Tuesday 28 February 2012

የዕንባ ዘለላ!


ዘና ብላችሁ ተቀመጡና አንድ ታሪክ ልንገራችሁ፤


በአህያ ቆዳ የተሰራ ቤት ይፈርሳል ጅብ የጮኸ እለት” ይላል የሀገሬ ሰው፤ ነገሩ ወዲህ ነው እነሆ በለንደን የምንኖር ሐበሾች በክራይ የምንገለገልበት ቤተክርስቲያን አለ፤ ቤተክርስቲያኑን ከነጮች ጋር በፈረቃ ነው የምንጠቀመው። እሁድ ጠዋት ለቅዳሴ እንገባና ከሰአት ነጮቹ ገብተው የራሳቸውን ፕሮግራም ያካሄዳሉ። ሲፈልጉ ስፖርት ይሰሩበታል ደስ ሲላቸውም ይደንሱበታል! እኛም በየሳምንቱ ለቅዳሴ እየተገለገልንበት እንዲህ እያለ ይቀጥላል። ይህ የእንግሊዝ አብያተክርስቲያናት ጸባይ ነው፤ ድሮ አባቶቻቸው ያወረሷቸው በእየ 7 እርምጃ የተሰሩ ቤተክርስቲያን ነበራቸው፤ አሁን በእየ 3 እርምጃ የተሰሩ የጭፈራ ናይት ክለብ አላቸው፤              ከቤተክርስቲያናቸው ስር /under ground/ የጭፈራ ቤት ተሰርተዋል፤ ዛሬ አውሮፓዊያኑ ከጥንት ነዋሪዎች በስተቀር ቤተክርስቲያን የሚመጣ ህዝብ የላቸውም፤ ስለዚህም ቤተክርስቲያኑ ይሸጥና የጭፈራ ቤት ይሆናል ማለት ነው።


ጨረቃ ብትደምቅ አታሞቅ የሰው ቤት አያደምቅ” ነውና ነገሩ ሰሞኑን በምንገለገልበት ቤተክርስቲያን ውስጥ ያለው ቤተ መቅደስ እንዲፈርስ ጠይቀዋል፤ “ሂድ አትበለው እንዲሄድ አድርገው እንደ ማለት ነው። ቢሯችንም ተዘግቶ አገልግሎቱ ቆሟል። ሰበካ ጉባኤው ሰሞኑን ተሰብስቦ ሌላ ቤተክርስቲያን ፍለጋ እየተሯሯጠ ነው። ሞት ቢዘገይ የቀረ ይመስላል አለች ሴትዮዋ እውነቷን እኮ ነው፤ እኛም ዝምታቸው ሲዘገይ የቀረ መሰለንና ቤተክርስቲያኑ የራሳችን መሰለን፤ በመጨረሻዋ ሰአት ላይም ተረባረብን፤ ይህን ያዩ የለንደን እማ ወራዎችም ሞት ሲደርስ ቄስ ጦር ሲደርስ ፈረስ” ብለው ተረቱ!


በእርግጥ ነጮቹ እስከ ዛሬ ቤተክርስቲያኑን እንድንጠቀም ስለፈቀዱልን ማመስገን ይገባናል፤ ሲጀመር የራሳችን አያያዝ ጥንቃቄ የጎደለው ነበር። ምዕመናንም በንፅህናው ረገድ ችላ ያሉ ይመስላል፤ የሰ/ት/ቤቱ ተማሪዎች በፅዳቱ ቢተጉም በአጠቃላይ አያያዛችን ላይ የጥንቃቄ ጉድለት ነበር፤ አንዳንድ እቃዎች ተሰበሩ፣ በካርፔንት እና በወንበሮች ላይም ሻማ ፈሰሰ፤ ይህን የመሰለ ወዘተ ተረፈዎች ሲደማመሩ ችግሩ ጎላና እነሱም መናገር ጀመሩ፤

*እስከ ሁለት ወር ድረስ ግዜ ተሰጥቶናል፤ ከዛ በኋላስ እንወጣለን ማለት ነው? ወይስ ምን ይመጣ ይሆን? የትንሣኤውን በዓልስ የት ይሆን የምናከብረው? መልካሙን ያሰማን።

ለዚህ ነው “የዕንባ ዘለላ” እናዋጣ የተባለው። ለጸሎት ስትቆሙ እስቲ ስለዚህ ጉዳይ አንዲት አባታችን ሆይ ድገሙ፤ እስቲ ሁላችንም ትንሽ የዕንባ ዘለላ እናዋጣ፤ እስቲ ተሳሉ; እስቲ የዕንባ ዘለላ አዋጡ፤ የእያንዳንዳችን የዕንባ ዘለላ ተጠራቅማ ምን አልባት ታላቅ ስራን ትሰራ ይሆናል ማን ያውቃል? እስቲ አብዝታችሁ ጭኹና ለምኑ፤ ከእልፍ አእላፋት የወፎች ጩኸት መካከል የልጇን ድምጽ ለይታ የምታውቅ ለየት ያለች የወፍ ዝርያ አለች፤ ከመካከላችንም እግዚአብሔር የመረጠው ጩኸቱ ይሰማ ይሆናል ማን ያውቃል?

