Friday 8 March 2013

“የምክር ዓይነቶች”


ዘና ብላችሁ ተቀመጡና አንድ አሪፍ ታሪክ ላውጋችሁ!
ክብርት ሚሽቴ በጊዜ አትገባ! ወጥ አትሰራ! አዬዬ…. እናንተዬዋ እስኪ ምከሩኛ? በአንድ ወቅት ሰዎች ማማሰያንለምን እዚህም እዚያም ድስት ውስጥ ትገቢያለሽ?” ብለው ጠየቋት። ማማሰያምባካችሁ እኔ ያልገባሁበት ድስት አይጣፍጥምአለች ይባላል! እንደ ማማሰያ እኔ ያላማሰልኩት ወጥ ሽንኩርቱ ማረሩ አይቀርም የሚሉ ብዙ ናቸው። እንደ ማማሰያ እዚህም እዚያም ውስጥ ገብተን ምክር ካልመከርን የሚሉ አይጠፉም። እንደ ማማሰያ እኔ ያልመከርኩት ምክር ካልሆነ ሞቼ እገኛለሁ የሚሉትን ማማሰያ ይቁጠራቸው።

በአንድ ወቅት በታክሲ ውስጥ ተሳፍሬ እየሄድኩ ነበር። ከዛሬ 15 ዓመታት በፊት የኾነውን ነገር እያሰብኩ በሐሳብ ባቡር ጭልጥ ብዬ ነጎድኩ….

ከዛሬ 15 ዓመት በፊትየሚሸጥ ትኩስ እንጀራ አለብዬ በለንደን የመጀመሪያ የሆነችውን የእንጀራ መሸጫ ሱቅ ከፈትኩ። የአካባቢው ነዋሪዎች ግን ድሮስ በነጻ ልታድለን ነበር? አሉ። እኔም የሚሸጥ የሚለውን ሰረዝኩናትኩስ እንጀራ አለየሚለውን ብቻ አስቀረሁ። ሰዎቹ ግን ድሮስ የሻገተ እንጀራ ልትሸጥልን ያምርሃል? አሉ። እኔም ትኩስ የሚለውን ሰረዝኩናእንጀራ አለብዬ ጻፍኩ። ነዋሪዎቹ ግን አሁንም ጤፍስ የለህም? ድርቆሽስ የለም? እያሉ ተሳለቁብኝ። ግራ ሲገባኝአለየሚለውን ብሰርዘውእንጀራየሚለው ብቻ ቀረ። ግራ ይግባኝ ቀኝ ይግባኝ ማን ይጭነቀው እቴ አሁንም እንጀራ ምን ይሁን? አሉኝ። እኔም ማስታወቂያውን ሙሉ ለሙሉ ሰረዝኩትና ከስሬ በለንደን የመጀመሪያ የሆነችውን የእንጀራ ቤት ተዘጋች! ይኸው እኔም እስከ ዛሬ እንጀራ እንደዘጋኝ አለሁ!! 

እናቴም እንደ ልጅነቴ ፀጉሬን እየዳሰሰችሞኝና ውኃ እንደ ወሰዱት ይሄዳልእያለች ተረተችብኝ። እንዲያውም ለልጄ ያልሆነ ለማን ሊሆን ኖሯል ብላ የለንደንን እማ ወራ ሰብስባ የተረት ቀን አዘጋጀችልኝ። ከተረት ዘሪዎቹ እማ ወራ መካከል እትዬ ጣይቱ ምክር ሊመክሩኝ ቸኩለው እየተንደረደሩ ሲመጡ ድንገት የቤቱ ክፈፍ አደናቀፋቸውና በጭንቅላታቸው ሲተከሉ ልናያቸው ነበር። እትዬ ጣይቱ ግን እንደ መውደቅ አሉናየእናቴ መቀነት አደናቀፈኝብለው አሳቁን። ወዲያውምክር ከድሃ ነበርሽ ማን ቢሰማሽብለው እንደለመዱት ወገባቸውን በእጃቸው ይዘው እያቃሰቱ የእርጅና ሳውንድ ትራክ አሰሙና ኧረ እርጅና ብቻህን ብለው ከአጠገቤ ተቀመጡ። በሁኔታቸው ሁሉም ሳቁ። እኔም ከትከት ብዬ ለመሳቅ አሰብኩናሆድ ካልሞላ ጥርስ መቼ ይስቃልብዬ መሳቄን ተውኩት።ሰዎች በሚሰጡህ አስተያየት ሁሉ እርምጃ የምትወስድ ከሆነ በዚህ ዓለም ላይ መኖር አትችልምአሉኝ እትዬ ጣይቱ በሹክሹክታ። እትዬ ጣይቱ ሀገር ቤት እያሉ አጥራቸውን በእጃቸው እየነቀነቁየሴት ምክር የሾህ አጥርየሚሉት አባባላቸው ትዝ አለኝ። መቼስ የእትዬ ጣይቱ ምክር በለንደን ከተማ ፍቱን መፍትሄ ነው። እንዲያውም በለንደኑ ኦሎምፒክ አክራሪዎች ችግር እንዳይፈጥሩ ብዙ ምክር መክረዋል ይባላል። ምከረው ምከረው እንቢ ካለ ጣይቱ ትምከረው ይባልላቸውም ነበር! 

እውነትም የምክር ዓይነቶች ብዙ ናቸው ለካ! ሁሉም ምክር ጠቃሚ አይደለም። ሁሉም ምክር ጎጂ አይደለም። በአንድ ወቅት አኪ ጦፌ ንጉሥ ዳዊት ላይ ክፉ ምክር መከረ። አኪ ጦፌ ለአቤሴሎምአባትህ ዳዊት ዮርዳኖስን ሳይሻገር አሁኑኑ ወርደን እንያዘውብሎ መከረው። ታማኙ የዳዊት አገልጋይ ኩሲ ግን በደንብ ተደራጅተን ዳዊትን እንግደለው ብሎ አቤሴሎም እንዲዘገይ አድርጎ በድብቅ ዳዊት ይሸሽ ዘንድ ላከበት። አኪ ጦፌ ምክሩ እንደከሸፈበት ሲያውቅ ታንቆ ሞተ። እኔ ያልመከርኩት ምክር ካልሆነ ሞቼ እገኛለሁ የሚሉትን ማማሰያ ይቁጠራቸው ያልኳችሁ ለዚሁ ነው። አሁን አባትና ልጅ ካልተጋደሉ ብሎ መታነቅን ምን እንበለው? “ሰውን አትመኑ አብዷል ዘመኑብንለው ደገኛ ሰዎችን መበደል ይሆንብናል። ዋሽተው የሚያስታርቁ እንዳሉ ሁሉ ዋሽተው ባል ከሚስት ልጅ ከእናት የሚለያዩ አሉ። በሰው አስተያየትና በሰው ሐሳብ ብቻ ከተመራን ትርፉ ይህ ብቻ ነው።ፈሪ ከውኃ ውስጥ ያልበዋልእንዲሉ አግባብ ባልሆነ ፍራቻ ብቻ የአቶ እገሌን ምክርአሜንብለን እንቀበላለን። ነፍስ ይማርና እትዬ ምክርሞትና እድሜ ቢፈሩት አይቀርምይሉ ነበር። አንድ ሰው እስከ የትኛው የልባችን ክፍል ነው መግባት የሚችለው? ልባችን ሁሉም ሰው ዘው የሚልበት በር የሌለው በረት መሆን የለበትም። አንዳንዱም ያስጨነቀው ያስጠበበው ችግር የሚቀልለት በማውራት ስለሚመስለው ለሰው ሁሉ ችግሩን ዘክዝኮ ያወራል። አጅሬ ሰይጣንም ከአፉ ቃላት እየመረጠ ችግሩን ይዘከዝክለታል። እዚህ ዝምታ በራሱ ድምጽ የሌለው ገዳይ ነውና ችግራችንን ታቅፈን መታፈን አለብን ለማለት አይደለም።ብዙ ዝምታ ይሆናል በሽታአይደል የሚባለው። ዐይነ ስውሩ በጥለሚዮስ በኢያሪኮ ጎዳና ላይ ሲጮህ ትዝ አይላችሁም? ሰው ሁሉዝም በልሲለው እሱ ግን አብዝቶ ጮኸ። ዐይነ ስውሩ በጥለሚዮስ ለማን መጮኽ እንዳለበት ያውቅ ነበር። የኢያሪኮ ነዋሪዎች የብዙዎቹ ምክርለዐይነ ስውር መስታወት እንደመሸለም ነበርወገኔ! አብዝተን መጮኽ ያለብን ወደ ላይ ነው! የሰውን ሐሳብ መስማት ባይጠላም ለምክሮች ሁሉ ግን የማጣሪያ ወንፊት ያስፈልገናል።ሞኝ ለጠበቃው ሚሥጢር ይሸሽጋልአሉ እትዬ ምክር። ሁነኛ መካሪ አባ ወራ እና እማ ወራ አሉን። ችግሩ በሀገርም ሆነ በቤተሰብ መካሪነት ከእነሱ መጣላታችን ነው።ሞኝ ከመካሪው ዕውር ከመሪው ይጣላልአሉ እትዬ ምክር።

ሰውየው በግ ሊገዛ በግ ተራ ወጣና ዐይኑን በግ ፍለጋ ያንከራትት ጀመር። በድንገት ጥቁርና ነጭ ዐይኑ ጥቁርና ነጭ በግ ላይ አረፈ። በጉን ስለወደደው ሊገዛው ቢፈልግም ጓደኞቹን ማማከር ፈለገ። አስተያየት እንዲሰጡትም ጠየቃቸው። አንደኛውላቱ አጭር ነውአለው። ቀጠለ ሁለተኛውቀንዱ የከረከረ ነውአለው። ሦስተኛውምበጉ ጥፍሩ ዘርዝሯል እየው እስኪአለው። ሰውየው ግራ ገባው። ግራ ቢገባው ቀኝ ቢገባው ለመካሪዎቹ ዋናው ምክራቸው መሰማቱ ብቻ ነው። በመጨረሻም ሰውየው ልቡ የወደደውን በግ እንደ ዐይነ ስውር የፊደል መቁጠሪያ በእጁ እየዳሰሰይህ በግ ስንት ነው?” ብሎ በግ ሻጩን ጠየቀ። 

አንድ ብር ብቻ ነው ጌታዬበግ ሻጩ መለሰ። 

ደግሞ አንድ ብር ብቻ ይለኛል እንዴ! በአንድ ብር በግ ከምገዛ በቅሎ መግዛት አይሻለኝም እንዴ?” አለ ሰውየው በንዴት።

በግ ሻጩምጌታዬ እኔ የማውቀው የበጉን ዋጋ ብቻ ነው፤የሚጣፍጦትን እርሶ ያውቃሉአላቸው ይባላል!! 


ሰው ብዙ አስተያየት ብዙ የምክር ዓይነቶችን ሊሰጥ ይችላል። የሚጠቅመንንና የሚጣፍጠንን የምናውቀው ግን በግ ሻጭ እንዳለው እኛ ብቻ ነን። 

ከተሳፈርኩበት የሐሳብ ባቡር በድንገት ያነቃኝ የመኪናው ክላክስ ነበር። በተሳፈርኩበት ታክሲ ውስጥ የተወሰኑ ሰዎች በአንድ ጉዳይ ላይ ይመክሩ ይዘክሩ ይከራከሩም ነበር። አንዱ ተነሳና መፅሐፍ ቅዱስላዘነ ሰው የወይን ጠጅ ስጡት ድህነቱን ይርሳይላልና ለድህነት መጠጥ ፍቱን መድኃኑቱ ነው አለ። ቀጠለ ሁለተኛው።ላዘነ ሰው መጠጥ ያስፈልገዋልብሎ የታክሲ ተሳፋሪውን በሙሉ በዐይኑ እያማተረ መከረን። እንዲያውምወይን ያስተፈስ ልበ ሰብብሎ ግዕዙንም ጨምሮ ሽንጡን ይዞ ተከራከረ። ሦስተኛው ግንላዘነ ሰው የወይን ጠጅ ስጡት ድህነቱን ይርሳየሚለው ጥቅስ በመፅሐፍ ቅዱስ ይኑር አይኑር አላውቅምና የምለው የለኝም አለ። 

ክርክራቸውን ስሰማ ገረመኝ። አንዱ ስለ ድህነት ይናገራል ሌላው ስለ ኃዘን ይናገራል ጥቅሱ ግን ከሚሉት ጋር አይገናኝም። ነገሩ እንዲህ ነው። 


ወወይነ ይስተዩ ትኩዛን ከመ ይርስዕዋ ለኀዘን ወሕማም ኢይዝክሩ እንከ።

ላዘነ ሰው የወይን ጠጅ ስጡት ድህነቱን ይርሳ” [ምሳሌ 31: 6]

ይህ ጥቅስ ትርጓሜው ምን ይሆን? “ላዘነ ሰው የወይን ጠጅ ስጡት ድህነቱን ይርሳሲል ባዘንን ቁጥር መጠጥ እንጠጣ ማለት ነውን? ከቶ አይደለም። 

ላዘነ ሰው (በንስኃ ለተመለሰ ሰው) ወይን ስጡት (ሥጋ ወደሙን አቀብሉት) ድህነቱን ይርሳ (ከእግዚአብሔር ፀጋ ተለይቻለሁ ብሎ አያስብ) ከእግዚአብሔር ጸጋ መየለየት ድህነት ነውና አሁን ግን ንስኃ ስለገባ ይህን ድህነቱን ይርሳ! [ምሳሌ 31: 6]

