ቅዱሳን በተጋድሎ የሚያገኙት ማዓረጋት አሉ፤ እነሱም አሥሩ ማዕርጋተ ቅዱሳን በመባል ይታወቃሉ። ከወጣንያን እስከ ፍፁማን በቅደም ተከተል እነሆ ለበረከት ፦
[1ኛ] ጽማዌ፦ ጽማዌ ማለት ሕሊናን ለእግዚአብሔር ብቻ ለማስገዛት ዝም ማለት ነው። አንደበት እሣት ነው ስለሚል እነ አጋቶን ከአፋቸው ክፉ እንዳይወጣ ድንጋይ ጎርሰው ዝም ብለው ነበር [ያዕቆብ 3:6] አባቶችን ስናይ የሰላምና የፀጥታ መንፈስ የምናይባቸው በዚህ መዓረጋቸው ነው።
[2ኛ] ልባዌ ፦ ልባዌ ማለት ማስተዋል ማለት ነው። በዚህ መዓረግ የደረሱ አባቶች መላዕክት ሲወጡና ሲወርዱ ያያሉ።
[3ኛ] ጣዕመ ዝማሬ፦ የሚዘምሩትንና የሚፀልዩትን ማር ማር እያላቸው በማጣጣም የሚያመሰግኑበት መዓረግ ነው። ሲዘምሩ እንደ ዳዊት የንግስና ካባቸው እየወለቀ ይዘምራሉ፤ እኛስ? ብዙ ፀሎት ቢፀልዩም በእግዚአብሔር ፊት እንደቆሙ ስለሚያውቁ በእሣት ዳር እንደቆመ ሰው ሕሊናቸው አይባዝንም፤ እኛ አንድ አባታችን ሆይ ስንፀልይ ሕሊናችን ስንት ግዜ ይባዝን ይሆን? አንድ ታላቅ ባህታዊ አቡነ ዘበሰማያት ብቻ እያለ ለብዙ ዘመናት ይጸልይ ነበር፤ መልዐክ ተገልጦ ይትቀደስ ስምከ በል እንጂ አለው፤ ባሕታዊውም አባታችን ሆይ የሚለውን ቃል ጣዕሙን እንደ ማር መቼ በአፌ ጠገብኩት አለ ይባላል።
[ቀጣዩን ገጽ ይመልከቱ]
[4ኛ] አንብዕ፦ ስለ ራሳቸው ሃጢአትና ጌታችን ስለተቀበለው መከራ፤ ስለ እመቤታችን ስደት እያሰቡ እንደ ሰን ውሃ የሚያለቅሱ ቅዱሳን ናቸው። ሐዋርያው ዩሐንስ ጌታን በመስቀል ላይ ካየበት ቀን ጀምሮ ያለቅስ ነበር፤ ፊቱ በሃዘን የተሞላ በመሆኑ ስሙ “ቅዱረ ገጽ ሐዋርያ” ተብሏል። ቅ/አርሳንዩስ አብዝቶ በማልቀሱ በፊቱ ላይ የእንባ መውረጃ ምልክት ነበረው። ዳዊት አልጋዬን በእንባዬ አጥባለሁ ማለቱ የእንባውን ብዛት ሲነግረን ነው [መዝ 6:6]
[5ኛ] ኩነኔ፦ በማዕርጋት ሂደት ኩነኔ ማለት ሥጋን ለነፍስ ማስገዛት ማለት ነው። ሰው ሥጋና ነፍስ የሚዋጉበት የውጊያ ከተማ ነው፤ ሥጋ ሲያሸንፍ ነፍሰ ገዳይነት; ዘማነት; ጥላቻ; ቅናት; ስካር ይነግሳሉ። ነፍስ ስታሸንፍ ሥጋን ታዘዋለች፤ ስገድ ፁም ፀልይ ስትለው ይታዘዛል። የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ፍቅር ሰላም ትዕግስት ሁሉ ገንዘብ ይኾናሉ[ገላትያ 5:22]
[6ኛ] ፍቅር፦ ፍቅር ማለት እግዚአብሔር ሊፈጥር ያልናቀውን ፍጥረት ሁሉ መውደድ ፤ የሚወዱንን መውደድ ብቻ ሳይሆን የሚጠሉንንም መውደድ መቻል ማለት ነው። ቅዱሳን መናፍቅ ክርስቲያን ሳይሉ ሰውን ሁሉ ይወዳሉ፤ ይህም “ፍቅረ ቢጽ” ይባላል። ዘር ተራራ ሸለቆ በቅዱሳኑ ዘንድ ቦታ የለውም፤ በዓለም ዘንድ ሗላ ቀርነት ነው፤ በክርስቲያን ዘንድ ደግሞ የሗላ ቀርነት መጨረሻ ነው። ሃገራችን በሰማይ ነው እንዳለ [ፊሊጲስዩስ 3:20]
[7ኛ] ሑሰት፦ ቅዱሳን በአንድ ሃገር ሆነው በሌላ ሃገር የሚደረገውን የማወቃቸው ማዕረግ ሑሰት ይባላል። ለምሳሌ ኤልሳዕ በኢየሩሳሌም እያለ የሶርያው ንጉስ ወልደ አዴር በቤተ መንግስቱ ምን እንደሚማከር ያውቅ ነበር።
[2ኛ ነገ. 6:8] [ቀጣዩን ገጽ ይመልከቱ]
[8ኛ] ንጻሬ መላዕክት፦ ቅዱሳን በዓለም ላይ ሆነው በሶስቱ የመላዕክት ከተሞች [በኤረር በራማ በኢዮር] መላዕክትን የማየታቸው ማዕረግ ነው።
[9ኛ] ተሠጥሞ ብርሃን፦ የብርሃኑ መዓዛና ጣዕም ነፍስን ከሥጋ እለይ እለይ በሚያሰኝ በብርሃን ባህር ሲዋኑ ማደር ማለት ነው።
[10ኛ] ከዊነ እሣት፦ ከዊነ እሣት የማዕረጋት መጨረሻ ነው፤ በዚህ ማዕረግ የደረሱ ቅዱሳን ሰውነታቸው አጋንንትን እንደ እሣት የሚያቃጥልና የማያስቀርብ ይሆናል። በአንድ ወቅት ቅ/ጳኩሚስ በአንዲት ሴት ላይ ብዙ አጋንንት ሰፍሮባት አየ፤ ይህን ግዜ ጌታዬ ሆይ ይህን ሁሉ አጋንንት እንዴት ትችለዋለች ብሎ አጋንንቱ ወደ እሱ እንዲተላለፉ ለመነ፤ ይህን ግዜ አጋንንቱ ወደ እሱ ገቡ፤ ቅ/ጳኩሚስ በፀሎቱ ብዛት መቀመጫ ቢያሳጣጨው በእሳት ተቃጠልን እያሉ እየጮሁ ወተዋል። ቅ/ ባስልዮስም ለዚህ ማዕረግ በመድረሱ ተዋስያን በሰውነቱ ላይ ሲያርፉ እሳት ውስጥ እንደገቡ ተቃጥለው ሲወድቁ ቅ/ኤፍሬም አይቷል።
የእነ ተክለሐይማኖት ገድል ሲነበብ አጋንንቱ የሚጮሁት በዚህ ከዊነ እሣት ማዕረጋቸው ነው።
ወ ሥ በ ሐ ት ለ እ ግ ዚ አ ብ ሔ ር
[ተክለ መድህን]
No comments:
Post a Comment