Saturday 12 May 2012

“አንቺ ሴት ከአንቺ ዘንድ ምን አለኝ”


ጌታ ለእመቤታችን አንቺ ሴት ከአንቺ ዘንድ ምን አለኝ አላት፤ ይህም ግሩም የሆነ ሚስጢርን በውስጡ ይዟል; እስቲ ቃሉን ለሁለት ከፍለን እንየው፦

አንቺ ሴት

ይህን ቃል ለመጀመሪያ ግዜ የተጠቀመው አዳም ነበርአዳም በግብረ ሥላሴ ከህቱም ድንግል መሬት (ከአፈር) ተፈጠረ፤ ከባድ እንቅልፍ ተኝቶ ሳለ ከግራ ጎን ዐጥንቱ ሔዋን ተፈጠረች። አዳም ከእንቅልፉ ነቅቶ ሔዋንን ከጎኑ ቢያት “ይህች ሥጋ ከሥጋዬ ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት ሲል ሴት አላት። ጌታችንም እመቤታችንን ከሥጋሽ ሥጋ ከነፍስሽ ነፍስ ነስቼ ከአንቺ ተወልጄ ዓለምን ኹሉ አዳንኩ ሲል “አንቺ ሴት” አላት። አንድም አዳም ከህቱም ድንግል መሬት ወይም ከአፈር መፈጠሩ እመቤታችን በህቱም ድንግና ጌታን የመውለዷ ምሳሌ ነው። አንድም ከአዳም ጎን ዐጥንት ሲነቀል አዳም ህመም አለመሰማቱ እመቤታችን ያለ ህመም ጌታን የመውለዷ ምሳሌ ነው። አንድም እግዚአብሔር አዳምን ከፈጠረ በኋላ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ አለ፤ ይህም አዳምን ሳይሆን እመቤታችንን ነው; እንዴት ቢሉ ወልድ ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ከሶስቱ አካል አንዱ ስለሚሆን ነው”


ከአንቺ ዘንድ ምን አለኝ፦

መፅሐፉ አጋንንት ያምናሉ ይንቀጠቀጣሉም ይላል; ነገር ግን ጌታን “ከአንተ ዘንድ ምን አለን” አሉት፤ አጋንንት ይህን ሲሉ ጌታን ንቀውት እንዳልሆነ ግልፅ ነው። አንድም ሱናማዊቷ ሴት ልጇን ከሞት እንዲያስነሳላት ነብዩ ኤልዕን ጌታዬ ሆይ “ከአንተ ዘንድ ምን አለኝ” አለችው። አንድም ዳዊት ልጁን አቤሴሎምን ሊገድሉበት ሲሉ እናንተ ሰዎች “ከእናንተ ዘንድ ምን አለኝ” አላቸው። ይህም የአክብሮት እንጂ የመናቅ ንግግር አለመሆኑ ግልጽ ነው።
******** // ********

ሐዋርያዊ ቅብብሎሽ “Apostolic Succession”

የቤተክርስቲያን ራስ ጌታ ነው። ከጌታ ቀጥሎ
“እስከ ዘመናችን” ያሉትን አባቶች በቅደም ተከተል አብረን እንያቸው!!



 የሐዋርያት አለቃ ቅ/ጴጥሮስ ነው።

ከቅዱስ ጴጥሮስ ቀጥሎ ቅ/ማርቆስ።

ቅ/ማርቆስ ግብጽ ሄዶ መንበሩን በግብጽ አደረገ።

ከቅ/ማርቆስ ቀጥሎ አንያኖስ ነው።

ከአንያኖስ ቀጥሎ 20 ፓትርያርክ አሉ። 20ኛው አትናቴዎስ ነው።

ከአትናቴዎስ ቀጥሎ ከሳቴ ብርኅን አባ ሰላማ /ፍሬምናጦስ/ ይህን ሐዋርያዊ ቅብብሎሽ ወደ ሀገራችን አመጣልን።

ፍሬምናጦስ ኢትዮጲያዊ አይደለም። አንድ ነጋዴ ሲድራኮስ እና ፍሬምናጦስ የሚባሉ ሁለት ልጆቹን ይዞ አንድ ነጋዴ ቤት ገብቶ መኖር ጀመረ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ነጋዴው ሞተ። ልጆቹም በገበሬው ቤት መኖር ጀመሩ። ፍሬምናጦስም የኢትዮጵያዊያንን እምነትና ባህል አደንቃለሁ። ለምን ሥጋ ወደሙን አትቀበሉም? ብሎ ገበሬውን ጠየቀው። ገበሬውም ካህናት ስለሌሉን ነው አለው። ፍሬምናጦስም በኢዛና እና ሳይዛና ፈቃድ ግብጽ ሄዶ ፕትርክናን ከአትናቶዎስ ተቀበለ።


የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ፍሬምናጦስ ነው።

ከዚህ ጊዜ በኋላ ለብዙ ዘመናት ኢትዮጵያ በግብጽ ፓትርያርኮች ስትመራ ቆይታለች።

የመጀመሪያው አራቱ ኢትዮጲያዊያን ጳጳሳት በ1921 ተሾሙ! 

አቡነ ሚካኤል
አቡነ ጴጥሮስ
አቡነ አብርሐም
አቡነ ይሥሐቅ ናቸው።

ከዚህ ጊዜ በኋላ በግብጽና በኢትዮጲያ መካከል ለሃያ አመታት ያክል ሀገራችን ኢትዮጵያዊ ጳጳስ ያስፈልጋታል አያስፈልጋትም በሚል ሽኩቻ ውስጥ ነበሩ።

ይህ እልህ አስጨራሽ ሽኩቻ አለፈና በ1940 ሌሎች አራት ጳጳሳት በግብጻዊው ፓትርያርክ በአቡነ ዮሳብ ተሾሙ።

አቡነ ሚካኤል
አቡነ ያዕቆብ
አቡነ ባስልዮስ
አቡነ ጢሞቴዎስ ናቸው።

ከእነዚህ ጳጳሳት አቡነ ባስልዮስ የመጀመሪያው ኢትዮጲያዊ ሊቀ ጳጳስ ኾነው ተሾሙ!! በዚህች እለት 21 ጊዜ መድፍ ተተኮሰ! ታላቅ ደስታ ነበርና! ጊዜውም በ1943 ዓ.ም ሲኾን ለአቡነ ባስልዮስ ሊቀ ጵጵስናውን የሰጡት የግብጹ ፓትርያርክ አቡነ ዮሳብ ነበሩ።
ከ1951-1963 ዓም ድረስ የመጀመሪያው ኢትዮጲያዊ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ባስልዮስ የመጀመሪያው ኢትዮጲያዊ ፓትርያር ኾኑ!!

በርግጥ ከአቡነ ባስልዮስ በፊት አቡነ አብርሐምና አቡነ ዮሐንስ የሚባሉ ሌሎች ሁለት ፓትርያርክ ነበሩ። ነገር ግን የኢጣልያው መንግስት ስለሾማቸው ቤተክርስቲያናችን ሕጋዊ ፓትርያርክ አድርጋ አትቀበላቸውም። የመጀመሪያው ሕጋዊ ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ አቡነ ባስልዮስ ናቸው።

ከአቡነ ባስልዮስ ቀጥሎ ፓትርያር አቡነ ቴዎፍሎስ ናቸው።

ከአቡነ ቴዎፍሎስ ቀጥሎ አቡነ ተክለሐይማኖት ናቸው።

ከአቡነ ተክለሐይማኖት ቀጥሎ አቡነ መርቆርዮስ ናቸው።

ከአቡነ መርቆርዮስ ቀጥሎ አቡነ ጳውሎስ ናቸው።

በነብያትና በሐዋርያት መሰረት ላይ ታንጻችኋል! የማዕዘኑ ድንጋይም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ኤፌ [2: 20] እንዲል የቤተክርስቲያን ራስ ጌታ ነው! በነብያትና በሐዋርያት መሰረት ላይ ስለታነጽን ሐዋርያዊ ቅብብሎሽን በሚገባ ማወቅና መረዳት አለብን። ፍትሕ መንፈሳዊ በአምስተኛው አንቀጽ ቁጥር 164 በሚያዝዘው መሠረት ቅዱስ ሲኖዶስ በዓመት ሁለት ጊዜ መደበኛ ስብሰባ ያካሂዳል፡፡ የመጀመሪያው ጉባኤ በየዓመቱ ጥቅምት 12 ቀን ሲኾን የሁለተኛው ጉባኤ ደግሞ ትንሣኤ በዋለ 25ኛው ቀን /በርክበ ካህናት/ የሚካሄደው ነው፡፡




2 comments:

bini-Ethiopianism said...

please please change the fonts to black.we cant read it.white font color will reflect to mobile screen so its hard to read.please please change the font color to black so we can enjoy ur blog!God bless u!

ዮናስ ዘካርያስ said...

ለአስተያየቱ አመሰግናለሁ። ብሎጉን ቀስ በቀስ ለማስተካከል እሞክራለሁ!