ለጸሎት በቆማችሁ ግዜ ይህችን ጉዳይ በእግዚአብሔር ፊት አቅርቡ፤ እስቲ እንደ ነብያቱ በዕንባ ዘለላ ጭምር ልመናችንን እናቅርብ፤ የኢየሩሳሌም ቅጥር እና ቤተ መቅደሱ ሲፈርስ ነህምያና ኤርሚያስ ያደረጉት ትዝ እንደሚለን የታመነ ነው። ነህምያ የንጉሥ አስተናጋጅ ነበር፤ በቤተ መንግሥት እየኖረ ይህንንም በሰማሁ ግዜ ተቀምጬ አለቀስኩ” አለ፤የኢየሩሳሌም ቅጥር መፍረሱን፣ ቤተመቅደሱ መፍረሱን፣ሰው ከእግዚአብሔር መራቁን በሰማ ግዜ አለቀሰ፤ ብዙ ግዜም እፀልይና እጾም ነበር ነህምያ [1: 4] እንዲሁ ነብዩ ኤርሚያስም ቤተመቅደሱ መፍረሱን አይቶ አለቀሰ፤ ሰቆ. ኤር. [3: 44]

የሁለቱን እንባ ወደ  እግዚአብሔር ሊያቀርብ ደገኛ የሆነ አንድ የከበረ መልአክ በእግዚአብሔር ፊት ቆመ፤ ይህ መልአክ  እግዚአብሔርን ምን ብሎ ነበር የለመነው? እግዚአብሔርስ ለዚህ ደገኛ መልአክ ምን ብሎ ይሆን የመለሰለት? 
አቤቱ የሠራዊት ጌታ ልዑል እግዚአብሔር ሆይ እነዚህን 70 አመት /እስራኤል በባቢሎን የተወረችበት 70 አመታት/ የተቆጣሃቸውን የኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች የማትምራቸው እስከ መቼ ድረስ ነው፤ እያለ እግዚአብሔርን ለመነ፤ እግዚአብሔርም ደስ በሚያሰኝና በሚያጽናና ቃል ለመልአኩ መልሶለት ለኢየሩሳሌምና ለይሁዳ ከተሞች ምህረትን አደረገ! የኢየሩሳሌም ቅጥር በእነ ነህምያ ተሰራ! ቤተ መቅደሱም በእነ ዘሩባቤል፣ ዘካርያስና ሐጌ አስተባባሪነት ተሰራ! በዚህ ታሪክ ውስጥ የመልአኩን ምልጃ ልብ ይበሉ፤ ትንቢተ ዘካርያስ [1: 12]

የእምነት ጸሎት ኃይልን ታደርጋለች” እንዳለ ሐዋርያው እነሆ የዕንባ ዘለላ ይህን የመሰለ ግዳጅን ትፈጽማለች! 

በስደት ሀገር መስኮቱን ወደ ኢየሩሳሌም ከፍቶ የሚጸልየው ሰው ማን ነበረ? በስደት ሀገርማ ብዙዎች እግዚአብሔርን ይዘው ድንቅ ስራውን አዩ፤ አብርሐም ፣ ሙሴ ፣ ዮሴፍ ፣
እግዚአብሔርን ይዘው ተሰደዱ፤ ነብዩ ዳንኤልም በስደት ሀገር መስኮቱን ወደ ቅድስት ሀገር ከፍቶ ይጸልይ ነበር።

እኛም በስደት ያለን እንደ ነብዩ ዳንኤል መስኮታችንን ወደ ቅድስት ሀገር ኢትዮጲያ ከፍተን የምንጸልይበት ብርቱ ጉዳይ አለ፤ ይህ ብርቱ ጉዳይ “የዕንባ ዘለላ የምናዋጣበት ብርቱ ጉዳይ ነው” እነሆ እንደ ያዕቆብ ልጆች እንጀራን ፍለጋ በምድረ አውሮፓ ወደ ለንደን ተሰደድን፤ ስደትን ለስደተኛ ማን ያስረዳዋል? ወንጌሉ “ማንም ከዛሬ ጀምሮ ጌታን እወቅ ብሎ አያስተምርም፤ ምክንያቱም ከታናሽነት ጀምረው ሁሉም ያውቁኛል” እንደሚል ስደትን ለሚያውቃት ማንም አያስረዳውም።

ስለስደት እንነጋገር ከተባለ ግን ስደት 4 ልጆች አላት፤ ናፍቆት ፣ ብቸኝነት ፣ የሚፈራረቁ ሀዘንና ደስታ ናቸው።

የስደት ልጆችን የምታጽናና አንዲት እናት አለች፤ ይህችም ቤተክርስቲያን ናት።


በስደት ያዘነው ሁሉ በቤተክርስቲያን በርከክ ብሎ አንድ ሁለቴ የሰላም አየር በርጋታ ሲተነፍስ ያኔ የውስጥ ሰላምን ያገኛል! ይህች ቤተክርስቲያን በስደት ሀገር ለስንቱ መጠለያ ሆነች? ስንቱን አጽናናች? ስንቱን የነፍስ ረፍት ሰጠች? ይህን ሳስብ ሁሌ ይገርመኛል! አንድ ታላቅ ሰው “ቤተክርስቲያን ባትኖር ኖሮ ሐበሻ በስደት ሀገር ቆሞ መሄድ አይችልም ነበር” ብለዋል። ይህ በእርግጥ እውነት ነው፤ የእኛ ጸባይ በህብረት መኖር ነው፤ ከሌላው አለም ሲነጻጸርም እኛ ሀዘንን መቋቋም አንችልም። ለዚህ ነው “ቤተክርስቲያን ባትኖር መቆም አንችልም” ያለው። አሁን ግን ይህች መጠለያ ቤተክርስቲያናችን እኔ እንዳቆምኳችሁ እናንተም አቁሙኝ እያለች ነው፤

ይህች ጽሁፍም ዋና አላማዋ ለዚህ ጥሪ አንዳች መልስ እንሰጥ ዘንድ ነውና አንብበን ብቻ ዝም አንበል፤ መንገድ በሀሳብ አይደረስም” እንዲል ማሰብ ብቻ ሳይሆን  አንዳች ነገር በተግባር እንስራ፤ “ስራ የሌለው እምነት ሙት ነው” እንዳለ ሐዋርያው እምነታችን ሕያው እንዲሆን እስቲ አንዳች ነገር እንስራ፤ ጫማ የለም ብለው የሚያጉረመርሙ እግር የሌላቸውን አይተው ይጽናኑ” እንደሚል እኛም ሳናጉረመርም አንዳች ስራን እንስራ፤  ሰው እናቱ ብትራብ ዝም አይልም ከአፉ ነጥቆ ይሰጣታል፤ ምንም የስደት ኑሮ ባይደላም እናት ናትና የሚወጣ ገንዘብ እንኳን እንደየ አቅማችን ብናደርግ ለታሪክ የሚሆን ትንሽ ስራ ሰራን ማለት ነው።



ነህምያ እኛ ባሪያዎቹ እንነሳለን የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል” እንዳለ እስቲ እግዚአብሔር እንዲያከናውንልን እኛ ባርያዎቹ እንነሳ፤ እስቲ እናንተም ያላችሁን ሀሳብ አቅርቡ፤

ከእንግሊዝ ውጪ የምትኖሩ ወገኖቻችንም እስቲ በጸሎት እርዱን፣ በሀሳብ አትርሱን፣ እናንተ ስትጸልዩ እኛ የዕንባ ዘለላን ስናዋጣ የነብያቱን እንባ ያሳረገ መልአክ የእኛንም ያሳርግ ይሆናል ማን ያውቃል?        


 
 የዕንባ ዘለላን አዋጡ!


  

3 comments:

ሳሚ(ወ/ሚካኤል) said...

እግዚአብሄር ያውቃል! በርቱ ልባችሁ ይጽና! ነገርን ሁሉ ከምስጋና ጋር በጸሎት እና በምልጃ በእግዚአብሄር ፊት አቅርቡ እንጅ በአንዳች አትጨነቁ!!! ድንቅ አድራጊው እና የቤተክርስቲያን ራስ የሆነው እሱ ክርስቶሰ የማታቁትን ድንቅ ነገር ባህዛብ ምድር ላይ ሊያሳየን እንደ እምነት ጽናታችን መጠን ቕርብ ነው!!! የኢትዮጵያ አምላክ ይርዳን!!!
ሳሚ ካገር ቤቲቱ ሰመራ!

ሳሚ(ወ/ሚካኤል) said...

እግዚአብሄር ያውቃል! በርቱ ልባችሁ ይጽና! ነገርን ሁሉ ከምስጋና ጋር በጸሎት እና በምልጃ በእግዚአብሄር ፊት አቅርቡ እንጅ በአንዳች አትጨነቁ!!! ድንቅ አድራጊው እና የቤተክርስቲያን ራስ የሆነው እሱ ክርስቶሰ የማታቁትን ድንቅ ነገር ባህዛብ ምድር ላይ ሊያሳየን እንደ እምነት ጽናታችን መጠን ቕርብ ነው!!! የኢትዮጵያ አምላክ ይርዳን!!!
ሳሚ ካገር ቤቲቱ ሰመራ

Anonymous said...

That is quit good to hear from you such an amazing blog posting deed.
I shared your blog on my toolbar
http://masho.ourtoolbar.com