የሠራዊት ጌታ የልዑል እግዚአብሔር አገልጋይ
“መላዕክት”
v ከእግዚአብሔር ዙፋን ስር ትዕዛዝ በወጣ ግዜ ኪሩቤል ተቀብለው ለሱራፌል ያስተላልፋሉ ፤ ሱራፌልም ለሚካኤልና ለገብርኤል ለሩፋኤልም ያደርሳሉ; ሚካኤል ለፍጥረቱ በጎም ይሁን ክፉ ትዕዛዙን ይፈጽሙ ዘንድ መላዕክትን ያዛቸዋል፤ ኪሩቤልና ሱራፌል መላዕክቱም ሁሉ አቤቱ የእጅህን ስራ አታጥፋ እያሉ ቀን ከማት ይለምናሉ። ጥበቃቸውና ልመናቸው አይለየን፤ አሜን።
v የመላዕክት አለቃ፦
ድርሳነ ሩፋኤል ላይ 7 ሊቃነ መላዕክት ቢኖሩም አለቃቸው ቅ/ሚካኤል ነው ፤ የስሙ ትርጓሜም መኑ ከመ እግዚአብሔር [እንደ እግዚአብሔር ያለ ማን ነው] ማለት ነው።
የመላዕክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል
v ብዙ ግዜ የመላዕክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ከዲያቢሎስ ጋር በተከራከረ ግዜ እግዚአብሔር ይገስፅህ አለው እንጂ አልተከራከረም ሲባል ሰምተናል;እነሆ ታሪኩ እንዲህ ነው፦ ሊቀ ነብያት ሙሴ እጅግ ታዛዥና የዋህ ስለነበር ሀገረ ከንዓንን ለማየት ወደ ናባው ተራራ በወጣ ግዜ ሁለት መላዕክት በአረጋውያን ተመስለው መቃብር ሲቆፍሩ ሲያይ ላግዛቹ ብሎ መቆፈሪያውን ተቀበላቸው፤ እነሱም በመጨረሻ “ሰውየው በአንተ ልክ ነውና እስቲ ገብተህ ለካልን አሉት” እሱም በየዋህነቱ ጉድጓዱ ውስጥ ገብቶ እንደተኛ እንደ እንቅልፍ አሸልቦት በዚያው ዐረፈ; መላዕክትም ቀበሩት። እስራኤላዊያን ሙሴን እጅግ ስለሚወዱት የሙሴን መቃብር እንደ ጣዖት እንዳያመልኩት እግዚአብሔር የሙሴን መቃብር ሰወረው፤ ነገር ግን ጠላት ዲያቢሎስ ሊያሳያቸው በመነሳቱ ቅዱስ ሚካኤል ተቃወመው; በመጨረሻም ቅዱስ ሚካኤል ዲያቢሎስን እግዚአብሔር ይገስጽህ ብሎ ከራሱም ሰወረበት።
Source፦ the Assumption of Moses
የሐዋርያው ይሁዳ መልዕክት ቁጥር 8
v የቅ/ሚካኤል ትዕግስት፦ ሚካኤል ትዕግስተኛ መልአክ በመባል ይታወቃል ፤ ስለ ሙሴ ሥጋ ከዲያቢሎስ ጋር ሲከራከር እግዚአብሔር ይገስጽህ አለው እንጂ ቀድሞ ዘንዶውን እንዳሸነፈ ሊዋጋው በቻለ ነበር። አይሁድ ጌታን ሲሰቅሉት መልአኩ ቅ/ገብርኤል ሰይፉን አወጣ ፤ ቅ/ሚካኤል ግን በአይሁድ ስራ አዝኖ ፈጣሪን ፍጡራን ሰቀሉት እያለ በአርምሞና በትዕግስት አያቸው ይላል ድርሳኑ።
v የቅ/ሚካኤል አበይት በአላት፦ ቅ/ሚካኤል ሁለት ታላላቅ በዓላት አሉት
1) ሰኔ 12 ዲያቢሎስን አሸንፎ በምትኩ ሊቀ መላዕክት ሆኖ የተሾመበት ቀን ነው። ሰኔ 12 አፎምያንም የረዳበት ቀን ስለሆነ በአሉ በታላቅ ክብር ይከበራል።
2) ህዳር 12 ሕዝበ እስራኤልን በክንፎቹ ጥላ ከበረሃው ፀሐይ ከልሎ ከግብጽ ምድር እየመራና እየጠበቀ ከንዓን ያገባቸው እለት ነው። መላዕክቱ በክንፋቸው የእግዚአብሔር ስም ስለተፃፈበት ህዝቡን ይጠብቃሉ ፤ የመላዕክቱን ስም የመጨረሻውን ፊደል ስናይ ኤል ብሎ ይጨርሳል፤ ለምሳሌ ሚካኤል ገብርኤል ራጉኤል… ይህም “ስሜ በሱ ላይ ነውና” እንደሚል የእግዚአብሔር የምህረት ስም ስለሆነና በክንፎቻቸው ስለተፃፉ መላዕክቱ ይጠብቁናል። [ዘፀ 23:20]
“ቅ/ሚካኤል ሰዓሉ ወረድኤቱ የሃሉ ምስሌነ ለዓለም ዓለም አሜን”
ቅ/ገብርኤል
v የስሙ ትርጉም እግዚአብሔር ሃያል ነው የተባለው መልአኩ ቅ/ገብርኤል መላዕክትን ጽኑና ቁሙ ብሎ ስላጸናቸው ቀድሞ በመላዕክት ማዕረግ መጨረሻ የነበረው ሊቀ መላዕክት እንዲሆን ተሾመ፤ እመቤታችንንም እንዲያበስራት ክብርን አገኘ።
v አይሁድ ጌታን ሲሰቅሉት ቅ/ገብርኤል ሊታገስ አልቻለምና ሰይፉን አውጥቶ
ሁሉን ሊጨርስ ነበር፤ ጌታም ተው ሰይፍህን መልስ ብሎ ቢከለክለው “የአንተ ምህረት እስከመቼ ነው” ብሎ ሰይፉን ወረወረው ፤ ያም ሰይፍ እየተምዘገዘገ ወርዶ የምኩራቡን መጋረጃ ለሁለት ቀደደው።
ቅ/ሩፋኤል
v ሩፋኤል ማለት ሰውን አስደሳች ማለት ነው። ቅ/ሩፋኤል ፈታሔ ማህፀን በመባል ይታወቃል ፤ እናቶች ከፀነሱ ግዜ ጀምሮ ድርሳኑን እያነበበቡ ይለምኑታል; እንደእምነታቸውም ይሆንላቸዋል።
v ሣራ አስማንድዮስ የተባለ አጋንንት አድሮባት 7 ባሎች ባገባች ለሊት ይሞቱባት ነበር ፤ ቅ/ሩፋኤልም ይህን አጋንንት አርቆላት ጋብቻዋን ባረከላት። በዚህም ምክንያት ቅ/ሩፋኤል “መልአከ ከብካብ” ይባላል። ጦቢት5:12
v የሰማይ መዛግብትን በእጁ የሚጠብቅ ስለሆነ “ አቃቤ ኖሃቱ ለአምላክ”
ይባላል። እግዚአብሔር እንዳዘዘው የሚከፍተውና የሚዘጋው እርሱ ነው።
v ጳጉሜ 3 በእለቱ ለሚደረግ ጸሎት እንዲያሳርግ ቃል ኪዳን አለውና 600
አቡነ ዘበሰማያት የሚደግሙ አሉ።
“መላዕክት ከዘመነ አበው እስከ ዘመነ ሐዋርያት”
v አብርሐምና መላዕክት፦ አብርሐም ለይሥሐቅ ሚስት እንዲያመጣለት አገልጋዩ እያውብርን አዘዘውና እንዲህ አለው፦ እግዚአብሔር መልአኩን በፊትህ ይልካል [ዘፍ.24:7] እነሆ በመንገዳችን ሁሉ እንዲጠብቀን መልአኩን በፊታችን የሚልክ እግዚአብሔር ነው; እራሴን በእራሴ እጠብቃለሁ ማንንም አትላክ የሚል ይኖር ይሆን? ይህን ማለት የሚወዱ ቢኖሩ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ይላቸዋል ፤
“በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለአንተ ያዛቸዋል ፤
እግርህም በድንጋይ እንዳይሰናከል በእጆቻቸው ያነሱሃል” መዝ90:11
እንዃን ክርስቲያን ቀርቶ አህዛብም ያለግዜያቸው እንዳይሞቱ መላዕክተ ጽልመት ይጠብቋቸዋል!!!
v ሎጥና መላዕክት፦ ሎጥን ከሰዶምና ገሞራ ያዳኑት እግርህ በድንጋይ
እንዳይሰናከል በእጆቻቸው ያነሱሃል የተባለላቸው መላዕክት ናቸው; ዘፍ. 19:15።
ሎጥን ያዳኑት መላዕክትም መኳንንት በመባል ይታወቃሉ።
”መላዕክቱ ሎጥን ከሰዶምና ገሞራ ሲያድኑት”
v ያዕቆብና መላዕክት፦ ታላቁ አባት ያዕቆብ የልጅ ልጆቹን ምናሴንና
ኤፍሬምን ሲባርክ እጁን በራሳቸው ላይ በመስቀለኛ አመሳቀለና እንዲህ አለ;
ከልጅነቴ ጀምሮ የመገበኝ እግዚአብሔር ፤ ከክፉ ሁሉ ያዳነኝ መልአክ
እነዚህን ብላቴኖች ይባርክ። ዘፍ 48:15
v ክቡር ዳዊትና መላዕክት፦
ዳዊት በገናውን እየደረደረ የዘመረውን እስቲ እንስማ; [መዝ33:7]
“የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል ያድናቸውማል”
“ይትዓየን መልአከ እግዚአብሔር አውዶሙ ፤ ለእለ ይፈርሆ ያድሃኖሙ”
v ኢያሱና መላዕክት፦ የስሙ ትርጉም መድሃኒት የተባለው ኢያሱ
በቅ/ሚካኤል ፊት ሰገደ; ኢያሱ 5:14
v ነብዩ ዳንኤልና መላዕክት፦ የስሙ ትርጉም እግዚአብሔር ዳኛዬ ነው የተባለው ነብዩ ዳንኤል ስለ ቅ/ሚካኤል እንዲህ አለ፦
ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ ፤ በተዘጋ ጉድጓድ ሲያጽናናው ደግሞ
“ከሚካኤል በቀር የሚያጽናናኝ የለም አለ” ዳን. 10:13 ፤ 10:21
v በዚያም ዘመን /በአለም ፍፃሜ/ ስለህዝቡ የሚቆመው ሚካኤል ይነሳል። ዳን 12:1
v የቃሉን ድምጽ በሰማሁ ግዜ ደንግጬ በምድር ላይ በግንባሬ ተደፈሁ። ዳን 10:9
v ካህኑ ዘካርያስና መላዕክት፦ የስሙ ትርጉም እግዚአብሔር ያስታውሳል
የተባለው ካህኑ ዘካርያስ መልአኩ እግዚአብሔርን እንዲህ ብሎ ሲለምን ሰማ; “የሠራዊት ጌታ ልዑል እግዚአብሔር ሆይ እነዚህን 70 አመት የተቆጣሃቸውን ኢየሩሳሌምንና የይሁዳ ከተሞች የማትምራቸው እስከመቼ ድረስ ነው? ብሎ መልአኩ ለመነ; እግዚአብሔርም መልአኩን በሚያስደስት ቃል መለሰለትና ለከተማዋ ምህረትን አደረገ። ዘካርያስ 1:12
v ሐዋርያው ቅ/ጴጥሮስና መላዕክት፦
መላዕኩ ቅ/ሚካኤል እለተ በዓሉ በ12 እንደሆነ በሐዋርያት ስራ
ምዕራፍ 12 ላይም ስለ ቅ/ሚካኤል የተጻፈ ታሪክ አለ; ንጉስ ሄሮድስ
ቅ/ጴጥሮስን ሲያስር ቤተክርስቲያን አብዝታ ፀለየች፤
መልአኩ ቅ/ሚካኤል ተልኮ ቅ/ጴጥሮስን ከእስር አወጣው።
ሄሮድስ ግን በመልአኩ ተቀስፎ ትል በልቶት ሞተ ይለናል። የሐዋ.12:1
”ቅ/ሚካኤል ጴጥሮስን ከእስር እንዳወጣው”
v ሐዋርያው ቅ/ጳውሎስና መላዕክት፦ የማመልከው የእግዚአብሔር መልአክ በፊቴ ቆሞ ነበር; የሐዋ. 27:23። የማመልከው ሲል ፈጣሪ የሆነ ማለቱ ሳይሆን የምሰግድለት የማከብረው መልዐክ ማለቱ ነው።
v የመላዕክት ምልጃ፦ መላዕክትን በአርያም ፅኑና ቁሙ ያለው ቅ/ገብርኤል እንዲህ አለ “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ” ሉቃስ1:9። የምቆመው የሚለው ቃል ቀጥ ብሎ መቆም ሳይሆን ስለእኛ የሚማልድ የሚለምን መሆኑን ለመግለጽ ነው ፤ ምሳሌ እንውሰድ፦ የተመረጠው ሙሴ በፊቱ ባይቆም ኖሮ በመቅሰፍቱ ባጠፋቸው ነበር ይላል; መዝ 105:23። ሙሴ በፊቱ ባይቆም ኖሮ ማለት ቀጥ ብሎ መቆም ሳይሆን በመቅሰፍቱ ግዜ ሙሴ ስለህዝቡ ፀልዮ ህዝቡ ከመቅሰፍት ስለዳኑ ነው; ዘፀ. 32:9። ስለዚህም በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ ሲል ስለእኛ የሚለምን መሆኑ ግልጽ ነው ማለት ነው።
v መላዕክት ጠባቂ ናቸው፦ የሠራዊት ጌታ ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ
ይላል; በመንገድህ ይጠብቅህ ዘንድ መልአኬን ወደ አንተ እሰዳለሁ ፤ ስሜ በሱ ላይ ነውና ሃጢአት ብትሰሩ ይቅር አይልም። ዘፀ 23:20 ሃጢአት ብትሰሩ ይቅር አይልም ሲል ስልጣኑን ለመግለጽ ነው። ለምሳሌ ቅ/ገብርኤል የተላከው ዘካርያስን እንዲያበስር ነበር ነገር ግን ስልጣን ስላለው ይህ እስከሚሆን ድዳ ትሆናለህ ብሎታል።
v ሁለቱ ጠባቂ መላእክት፦ “በመንገድህ ይጠብቅህ ዘንድ መልአኬን ወደ
አንተ እሰዳለሁ” ተብሎ በዘፀ 23:20 ላይ እንደተጻፈው እያንዳንዱ ሰው 2 ጠባቂ መላዕክት አሉት። አንዱ በቀን ሲጠብቀን ሁለተኛው በለሊት ይጠብቀናል። በሃጢአት ስንወድቅ ንስሃ እንድንገባ ይረዱናል፤ ዘወትር በሃጢአት ብንኖር ግን ብርሃን ከጨለማ ህብረት የለውምና ጠባቂ መላዕክት ጥለውን ይሄዳሉ፤ [2ኛ ቆሮ 6:14]
v የመላዕክት ቁጥራቸው፦ መላዕክት በነገድ 100 ናቸው ፤ የሰው ልጅ 3
ነገድ ብቻ ቢሆንም በዓለማችን 6 ቢሊዮን የሚደርስ ህዝብ አለ። በዚህ ስናስበው የመላእክት ቁጥር እጅግ ብዙ እልፍ አእላፍ ወትልፊተ አእላፋት እንደሆኑ በጥቂቱ ያስረዳናል።
v ትንሳኤ አላቸውን? መላዕክት ስለማይሞቱ ትንሳኤ አይነገርላቸውም።
ከ22ቱ ስነፍጥረት የሰው ልጅ ብቻ ነው ትንሳኤ ያለው ፤ እንስሳት
ሲሞቱ ሥጋቸው በስብሶ ይቀራል ትንሳኤ የላቸውም።
v መላዕክት መቼ ተፈጠሩ? መላዕክት አንድ ግዜ የተፈጠሩና የማይባዙ
ናቸው ፤የተፈጠሩትም በእለተ እሑድ ነው ኩፋሌ 2:6
v ፀሎት በመላዕክቱ ሲያርግ፦ መላዕክት የቅዱሳኑን ጸሎት ወደ እግዚአብሔር ያሳርጋሉ; “የቅዱሳኑ ፀሎት ከዕጣኑ ጢስ ጋር ከመልአኩ እጅ ወደ እግዚአብሔር ፊት ወጣ” እንደሚል ራዕ 8:3።
v መናፍቃን ስለ መላዕክት ያላቸው ስህተት፦
መላዕክት ከሰዎች ጋር ረክሰዋል የሚሉ መናፍቃን አሉ፤ ባለማወቃቸውም ይስታሉ፤ መላዕክት ረቂቅ መናፍስት ናቸው፤ ሥጋ የላቸውም አይዳሰሱም እንዴት ከሰው ጋር የሰውን ባህርይ ይሰራሉ? መላዕክት የተፈጠሩት ከእሣት ነው እንዴት እሣት ከሥጋ ጋር አንድ ሊኮን ይችላል? ታሪኩ የሚጀምረው በኖህ ልጆች ነው፤ የኖህ ልጆች እንደ መላዕክት ለማመስገን ተመኙና በአንዲት ተራራ ላይ መኖር ጀመሩ፤ የቃየልን ልጆች ሲያዩ ግን ከዛች ተራራ ላይ ወረዱና ከቃየል ልጆች ጋር ረከሱ፤ በንፍር ውሃም ጠፉ። የኖህ ልጆች እንደ መላዕክት ለማመስገን ስለተመኙ ነው “መላዕክት” የተባሉት መናፍቃኑ ግን ተሳሳቱ፤
እንዴት እንደተሳሳቱ እንይ፦ በራዕይ ዩሐንስ ላይ ለ7ቱ የቤተክርስቲያን መሪ አባቶችን መላዕክት ይላቸዋል [ራዕ 1:20 ፤ 2:1] መላዕክት በሁለት መንገድ ይተረጎማል፦
[1ኛ] ረቂቃን መላዕክት እንደነ ሚካኤል [2ኛ] አገልጋይ መላዕክ ወይም መልዕክተኛ።
ስለዚህም የራዕይ ዩሐንስን ስታነብ መላዕክት የሚለው ቃል አገልጋይ የሆኑ ሰዎች
መሆናቸውን ልብ በል ፤ እንዲሁ ከቃኤል ልጆች ጋር የረከሱትም እንደ መላዕክት
ለማመስገን የተመኙት የኖህ ልጅ መሆናቸው ለእኛ እጅግ ግልጽ ነው።
v “አሥሩ ነገደ መላዕክት”
መላዕክት በነገድ 100 ሲሆኑ በተልዕኮ ደግሞ በ10 ይከፈላሉ፦
1) ሊቃናት /በፅራ አርያም/ 24ቱ ካህናተ ሰማይ ሲሆኑ አለቃቸው ቅ/ሰላታኤል ነው።
2) ኪሩቤል /በኢዮር/ መንበረ ሥላሴን /ፀወርተ መንበር/ ይሸከማሉ።
3) አርባብ /በራማ/ የእግዚአብሔርን መንበር በክንፎቻቸው ይሸፍናሉ ፤ ሰው ከሚደርስበት የዲያቢሎስ ሃይል ይጋርዳሉ። መዝ 90:11 አለቃቸው ቅ/ገብርኤል ነው።
4) መኳንንት /በኤረር/ የሰው ልጅ ልዩ ጠባቂ ናቸው ፤ በተለይ በአደጋ ግዜ ሎጥን እንዳዳኑት ፈጥነው ይደርሳሉ። አለቃቸው ቅ/ሰዳካኤል ነው።
5) መናብርት፦ ለእግዚአብሔርን እጅግ ቅርብ የሆኑ ናቸው; የሰውን ችግር ለእግዚአብሔር ያቀርባሉ; መዝ88:6 አለቃቸው ሩፋኤል ነው።
6) ሥልጣናት፦ መላውን ፍጥረት ለመጠበቅ ስልጣን የተሰጣቸውና የምጽአት አዋጅ አብሳሪ ናቸው። ዳን 12:1 ፣ ተሰ.2:1 አለቃቸው ቅ/ሱርያል ነው።
7) ሃይላት፦ በመንፈሳዊ ህይወት የዛሉና የደከሙ ክርስቲያኖችን የሚያበረታቱ ናቸው; ዘፍ.16:7 አለቃቸውም ቅ/ሚካኤል ነው።
8) ሱራፌል፦ በትንቢተ ኢሳያስ በምዕራፍ 6 ላይ የተገለጹትና ኢሳያስን ከለምጹ እንዲፈወስ ያደረጉት ናቸው።
9) መላዕክት፦ ፍጥረትን ሁሉ የሚጠብቁ ናቸው ፤ አለቃቸው ቅ/አናንኤል ነው።
10) አጋእዝት፦ አለቃቸው ሣጥናኤል ነበር፤ ሣጥናኤል የመላእክትን ሁሉ ጸሎት ወደ እግዚአብሔር ያሳርግ ነበር; ከክብሩ ሲዋረድ ሚካኤል በምትኩ ተሹሞበታል።
በእግዚአብሔር ፊት የሚቆሙ 7 መላዕክትን አየሁ [ራዕ 8:2] እንዳለ 7 ሊቃነ መልዕክት አሉ።
[7ቱ ሊቃነ መላዕክት]
1) ቅ/ሚካኤል
2) ቅ/ገብርኤል
3) ቅ/ሩፋኤል
4) ቅ/ራጉኤል
5) ቅ/ዑራኤል
6) ቅ/ፋኑኤል
7) ቅ/አፍኒን ናቸው።
[ቀጣዩን ገጽ ይመልከቱ]
v “የመላእክት ከተማ”
3ቱ የመላዕክት ከተማና 7ቱ ሰማያት ከላይ ወደ ታች በቅደም ተከተል
መንበረ መንግስት
ፅራ አርያም [ የሥላሴ መንበር]
ሰማይ ውዱድ
ኢየሩሳሌም (መንግስተ ሰማይ) [ሣጥናኤል ይኖርባት የነበረችውና ከሱ ተነጥቃ ለእኛ የተሰጠችው]
ኢዮር
ራማ *** [ሶስቱ ዐለመ መላዕክት; የመላዕክ ከተማ]
ኤረር
v መላዕክተ ብርሐንና መላዕክተ ፅልመት”
v ሙሴ በደመና አምድ እግዚአብሔርን እንዳነጋገረ የብርሐን መላዕክትም በመብረቅ መነጽር እግዚአብሔርን ያነጋግሩታል። እሣት ከውሃ ጋር በተገናኘ ግዜ ፈጥኖ እንደሚጠፋ ከግርማው የተነሳ እንዳይጠፉ በመብረቅ መነጽር ብቻ ያነጋግሩታል። የጌታን ትዕዛዝ የብርሃን መላእክት ስለሚነግሯቸው መላዕክተ ጽልመት የመብረቅ መነጽር የላቸውም።
v ለመላእክተ ብርሐንም ሆነ ለመላእክተ ፅልመት አለቃቸው “ቅዱስ ሚካኤል ነው"
የመናፍቃን ጥያቄ ስግደት ለመላዕክት ይገባል?
v ሐዋርያው ዩሐንስ ለመላዕኩ ሲሰግድ መልአኩ ይህን አታድርግ
እኔም እንዳንተ አገልጋይ ነኝ አለው። ራዕ 19:10 መናፍቃኑ ይህን ይይዙና ለመላዕክት ስግደት አይገባም ይሉናል፤ በውኑ ለመላዕክት ስግደት አይገባምን? በሚገባ ይገባል እንጂ። እነሆ ታሪክ እንዲህ ነው፦
v መልአኩ እኔም እንዳንተ አገልጋይ ነኝ አትስገድልኝ ያለው ሐዋርያው
ዩሐንስ ከመላዕክት ጋር በመዐረግ ተስተካክሎ ስለነበረ ነው። ቅ/ጳውሎስ
[በ1ኛ ቆሮ. 6:3] ላይ “የዚህን ዓለም ተውና መላዕክትን እንኳን እንድንገዛ አታውቁምን?” ያለው ሐዋርያት ከመላዕክት ጋር በክብር የሚተካከሉ ስለሆነ ነው፤ መልአኩም ዩሐንስን አትስገድልኝ ያለው አንተም እንደ እኔ በማዕረግ ተስተካክለሃል ሲለው ነው።
ሐዋርያው ዩሐንስ እንዴት የመላዕክትን መዐረግ እንዳገኘ፦
v ሐዋርያው ዩሐንስ በህይወቱ ጌታን ለመምሰል ይጥር ስለነበር ጌታ ይወደው ነበር። አንድ ቀን ጌታችን መታጠቂያውን ፈትቶ ባስቀመጠበት ወቅት አንሥቶ በመታጠቁ ፍትወት ሥጋዊ ወደማዊ ጠፍቶለት ኑሮው እንደ መላዕክት ሆኗል።
v ሐዋርያው ዩሐንስ ጌታ የሚወደው ሐዋርያ /ፍቁረ እግዚእ/ ሲሆን በእለተ አርብ በቀራንዮ የጌታን እንግልት ካየባት ቀን ጀምሮ ፊቱ በሐዘን ተቋጥሮ ይኖር ስለነበር /ቁዱረ ገፅ/ሐዋርያ በመባል ይታወቃል። የነጎድጓድ ልጅ የተባለለት; ለ99 ዓመታት በዚች ምድር ላይ የኖረና ከሐዋርያት ሁሉ ሞትን ያልቀመሰ ታላቅ ሐዋርያ ነው።
እስቲ በአንድምታ እንምጣ አንድም ሐዋርያው ዩሐንስ ለመላእኩ ሰገደ ብለናል; በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው ሐዋርያው ዩሐንስ መልአክ መሆኑን አቶ ነው እንዴ የሰገደው? እንኳን ታላቁ ሐዋርያ እኛም እግዚአብሔር ማን መላዕክትም ማን እንደሆኑ እናውቃለን። ወደሱ የመጣው መልአክ መሆኑን ያውቃል; ከመላዕኩ እጅ ተቀብሎ ራእዩን እንደፃፈ በራዕይ መግቢያ ላይ ተናግሯል። ሐዋርያው ግን ሰገደ; አንዴ አይደለም ከአንድም ሁለት ግዜ ሰገደ; የአክብሮት ስግደት እንደሚገባ ያውቃልና; ራዕ 19:10 ፣ 22:8። ይህ ባይሆንማ ከዩሐንስ በፊት የሰገዱት እነ ዳንኤልና ኢያሱ ባልሰገዱም ነበር ፤ የእግዚአብሔር ስራ በዘመናት አይለዋወጥምና ሚልኪያስ 3:6
v ታላቁ ሐዋርያ ለመላዕክት ስግደትን እንዳስተማረን እኛም ለእግዚአብሔር የአምልኮት
ስግደት ለእመቤታችን የፀጋ፤ ለመላዕክትም የአክብሮት ስግደትን እንሰግዳለን ፤
“በመፅሐፍ ቅዱስ የተፃፈውን እውነታ እያመንን እናነባለን እንጂ አንብበን አንክድም”
መላዕክትን በአርያም; ሐዋርያትን በአጽናፈ ዓለም
ጻድቃንን በገዳም; ሰማዕታትን በደም ያጸና
እኛንም በቀናችው በተዋሕዶ ኦሮቶዶክስ እምነታችን ያጽናን
ወ ሥ በ ሐ ት ለ እ ግ ዚ አ ብ ሔ ር
ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር፤ አሜን
የእመቤታችን ፀጋ የፀጋ ልብስ ይሁንልን ፤አሜን
[ተክለ መድህን]
No comments:
Post a Comment