Monday 19 August 2013

//ፍሬ አልባው ዛፍ//



ፍሬ የሌለው ረዥም ዛፍ አየሁ። የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ፍቅር ሰላም ትህትና መቼ ሞቱ? ማንስ ቀበራቸው? እነዚህ ሁሉ ሞተው አለማልቀሳችን ምንኛ ደፋር ብንሆን ነው?

ትዕግስት ቢሞት በፍቅር ይነሣል
ትህትና ቢሞት በፍቅር ይነሣል
እምነት ቢሞት በፍቅር ይነሣል
ፍቅር የሞተ ዕለት ወዴት ይደረሳል?

ፍሬ የሌለው እንደ ረጃጅም ዛፍ ሆንኩ። ፍሬ የበዛለት ዛፍ እንዴት የታደለ ነው?
ኦሪት ዘፍጥረት
1፥11 እግዚአብሔርም፦ ምድር ዘርን የሚሰጥ ሣርንና ቡቃያን በምድርም ላይ እንደ ወገኑ ዘሩ ያለበትን ፍሬን የሚያፈራ ዛፍን ታብቅል አለ እንዲሁም ሆነ።

እኔ ደካማው ግን በአሲድ እንደተጠቃ መሬት ፍሬ የማልሰጥ ሆንኩ።

መዝሙረ ዳዊት 1
1 ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ፥ በኃጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ፥ በዋዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ።
2 ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል፥ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል።
3 እርሱም በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደ ተተከለች፥ ፍሬዋን በየጊዜዋ እንደምትሰጥ፥ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል።
እኛ ግን የጠወለገ ቅጠልና ግንድ ብቻ ሆነናል።

መጽሐፈ ምሳሌ
11፥30 የጻድቅ ፍሬ የሕይወት ዛፍ ናት፥ ፤
እኛ ግን እንደ ሙት ባህር ሙት ዛፍ ሆነናል።
የሉቃስ ወንጌል
3፥9 አሁንስ ምሳር ደግሞ በዛፎች ሥር ተቀምጦአል፤ እንግዲህ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል ወደ እሳትም ይጣላል።
የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው። የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ እነዚህ ከሆኑ ጥላቻና ቁጣ፣ ክርክርና ከንቱ ወሬ የማን ፍሬ ናቸው?
ወደ ገላትያ ሰዎች 5
22 የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው።

አቤቱ ሆይ ረዥም ፍሬ አልባ ዛፍ እንዳልሆን ጠብቀኝ። 30፣ 60፣ 100 ፍሬ እንድናፈራ አንተ እርዳን፤ አሜን!

http://yonas-zekarias.blogspot.com/




No comments: