Wednesday, 24 July 2013

//ከሴቶች ሁሉ ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ//


ማርያም ርኩስ ነበረች የምትል ምላስ ክርስቶስን ለማርከስ የምትቅለበለብ ምላስ ትመስላለች። የክርስቶስ ሥጋና ደም ማን አረከሰው? የእናቱን ሥጋ ተዋህዶ ተወለደ። ታድያ ክርስቶስ የለበሰው ሥጋ ርኩስ ነው የሚል እርሱ ማን ነው?

የሉቃስ ወንጌል 2

22-24 እንደ ሙሴም ሕግ የ((መንጻታቸው ወራት በተፈጸመ ጊዜ፥ በጌታ ሕግ።)) የእናቱን ማኅፀን የሚከፍት ወንድ ሁሉ ለጌታ የተቀደሰ ይባላል ((ተብሎ እንደ ተጻፈ በጌታ ፊት ሊያቆሙት፥ በጌታም ሕግ።)) ሁለት ዋሊያ ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች ((እንደ ተባለ))፥ መሥዋዕት ሊያቀርቡ ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት። // ሉቃስ የሚያወራው ሕጉን ስለመፈጸማቸው ነው። ኢይምስልክሙ ዘመጻእኩ እስአሮሙ ለኦሪት /ሕግን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ እንዳለ ሕጉን ፈጽመዋል/ ለዚህ ነው ወንጌላዊው ሕጉ እንደተጻፈና እንደተፈፀመ የሚነግረን። ስለ ሕጉ እየነገረን እንደሆነ ቃላቱን ይመልከቱ፦ ((መንጻታቸው ወራት በተፈጸመ ጊዜ፥)) ((እንደ ተባለ))፥ ((ተብሎ እንደ ተጻፈ በጌታ ፊት ሊያቆሙት፥ በጌታም ሕግ።))

ሉቃስ ለኃጢአት መስዋዕት አቀረበች ሊላ አልደፈረም አላማው  ከመንፈስ ቅዱስ ነውና የነገረን ሕጉ ስለመፈጸሙ ነው። የኦሪቱ ሕግ ግን መስዋዕቱ ለኃጢአት መሆኑን በግልጽ ይናገራል፦
ኦሪት ዘሌዋውያን 12

6 የመንጻትዋ ወራትም በተፈጸመ ጊዜ፥ ለወንድ ልጅ ወይም ለሴት ልጅ፥ የአንድ ዓመት ጠቦት ለሚቃጠል መሥዋዕት፥ የርግብም ግልገል ወይም ዋኖስ ((ለኃጢአት መሥዋዕት)) ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ወደ ካህኑ ታምጣለት።

8 ጠቦት ለማምጣት ገንዘብዋ ያልበቃት እንደ ሆነ ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች፥ አንዱን ለሚቃጠል መሥዋዕት ሌላውንም ((ለኃጢአት መሥዋዕት ታቀርባለች)) ካህኑም ያስተሰርይላታል፥ እርስዋም ትነጻለች።

በዚህ አጋጣሚ የኦሪቱ ሕግ ሴት በረከሰች ጊዜ ቅዱስ ነገር አትንካ ይላል። ይህን ይዘው የጸሎት መጽሐፍ መንካት መስቀል መሳለም የሚፈሩ ሴቶች አሉ። ይህ ግን ልክ አይደለም። ሴት ልጅ በወር ተፈጥሮዋ ጊዜ ቅዱሳን መጻህፍትን ይዛ መጸለይ ትችላለች። ሌላው ሴት ልጅ በወር ተፈጥሮዋ ጊዜ ቤተ መቅደስ አትገባም። ወንድ ሲነስረው እጁ ቢደማ ቤተመቅደስ አይገባም። ምክንያም ስለረከስን ሳይሆን በቤተመቅደስ የሚፈሰው የክርስቶስ ደም ብቻ ስለሆነ ነው።

//ከሴቶች ሁሉ ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ//

ኦሪት ዘሌዋውያን 12
1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2 ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ((ሴት ብታረግዝ ወንድ ልጅም ብትወልድ፥ ሰባት ቀን ያህል የረከሰች ናት እንደ ሕመምዋ መርገም ወራት ትረክሳለች።)) // ማርያም ጌታን ስለወለደች ርኩስ ሆነች የሚል ከቶ ማን ነው? ቅ/ገብርኤል ፀጋን የተመላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ አላት እንጂ መርገመ ሥጋሽ ቀረልሽ እንኳን ደስ አለሽ አላላትም! ማርያም የረከሰች ከሆነች ይህ ሁሉ የመላኩ ምስጋና ስለረከሰች የተነገረ ነውን? ኢሳይያስን ጠይቁት ጽድቃችን እንደ መርገም ጨርቅ ነው እያለ ያለቅሳልና! እዚህ ደግሞ ፀጋን የተመላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ ሲላት ተገረምን! ሰው ሁሉ ጽድቅ በጎደለበት በጨለማ ዘመን ማርያም ግን ፀጋን የተመላሽ ሆይ ተባለች! እነሆ ኤልሳቤትም ከሴቶች ሁሉ ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ አለቻት! በኦሪቱ ሴት ሁሉ ወንድ ሲወልድ የረከሰ ነው ሲባል ማርያም ግን ከሴቶች ሁሉ ተለይታ የተባረከች ናት! መርገመ ሥጋ ወዴት ነበርክ? ከሴቶች ሁሉ ተለይታ የተባረከች ማርያምን ታረክሳት ዘንድ እንዴት አቅም አጣህ?

3 በስምንተኛውም ቀን ልጁ ከሥጋው ሸለፈት ይገረዝ።
4 ከደምዋም እስክትነጻ ሠላሳ ሦስት ቀን ትቀመጥ ((የመንጻትዋ ቀንም እስኪፈጸም ድረስ የተቀደሰን ነገር አትንካ)) ማርያምን ረከሰች የሚል ማን ነው? እስክትነጻ የተቀደሰን ነገር አትንካ እያለ ጌታን በማህፀንዋ ታቅፋ በደረትዋ አመቻችታ በጀርባዋ እንዴት አዘለች? እስኪ መልሱልን? የተቀደሰን ነገር አትንካ እያለ ልጅዋን ስታቅፍ ርኩስ ነበረን? እስኪ መልሳችሁ ይሰማ?

No comments: