል፡፡ ይህን አርኬ የድጓ መምህራን ጠዋት ጉባኤ ሲዘረጉ ተማሪዎቻቸውን ያስደርሷቸዋል፡፡

ከዚያም በኋላ ወደ መምህሩ ተመልሶ ትምህርቱን ቀጠለና ቅዱሳት መጻሕፍትን በሚገባ አጠና፡፡ ሢመተ ዲቁናን ቀጥሎም ሢመተ ቅስናን ተቀበለ፡፡ ቅዱስ ያሬድ ግእዝ፣ እዝልና አራራይን ከሦስት ወፎች/መላእክት በወፎች ተመስለው/ መማሩን ሊቃውንት ይገልጣሉ፡፡ እነዚህ በወፍ የተመሰሉ መላእክት እየመሩት ወደ አርአያም አርጎ የ24ቱን ካህናተ ሰማይ ዜማ ከተማረ በኋላ ጠዋት በ3 ሰዓት በአክሱም ቤተ ክርስቲያን «ሃሌ ሉያ ለአብ ሃሌ ሉያ ለወልድ ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ ቀዳሚሃ ለጽዮን ሣረረ ወበዳግመ አረአዮ ለሙሴ ዘከመ ይግበር ግብራ ለደብተራ» ብሎ አዜመ፡፡ ይህን ዜማ የደረሰበት ወሩ ታኅሳስ ቀኑም ዕለተ ሰኞ ነው ይባላል፡፡ የቅዱስ ያሬድ የመጀመሪያ ዜማው «አርያም» በመባል ይታወቃል፡፡ ይህም ከመላእክት ወይም ከሰማይ የተገኘ መሆኑን ለማጠየቅ የተሰጠው ስም ነው፡፡

ቅዱስ ያሬድ ይህንን ዜማ በተመስጦ ሲያዜም ንጉሡ፣ንግሥቲቱ፣ ጳጳሱ መኳንንቱና ካህናቱ ወደ አኩስም ቤተ ክርስቲያን ተሰባስበው መጥተው በአድናቆት ያዳምጡት ነበር፡፡ ምክንያቱም ገደለ ቅዱስ ያሬድ እንደሚገልጥልን ከዚያ በፊት በውርድ ንባብ ከሚደረግ ጸሎትና መንፈሳዊ አገልገሎት በቀር ይህን የመሰለ ዜማ አልነበረምና፡፡

የቅዱስ ያሬድ ድርሰት ብሉይን ከሐዲስ ያስማማ፣የሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን ትምህርት በሚገባ የያዘ፣ እንዲሁም ለልዑል እግዚአብሔር፣ለእመቤታችን፣ለቅዱሳን መላእክት፣ ለጻድቃንና ለሰማዕታት ተገቢ የሆነውን ምስጋና የያዘ ነው፡፡ ከዚህም በላይ ለአራቱ የዓመቱ ወቅቶች እንዲስማማ አድርጎ ለበጋ፣ ለክረምት፣ ለመጸውና ለጸደይ እንደሚሆን አድርጎ ከፋፍሏቸዋል፡፡ ለየበዓላቱም ተስማሚ ድርሰት መድቦላቸዋል፡፡ ይህንን ድርሰቱን በግእዝ፣ በእዝልና በአራራይ ዜማ ያዘጋጀው ሲሆን ለነዚህም ስምንት የዜማ ምልክቶች ሠርቶላቸዋል፡፡

የቅዱስ ያሬድ ዜማ አንዴት ሁሉንም ይመስጥና ወደ አርያም በመንፈስ ይወስድ እንደ ነበር ለማስረዳት በገድሉም በሌሎችም መጻሕፍት የተመዘገቡ ታሪኮች አሉ፡፡ አንድ ቀን ንጉሥ ገብረ መስቀል፣ንግሥቲቱ፣ ጳጳሱ፣ ካህናቱና ምእመናኑ በተሰባሰቡበት ቅዱስ ያሬድ ዜማውን ሲያዜም ንጉሡ በመመሰጡ የተነሣ በመሰቀል ተሰላጢኑ ጫፍ የቅዱስ ያሬድን እግር ወጋው፡፡ ነገር ግን ማንም አላወቀም ነበር፡፡ ቅዱስ ያሬድ መዝሙሩን ሲፈጽም ንጉሡ መስቀል ተሰላጢኑን ቢያነሳው የቅዱስ ያሬድ ደሙ ፈሰሰ፡፡ ንጉሡ በዚህ ደንግጦ ለዚህ ካሣ ይሆን ዘንድ የፈለግከውን ጠይቀኝ እሰጥሃለሁ ብሎ ቃል ገባለት፡፡ ቅዱስ ያሬድ ግን ከዚህ ዓለም ተለይቶ በምናኔ መኖርና መዝሙሩንም በሚገባ ማዘጋጀት እንደሚፈልግ ገለጠ፡፡ ምንም እንኳን አኩስምን ለቅቆ መውጣቱ ንጉሡን ቅር ቢያሰኘውም ቃሉን አንድ ጊዜ በመስጠቱ ምንም ሊያደርገው አልቻለም፡፡ ቅዱስ ያሬድም ከዚህ በኋላ አኩስምን ለቅቆ ወደ ስሜን ተራራ ጸለምት መጓዙ ይነገራል፡፡

በጐንደር ፎገራ በሚባል ሥፍራ ቅዱስ ያሬድ ጣዕም ያለው ዜማውን ሲዘምር ተጠምደው የሚያርሱ በሬዎች ድምፁን እየሰሙ ገበሬውን ሥራ ስለ አስፈቱት በዚህ ተናዶ ቅዱስ ያሬድን በጅራፍ እንደ ገረፈው ይነገራል፡፡ ቦታውም «ወርቀ ደም´ እየተባለ እስከ ዛሬ ይጠራል፡፡ ወርቃማና ንጹሕ ደሙ የፈሰሰበት ማለት ነው፡፡

ቅዱስ ያሬድ ዜማውን ያዘጋጀበት ዘመን ከ540-560 ዓ.ም. ባለው ጊዜ መሆኑ ይነገራል፡፡ ዜማውን ካዘጋጀ በኋላ 11 ዓመት አስተምሯል፡፡ በእርሱ ዘመን ተሰዓቱ ቅዱሳን በሃይማኖት ችግር ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ ተሰደው መጥተው ስለ ነበር ቅዱስ ያሬድ ከአንዱ ከአባ ጰንጠሌዎን የውጭውን ሀገር ቤተ ክርስቲያን ባሕልና ሥርዓት ይጠይቅ ነበር፡፡ በጆሮ የሰማውንም በዓይን ለማየት ሁለት ጊዜ ሮም የተባለችውን የቁስጥንጥንያ ቤተ ክርስቲያን ጐበኘሁ ይላል፡፡ «ወሪድየ ብሔረ ሮሜ ለቤተ ክርስቲያን ርዒክዋ» እንዲል፡፡ የታሪክ ምሁሩ ሥርግው ሀብለ ሥላሴ ለቁስጥንጥንያ ዜማ መነሻው ቅዱስ ያሬድ ነው ይላሉ፡፡ ለዚህም ማስረጃ የሚያደርጉት የቁስጥንጥንያን ዜማ የደረሰው ሊቅ ዜማውን አገኘው የሚባለው የቅድስት ሶፍያን ቤተ ክርስቲያን ሲዞር ከሰማው ዜማ ነው፡፡ ይህ ዘመን ደግሞ ቅዱስ ያሬድ ከተነሣበትና ወደ ሮሜ ሄድኩ ካለበት ዘመን ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ እናም ምናልባት ያ ሰው ዜማውን የሰማው የቅድስት ሶፍያ ቤተ ክርስቲያንን እየዞረ ሲዘምር ከነበረው ከቅዱስ ያሬድ ሳይሆን አይቀርም ይላሉ፡፡ Ancient and medival Ethiopian History/

ቅዱስ ያሬድ ማትያስና ዮሴፍ በተባሉ የአቡነ አረጋዊ ደቀ መዛሙርት መሪነት ወደ ደብረ ዳሞ ተራራ ላይ ወጥቶ ከጻድቁ ጋር በመገናኘትና የቤተ ክርስቲያኑን ሥራ እያደነቀ ዙሪያውን ከዞረ በኋላ «ዖድክዋ ወርኢኩ ሥነ ሕንፃሃ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን» ሲል ዘመረ፡፡ በዚያም ለአንድ ሳምንት ሰንብቶ ሄዷል፡፡

ቅዱስ ያሬደ ከአቡነ አረጋዊ እና ከዐፄ ገብረ መስቀል ጋር በመሆን በወሎ፣ በጎንደር፣ በሸዋ እና እስከ ጋሞጎፋ ብርብር ማርያም ድረስ በመሄድ አስተምሯል፡፡ አንዳንድ መረጃዎች የዐርባ ምንጭን ታሪክ ከቅዱስ ያሬድ፣ ከአቡነ አረጋዊ እና ከዐፄ ገብረ መስቀል ታሪክ ጋር ያያይዙታል፡፡ ሦስቱም ብርብር ማርያምን ለማየት ሄደው በነበረ ጊዜ በዛሬው ዐርባ ምንሥ አካባቢ ሠፍረው ነበር፡፡ በዚያ ቦታ ለወታደሩ የሚበቃ የሚጠጣ ውኃ በመጥፋቱ አቡነ አረጋዊ ጸልየው መሬቱን በመስቀል ቢመቱት ዐርባ ውኃዎች ፈለቁ ይባላል፡፡

ዐፄ ገብረ መስቀል የጣና ቂርቆስን ቤተ ክርስቲያንን በሚያሠራ ጊዜ በዚያ ቦታ ለሁለት ዓመት ተቀምጦ ድጓውን በማስተማሩ ምልክት የሌለው ድጓው እስከ ዛሬ በገዳሙ ይገኛል፡፡ ቀጥሎም የዙር አባን ቤተ ክርስቲያን ለማሠራት ወደ ጋይንት በተጓዙ ጊዜም በዚያ ሁለት ዓመት ዝማሬ መዋሥዕት የተባለ ድርሰቱን አስተምሯል፡፡ ይህ ቦታ እስከ ዛሬ የዚህ ትምህርት ማስመስከሪያ ነው፡፡

ቅዱስ ያሬድ ከዚያ በኋላ ወደ አከሱም ተመልሶ በመደባይ ታብር በተባለ ቦታ ቅዳሴያትን በዜማ አዘጋጅቷል፡፡ ይህ ቦታ ከአከሱም 15 ኪ.ሜትር ርቆ ይገኛል፡፡ ከዚህ በኋላ ለመጨረሻ ጊዜ አኩስምን ተሰናብቶ ለመሄድ ወደ ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ገባና «ቅድስት ወብጽዕት ስብሕት ወቡርክት ክብርት ወልዕልት አንቀጸ ብርሃን ማዕርገ ሕይወት» እያለ አንቀጸ ብርሃን የተባለውን ድርሰቱን ሰተት አድርጎ አዘጋጀው፡፡ ይህንን ድርሰት ሲያዜም አንድ ክንድ ያህል ከምድር ከፍ ብሎ ይታይ ነበር ይባላል፡፡




                                                                   ከአበው አንደበት           















                  

ገና ጥንት ያኔ . . . . . . .
ሰውም ሳይሰፍርባት አሜሪካ ታውቃ፣
ገና ጥንት ያኔ . . . . . . . . .
እንዲህ ሳትሠለጥን አውሮፓም ተራቅቃ፣

ገና ጥንት ያኔ . . . . . . . .
ዓለም፣ ከእንቅልፏ ሳትነቃ፣
እነ ሞዛርት እና እነ ቤት ሆቨን፣
የዜማን ምልክት ገና ሳይነግሩን፣
ያሬድ አንተ ነበርክ
የዜማን ቅማሬ የሠራህልን፣
                          . . . . . . . . . . . . . . . . . . . .
መንኮራኩር ሠርተው
ጨረቃ ላይ ወጥተው፣
አፈር ስላመጡ ዓለም ተደነቀ፣
ወሬው ተሟሟቀ፣
ከምዕራብ ተነሥቶ ከምሥራቅ ዘለቀ፣

ከሺ ዓመት በፊት ግን
ያሬድ የተባለ አንደ ሊቅ ነበረ፣
ጨረቃንም አልፎ ጠፈር ተሻገረ፣
 ሐኖስን ሰንጥቆ ሰማያት ውስጥ ገብቶ፣
አስደናቂ ዜማ ከመላእክት ሰምቶ፣
 አኩስም ላይ አዜመው
ከጽናጽል እና ከመቋሚያ አስማምቶ፣

ግና ምን ያደርጋል . . . . . . .
 ከጨረቃ አፈር የሚበልጥ ነገር፣
 ጨረቃም ላይ ካለው የሚበልጥ ምሥጢር፣
 ያሬድ ይዞ መጥቶ፣
 የሚናገር እና የሚያደንቅ ጠፍቶ፣
 ዓለም አያውቀውም አልሰማውም ከቶ፣

ያሬድ ግን ቅዱስ ነው
 ያሬድ ምሁር ሊቅ፣
 ያሬድ መተርጉም ነው
 ምሥጢር የሚያረቅቅ፣
 ያሬድ ፈላስፋ ነው
ያሬድ ባለ ቅኔ፣
ያሬድ ባለ ዜማ
የዜማው መጣኔ፣
ያሬድ ሐጋጊ ነው
ሥርዓት የሠራ፣
 ያሬድ መምህር ነው
ዕውቀትን ያበራ፣
ያሬድ ቀማሚ ነው
ብሉይ ከሐዲስ፣
ያሬድ ሰባኪ ነው
ነፍስ የሚመልስ፣
 ያሬድ አመልካች ነው
 ኖታን የፈጠረ፣
 ያሬድ መናኒ ነው
 በጸሎት የኖረ፣
       እነ ቸርችል፣ ፑሽኪን እነ ካኒንግሃም
      አደባባይ መንገድ ሲሰየምላቸው፣
      ያሬድን ስላጡት አዘነ ልባቸው፣
      ነቢይ በሀገሩ አይከብርም እንዲሉ፣
      እኒህ ኢትዮጵያውያን እጅግ ይሞኛሉ፣
     የእጃቸውን ንቀው ሌላ ያከብራሉ፣
     ብለው አዘኑብን በፈጸምነው ግፍ፣
     ያሬድን ረስተን ሌላውን ስናቅፍ፣

                                       አይበቃም ወይ ታድያ የሞኝነት ኑሮ፣
                                       መቅረት አለበት ወይ ታሪኩ ተቀብሮ፣
                                       ይተረክ ታሪኩ ይነገር ዝናው፣
                                       ይጠና ይመርመር ይታወቅ ሥራው፣
                                       መወያያ ይሁን በየሚዲያው፣
                                       መማማርያ ይሁን ትውልድ ያድንቀው፣

14 comments:

Moges Kahssay said...

Great job! Thank you our bro. Let the help of God and the intercession of our Lady st. Virgin Mary be with u

7:59am Dec 14

Yeti Mehari said...

Kale hiwot yasemalen ye Egziabher chernet ye emebetachin amalajinet ye melaekit teradaenet ye tsadkan ye semaetat ye kdusan bereket zeweter ayileyih ( ayileyen ) yemistir balebet mistirun yigletselih tebarek wendime !!!!

10 December 2011 02:05

Andu Neh said...

amlak yakibrlin mengeste semayat yawarselin
about an hour ago

Tewabe Gebremichael said...

Amen kalehiwot yasemalen yagelgelot zemenehen yabzalen!!!

Abate Bekele said...

Amen! Kale hiwote yasemaleo tsigawen yabezalhe!!!

Saba Gebre said...

Amen qale hiwot yasmalen dingle tbarkh!

Egzabheri Fkri said...

Eyu Kale hiwet yasemalen
3 hours ago

Alem Berhanu said...

kale hiwot yasemalne abezto abezto....yebarkelnefetsamihen yasamerlhe wendmie

Solomon Yohannes said...

Kale hiwot yasemalin!!!

Abebe Redahegn said...

kale heyewet yasemalen

Meron Fekru said...

·
kala hiwat yasamaln ba edma batana yetabkelne!!!

Friends with ደቂቀ ናቡቴ and 7 othersLoading...

Adane Girma said...

Delicious tnks ma friend.

Aklilu Zewde said...

Thankyou! Ma man! Egzer be cherinetu yitebiken! Kale hiwotin yassemalin.

Talew Adola Dheressa said...

Excellent innovation. 4 sure we'll keep in touch