እነዚያ የታክሲ ውስጥ ምክር መካሪዎቹ ምን አለ የማያውቁትን አናውቅም ቢሉ? “አናውቅም አስገድሎ አያውቅምትላለች እናቴ። ነገር ነገርን እንዲወልድ የወለደችኝ እናቴ የነገረችኝ ግጥም ትዝ አለኝ።

አንበሳ አረጀና ቤት በመዋሉ
አራዊት ተጨንቀው የት ደረሰ ሲሉ
ነብር ተነሳና ከመካከላቸው
አታላይዋ ጦጣ ክፉ ብትመክረው
እኔ ነኝ አንበሳ እጅ ንሱኝ አላቸው።

ነብር ነብር እንጂ አንበሳ እንዳልሆነ
ምንም የሚታወቅ ቢሆን የታመነ 
ደፍሮ ለመናገር ሁሉም ስለፈሩ
ለነብር ማደግደግ እጅ መንሳት ጀመሩ።

ሌሎች እንዲፈሩት እንዲሰግዱለት
አንበሳ ነኝ ብሎ በዋሸው ውሸት
አመነበትና ከጊዜ ብዛት
እሱም ማን መሆኑን ጀመረ መርሳት።

አንበሳ ነኝ ብሎ ተቀምጦ ቤቱ
ሌሎችም ነህ ብለው ሲሰግዱ በፊቱ
አንበሳ መኖሩን ገና በሕይወቱ
በሩቅ ሲወራ ድንገት በመስማቱ
መሬት ጠበበችው ተቆጣ በብርቱ።

ሁሉም አምኖ እንዲኖር ነብር ያለውን
ከእሱ ሌላ አንበሳ አለመኖሩን
አዋጅ አዋጅ ብሎ ሰብስቦ ዓለምን
አንበሳን ሰደበ ከፍ አድርጎ ድምጹን።

የተኛው አንበሳ እድሜ ተጭኖት
የነብርን ስድብ ሰማና ድንገት
አጉራርቶ ቢነሳ ወኔው ቀስቅሶት
ነብር ግራ ገባው መሄጃ ጠፋው
መሬት አፏን ከፍታ ድንገት አትውጠው
ሰማይ እንዳይወጣ ክንፍ አልነበረው።


ልቡን ፍርሃት ሞልቶት እየተጨነቀ
ጥፋተኛነቱን ወዲያው ስላወቀ
አንበሳም ዘቅዝቆ አየና ነብርን
እግሩን እየሳመ ምህረት ሲለምን
ሞት ሊፈርድበት የሚገባውን
ከእግሩ ስር አንስቶ ሳመው ጠላቱን!

አንበሳ በሰራው ዓለም ተገረመ
የወንጌልን ትዕዛዝ አይቶ እንደፈፀመ።


ይህችን ጽሑፍ እንደጨረስኩኝ ቀና ስል ሰጎን እንቁላልዋን አትኩራ እንደምትመለከት አንዱ ዓይኑን ሳይነቅል ትኩር ብሎ ያየኝ ነበር። እኔ በሐሳብ ባቡር ስሳፈር ለካስ ለብዙ ደቂቃዎች አትኩሮ ኑሯል። ሞት ይርሳኝ ረሳውህ አይደል? አልኩት። አንዳች ሳይመልስልኝ አሁንም አትኩሮ ያየኛል። ሀገሬን ቤተሰቤን አስጥሎ ያሰደደኝትኩስ እንጀራነበር አፍጥጦ ያየኝ። ምነው እንዲያውም በሰዎች አስተያየትና በምክር ዓይነቶች የተዘጋው የእንጀራ ቤት ትዝ አይላችሁም? አዎ እሱ ነበር አትኩሮ የሚያየኝ። እናንተም በምክር ዓይነቶች የደረሰባችሁ ታሪክ ሳይኖር አይቀርም።በከንቱ ምክር እኔም አለኝ ቁስል ያንተን የሚመስል፤ ሰውን ማመን ገደለኝ እኔን እየመሰለኝያላችሁም አትጠፉም። ምን አልባት ታሪካቸውን የሚያካፍሉን ይኖሩ ይሆናል ማን ያውቃል። 


ይህችን ጥሑፍ ጥፌ ኮምፒተሩን ላጠፋው ስልማነህ ልጄ እስኪ ያንን ማማሰያ አቀብለኝአለች እናቴ። 


እኔ ያልገባሁበት ድስት አይጣፍጥም አለች ማማሰያ!” አልኩኝ በልቤ።

© Visit this Blog! http://yonas-zekarias.blogspot.com/





40Like ·  · Promote · 

No comments: