Saturday 14 April 2012


“እንኳን ለብርኃነ ትንሣኤው በሠላም አደረሳችሁ!!!”

አሥሩ ሐዋርያት ጌታችን ከሞት መነሳቱን ለቶማስ ሲነግሩት ቶማስ “የችንካሩን ምልክት በእጆቹ ካላየሁ ፤  ጣቴንም በችንካሩ ምልክት ካላስገባሁ አላምንም” ብሎ ነበር።
ቶማስ ይህን ያለበት ራሱን የቻለ ምክንያት አለ፤ ይህም ቶማስ ትንሣኤ ሙታን የለም ብለው ከሚያምኑት ከሰዱቃዊያን ወገን ስለነበር ነው። ጌታችንም ቶማስ በእምነቱ እንዲጠነክር አስቀድሞ ለአሥሩ ሐዋርያት እንደተገለጠው ቶማስ ባለበት ዝግ ቤት ዳግመኛ ተገለጦ ዲዲሞስ የተባለው ሐዋርያ “ካላየሁ አላምንም” ያለውን ሁሉ እንዲያይና እንዲያምን አደረገ፤ 

“የቶማስ ምስክርነት”፦
ሐዋርያው ቶማስ ጣቴን በችንካሩ ምልክት ካላስገባሁ አላምንም ብሎ ነበርና ጌታችንም “እመን እንጂ ተጠራጣሪ አትሁን” ብሎ ሱራፌልና ኪሩቤል መንካት የማይችሉት ጌታ ጎኑን በእጁ እንዲዳስስ ለቶማስ ፈቀደለት ፤ ቶማስም እጁን ወደ ጌታ ጎን ዘረጋ; የመለኮቱ እሳት እጁን ሲፈጀው ሲያኮማትረው ወዲያው “አምላኬ” ብሎ መሰከረ።
ዮሐንስ 20:28

ቶማስ የጌታን ጎን ዳሰሰና አምላክነቱን መሰከረ።         

“የቶማስ መልስ  ለጆቫዊያን”፦  ጆቫዊያን ጌታ የተነሳው ሥጋውን በመቃብር ትቶ እንዲሁ በመለኮታዊ ኃይሉ ተነሳ ብለው ታላቅ ክህደትን ያስተምራሉ። ሐዋርያው ቶማስ ግን የጌታችንን ጎን እንደዳሰሰ አይተናል ፤ መንፈስ ብቻውን አይዳሰስምና ጌታችንም የተነሳው ሥጋውን በመቃብር ሳይተው ነው። እነማርያም መግደላዊትና ወደ መቃብሩ የሮጡት እነዚያ ደገኞቹ ሁለቱ ሐዋርያት የጌታን መግነዝ አዩ እንጂ መቼ ሥጋውን በመቃብር አገኙ? ሐዋርያው ቅ/ጴጥሮስ ጆቫዊያንን እንዲህ ይላቸዋል፦”የዳዊት መቃብር በመካከላችን አለ የክርስቶስ ሥጋ ግን በመቃብር እንዳልቀረ እንመሰክራለን” የሐዋ. 2:29 እኛም ከሐዋርያው ተቀብለን እንዲህ አልን “እዩና እመኑ ሰዎች ድንጋዩ ተፈነቃቅሏል ሞትን ድል አድርጎ ሥጋውን በመቃብር ሳይተው ተነስቷል” እያልን እንዘምራለን።
ቅ/ጴጥሮስ በመንፈስ ሄዶ በወህኒ ቤት ላሉት ነፍሳት ሰበከላቸው” 1ኛ ጴጥሮስ [3: 15] እንዳለ ጌታ በነፍስ ብቻ ሲኦል ወረደ ብለን እናምናለን፤ መናፍቃኑ ግን ጌታችን በነፍስና በሥጋው ሲዖል ወረደ ይላሉ፤ ታላቅ ክህደት! ሲጀመር ሥጋ ወደ ሲኦል ይወርዳል እንዴ? ነፍስ እንጂ ሥጋ ሲኦል አይወርድም፤ በዚህ ቃል ብቻ የመናፍቃኑን መልስ መመለስ ይቻላል። በሥጋው በመቃብር ነበር፤ በዘባነ ኪሩብ ነበር፣ አለ ፣ ይኖራልም። በሥጋው ሞተ በመለኮቱ ሕያው ነው። ሲነሳም ሥጋውን በመቃብር አልተወም፤ ቶማስ እንደ ዳሰሰው፣ ማርያም መግደላዊት መቃብሩን ባዶ ሆኖ እንዳየችው፣ ቅ/ጴጥሮስ እንደ መሰከረው ሐዋ [2: 29]

ማርያም መግደላዊት አትንኪኝ”፦ አንዳንድ ሰዎች ጌታችን ለቶማስ ጎኔን ዳስ ብሎ ለማርያም መግደላዊት ግን ወደ አባቴ አላረግሁምና አትንኪኝ” ያላት ከትንሳኤ በኋላ ሴቶች ጌታን መንካት ስለማይችሉ ነው ይላሉ ፤ ይህ ግን የተሳሳተ ሃሳብ ነው። ምክንያቱም እግሩን ይዘው የሰገዱለት ሴቶች ስለነበሩ ነው፦ “ሁለቱ ሴቶች ቀርበው “እግሩን ይዘው” ሰገዱለት” ማቴ 28:9 ማርያም መግደላዊትን አትንኪኝ ብሎ ለቶማስ ዳሰኝ ያለው ሥልጣነ ክህነት ለወንድ ብቻ ስለሆነና ሥጋ ወደሙን የሚዳስስ ወንድ ብቻ ስለሆነ ነው።

“አንሥኡ እደዊክሙ ቀሳውስ” ፦ ዲያቆኑ ይህን በሚልበት ጊዜ ንፍቁ ካህን ማሕፈዱን /የሥጋ ወደሙን መሸፈኛ/ ከጻሕሉ /የሥጋ ወደሙ ማስቀመጫ/ ላይ ያነሳል ፤ ይህም የጌታ መልአክ የመቃብሩን ድንጋይ የማንከባለሉ ምሳሌ ነው። ከዚህ በኋላ ጌታችን በምሴተ ሐሙስ ሕብስቱን እንደያዘው ዋናው ካህንም ሕብስቱን ከፍ አድርጎ ይይዘዋል ፤ ይህም የጌታ ትንሣኤ ምሳሌ ነው። እንኳን ለብርኃነ ትንሣኤው በሠላም አደረሳችሁ!!!

No comments: