Thursday, 25 July 2013

ጥንተ አብሶ


በዲያቆን ኅብረት የሺጥላ 
**የሰው ዘር ናት ማለት በራሱ ጥንተ አብሶ አለባት አያሰኝም፡፡
**ድንግል ማርያም የሞተችው ልጇ ጥንተ አብሶን ካስወገደ በኋላ መሆኑን ልብ ማለት ይገባል፡፡ 
**እኛን እንዳዳነንና እንደቀደሰን ተሰቅሎ፣ ሞቶ፣ ደሙን አፍስሶ ሥጋውን ቆርሶ አዳናት ቢባል ካልዳነችና ካልነጻች ሴት ተወለደ ማለት ነውና ሁሉን ነገር ከንቱ ያሰኛል፡፡ አስቀድሞ ካነጻት በኋላ ከእርሷ ተወለደ የሚባል ከሆነ ደግሞ ያው ዓለሙ ሁሉ ከመዳኑ በፊት ድኅነት በልዩ መንገድ ለእርሷ እንደተደረገ ማመን ግድ ነው፡፡
**‹‹ይህማ ካቶሊኮች ትምህርት ነው›› ፖለቲከኛነት እንጂ መንፈሳዊነት አይደለም፡፡
**የክርስትና እምነታችን ከግብጽ እንዳልመጣልን የታመነ ነው፡፡ 
**‹‹አቡነ እገሌ እንዲህ ያምኑ ነበር፤ አባ እገሌ እንዲህ ብለው ጽፈዋል፤ እንዲህ አስተምረዋል›› ኢየሱስ ክርሰቶስ የመሠረታትን ቤተ ክርስቲያን ክብር የሚነካና በግለሰብእ የተመሠረች ሃይማኖት አድርጎ መቁጠር ነው፡፡ 

ከሁሉ አስቀድሞ ‹‹ጥንተ አብሶ›› ማለት ምን ማለት እንደሆነ መረዳት ይኖርብናል፡፡ በአጭሩ ‹‹ጥንት›› ማለት መነሻ፣መጀመሪያ ማለት ሲሆን ‹‹አብሶ›› ማለት ደግሞ በደል ማለት ነው፡፡ ሁለቱ ቃላት ተናበው የሚፈጥሩት ሐረግ ‹‹ጥንተ አብሶ›› ሲሆን የበደል መጀመሪያ የሆነ በደልን ያመለክታል፡፡በነጻ ፈቃዳቸው አስበው መበደል የሚችሉ የፍጥረት ወገኖች ሰዎችና መላእክት ናቸው፡፡ በሰማይ በደል የተጀመረው በዓለመ መላእክት ሲሆን በደለኞቹም ሰይጣንና ሠራዊቱ ናቸው፡፡ የሰዎች ልጆች ስለፈጸሙት በደል የምንነጋገር ከሆነ ግን በመጀመሪያ የበደሉ አዳምና ሔዋን ናቸው፡፡ የአዳምንና የሔዋንን በደል የውርስ ኃጢአት ከማለት ይልቅ ጥንተ አብሶ ማለት የበለጠ ይገልጠዋል፡፡ ያ የቀደመ በደል ተወግዷል፡፡ የሰው ልጆች በሙሉ በወልደ ማርያም በኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ቤዛነት
ከቀደመው በደል ነጻ ወጥተዋል፤፡፡ ይህን ማስተዋል ስለተሣነው ሰው መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር ‹‹እነዚህ ነገሮች የሌሉት ዕውር ነውና፥ በቅርብም ያለውን ብቻ ያያል፥ የቀደመውንም ኃጢአቱን መንጻት ረስቶአል።›› በጥቅሱ መሠረት ዓይነ ልቡናው የታወረ ካልሆነ በቀር ማንም ቢሆን ከቀደመው ኃጢአት የነጻ መሆኑን መዘንጋት የለበትም፡፡ ይህን መርሳት አምላካችን የከፈለልንን ዋጋ እንደ ከንቱ መቁጠር ነውና፡፡ (2ጴጥ 1፥9)

ጥንተ አብሶ አለባት የሚሉ ሰዎች የሚያቀርቧቸው መከራከሪያዎች 

1.ኛ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከኢያቄምና ከሃና በሩካቤ በዘር የተወለደች የባሕርያችን መመኪያ ፍጽምት ሰው ናት፡፡ እንዲያውም ቤተ ክርስቲያን የቀደሙትን አበው ቃል እና መጽሐፍ ቅዱስን ዋቢ በማድረግ ‹‹ቅድስት ድንግል ሰማያዊት ናት/ የሰው ዘር አይደለችም/ የሚል ቢኖር ውጉዝ ይሁን›› እያለች አጥብቃ ታስተምራለች፡፡ (ሃይ.አበ 123፥8) ይሁን እንጂ የሰው ዘር ናት ማለት በራሱ ጥንተ አብሶ አለባት አያሰኝም፡፡ አንዳንዶች ሰው ከሆነች ጥንተ አብሶ እንዴት አልኖረባትም እያሉ ይሞግታሉ፡፡ ይህም የጥንተ አብሶን ምንነት ካለማወቅ የሚመጣ ሙግት ነው፡፡ ጥንተ አብሶ በደልና የበደል ውጤት እንጂ ራሱን የቻለ ፍጥረት አይደለም፡፡ ማለትም ሰው እንደተፈጠረባቸው እንደ አራቱ ባሕርያተ ሥጋ እንደ እሳት፣ ነፋስ፣ ውኃና አፈር አይደለም፡፡ አዳም ሳይበድል በፊት ሰው ነው፡፡ መተላለፍ ካገኘውም በኋላ ሰው ነው፡፡ ጥንተ አብሶ የሌለበት ሰው ሊኖር አይችልም አይባልም፡፡ ድንግል ማርያም ጥንተ አብሶ አልደረሰባትም ነገር ግን ሰው ናት፡፡ ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስም ጥንተ አብሶን ያጠፋ ፍጹም ሰውና አምላክ ነው፡፡ እኛም ክርስቲያኖች ጥንተ አብሶ ጠፍቶልናል፡፡ ነገር ግን አሁንም ሰዎች ነን፡፡ ስለዚህ ድንግል ማርያም ሰው እስከሆነች ድረስ ግድ ጥንተ አብሶ ነበረባት ማለት ጥንተ አብሶን ተፈጥሮአዊ ማድረግ ነውና ስሕተት ነው፡፡ ጥንተ አብሶ በሰው አለመታዘዝ ምክንያት የመጣ በደል እንጂ ከሰው ልጆች ጋር አብሮ የተፈጠረ ተፈጥሮአዊ ባሕርይ አይደለም፡፡ አዳምም ራሱ በጥንተ አብሶ ከመገኘቱ በፊት ሰው መሆኑን መርሳት አይገባም፡፡

2.ኛ ድንግል ማርያም በ64 ዘመኗ ሞታ በልጇ ሥልጣን ተነሥታለች፡፡ በሦስተኛውም ቀን አሳርጓታል፡፡ ይኸውም ሲሰላ ሞትን ይገድል ዘንድ የሞተው ልጇ በሥልጣኑ ተነሥቶ ካረገ ከ15 ዓመታት በኋላ ይሆናል፡፡ የእርሷ ሞት ‹‹ሁሉን የሚያስደንቅና›› ምክንያት ያለው ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ እንደተናገረው ልጇ በፍርድ እንደማያዳላ የሚያስተምር እና እርሷ የሰው ዘር እንጂ የመላእክት ዘር አለመሆኗን የሚያረጋግጥ ክንውን ነው፡፡ መላእክት እንደ ሰው አይሞቱምና፡፡ ይሁን እንጂ በመሞቷ ምክንያት ብቻ ጥንተ አብሶ ስለነበረባት ነው እያሉ የሚጽፉ አሉ፡፡ ድንግል ማርያም መሞቷ ከላይ የጠቀስነውን እውነታ እንጂ ጥንተ አብሶ ነበረባት አያሰኝም፡፡ የሞተችው ልጇ ጥንተ አብሶን ካስወገደ በኋላ መሆኑን ልብ ማለት ይገባል፡፡ በጥንተ አብሶ ምክንያት ሞተች ማለት ጥንተ አብሶ አልተወገደም ማለት ነውና ከባድ ክህደት ነው፡፡ መሞት ብቻውን ጥንተ አብሶ መኖሩን ያሳያል የሚባል ከሆነ ክብር ይግባውና ኢየሱስ ክርስቶስም ሞቶ ስለተነሣ ጥንተ አብሶ ነበረበት እንደማለት ይቆጠራል፡፡ ይህ ደግሞ አይሁድ ከፈጸሙት የሚከፋ ኃጢአት ነው፡፡ እንኳን ድንግል ማርያም እኛም የምንሞተው ሞት በጥንተ አብሶ ተይዘን አለመሆኑን መረዳት አለብን፡፡ ቅዱስ ቄርሎስ ሞትን በሃይማኖተ አበው ወደ መንግሥተ ሰማያት እንገባበት ዘንድ ኢየሱስ ክርስቶስ በሞቱ መርቆና ከፍቶ ያዘጋጀልን ‹‹አዲስ መንገድ›› ይለዋል፡፡ (ሃይ.አበ 80፥17) ቅዱስ ባስልዮስም በጸሎቱ ስለ ሞት ሲናገር ‹‹ለባሪያዎችህ ሞት የለባቸውም ፍልሰት እንጂ›› በማለት ሞትን ‹‹ፍልሰት›› ሲል ሰይሞታል፡፡ (እግዚአ ሕያዋን) ለሚያምኑ ሁሉ ‹‹ሞት ጥቅም›› ነው እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ (ፊል፥121) ስለዚህ ድንግል ማርያም ሞታ መነሣቷ የታመነ ቢሆንም ይህን እየጠቀሱ ጥንተ አብሶ አግኝቷት ነበር ማለት ስሕተት ነው፡፡

3.ኛ እመቤታች በጸሎቷ መሃል ‹‹መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች›› ማለቷን ቅዱስ ሉቃስ በወንጌል መዝግቦልናል፡፡ (ሉቃ1፥47) ‹‹መድኃኒቴ›› ማለቷን በመጥቀስ እንደማንኛውም ሰው ከጥንተ አብሶ መዳን የሚያስፈልጋት ስለነበረችና ስላዳናት ‹‹መድኃኒቴ›› አለች በማለት የሚከራከሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ ይህ ቃል እመቤታችን በሃይማኖት የተናገረችው ነው፡፡ አምላክ የሌለው የለምና ሁሉም አምላኬ ሊል ይችላል፡፡ ‹‹መድኃኔቴ›› የሚል ግን የወደደና ፈቅዶ የተቀበለ፤ የተደረገለትንም ያወቀ ሰው ነው፡፡ ስለዚህ እመቤታችን ጥበቃውን እና ያደረገላትን በማድነቅ ፈጣሪዋን ያመሰገነችበት የደስታ ቃል ነው፡፡ ጥንተ አብሶ ነበረባት ግን አያሰኝም፡፡

ምክንያቱም ሰው ዳነ የሚባለው ከደረሰበት ነገር ሲድን ብቻ አይደለም፡፡ ሊደርስበት ከነበረ ነገር የተሰወረ ሰው ተረፈ ወይም ዳነ ይባላል፡፡ መድኃኒትም መድኃኒት የሚባለው የታመመውን ሲፈውስ ብቻ አይደለም፡፡ ገና ያልታመሙ እንዳይታመሙ የሚከላከልም እንዲሁ መድኃኒት ይባላል፡፡ በዚህ ማብራሪያ መሠረት ድንግል ማርያም ‹‹መድኃኒቴ›› ያለችው ጥንተ አብሶ ሳይደርስባት ስለሰወራትና ስላዳናት እንጂ እንደማንኛውም የሰው ዘር ጥንተ አብሶ ካገኛት በኋላ አድኗት አይደለም፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ያለው ጥቅስ ከላይ ያብራራሁትን ሐሳብ የሚደግፍ ቃል ይገኝበታል፡፡ የግብጹ ፈርዖን የእስራኤል ሴቶች ሲወልዱ ወንዶች ከተወለዱ ወዲያው እንዲገድሏቸው አዋላጆችን ሁሉ አዝዞ ነበር፡፡ ነገር ግን አዋላጆቹ በንጉሡ ትእዛዝ መሠረት ሳይገድሉ አንዳንድ ወንዶችን እንዲሁ ተውዋቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ንጉሡ የግብፅም ንጉሥ አዋላጆችን ጠርቶ። ለምን እንዲህ አደረጋችሁ? ‹‹ወንዶቹን ሕፃናትንስ ለምን አዳናችሁ? አላቸው።›› (ዘጸ1፥18) እነዚህ ሕጻናት በሌሎች ሕጻናት የተፈረደው ፍርድ ተፈጻሚ ስላለሆነባቸው ‹‹ዳኑ›› ተባለ፡፡ ልብ በሉ ‹‹ዳኑ›› የተባለው ከበሽታ ቢሆን ሕመም አግኝቷቸው ነበር ለማለት እንከጅል
ይሆናል፡፡ እነዚህ ሰዎች የዳኑት ፈርዖን አውጆት ከነበረው የሞት ፍርድ ነበር፡፡ ታዲያ እነዚህ ሕጻናት ከሞት ዳኑ ማለት ሞተው ተነሡ ማለት ነው ወይስ ሳይሞቱ ቀሩ?

በተመሳሳይ ሁኔታ እመቤታችንም መድኃኒቴ ማለቷ በዕደ እግዚአብሔር ከጥንተ አብሶና በአዳም ከተፈረደው ፍርድ ስለተጠበቀች እንጂ ረክሳ ስለተቀደሰች አይደለም፡፡ ሎቱ ስብሐት! እንዲሁ በዘሮቹ ሁሉ ላይ በአዳም ምክንያት ፍርድ የተፈረደባቸው ሆኖ ሳለ እርሷ ግን የአዳም ዘር ብትሆንም ቅሉ ያ ዕዳ አላገኛትምና ከዚያ ሁሉ የዳነች ናት፡፡ ያዳናትም አምላኳ ነውና ‹‹አምላኬ፣ መድኃኒቴ›› አለች፡፡ ሊደርስብን ካለ ወይም ከተቃጣ ነገር ወይም እንደሚደርስ ከሚገመት ነገር ነጻ መሆን ራሱ መዳን ይባላል፡፡ ለምሳሌ ሕጻናት ገደል እንዳይገቡ እሳት እንዳያቃጥላቸው ነጠቅ ብታደርጓቸው ዳኑ አይባልምን? ሐዋርያው ጴጥሮስ የሞት ፍርድ ሳይፈረድበት ከእስር ቤት መልአኩን ልኮ ስላዳነው ‹‹አዳነኝ›› ማለቱ ተጽፎአል፡፡(የሐዋ12፥11)

ድንግል ማርያምን ዓለም በዳነበት መንገድ ዳነች፣ ነጻች እያሉ መናገር እናትነቷን መካድ ነው፡፡ እኛን እንዳዳነንና እንደቀደሰን ተሰቅሎ፣ ሞቶ፣ ደሙን አፍስሶ ሥጋውን ቆርሶ አዳናት ቢባል ካልዳነችና ካልነጻች ሴት ተወለደ ማለት ነውና ሁሉን ነገር ከንቱ ያሰኛል፡፡ አስቀድሞ ካነጻት በኋላ ከእርሷ ተወለደ የሚባል ከሆነ ደግሞ ያው ዓለሙ ሁሉ ከመዳኑ በፊት ድኅነት በልዩ መንገድ ለእርሷ እንደተደረገ ማመን ግድ ነው፡፡ እዚህ ድረስ መምጣት ግድ ከሆነ እንደ ኦርቶዶክሳዊያኑ አስቀድሞ ጠበቃት ማለት ክፋቱ ምን ላይ ነው? የበለጠ ፍጹምና መንፈሳዊው የእምነት መንገድ ይልቅ እንዲህ ማመን ነው፡፡ ምክንያቱም ሊወለድባት ሲልም ቢሆን ለብቻዋ ማንጻቱ ላይቀር ከእርሷ ለመጸነስ እስኪመጣ ድረስ ሁሉን እያወቀ ከጥንተ አብሶ ጋር እንድትቆይ አደረገ ከማለት አስቀድሞ በንጽሕና ጠብቆ አኖራት ማለት የበለጠ የቀና ነውና፡፡ ሰው እንኳን ቆይቶ የሚመገብበትን ቁስ ወድቆ ቢያይ ልበላበት ስል አጥበዋለሁና እስከዚያ ይንከባለል ብሎ ችላ እንደማይል የታመነ ነው፡፡ አምላክ እስክወለድባት በጥንተ አብሶ አድፋ ትቆይ ብሎ እናቱን ተዋት ማለት የማይመስል ነገር ነው፡፡

4.ኛ አንዳንዶች ‹‹ድንግል ማርያምን ጥንተ አብሶ ከቶ አላገኛትም›› የሚለውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ሲሰሙ ‹‹ይህማ ካቶሊኮች ትምህርት ነው›› በማለት ለማስተባበል ይሞክራሉ፡፡ ይህንኑ ሐሳብ በጽሑፍ ያቀረቡ ሰዎች አሉ፡፡ ካቶሊኮች ድንግል ማርያም ጥንተ አብሶ የለባትም ስላሉ ከእነርሱ ለመለየት ስንል እኛ የሌለባትን ጥንተ አብሶ አለባት ብንል ተገቢ አይደለም፡፡ ልዩነቶቻችን እንደተጠበቁ ሆነው ከካቶሊኮች ጋር የምንጋራቸው በርካታ ሃይማኖታዊ ጽንሰ ሐሳቦች አሉ፡፡ እነርሱን ላለመምሰል የምንመሳሰልባቸውን ሐሳቦች ሁሉ የኛ አይደሉም የምንል ከሆነ በዚህ መንገድ ስንቱን ልንጥል ነው? እውነትን መያዝ እንጂ እነ እገሌ ስለያዙት ብሎ መጣል ምክንያታዊ አያሰኝም፡፡ ከእነርሱ ጋር ለመመሳሰል ብለን እንዳልያዝነው ሁሉ ላለመመሳሰል ብለንም እውነቱን አንጥልም፡፡ በሌላ ስውር አላማ፣ ወይም መጠን አልባ የካቶሊክ ግላዊ ጥላቻ ይዞ፣ ወይም ደግሞ እነርሱን የሚቃወም ሁሉ ሐሳቤን ይቀበልልኛል በሚል ይህን የመሰለውን ሁሉ ምክንያት እያደረጉ ማቅረብ ፖለቲከኛነት እንጂ መንፈሳዊነት አይደለም፡፡

5.ኛ ሌላው ነጥብ የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያት ከእኅት አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዷ ናት፡፡ ለበርካታ መቶ አመታት ለቡራኬና ለክህነት አባቶችን ከግብጽ ስናገኝ ኖረናል፡፡ ይሁን እንጂ የክርስትና እምነታችን ከግብጽ እንዳልመጣልን የታመነ ነው፡፡ ስለሃይማኖት ትምህርት የራሳችን ሊቃውንት ነበሩን፤ አሉንም፡፡ በረጅም ታሪኳ የግብጽ ቤተ ክርስቲያን በርካታ ሀብቷን የሚያሳጣና የሚለውጥ ፈተና አጋጥሟታል፡፡ ዋና ዋናዎቹ ተግዳሮቶቿ በፕሮቴስታን አገር ለበርካታ ዘመናት ቅኝ መገዛቷ፣ እስካለንበት ዘመን በሙስሊሞች የበላይነት መመራቷ፣ እና አዎንታዊውን ትተን በራሷ ልጆች የተደረጉ አሉታዊ ለውጦች ናቸው፡፡ ከዚህ ሁሉ ፈተና በኋላ የቤተ ክርስቲያኒቱ እስካሁን መኖር በራሱ በጎ ዕድል ነው፡፡ ስለዚህ አሁን ያሉት የሃይማኖት ተወካዮቿ እንደ ቀድሞዎቹ እንደ አትናቴዎስና እንደ ቄርሎስ ያለ አቋም ባይኖራቸው መደነቅ የለብንም፡፡ የግብጽ ቤተ ክርስቲያን የወደደችውን ማመንና ማምለክ መብቷ መሆኑን መርሳት የለብም፡፡ ከኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጋር ያላት እኅትማማችነት በጠና ቢታመምም ሞተ የሚባል አለመሆኑም እጅግ በጣም መልካም ነው፡፡ በአንድ ርእሰ ጉዳይ ዙሪያ የሁለቱን
እኅት አብያተ ክርስቲያናት አቋም ስንተነትን እነዚህን ሁሉ ጉዳዮች ከግምት ሳናስገባ ከሆነ የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ እንደርሳልን፡፡ ጥንተ አብሶን በተመለከተ ሁለቱን አኀት አብያተ ክርስቲያናት በማስተያየት ወደተሳሳተ መደምደሚያ የሚደርሱ ሰዎችም ይህንን ማስተዋል ያልቻሉ ናቸው፡፡

6.ኛ ‹‹አቡነ እገሌ እንዲህ ያምኑ ነበር፤ አባ እገሌ እንዲህ ብለው ጽፈዋል፤ እንዲህ አስተምረዋል›› እያሉ የግለሰቦችን ቃልና ጽሑፍ ለሃይማኖታዊ ጉዳይ በማስረጃነት የሚያቀርቡ አሉ፡፡ ይህ አካሄድ በራሱ የግለሰብእ ተጠቂ መሆንን ያሳያል፡፡ በተቃራኒዉም ተመሳሳይ ማስረጃ ማቅረብ ቢቻልም ሁለቱም መንገድ ከንቱነት ያለበት በመሆኑ ከዋና ዋና ምንጮች በመነሣት ሐሳብን መግለጥ የበለጠ መልካም ነው፡፡ የራሳቸውን ገድል ያልፈጸሙ መዋቲያንን ዋቢ ማድረግ ኢየሱስ ክርሰቶስ የመሠረታትን ቤተ ክርስቲያን ክብር የሚነካና በግለሰብእ የተመሠረች ሃይማኖት አድርጎ መቁጠር ነው፡፡ ሰው ከዚህ ቀደም የተናገረውን ዛሬ የማይደግም ተለዋዋጭ መሆኑንም መርሳት አይገባም፡፡ ስለዚህ ይህን መሰሉን ምክንያት በቁሙ ውድቅ ማድረግ እንጂ ምላሽ መስጠት አያስፈልገውም፡፡

ድንግል ማርያም ጥንተ አብሶ ነበረባት የሚሉ ሰዎች ሁሉ ከላይ የተጠቀሱትን ክብደት የሌላቸው ምክንያቶች ሁሉ እንደ ማስረጃ የሚያቀርቡት ከተነሡበት አጀንዳ ጋር የሚያቀርቡት መከራከሪያ ዝምድና እንደሌለው ሳይረዱ ቀርተው ብቻ አይደለም፡፡ እንዲያው በግምት ብዙ ብንወረውር አንዱ ሳይመታልን አይቀርም ብለው እንጂ፡፡ በተጨማሪም ማስተላለፍ ለፈለጉት መልእክት ድጋፍ የሚሆን ሌላ አሳማኝ ማስረጃ ማቅረብ እንደተቸገሩም ያሳያል፡፡ ሌሎች ይመኑላቸው እንጂ ስለሚናገሩት ነገር እውነትነት ስላቀረቡትም ማስረጃ ተአማኒነት ደንታ የሌላቸው ሰዎች ከዚህ የተለየ መንገድ የላቸውምና አቀራረባቸው ድንቅ አይደለም፡፡

No comments: